Saturday, 30 March 2019 13:54

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

 ሄንሪ ሹገር የሚባል ሀብታም ሰው ነበር፤ ገብጋባና ስስታም! … ካርታ መጫወት የሚወድ፡፡ አንድ ቀን ጓደኛው ቤት ካርታ የመጫወት ተራውን እየጠበቀ ሳለ ‹ከመቀመጥ› ይሻላል ብሎ ሲዘዋወር መጽሃፍት ወደ ተደረደሩበት ቦታ እግሩ ጣለው፡፡ እየመራረጠም ሲመለከት አንዲት ትንሽ መጽሃፍ ትኩረቱን ሳበች … “A man who could see without his eyes” የምትል፡፡
ሄንሪ ሹገር መጽሃፏ ስለመሰጠችው የመጣበትን ጉዳይ ትቶ በትጋት ማንበብ ጀመረ፡፡ መጽሃፏ ኢምራት ካን የተባለ ‹ዮጊ› ለስምንት ዓመታት ያህል ዓይኖቹን አንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር በማሰልጠን (concentrate በማድረግ)፣ የዓይኖቹ ብርሃን ‹በነገሩ› ውስጥ ዘልቆ ጀርባቸውን ማየት እንደቻለ የሚተርክ ነበር፡፡ ሄንሪ ሹገርም የኢምራት ካንን ዓይነት ችሎታ ቢያዳብር የሌሎችን ተጫዋቾች ካርታ ከጀርባ እየተመለከተ ገንዘባቸውን እንደሚሞልጭ ለማሰብ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡
ወደ ቤቱ ተመልሶም ያነበበውን ነገር ያለመታከት ቀንና ሌሊት መለማመድ ጀመረ፡፡ ከሶስት ዓመታት በኋላ ወረቀት ላይ የተፃፈን ነገር ከጀርባ ተመልክቶ ማንበብና መለየት ቻለ፡፡ … የተመኘው ደረሰ፡፡ .. በከፍተኛ ንቃት ወደ ቁማሩ ተመለሰ፡፡
ሰውየው በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንዳሰበው ሚሊዬነር መሆን አላዳገተውም፡፡ ውስጡ ግን ምቾት የለም፡፡ አንድ ቀን ከቤቱ አፓርትመንት ላይ ሆኖ ዕልፍ፣ አዕላፍ የከተማው ሰዎች ኑሯቸውን ለማሸነፍ ወዲያ ወዲህ ሲታትሩ ተመልክቶ “እኔ በቀላሉ ያገኘሁት ብዙ ገንዘብ አለኝ፣ የመጣሁበት መንገድ ግን የተሳሳተ ነው፡፡ ለዚህ ነው ምቾት የማይሰጠኝ” በማለት ረዥም ጊዜ ሲያስብና ራሱን ሲመረምር ከቆየ በኋላ ቤቱ ውስጥ ያከማቸውን ገንዘብ በመስኮት ወደ ጎዳናው በተነ፡፡
የጎዳና ህፃናት፣ አላፊ አግዳሚው፣ ትራፊክ ፖሊሶቹ እንኳ ሳይቀሩ አየር ላይ የሚንሳፈፉትን የብር ኖቶች ለመቅለብ ሲራወጡ የነበረው መራኮት አሳዘነው፡፡ “ለድሆች ወገኖቼ ትርጉም ያለው ስራ መስራት አለብኝ” ሲል ለራሱ ቃል ገባ፡፡ … እዚህ ጋ ለህይወት የነበረውን አመለካከት ቀየረ፡፡ ትራንስፎርም አደረገ፡፡ … ሄንሪ ሹገር!!
በሚቀጥለው ቀን የከተማውን ዋና አካውንታንትና ታዋቂውን ሜክአፕ አርቲስት በከፍተኛ ገንዘብ ቀጠራቸው፡፡ አካውንታንቱ በተከፈተለት ቢሮ የገንዘቡን አስተዳደር ሲቆጣጠር፣ አርቲስቱ ደግሞ ከሱ ጋር ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎችና ታላላቅ ቁማር ቤቶች እየተዘዋወረ የፊቱን ገፅታዎች በሜክ አፕ ይቀያይሩለታል፡፡ ሲፈልግ የካናዳ መስፍን፣ ሲፈልግ የዐረብ ልዑል እየመሰለ ብዙ ገንዘብ መሰብሰብና ለንደን ወደ ሚገኘው ቢሮ ማስተላለፍ ስራው ሆነ። ገንዘቡ የሚውለው በየቦታው ለከፈቷቸው፣ እናት አባት ለሌላቸው ህፃናት መርጃ (Orphanage) ነበር። ሰውየው ለራሱ ብሎ የሚያስቀረው አንድ ሳንቲም አልነበረውም፡፡ እንደውም አንድ ቀን ከአርቲስቱ ጋር ምሳ በልተው የሚከፍሉት በማጣት እንደተቸገሩ ተፅፏል፡፡ የዛን ዕለት ጠዋት ግን ብዙ ገንዘብ ወደ ባንካቸው አስተላልፈዋል፡፡
ሄንሪ ሹገር ካለፈ በኋላ “The True Story of Henery Sugar” በሚል ርዕስ ታሪኩን የፃፈው አካውንታንቱ ነው፡፡ መጽሃፉ እስከ ታተመበት ጊዜ ድረስ ብዙ ድሃ ህፃናት እየተማሩ ያደጉትና አገር የገነቡት በሱ ገንዘብና ጥረት መሆኑን ማንም አያውቅም ነበር፡፡
“…Nothing is at last sacred, but the integrity of your own mind” የሚለን ታላቁ ኤመርሰን ነው፡፡
***
ወዳጄ፡- አንድን ዕቃ “ጥሩ ነው” የሚያሰኙት ምክንያቶች (qualifications) አሉት፡፡ ለምሳሌ ወንበር ቢሆን የተሰራበት ዕንጨት ወይም ማቴሪያል፣ ዲዛይንና ምቾቱ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ እንጨቱ ጥሩ ሆኖ ዲዛይኑ ቀሽም ቢሆን፣ ወይም ሲቀመጡበት የማይመች ከሆነ ምን ዋጋ አለው? .. የተከሉት ዛፍም አድጎ ፍሬ ካላፈራ ወይም ጥቅም ካልሰጥ ትርፉ ምንድነው? … ሀሳብም እንዲሁ ነው፡፡ ጥናት ማስጠናት፤ ዕቅድ ማዘጋጀት ጠቃሚ ነው፡፡ ስራ ላይ ካልተዋለና በተግባር ካልተተረጎመ ግን ኪሳራ ነው፡፡ .. የበጀት ኪሳራ! የጊዜና የኢነርጂ ኪሳራ!
እኔ እንደሚገባኝ ዋናው ችግር የነበረው ስርዓት፣ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ የሰረፀው የጅምላ ወይም የዕዝ አስተሳሰብ (The herd instinct in the individual) የፈጠረው ቀውስ ነው፡፡ “እኔ ምን እያደረግሁ ነው? … የማስበውስ ምንድነው?” ብለን ከመጠየቅ ይልቅ ሌሎች ስለሚያስቡት ነገር እንጨነቃለን፡፡ በቀደምለት በሬዲዮ የሰማሁዋት ታሪክ ጥሩ ምሳሌ ስለሆነች ላጫውትህ፡-
ንጉሡ የከተማውን ሰዎች “የምትወዱኝ ከሆነ አንዳንድ ኩባያ ወተት እዚህ ውስጥ ጨምሩልኝ” ብሎ ትልቅ በርሜል አስቀመጠላቸው አሉ፡፡ ሁሉም ሰው እንደተባለው አደረገ፡፡ አንድ ሰው ግን ወተት ሳይሆን ውሃ ነበር የጨመረው፤ በርሜል ሙሉ ወተት አንድ ኩባያ ውሃ ቢገባ ምንም ለውጥ አያመጣም በማለት፡፡ በመጨረሻ በርሜሉ ሲከፈት ግን ሙሉ በሙሉ የተሞላው በውሃ ነበር፡፡ ምክንያቱም … መጨረሻ ላይ እነግርሃለሁ፡፡
ወዳጄ፡- ወንበሩ አይቀየር፣ ግድግዳው ቀለም አይቀባ .. ግድየለም፡፡ አጥፊዎችም በይቅርታ መታለፋቸው ጥሩ ነው፡፡ አስተሳሰብ ካልተቀየረ፣ በደል ተሰርዞ ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት ካልተጀመረ ግን ለውጥ በምን ይገለፃል? … የተሃድሶ ፍሬስ ምንድነው?
ሌላ ሌላውን ትተን ስንቶች የተሰደዱበት … ስንቶች ህይወታቸውን የገበሩበት፣ ስንቶች ወህኒ የማቀቁበት፣ አገር ተሸማቃ ትንሽ የሆነችበት፣ የመጭውን ትውልድ ፀሐይ ያበራል፣ የዴሞክራሲ መሰረት ይጣልበታል፣ ራስን የመቻል ተስፋን አርግዟል ብለን ያመንንበት ‹ሪፎርም› እየተወላገደ ማየት ያሳዝናል፡፡
“ባዲስ መልክ ስራ ጀምረናል” እያሉ እንደሚያሞኙን ምግብ ቤቶችና አገልግሎት ሰጭዎች፣ ተሃድሷችንም የይስሙላ እንዳይሆን ስጋት አለ፡፡ ወይም ወደ ታች የመውረድ አቅም አጥቷል፡፡ ወይም ቀድሞ የነበረው የእዝ ሰንሰለት ጠፍሮታል፡፡
‹ብዙዎቹ› የፖለቲካ፣ የአስተዳደር፣ የደህንነት፣ የደንብ ማስከበር፣ የሸማቾች ህብረት ስራና የመሳሰሉት በቀጥታ ከኢህአዴግና ከመንግስት መዋቅሮች ጋር የተሳሰሩ አገልግሎቶችን የሚመሩ ሰዎች፣ መዝገበ ቃላታቸው ውስጥ “ተሃድሶ” የሚል ቃል ተሰርዟል፡፡ “የወረት ውሻ ስሟ ማንጠግቦሽ ነው” እንደሚባለው፣ ተሃድሶ ለነሱ የአንድ ሰሞን ሆያሆዬ፣ የአንድ ሰሞን ግርግርና ወከባ ነገር ይመስላል፡፡ … እንደ ሌሎቹ መጪና ሂያጂ ሃሳቦች!!
ቢፒ አር መጣ - ሄደ ተመለሰ
ካይዘን መጣ - ሄደ ተመለሰ
አንድ ላምስት መጣ - ሄደ ተመለሰ
“እንትና” ብቻ ቀረ ቤት እያፈረሰ! …
ብለው እንደሚቀልዱት ተሃድሶንም ወረት አድርገውታል፡፡ የወረት ነገር ከተነሳ “…    Nova Scopa Scopa bene!” ይላሉ ጣሊያኖች። አዲስ መጥረጊያ በደንብ ይጠርጋል ማለታቸው ነው … እስኪሸራረፍ ድረስ፡፡ የሆኖ ሆኖ ወዳሄ፡፡ … “እንትና” ማነው? ሪፎርሙ አልገባውም እንዴ?
***
ወደ ቅድሙ ጨዋታ ስንመለስ፡- በርሜሉ ሲከፈት ሙሉ በሙሉ ውሃ ነበር ብለናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በየበኩሉ፣ ያሰበውና ያደረገው፣ ሰውየው እንዳሰበውና እንዳደረገው ስለሆነ ነበር፡፡
ሠላም!!

Read 1100 times