Saturday, 30 March 2019 13:55

ኢትዮጵያዊነት የተቀነቀነበት “ጉማ ፊልም ሽልማት”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


           “ጉማ ሁሌም ይቀጥላል” በሚለው መርሁ ከ6 ዓመታት በፊት በዳይሬክተር ዮናስ ብርሃነ መዋና በድርጅቱ “ኢትዮ ፊልም” ፒኤልሲ የተቋቋመውና ከዓመት ዓመት እያደገ የመጣው “ጉማ ፊልም ሽልማት” (Gumma Film Awards)፤ ስድስተኛው ዙር የሽልማት ሥነ ስርዓት ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በድምቀት ተከናውኗል፡፡ የብሔራዊ ቴአትር በሮች በ11 ሰዓት ተከፍተው በ12 ሰዓት ፕሮግራሙ እንደሚጀመር ቢገለፅም፣ በእንግዶች ተጠናቅቀው አለመግባት የተነሳ ከምሽቱ 1፡10 ነበር የተጀመረው - መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ሲበር ቢሾቱ ላይ በደረሰበት የመከሰስ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ የቦይንግ 737 ማክስ ስምንት አውሮፕላን ተሳፋሪዎችና የበረራ ሰራተኞች ቡድን አባላት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ፡፡
በመድረክ አመራሩ የተዋጣለት አርቲስትና የማስታወቂያ ባለሙያው ሽመልስ በቀለ፤ በየመሃሉ ጣል በሚያደርጋቸው ቀልዶቹና ፈጠራዎቹ ታዳሚውን ሲያዝናና ነበር ያመሸው፡፡ ከነዚህ መካከል ሁሌ እንደሚያደርገው የተወዳዳሪ እጩ ፊልሞችን ርዕስ በመገጣጠም ትርጉም የሚሰጥ ቃል በመመስረት ታዳሚውን አዝናንቷል፡፡
ሽመልስ በቀለ ከለውጡ በኋላ ያሳለፍነውን አንድ ዓመት ወደ ፊልም ዘውግ በመቀየር፣ ተዋናዩ ከ100 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም መድረኩ ኢትዮጵያን አድርጎ ሰው በአደባባይ ተሰቅሎ የሞተበትን ትዕይንት “ሆረር”፣ “ዴሞክራሲ ይሰፍናል፤ አገር ወደ ፊት ትሻገራለች” የተባለውን “ሰስፔንስ”፣ ፖለቲከኞች ከእስር መፈታታቸውንና ስደተኛ መመለሱን “አክሽን”፣ አንዳንድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጋር በተያያዘ የሚነገሩ ቀልዶችን “ኮሜዲ”፣ ሽሙጦችን “ሳታየር ኮሜዲ” በማለት የአንድ ዓመቱን የለውጥ ሂደት፤ ከ“ጉማ ፊልም ሽልማት” ጋር ለማጣጣም የፈጠረው አዝናኝ አቀራረብ ታዳሚውን ማዝናናት ብቻ ሳይሆን አስደምሟል፡፡
ሽልማቱ የተጀመረው ከ“የህይወት ዘመን ተሸላሚ” ነበር፡፡ “ምርት 3 ሺህ ዓመት” “ሳንኮፋ” እና “ጤዛ” በተሰኙትና ሌሎች ፊልሞቹ የሚታወቀው አገር ወዳዱ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ነበር ተሸላሚው። የክብር ካባው፣ የጉማ ሽልማት ዋንጫና የምስክር ወረቀቱ ወደ አሜሪካ ከተላከለት በኋላ “ለታዳሚዎቼ አክብሮትና ፍቅር አለኝ፤ በርቱ በፅናት ተጓዙ” የሚል መልዕክት ማስተላለፉን፣ እሱን ሊሸልም ተጠርቶ መድረክ ላይ የወጣው ከፍተኛ የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ ተናግሯል፡፡
“ምርጥ የተማሪ አጭር ፊልም” በሚለው ዘርፍ፣ በዕጩነት ከቀረቡት ፊልሞች ውስጥ በ “ዘፀአት” ፊልሙ ያሸነፈው ወጣት አማኑኤል ዘሪሁን፤ ከአቶ ወንድሙ ካሳዬ ቸርነት ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ ባደረገው ንግግር፤ “ጥበብና አገር ዝቅ ብለው ሲሰሩላቸው በሰው ፊት ከፍ አድርገው ያቆማሉ” ካለ በኋላ፣ “አገራችን በደምና በፀሎት የቆመች በመሆኗ በማንም አትፈርስም፤ አንድ ዛፍ ትከሉ ሳይል ዱላ ይዛችሁ ዝመቱ የሚል መሪ በዚህ ዘመን ልናይ አይገባም” ሲል ባስተላለፈው መልዕክት፤ አዳራሽ ሙሉ ጭብጨባ ተችሮታል፡፡
በ“ምርጥ አጭር ፊልም ዘርፍ” ለውድድር ከቀረቡት ፊልሞች ውስጥ “ሌላው ጀግና” በተሰኘው ፊልሙ የአብስራ ወንዱ ያሸነፈ ሲሆን ከአንጋፋውና የረጅም ጊዜ የካሜራ ባለሙያው ከአቶ እንዳልክ አያሌው ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡ በዚህ ዘርፍ “ጉም”፣ “ተስፋን ፍለጋ”፣ “ሰውነት እና ካይላ” የተሰኙ ፊልሞች ቀርበው ነው “ሌላው ጀግና” ያሸነፈው፡፡
“ምርጥ ድምፅ” በሚለው ዘርፍ፣ “በእናት መንገድ”፣ “በዛ በክረምት”፣ “ድንግሉ”፣ “አንድ እኩል” እና “ወደኋላ” የተሰኙ ፊልሞች በእጩነት ቀርበው፣ “ድንግሉ” በተሰኘው ፊልም አናንያ ኃይሉ አሸንፎ፣ ከሙዚቃ አቀናባሪው አቤል ጳውሎስ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
ከነዚህ ሽልማቶች በኋላ የዕለቱ የክብር እንግዳ፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ብዙነሽ መሰረት ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ኪነ ጥበብ ሀይል አላት፤ ይህንን ሀይል በአግባቡ መጠቀም ብልህነት ነው፤ ጉማ ይህን እያደረገ ጥበብንም ሙያተኞችንም እያከበረ” በመሆኑ አድናቆት እንዳላቸውና ወደፊትም መስሪያ ቤታቸው ድጋፉ እንደማይለይ ቃል በመግባት፣ ለተሸላሚዎች መልካም እድል ተመኝተዋል፡፡
በምርጥ የፊልም ሙዚቃ” ዘርፍ “ሚስቴን ዳርኳት” የተሰኘው ፊልም ያሸነፈ ሲሆን የዘፈኑ የግጥም ደራሲው ወንዶሰን፣ ዜማ ደራሲው አህመድ ተሾመ (ዲንቢ) እና በድምፅ የተጫወተው መሳይ ተፈራ፤ መድረክ ላይ ወጥተው ከድምፃዊት ፀደንያ ገ/ማርቆስ እጅ ሽልማታቸውን ወስደዋል፡፡ አምና በዚህ ዘርፍ “በታዛ” ፊልም ዘሪቱ ከበደ (ቤቢ) አሸናፊ ነበረች፡፡
በ“ምርጥ ስኮር” ዘርፍ የ“ሲመት” ፊልም አቀናባሪው ሱልጣን ኑሪ (ሶፊ) አሸንፎ፣ ከአንጋፋው የዘፈን ግጥም ደራሲ፣ ድምፃዊ፣ ተወዛዋዥና በተለይ በማንዶሊን ተጫዋችነቱ ከሚታወቀው ጋሽ አየለ ማንዶሊን እጅ ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ ባስተላለፈው መልዕክት፣ “ሲመት ፊልም ስኮሩ የተሰራው አገር በቀል በሆኑ፣ በእጃችን ላይ ባሉ መሳሪያዎች ነው፡፡ እጃችን ላይ ባሉና በራሳችን የሙዚቃ መሳሪያዎች ተዓምር መስራት እንችላለን ይሄ ኤሌክትሮኒክስ ምናምን የሚባለው አስፈላጊ አይደለም” ያለ ሲሆን አንዳንድ ታዳሚዎች ይህቺ ነገር ሮፍናንን ለመሸንቆጥ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በምርጥ “የገፅ ቅብ (ሜካፕ)” ዘርፍ “ውሃና ወርቅ”፣ “ዋሻውና ሲመት” በእጩነት ቀርበው የነበረ ሲሆን መሰረት መኮንን በ“ሲመት” ፊልም አሸንፋ ሽልማቷን ከአንጋፋው ሰዓሊ ዜናነህ አስፋው ተቀብላለች፡፡ አምና በዚህ ዘርፍ ባለቤቷ ታደሰ ንጉሱ በ“የእግዜር ድልድይ” ፊልም አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በ“ምርጥ ወጥ የፊልም ፅሑፍ” ከቀረቡት እጩ ፊልሞችና ደራሲዎች በሀይሉ ዋሴ፤ “በእናት መንገድ” በተሰኘው ፊልሙ አሸናፊ ሲሆን በተወካዩ አማካኝነት ሽልማቱን ወስዷል፡፡ እንደ ፖለቲከኞች ሳይሆን “እንደ እናት ልብ ያኑረን” የሚል መልዕክት አስተላልፏል - ተሸላሚው፡፡ ከዚህ ሽልማት ቀጥሎ በየዓመቱ እንደሚደረገው ሁሉ በዓመቱ በህይወት የተለዩ አርቲስቶች የሚዘከሩበት “ማስታወሻ” በተሰኘው ፕሮግራም ተዋናይ አብነት አየለ፣ ተዋናይ መስከረም ወንድምአገኝ፣ አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) በቅርቡ ምፅዋ ያረፈው ኤዲተር ሀይሌ መብራቱ፣ ደራሲና ተዋናይ ጌታቸው ደባልቄ፣ የመድረኩ ንጉስ ፍቃዱ ተ/ማርያምና ተዋናይት ህይወቴ አበበ ተዘክረዋል፡፡
በ“ምርጥ ኤዲቲንግ” ዘርፍ “ወደኋላ” በተሰኘው ፊልም ልዑል አባዲ ሲያሸንፍ፣ በ“ምርጥ ሲኒማቶግራፊ” ዘርፍ፣ በ“ውሃና ወርቅ” ፊልም ያሸነፈው እውነት አሳሳኸኝ፣ በተወካይ ሽልማቱን ወስዷል፡፡ እንደ ሽመልስ በቀለ አገላለፅ፤ የዘንድሮውን ሽልማት በተወካይ የወሰዱት ብዙ ናቸው፡፡ በ“ምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይት” በ“ሞኙ የአራዳ ልጅ አራት” ፊልም ህፃን ማክቤል ሄኖክ ያሸነፈች ሲሆን ህፃኗ በእናቷ በኩል ከሞዴልና ተዋናይት መቅደስ ፀጋዬ እጅ ሽልማቷን ተቀብላለች፡፡ በ“ምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ” ዘርፍ በ “ጃሎ” ፊልም በሀይሉ እንግዳ አሸንፎ፣ ከአንጋፋው ተዋናይ ደረጀ ደመቀ እጅ ዋንጫውን ተቀብሏል፡፡
በ“ምርጥ ረዳት ሴት ተዋናይት” ዘርፍ አንጋፋዋ ዘነቡ ገሰሰ፣ አሸንፋ ሽልማቷን ከተዋናይት መርከብ በልሄር ከተቀበለች በኋላ “እግዚአብሔር ለሁሉም ቀን አለው፤ ስላከበራችሁኝ አመሰግናለሁ፤ ጉማ የተደበቀን ያወጣል” በማለት እንባ እየተናነቃት ከመድረክ ወርዳለች፡፡ በ“ምርጥ ረዳት ተዋናይ ዘርፍ” እጩ ከነበሩት መካከል ካሳሁን ፍስሃ (ማንዴላ) “ወደኋላ” በተሰኘው ፊልም አሸንፎ መድረክ ላይ ከወጣና ከአንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ተዋናይ፣ ተራኪና፣ ተርጓሚ ተፈሪ አለሙ እጅ ዋንጫውን ከተቀበለ በኋላ ባደረገው ንግግር፣ ሰውን ያዝናና ሲሆን በተለይ ዋንጫውን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ “ኢትዮጵያ አገራችንን ቅዱስ ሚካኤል ይጠብቃት” ሲል፣ ሰው አሜን ከማለት በሳቅ ወደ መንከትከቱ አዘንብሎ ሲስቅ አምሽቷል፡፡
በ“ምርጥ መሪ ተዋናይት ዘርፍ” በ “አስነኪኝ” ዕፀህይወት አበበ፣ በ“ሲመት” መስከረም አበራ፣ በ“ትህትና” አዚዛ አህመድ፣ በ“አንድ እኩል” ሶኒያ ኖዬል እጩ የነበሩ ሲሆን ሲኒያ ኖየል በ“አንድ እኩል” አሸናፊ ሆናለች፡፡ የዚህ ዘርፍ ሸላሚ የሆኑት ከ63 ዓመት በላይ በድምፅ በተዋናይነትና በተለያዩ የኪነ ጥበብ ዘርፎች ያገለገሉት አርቲስት የሺ ተክለ ወልድ እጩዎቹን በቪዲዮ እንመልከት ብለው እጪዎቹ በቪዲዮ ከታዩ በኋላ አሸናፊዋን ሳይሸልሙ ረስተው ፈጣሪ ይባርካችሁ ኑርልኝ እንዳከበራችሁኝ ክበሩ ብለው ሊወርዱ መድረኩን ካጋመሱ በኋላ በመድረክ መሪው ተይዘው ተመልሰው ሽልማቱን ሰጥተዋል። ይህ ትዕይንት ታዳሚውን በሳቅ እንዲያውካካ አድርጎታል፡፡
በ“ምርጥ ወንድ ተዋናይ” ዘርፍ፣ ደመወዝ ጎሽሜ “በእናት መንገድ”፣ ግሩም ኤርሚያስ በ “ውሃና ወርቅ”፣ ታሪኩ ብርሃኑ በ “ሞኙ ያራዳ ልጅ 4”፣ ኤርሚያስ ታደሰ በ“አላበድኩም” ታጭተው ኤርሚያስ ታደሰ በ “አላበድኩም”አሸንፎ ከአንጋፋው የኪነ ጥበብ ሰው ተክሌ ደስታ ሽልማቱን ወስዷል፡፡
ላለፉት 6 ዓመታት የጉማ ሽልማት ብቸኛና የክብር ስፖንሰር ሆኖ በቀጠለው በደሌ ቢራ ስም ለህዝብ እይታ ቀርቦ በሚሸለመው የ“በደሌ ስፔሻል ምርጥ የህዝብ ምርጫ ፊልም ዘርፍ” “ድንግሉ”፣ “ሞኙ የአራዳ ልጅ 4”፣ “በእናት መንገድ”፣ “ሚስቴን ዳርኳት” እና “ሀ እና ለ2” በእጩነት ቀርበው “ሚስቴን ዳርኳት” አሸንፎ የሄንይከን ኩባንያ የውጭ ግንኑነትና ሰስተይነብሊቲ ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ፈቃዱ በሻህ ሽልማት ተበርክቷል፡፡ አምና በዚህ ዘርፍ የዮሴፍ ካሳ “አፄ ማንዴላ” ፊልም አሸናፊ ነበር።
በ“ምርጥ ዳይሬክተር” ዘርፍ በሀይሉ ዋሴ በ “እናት መንገድ” ፊልሙ ሲያሸንፍ፣ በአምና የዚህ ዘርፍ በ“ታዛ” ፊልም አሸናፊ ከነበረችው ቅድስት ይልማ ሽልማቱን በተወካይ ሲወስድ፣ በ“ምርጥ ፊልም ዘርፍ”ም በሀይሉ ዋሴ ለ3ኛ ጊዜ አሸንፎ ከኢዮሃ ኢንተርቴይንመንትና ኢቨንትስ ዋና ስራ አስኪያጅ ከወ/ሮ አዩ አለሙ እጅ ሽልማት ተቀብሏል። “ሲመት”ና በ“እናት መንገድ” ፊልሞች በ3 ዘርፍ በማሸነፍ መሪ ሆነዋል፡፡
በ18 ዘርፍ የታጩ ከ80 በላይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በተሳተፉበት በዘንድሮው ሽልማት፤ ዋንጫቸውን ለኢትዮጵያ ሰላም ለሚዋደቁና ለሚፀልዩ መታሰቢያ ያደረጉ፣ አገራችን ሰላም እንድትሆን የተመኙ ብዙዎች ሲሆኑ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከፍ ከፍ ያለችበት ምሽት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በ“ለውጡ ኢትዮጵያውያንን ብዙ ተስፋ ሰንቀውበት የነበረ፣ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ተስፋችን የደበዘዘበት ጊዜ ቢሆንም አሁንም በአገራችን ተስፋ አንቆርጥም” ብሏል - መድረኩን የመራው አርቲስት ሽመልስ በቀለ በንግግሩ፡፡ የ“ጉማ ምርጥ የዓመቱ ፋሽን አለባበስ” በሚለው አርቲስት መቅደስ ፀጋዬና አርቲስት ሄኖክ አለማየሁ ተመርጠው፣ ከምሽቱ 4፡30 ሥነ ስርዓቱ የተጠናቀቀ ሲሆን ቦሌ በሚገኘው ቤስት ዌስተርን ሆቴል በተደረገ “አፍተር ፓርቲ” የእራት ግብዣ ፕሮግራሙ ተቋጭቷል፡፡     


Read 1493 times