Saturday, 30 March 2019 13:54

ቀታሪ ግጥም

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(2 votes)

 (እግዜርን ከምድረ ገፅ ያባረረ “የግል ጸሎት”) “ግጥምን የማያውቅ እግዜርን አያውቅም”
                                   
            “ስነ-ግጥም በስነ-ግጥማዊ እውነትና ውበት ላይ የተመሰረተ የህይወት ሒስ ነው” ይለናል -- ማቲው አርኖልድ፡፡ የጎደለንን የሚያሟላ፤ ርሀባችንን የሚያስታግስ የላቀ የህይወት አቅም ያላብሳል --ያለ ይመስለኛል። “የልቤ ጸሎት” አሰነኛኘቱ አያዎ ነው፡፡ የአቀራረቡ ትኩስነት ምንጩ ይኸው ነው፡፡ የዘይቤው ብርታት ስሜቱን ወደ መሳለቅ አንሮታል። መሳለቁ ከዙፉኑ አቻነት ይመነጫል፡፡ የህልውና አቻነት። የአቅም አቻነት፡፡ ኸረ እንዲያውም የሰውን ልጅ የበላይነት ያስረግጣል። ማለትም በተሰጠው ላይ ተመስርቶ ሌላ የላቀ ነገር በመስራት (በማሳየት) ተገልጿል-- በመጀመሪያዎቹ አራት ስንኞች። ስም ሲሰጠው ቅፅል ስም ይጨምራል -- የሰው ልጅ፡፡ ቤት ሲሰጠው “እልፍኝ፣ ሳሎን” ያክልበታል፡፡ ይህን በማድረጉ፣ ቁጣ ስላተረፈ ለዚሁም ተመጣጣኝ ምላሽ ያዘጋጃል፤ ከፊቱ ገለል ማድረግ፡፡ ጭራሽ በህይወት ዘመኑ ላያገኘው፣ ላይነ ስጋ ላይበቃ ለዘላለሙ ያሰናብተዋል፡፡ ይህም በመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች ተገልጿል፡፡ እነሆ፦
“ፊትህ ቢገስፀን ፣ ፊትህን እዳናይ
ከምድር አንሥተን፣ ሰቀልንህ ከሰማይ”
በባህላችን “ፊት” የገመና መስፈሪያ ነው፤ ለተመልካች፡፡ የውስጥን ጉድ ለአደባባይ ያጋልጣል፡፡ “የፊት ወዳጅህን በምን ቀበርከው? በሻሽ፤ የኋለኛው እንዳይሸሽ” -- ብሂልን ያስታውሰናል፡፡ ይቀትራል፡፡
[ቀታሪ÷ ስሩ ቀተረ ነው፡፡ ቀተረ÷ እኩል ለመሆን ተከታተለ÷ ተቀታተረ÷ ተመለካከተ÷ ተወዳደረ÷ ተተካከለ÷ ተመዛዘነ÷ ተፈካከረ÷ ተፈላለገ (አስ) ከባለ ቀትር አትቀታተር፡፡ (ከሣቴ ብርሃን ተሠማ÷ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት÷ ገፅ ፫ ፻ ፹ ፬÷2008 ዓ.ም)  ግጥም ምንጬ ህይወት ነውና (ቋንቋው (መንገዱ) አዕምሮን፣ ስሜቱ ልብንና መልዕክቱ ልቦናን ይቀትራል።) አዕምሮን፣ ልቦናንና ልብን የቀተረ ከምናብ የሚፈለቀቅ የፀነነ የጥበብ ውጤት ነው። መቀተሩ ከልማድ ጋር የሚደረግ ግብግብ ነው። ፈጠራ ደግሞ ልማድን መሻገር ይጠይቃል። ከልማድ ያልተሻገረ ግጥም ነፃ አያወጣም፡፡ አይታኘክም-የተመጠጠ ነውና፡፡]
* * *
ቁጥር 5
የልቤ ጸሎት
አቤቱ! አንተ ስም ሰጠኽን፣
እኛ ቅጽል ፈጠርን
አንተ ቤት ሰጠኽን፣
“እልፍኝ፣ሳሎን” ጨመርን
ፊትህ ቢገሥፀን፣ ፊትህን እንዳናይ
ከምድር አንሥተን፣ሰቀልንህ ከሰማይ፡፡
(በዕውቀቱ ስዩም፣ ስብስብ  ግጥሞች፣
2001 ዓ.ም፣ ገፅ 119)
“ፊትህ ቢገሥጸን፣ ፊትህን እንዳናይ” የሚለው ስንኝ አንድም ከስረ መሰረቱ የሰው ልጅ በገነት በነበረበት ሰዓት የደረሰበትን አምላካዊ ተግሳፅ፣ ቁጣ የሚያስታውስ ነው፡፡ ሁለትም ከእየሱስ መወለድ ጋር ተያይዘው የመጡ የምክር፣ የአስተምህሮ ጉዳዮች በሰው ልጅ ዘንድ እንደ ተግሳፅ መቆጠራቸውን የሚጠቁም ስንኝ ነው። ምክንያቱ ደግሞ “ነፃነቴን የሚነጥቁ ተግባራት ተፈፅመውብኛል፡፡ በህልውናዬ ላይ ያለ አግባብ ቁማር ተቆምሮብኛል፡፡ ፍርዱ የእኔን የሞራልም ሆነ የንቃት ደረጃ የሚመጥን አይደለም” የሚል ይመስለኛል-- ሰው፡፡ የሰውን ልጅ   ዋጋ ያመለክታል፡፡ [ይህ ለሰው ልጅ ብቻ  የተሰጠ የንቃት ችሎታ ነው፡፡ ይህ ንቃቱ ለተፈጥሮም ሆነ ለፈጣሪው መገለጫ ነው፡፡ ስለሆነም የሰው ልጅ በንቃቱ ባደገ ቁጥር በህብር ይሰፈራሉ፡፡ መስፈሪያውም ስነግጥም ነው፡፡]
ይህ መለኮታዊ ተግባር በሰዎች እርምት እያገኘ የዘለቀ መሆኑ በስንኞቹ ላይ የተገለፁት የአመፅ ተግባራት ይጠቁማሉ፡፡ የሂደቱ ውጤት “ከምድር አንሥተን፣ ሰቀልንህ ከሰማይ” በሚለው ስንኝ ተገልጿል፡፡ እዚህ ላይ የሰውን ልጅ የሀይል ብርታት አይደፈሬ ያደርገዋል። ያከረዋል፡፡ ይቀትረዋል። መለኮትን በሰው መዳፍ ስር ይጥለዋል። ይማርከዋል። ፍርዱም በሰው ልጅ የበላይነት ይጠናቀቃል፤ ለዘላለሙ ምድርን በማስለቀቅ፡፡ ለዚህ ይሆን ዳንቴ፤ “ግጥምን የማያውቅ እግዜርን አያውቅም”   በመለኮትና በሰው መካከል የቆመች ወጋግራ ናት --ያለ ይመስለኛል፤ የሁለቱን ገመና የተሸከመች። የመጨረሻው ስንኝ የግጥሙ እንብርት ነው፤ የህይወት ሰበዝ የሚመዘዝበት ቋት፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው የመለኮት በተለይም የእየሱስ ብቃት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡ በመሆኑም የሰዎች አልሸነፍ ባይነት በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ለመባረሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ አንድም የእየሱስ በመስቀል ላይ መሰቀል ማሳያ ነው፡፡ መለኮታዊ ሀይል ኖሮት ነገር ግን አይሁዶችን (ሁሉንም የሰው ልጅ) ማሳመን ባለመቻሉ የደረሰበት በደል ተጠቃሽ ነው፤ ምስኪን እየሱስ፡፡ ሁለትም ከእነዘላለሙ (በህይወት እስካለን) ወደ ምድር ላይመለስ ሰማይ ላይ ሰቅለነዋል -- የሚል ትርጉም አለው፡፡ በዚህም ምክንያት ከርስቱ፣ ከሀብቱ፣ ከይዞታውና ከምድራዊ ህልውናው የተፈናቀለ ብቻም ሳይሆን ከነጭራሹ የተባረረ የመጀመሪያው ህላዌ ይሆናል፡፡ ይህም እሳቤ ገነት ምድር እንደሆነች፣ ከአዳምና ሄዋን ይዞታ የተባረረው፣ወደ ግዞት የተላከው የመጀመሪያው ሆኖ ተገልጿል፡፡ ባይሆንማ ተመልሶ ወደ መሬት ባልመጣ ነበር፡፡ ይህም አገላለፅ የእግዜር ህልውና የሚገለፀውም ሆነ የሚተረጎመው በሰው እንደሆነ ይጠቁመናል፡፡ ይህ ደግሞ እግዜርን የሰው እስረኛ ያደርገዋል፡፡ ግጥሙም የሚለው ይኸው ነው፡፡
ይህ ጭብጥ በኢትዮጵያ የስነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ኸረ እንዲያውም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተገለጠ አይመስለኝም!! ይህ ዘመን ያበረከተው ትልቁ አተያይ ይመስለኛል፡፡ ነባሩን(ትውፊታዊ) እና ሃይማኖታዊውን አመለካከት የገለበጠ ብቻም ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የህልውና ምንጭ  መሆኑን ያበሰረ ግጥም ነው፡፡ ይህም ገጣሚውን ልዩ ቦታ ያሰጠዋል፡፡
ግጥሙ በአያዎ ዘይቤ ቢቀርብም ንቡር ጠቃሽና ምፀት ዘይቤን የተሸከመ ነው (በዘይቤ የተሞሸረ)፡፡ ንቡር ጠቃሽነቱ የገነት መገኛ፣ የእየሱስን መሰቀልና የመለኮትን ሰማያዊ አለም የሚተርኩ ተረኮችን የሚያስታውስ መሆኑ ላይ ነው፡፡ በንቡር ጠቃሽና በአያዎ ዘይቤዎች ውህደት (ኪናዊ ቅንብር) አማካኝነት የሀሳብ አዲስነት (ትኩስነት) ፈልቋል። ስለሆነም የሰው ልጅ ቀድሞም እዚሁ ነበር፣ ዛሬም እዚሁ አለም ላይ አለ፡፡ የተባረረውም ሆነ ተመልሶ የመጣው እራሱ መለኮት (“እየሱስ” )ነው --- የሚል ፍቺ ይሰጠናል፡፡ ለዚህ ይሆን እንዴ! የጎዣም ማህበረሰብ “አዳምና ሄዋን የተፈጠሩትም ሆነ የኖሩት በጣናና በአካባቢው”  እንደሆነ የሚተርክልን? ከሆነ ነገር ተበላሸ፡፡ አጃኢብ ነው!!  ---የፊት ምስጋና ለሁዋላ ሃሜት ያስቸግራል-እንዲል ብሂሉ፡፡ ይቀትራል፡፡ መቀተሩ  ከልማድ ጋር ግብግብ  እንድንፈጥር ወጥሮ ስለሚይዘን ነው፡፡ ልማድን የተሻገረ አተያይ በመሆኑ ያማል። እንዲያውም የመጨረሻዎቹን ሁለት ስንኞች ደጋግሜ ሳኝካቸው “እግዜር የሰውን ልጅ ከገነት እንዳባረረው ሁሉ (መጽሐፍ ቅዱስን ልብ ይሏል)  የሰው ልጅም እግዜርን ከምድረ ገፅ አባረረው” በሚል ተተክቶ በአእምሮዬ ያቃጭልብኛል፡፡ የተራኪው “የልብ ፀሎት” ይህ ይሆን እንዴ?
ግጥሙ ዜማዊ ነው፤ የፀሎት፡፡ እንጉርጉሮ በመሆኑ ቀታሪ ነው፡፡ ያስቆዝማል፡፡ ፍቺው የትየለሌ ነው፡፡ የዛሃውን ጫፍ (እንብርት)ላገኘ ሲመዝ፣ ሲያፍታታ ቢከርም ይመሽበታል እንጂ አያልቅም። ምጣኔው የተስተካከለ ሁነኛ ምት አለው፡፡ ስለ ግጥሙ ብዙ የምለው ነገር ቢኖርም እንደ ስነ-ግጥም ኩሩ ለመሆን ያክል ልደምድመው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1467 times