Saturday, 06 April 2019 14:56

ቦይንግ ለአውሮፕላን አደጋው ሃላፊነቱን ወስዶ ይቅርታ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


                                   ኬንያውያን የኢትዮጵያ አየር መንገድንና ቦይንግ ኩባንያን ሊከስሱ ነው


             ቦይንግ ኩባንያ መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም ከቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰተውና 157 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ከሶፍትዌር ችግር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ያስታወቀ ሲሆን፣ በአደጋው በደረሰው የህይወት ህልፈት ማዘኑን በመግለጽም፣ የሟች ቤተሰቦችን ይቅርታ ጠይቋል፡፡
የቦይንግ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሚዩለንበርግ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ አየር መንገድና የበረራ ቁጥር 302 እንዲሁም በላየን ኤር የበረራ ቁጥር 610 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላይ ለተከሰቱትና በድምሩ 346 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት ለዳረጉት ሁለቱም አደጋዎች ምክንያት የሆነው የአውሮፕላኑ የበረራ ቁጥጥር ስርዓት ሶፍትዌር ችግር እንደነበር በማመን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው በትዊተር ገጻቸው ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መግለጫ፣ ቦይንግ ኩባንያ በአውሮፕላኑ ሶፍትዌር ላይ የነበረውን ችግር በአፋጣኝ ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍና መሰል አሳዛኝ አደጋዎች በፍጹም እንዳይከሰቱ ለማስቻል እጅግ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ መጋቢት 1 ቀን ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ በነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ላይ ምርመራ ሲያደርግ የቆየውን ቡድን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ አደጋው በፓይለቶች ስህተት የተፈጠረ አለመሆኑንና አውሮፕላኑ በእለቱ መብረር የሚያስችለው የፀና ሰርተፊኬት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
አብራሪዎቹ በረራውን ለማድረግ የሚያስችል ብቃትና ተገቢው የበረራ ፍቃድ ያላቸው መሆኑ፤ አውሮፕላኑ ለበረራ ሲነሳ በትክክለኛ መስመርና ለመብረር በሚያስችል ሁኔታ ላይ እንደነበር፤  አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስችላሉ ተብለው በቦይንግ የተቀመጡትን የበረራ መመሪያዎች ተከትለው አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር በተደጋጋሚ ቢሞክሩም ሊቆጣጠሩት እንዳልቻሉ መረጋገጡንም ወ/ሮ ዳግማዊት በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የዚህ የአውሮፕላን አደጋ የምርመራ ሂደት አለማቀፍ ልምድ ያላቸውን ድርጅቶች ጨምሮ በጋራ የተሰራ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ዳግማዊት፤ በቀጣይም ሙሉ የአደጋው የምርመራ ውጤት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከአደጋው የምርመራ ውጤት በመነሳትም አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስቸገረው የበረራ ቁጥጥር ስርአቱ በአምራች ኩባንያው በድጋሚ ሊፈተሽ እንደሚገባና የአውሮፕላኑ ስሪት ወደ በረራ ከመመለሱ በፊት በበረራ ወቅት የሚያስቸግረውን ክፍል ኩባንያው በድጋሚ ሊያስተካክል እንደሚገባ የደህንነት ምክረ ሀሳቦችም ለኩባንያው ቀርቧል፡፡  
በሌላ በኩል፤ በዚሁ አደጋ ከሞቱት መካከል 32ቱ ኬንያውያን እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን የእነዚህ ኬንያውያን ቤተሰቦች በጋራ የህግ ጠበቃ ቀጥረው ቦይንግንና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመክሰስ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኬንያውያኑ ቤተሰቦች በጠበቆቻቸው በኩል ባደራጁት ክስ፣ ለአደጋው መንስኤ ቦይንግና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊነት ወስደው ካሳ እንዲከፍሉ የሚጠይቅ ነው፡፡ ክሱ የሚመሰረተውም በአሜሪካን ሃገር በሚገኝ ፍርድ ቤት ይሆናል ተብሏል፡፡ ከዚሁ አደጋ ጋር በተያያዘ ቀደም ብሎ የቤተሰባቸውን 1 አባል በአደጋው ያጡ ሩዋንዳውያን ቤተሰቦች ቦይንግን መክሰሳቸው ታውቋል፡፡
ከ6 ወራት በፊት በተመሳሳይ በኢንዶኔዢያ በተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ቤተሰቦቻቸውን ያጡ አካላትም ቦይንግ ኩባንያ ላይ ተመሳሳይ ክስ ሰሞኑን ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
ይህን የምርመራ ውጤት ተከትሎ፣ በአየር መንገድ ድረ ገፅ መግለጫ የሰጡት የአየር መንገድ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም በበኩላቸው፤ "በአደጋው ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት ዛሬም ሃዘናችን መሪር ነው፤ ነገር ግን ችግሩ በአብራሪዎቻችን የተፈጠረ አለመሆኑ መታወቁ ጠቃሚ ነው" ብለዋል፡፡ "በአብራሪዎቻችን በእጅጉ እንኮራለን” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ አሁንም አየር መንገዱና 16ሺህ ሰራተኞች በሙሉ አቅማቸው ደንበኞቻቸውን ለማገልገል ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

Read 907 times