Print this page
Saturday, 06 April 2019 15:01

የሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ ሶማሊኛ ቋንቋ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ሊቀላቀሉኝ ይችላሉ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ከሰሞኑ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው ስያሜውን ከ “ኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ” ወደ “ሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ” ቀየረው የሶማሌ ክልል ገዥ ፓርቲ፤ ከእንግዲህ ማንኛውም ሶማሊኛ ቋንቋ መናገር የሚችል ኢትዮጵያዊ በአባልነት ሊቀላቀለኝ ይችላል ብሏል፡፡
ፓርቲው በጅግጅጋ ከተማ ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው ጉባኤ በድጋሚ አቶ አህመድ ሽዴን ሊቀ መንበር፣ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ ኡመርን ም/ሊቀ መንበር አድርጎ መርጧል፡፡
ፓርቲው ስያሜውን በቀየረበት ውሳኔውም ከእንግዲህ በዲሞክራሲና በእኩልነት የሚያምንና በሶማሊኛ ቋንቋ መግባባት የሚችል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲቀላቀለው ጥሪ አቅርቧል፡፡
ፓርቲው በቀጣይ ዋነኛ ትኩረቱን ሀገራዊ መሰረቱን በማስፋት ላይ እንደሚያደርግና  ከሌሎች የሃገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በመጣመርና በመዋሃድ ፖለቲካዊ ሚናውን እንደሚወጣም አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ቀደም ሲል ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፀምበት የነበረውንና በአለመረጋጋት ውስጥ የቆየውን ክልሉን በማረጋጋትና የጉዳት ሰለባዎችን በማቋቋም ሥራ ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡
ከአፋርና ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ከ668 ሺህ በላይ የሚሆኑትን የክልሉን ተወላጆች በማቋቋም ተግባር ላይ እንደሚሰራ ያስታወቀው የክልሉ መንግስት፤ እነዚህን ተፈናቃዮች በ7 የክልሉ ዞኖች በ22 የተመረጡ ቦታዎች እንደሚያሰፍርም ጠቁሟል፡፡ ለስራው ማስፈፀሚያ 4.9 ቢሊዮን ብር መመደቡም ታውቋል፡፡

Read 6439 times