Saturday, 06 April 2019 14:59

“የዶ/ር ዐቢይ መንግስት የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ላይ ማተኮር አለበት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)


•የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል
•ፖለቲካዊ መረጋጋትን በማስፈን የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ይገባል

ቀጣዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ዓመት የስልጣን ዘመን፣ የዜጎችን ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘውን የሸቀጦች የዋጋ ንረት በመቆጣጠርና የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ ላይ ማተኮር አለበት ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡
የታክስ ገቢ ጨምሯል በዚያው ልክ የመንግስት ወጪ ቀንሷል እየተባለ መንግስት በዚህ ዓመት ብቻ ከብሔራዊ ባንክ 23 ቢሊዮን ብር መበደሩ የኢኮኖሚ ሁኔታው በከፍተኛ ተቃርኖ ውስጥ መግባቱን አመላካች ነው ያሉት የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ፤ የስራ አጥ ቁጥር መበራከቱንና በርካታ ፕሮጀክቶች እየተቋረጡ መሆኑን በመጥቀስም መንግስት ከታክስ የሰበሰበውን፣ ከባንክ የተበደረውንና አላስፈላጊ ወጪን በመቀነስ የቆጠበውን ገንዘብ የት አደረሰው? ሲሉ ይጠይቃሉ - ከዚህ አይነቱ ተቃርኖአዊ አካሄድ መላቀቅ እንዳለበት በማሳሰብ፡፡
የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን በተመለከተም ጠ/ሚኒስትሩና የብሔራዊ ባንክ ገዥው የሚገልፁት አሃዛዊ መረጃ የተጣጣመ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሼ፤ በዚህ ጉዳይ ላይም ግልፅ መረጃ መቅረብ አለበት ብለዋል፡፡
በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም እስከ ዛሬ ሃገሪቱ የተጓዘችበት የኢኮኖሚ ስርአት በባለሙያዎች መፈተሽ አለበት የሚሉት የኢኮኖሚ ተንታኙ፤ ምርታማነትን በማሳደግ ላይም ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላው አቶ ሙሼ በአፅንኦት ያነሱት ጉዳይ የወጪ መቀነስንና ቀዳሚ ተግባራትን የመለየት ጉዳይ ነው፡፡ መንግስት አሁን ያለውን ውስን የፋይናንስ አቅም በመሰረታዊ የህብረተሰቡ ችግሮች ላይ ማዋል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ያን ያህል አስጊ ሁኔታ በሌለበት በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ የሃገሪቱን ውስን የፋይናንስ አቅም ማዋል አይገባም የሚሉት አቶ ሙሼ፤ በተለይ የባህር ሃይልን ለማቋቋም አሁን ጊዜው አይደለም ባይ ናቸው፡፡
“የባህር ኃይል ውድ የወታደራዊ መስክ ነው፤ መርከብ መግዛት፣ የባህር ክልል መከራየት፣ መሳሪያና ሎጀስቲክስ ማሟላት አሁን ካለው የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ አይደለም” ብለዋል፡፡
መንግስት በቀጣይ አንድ ዓመት ከሁሉም በላይ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት ላይ ማተኮር አለበት ሲሉ አቶ ሙሼ ይመክራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በቅድሚያ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ የባንክና ኢንሹራንስ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ፣ በተለይ የሃገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ የሚዘውረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይቀርፋል ባይ ናቸው - ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡፡ ለዚህም መንግስት በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግን ቀዳሚ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
በዚያው ልክ የሃገሪቱን የካፒታል ስርአት (የሀብት አጠቃቀም) የሚቆጣጠሩ ብቁ ባለሙያዎችን ከውጭም ቢሆን አፈላልጎ መቅጠር አለበት የሚሉት ምሁሩ፤ ይህም ሀገሪቱ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ጠንካራ የቁጥጥር ስርአት ለማበጀት ይረዳል ይላሉ፡፡
የሃገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማሳለጥ የፖለቲካ ጥመቶች መስተካከል አለባቸው የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ ትክክለኛ የህዝብ አስተዳደርን በወረዳዎችና በክፍለ ከተሞች ደረጃ መመስረት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች ላይ የሚሰሩ ሰዎች የህዝብ አስተዳደር ባለሙያዎች መሆን እንዳለባቸው የገለፁት ምሁሩ፤ ቦታውን መያዝ ያለባቸውም በፖለቲካ ሹመት ሳይሆን በስራ ማስታወቂያ ውድድር ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡
ከምንም በላይ መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ ሰራተኛውንና ጡረተኛውን የህብረተሰብ ክፍል እየጎዳ ያለውን የዋጋ ግሽበት መቆጣጠር ላይ ማተኮር አለበት ያሉት ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ አቢስ ጌታቸው የዋጋ ግሽበቱ መንስኤም ከስር መሰረቱ ተጠንቶ ዘላቂ መፍትሄ ያሻዋል ብለዋል፡፡ ለዋጋ ግሽበቱ ዋነኛ መንስኤ ብሔራዊ ባንክ ለመንግስት በገፍ የሚያበድረው ብር ነው የሚሉት አቶ አቢስ፤ ይህንን በአግባቡ መፈተሽ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ፖለቲካዊ መረጋጋትን በማስፈን በልዩ ትኩረት የውጪ ኢንቨስትመንትን መሳብ ላይም ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ብለዋል - የኢኮኖሚ ባለሙያው፡፡ ፖለቲካዊ መረጋጋት ለማምጣትም የመረጃ ዘዴን ማስፋት፣ ህብረተሰቡን ለጥርጣሬና ውዥንብር ከሚዳርጉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች መቆጠብ ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡

Read 5616 times