Saturday, 06 April 2019 15:04

ጠ/ሚኒስትሩ በቀጣይ ህገመንግስቱን በማሻሻል ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)


ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ አንድ ዓመት በሚኖራቸው የስልጣን ዘመን በዋናነት ህገመንግስቱን በማሻሻል የህግ የበላይነትን ማስከበር ላይ አተኩረው እንዲሠሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የመከሩ ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩ በበኩላቸው፤ ዲሞክራሲን ተቋማዊ ማድረግ ቀዳሚ የመንግስት ተግባር ይሆናል ብለዋል፡፡
ያለፈው አንድ አመት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመን በአመዛኙ ጠንካራና ስኬታማ እንደነበረ ለአዲስ አድማስ የገለፁት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ በቀጣይ መንግስት ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራው የሚገባው ህገ መንግስቱን ማሻሻል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
አሁን ያለው ህገ መንግስት በሀገሪቱ ለሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ችግሮች አንዱና ዋነኛ ምንጭ ነው ያሉት አቶ ሙሉጌታ፤ መንግስት ህዝቡን የሚጠይቅበት እንጂ ህዝቡ መንግስትን የሚጠይቅበት ህገ መንግስት አይደለም ብለዋል፡፡
በቀጣይም መንግስትን ከህዝብ በላይ የሚያደርግ ህገመንግስት ይዞ መጓዝ ይበልጥ የሀገሪቱን ፖለቲካ ያወሳስባል ያሉት ም/ፕሬዚዳንቱ፤ ህገ መንግስቱ የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት መሻሻል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ይህን የአቶ ሙሉጌታን ሃሳብ የሚጋሩት የሠማያዊ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር አቶ አበበ አካሉም፤ የህገመንግስቱ መሻሻል ጉዳይ በቀጣይ አንድ አመት ውስጥ መከናወን አለበት ብለዋል፡፡
ይህን እንደ ሀገር ያላግባባንን ህገመንግስት ይዘን ለምርጫ መቀመጥ አስቸጋሪ ውጤት ይኖረዋል ያሉት አቶ አበበ፤ ህገመንግስቱ መሻሻል የሚችልበትን ዘዴ ማፈላለግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ህገ መንግስቱን ማሻሻል የሚለውን ሃሳብ የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌውም ይጋራሉ፡፡
ህገመንግስቱ የሀገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ምንጭ ነው የሚል አቋም ያላቸው አቶ ልደቱ፤ የለውጥ አመራሩ ህገ መንግስቱን ወደ ማሻሻል እስካልገባ ድረስ የሀገሪቱ የፖለቲካ እርስ በእርስ አለመተማመንና መጠራጠር ይቀጥላል፤ ችግሩ ሠፍቶም ሀገር አልባ ሊያደርገን ይችላል ብለዋል፡፡
“ዜጐች በህይወት የመኖር፣ በመላ ሀገሪቱ ያለ ስጋት ተዘዋውሮ ሀብት የማፍራት ዋስትና ማጣት ውስጥ ናቸው” የሚሉት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ቀጣዩ ጠንካራ የቤት ስራ ሊሆን የሚገባው የህግ የበላይነትን አረጋግጦ፣ ለዜጐች ጥበቃ ማድረግ፣ የዜጐችን ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር፣ ሀብት የማፍራት ዋስትና ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
“በቀጣይ አንድ አመት ውስጥ የአንድም ሰው ህይወት በከንቱ ማለፍ የለበትም፤ አንድም ሰው ከቀዬው በግጭት መፈናቀል አይገባውም” ያሉት አቶ ሙሉጌታ፤ “መንግስት ይሄ እንዳይፈጠር ማድረግ የሚሳነውና ያለፈው አመት ዳተኛነት የሚደገም ከሆነ መንግስት እንደ መንግስት፣ ሀገርም እንደ ሀገር ለመቀጠል ይቸገራል” ብለዋል፡፡
የህግ የበላይነትን ማስከበርና ለማስከበር አስፈላጊውን ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ የፖለቲካ መረጋጋትን ያመጣል የሚሉት የሰማያዊ ፓርቲው አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፤ ጠ/ሚኒስትሩ በተለይ በየክልሉ የተፈጠረውን መድረሻው የማይታወቅ የመንጋ ፖለቲካ ማስቆም አለባቸው ብለዋል፡፡
“ራሳቸውን ቄሮ፣ ኤጄቶ፣ ፋኖ ብለው የሚጠሩ አካላትም በህግና በስርአት መንቀሳቀስ አለባቸው፤ ይህ ካልሆነና እንዳለፈው አመት በቸልታ የሚታይ ከሆነ፣ መንጋዊ እንቅስቃሴዎች የመንግስትን ስልጣን የሚሸረሽሩ አለፍ ሲልም ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ የሚከቱ ይሆናል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
“ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ህግ የማያከብሩ ከሆነም ቆንጠጥ መደረግ አለባቸው” ብለዋል የፓርቲው አመራር - አቶ አበበ፡፡
ባለፈው አንድ አመት የነበረው ፖለቲካዊ ለውጥ በዋናነት በላይኛው አመራር ተንጠልጥሎ የቀረ ነው ያሉት አቶ አበበ፤ እስካሁን የነበረው የለውጥ ሂደት በአሮጌ አቋማዳ አዲስ ወይን ጠጅ ማስገባት ነበር፤ አሁን ግን አቁማዳውም መለወጥ አለበት ብለዋል፡፡
የሚነሱ የማንነትን የክልል ልሁን ጥያቄዎችም እልባት ማግኘት አለባቸው የሚሉት ፖለቲከኛው፤ የፌደራል መንግስቱ በክልሎች የተነጠቀውን የበላይነት አቅም መልሶ ማግኘት እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ፓርቲያቸው በ2012 ዓ.ም ምርጫ መካሄድ አለበት የሚል አቋም እንዳለው የገለፁት የኦፌኮ ዋና ፀሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ በበኩላቸው፤ በቀጣይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የትኩረት አቅጣጫ መሆን ያለበት ለምርጫው ሁኔታዎች የሚመቻቹበትን መንገድ ማደላደል መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ አካላት ላይም የህግ የበላይነት ማስከበር ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባል ያሉት አቶ ጥሩነህ፤ ቀደም ሲልም በህዝብ ላይ ወንጀል የሠሩ ሀይሎችን ለህግ ማቅረብም ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ የቀጣዩ 1 አመት የስልጣን ጊዜ ትኩረታቸውን በጠቆሙበት ንግግራቸው፣ በክልሎች መካከል ያለውን ግጭትና መጠራጠር ማስቆም፣ ዲሞክራሲን ተቋማዊ የማድረግ ስራን ማጠናከር፣ ገለልተኛ  ነፃ ሁሉን በእኩል አይን የሚያዩ ተቋማትን እውን ማድረግ እንዲሁም ሠላም፣ ይቅርታና ፍቅርን በመላ ሀገሪቱ ማስፈን እቅዴ ነው ብለዋል፡፡  

Read 6325 times