Saturday, 06 April 2019 15:06

የሕይወት ዝማሬ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)

 አንዳንዴ ካልሆነ ጧት ወጥቼ ማታ ስለምገባ ከጐረቤቶቼ ጋር ብዙም ትውውቅ የለኝም፡፡ አልፎ አልፎ እያነበብኩ አሊያም እረፍት መውሰድ ፈልጌ ሳረፋፍድ ብቻ ግድግዳ የሚጋሩኝን ሰዎች የቤት ሠራተኛ ደጅ ላይ አገኛታለሁ፡፡ ወይ ምሥር ትለቅማለች አለዚያም በርበሬ ትቀነጥሳለች፡፡ ሲብስ ደግሞ ከሠል ታቀጣጥላለች፡፡
“እንደምን አደርክ?” ትለኛለች፤ በባላገር ቅላፄ፡፡
እኔም ፈገግ ብዬ “አንቺስ እንዴት ነሽ” እላታለሁ፡፡
በአንዳንድ ጓደኞቼ አጠራር፤ ሽንኩርት የምትባል ዐይነት ናት፡፡ እኔ ደግሞ ጥሎብኝ በዕድሜ ለጋ ሴቶች ሽንኩርትነታቸው ሳይሆን ጨቅላነታቸው ያሳዝነኝና ሕይወታቸውን በትንቢት እየለካሁ አዝናለሁ፡፡
“አንዱ ይለክፉትና ታረግዝና … ጐዳና ትወድቅና … ምናምን ምናምን ….” ዕድሌ ነው ምን ላድርግ? ከየት እንዳመጣሁት አላውቅም፡፡ ከእናቴ ይሆን ከአባቴ ቀኝ ቀኙን ለራሴ መመኘት አልፈጠረብኝም፡፡ ይሁን እንጂ እርሷ ግን ሥታየኝ እንደ ሌላው ወንድ ነው፡፡ ይቀላውጣል ብላ ሳታስብ እንደማትቀር ቁልጭልጭ ዐይኖቿ ያወራሉ፡፡
ከሷ ቀጥሎ በረንዳውን ሳቋርጥ፣ ከመታጠፊያዬ ቀጥሎ ያለው ክፍል ያለች ቀይ ወጣት ባለትዳር ሴት ትገጥመኛለች፡፡ ፀጉርዋ ዞማ፣ አዘውትራ መነጽር የምታደርግ ናት፡፡ ገራገርነት የሚታይባት፣ በተስኪያን ወዳድ ዐይነት ናት፡፡ እርሷን ሠላም ማለቴ አይቀርም፡፡ እርሷም ወጧን እያማሳለች ወይም ምድጃዋ አጠገብ በበርጩማ ተቀምጣ፣ ጠበቅ ባለድምፅ፤ “እግዚአብሔር ይመስገን” ትላለች፡፡ የሆነ ልብ የሚነካ አቀራረብ አላት፡፡ እንደ ዕድሜዋ ቀበጥ አይደችለም፤ ሃይማኖታዊ ልጓም ያላትና የተረጋጋች ናት፡፡
እኔ ከሁሉ የምትለይብኝ ማታ ከሦስት ሰዓት በኋላ የምትመጣ፣ አንድ ግድግዳ ተጋሪዬ ናት፡፡ በድምጽዋ በጣም አውቃታለሁ፡፡ በሳቋ ዜማ እደመማለሁ፡፡ በተለይ ስልክ ስታወራ፣ ወንዶችን የምታባብልበት ቅላፄ ይገርመኛል፡፡ ባለቤቷ አብሯት ይኑር-አይኑር የማውቀው ነገር የለም፡፡ አንዳንዴ ግን የወንድ ድምጽ እሰማለሁ፡፡ እስካሁን ግን በዐይነ ሥጋ እርሷንም ወንዱንም አይቼአቸው አላውቅም፡፡
ብዙ ጊዜ ድምፅዋን ብሠማም፣ ወደ ማነብበው መጽሐፍ ወይም ወደማደምጠው ሬዲዮ ቀልቤ ስለሚወሰድ ትኩረት አልሰጣትም፡፡ ያንን ማድረግ የሚያቅተኝ በልጅነቴ አደምጠው የነበረውን የፀሃዬ ዮሐንስ ዘፈን ከዘፈነች ነው፡፡
ከከንፈርዋ ደጃፍ፣ ከጥርሷ የዋለው፣
የእጇ ላይ መፋቂያ እንጃ ምን እንዳለው፣
አፈካው አፈካው አፈካው በነጩ
ሠብራ የምትፍቅበት የወይራ ልምጩ
… ስትል ጣሪያ ቀድጄ ወደ ልጅነቴ እከንፋለሁ፡፡ ወደ ተማርኩባት ትምህርት ቤት፤ ወደ ጓደኞቼ ወደ መምህሮቼ፣ ወደ ሻይ ቤት፣ ወደ ኳስ ሜዳ፣ ወደ ጥናት ሰዓት!
ከጓደኞቼ ጋር ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈን ሴት ተማሪዎችን እየተከተልን ወሬ ስናንሾካሹክ፣ ሻይ ቤት ገብተን ሙዚቃ ስናዳምጥ ትዝ ይለኝና ሁሉን ነገር እተወዋለሁ፡፡ የማነብበውን መጽሐፍ ከድኜ ትዝታዎቼን እፈትላለሁ፡፡ ስፖርት ሻይ ቤት … ሰሜን ሻይ ቤት … ብዙ ቦታ ገብቼ የጧቱን ፉል፣ የማምሻውን ሻይና ቀሽር አስባለሁ፡፡ ትዝታዬ ብዙ … ናፍቆቴም ሩቅ ይሆንብኛል፡፡
ክፍል ውስጥ ወሬ አታውሩ የሚለው ገገማ አለቃ እያናደደን በወረቀት ስንጻጻፍ ቆይተን ወረቀታችንን ይነጥቀን ለመምህር የተሰጠብንን ቀንማ መቸም አልረሳውም፡፡ እኔና ፍቃዱ የሚባል ጓደኛዬ ፍቅር ነገር ጀማምሮን፣ እርሱ አሮጌ አራዳ ያለችውን ዐይነ ትልልቅ ልጅ ብርሃኔን አፍቅሮ፣ እኔ ደግሞ ፀጉርዋ ቁልቁል የተደፋውን ሙሉካ ላይ ወድቄ ስለነበር ፍቅራችን ጨምሮ ነበር፡፡ መንገድም ላይ ሳይቀር ከእርሱ ጋር ማንሾካሾካችን አይቀርም፡፡ እነርሱም እንደኔና እንደርሱ ተጣምረው አይላቀቁም፡፡ ባንድ ቀንበር እንደተጠመዱ በሬዎች ሁሌ አብረው ናቸው፡፡
ታዲያ ያን ዘፈን አልረሳውም፡፡ ፍቃዱ ደግሞ እንደኔው የፀሐዬን
ኧረ ተይ አንቺ ልጅ ያዝ ያዝ ጠበቅ አርጊኝ
ያዝ ያዝ ጠበቅ አርጊኝ
የቀረው ቀርቶብኝ፡፡
… የሚለው ካፉ አይለየውም፡፡ እርሱ በድምጽ ሲያንጐራጉርም ልዩ ነው፡፡ ወፍ ይጥላል፡፡ የኔ ድምጽ ግን ልቅሶ ይሁን ዘፈን አይለይም፡፡ አንዴ እንዲያውም አንዷ ተማሪ “የምታለቅስ ይመስላል…” ብላኝ በሽቄ ነበር፡፡
ደግነቱ እንደዚያ ሰትለኝ ሙሉካ አልነበረችም፡፡ እርሷ ከሌለች ደግሞ ዓለም ሁሉ ያሻውን ቢል ግድየለኝም፡፡ እርሷ ብቻ ናት ለኔ ቁምነገር!
በጣም የሚገርመኝ ደግሞ ልክ ከኔ ክፍል ሦስተኛው ክፍል ላይ ያለችው ሴት በተቃራኒው መዝሙር መክፈቷ ነው፡፡ ይህቺ ጐኔ ያለችው በዐለማዊ ዘፈን ነፍሴን ስትቆላት፣ ያቺኛዋ በመንፈሳዊ ዜማ ታረጋጋኛለች፡፡ ግን እንደዚያም እያሳበደችኝ ዘፈኑን ስታቀብጠው ደስ ይለኛል፡፡ የነፍስ ቅኝቷ ባለ ስንት አውታር እንደሆነ ግራ የሚገባኝ ለዚህ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዜማ ስትሰማ ቅልስልስ ትልና፣ የቀበጠ ሙዚቃ ሲመጣ እንደ ባህር ዳር ቄጠማ መወዛወዝ ያምራታል - ወላዋይ ናት!
አንዳንዴ ይህ ችግር የኔ ብቻ ይመስለኝና ከጓደኞቼ ጋር ስጫወት የእነርሱም ተመሳሳይ እንደሆነ ይነግሩኛል፡፡ በተለይ “ፍቅርና የፍቅር ዜማ ቁርኝት ጥልቅ ስለሆነ፣ ትዝታ በቆፈረ  ቁጥር ብቅ እያለ ይጐነትልሃል” ይሉኛል፡፡
እኔ ግን ሙዚቃዬ መጻሕፍት ናቸው፡፡ አዲስ ሀሳብ ሳገኝ ለኔ አዲስ ሙዚቃ ነው፤ ነፍሴ ትደንሳለች፡፡ አንዳንዴ በደስታ እሰክራለሁ፣ ሌላ ጊዜ በሀዘን እቆራመዳለሁ፡፡ ልብ ወለድ ከማንበብ ይልቅ ታሪክ ሳነብብ ፣ ሰው የሆንኩ ይመስለኛል፤ ዘመንን የመዘንኩ ያህል እንጠራራለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ግን ጐረቤቴ ትዘፍናለች፡፡ ሠራተኛዋ ታስካካለች፡፡ ሌላኛዋ መዝሙር ከፍታ ታንጐራጉራለች፡፡ የማናችን ምርጫ የተሻለ እንደሆነ ለመመዘን የሚያስችል ጥናት ባይኖረኝም፣ ያቺ ፈጣሪዋ ላይ እንደ ሀረግ የተጠመጠመችው ሴት ከሁላችን ይልቅ ደስተኛ እንደሆነች ያስታውቃል፡፡ ሠላምታዋ ጨዋታዋ…
አልፎ አልፎም ቢሆን ይሰማኛል፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ ምሽት ላይ መስኮቴን ከፍቼ ሳይ፣ በሌላኛው ብሎክ ውስጥ ስትደንስ የማያት ወጣት ታስቀኛለች፡፡ በተለይ ከሦስት ሰዓት በኋላ ፀጉሯን ተሰርታ ስትጨርስ … ቁም ሳጥን ፊት ለፊት ቆማ ስትደንስ አይና ለብቻዬ እስቃለሁ፡፡ የዕድሜዋ ፍም ላይ ሳይሆን ነበልባሉ ላይ መጣዷ ስለሚገባኝ በፈጣሪ ስራ እደነቃለሁ፡፡ ሰው እንደሚያያት እንኳ ለማሰብ ዕድል አትሰጥም፡፡ እርሷ የምታየው ራሷን ብቻ ነው፡፡ ስለሌላው ምን አገባት?
እንግዲህ ለኔም ሕይወት ማለት የዚህ ሁሉ ድራማ ትዕይንትና የራሴ አሮጌ ትዝታ ስዕሎች ክምር ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተጠራቅሞ ሲያስቀኝና ሲያስለቅሰኝ ይኖራል፡፡ ተያይዘን ወደ መቃብር ነው! … ሌላ ምንም አዲስ ነገር የለም! ጠቢቡ እንዳለው ነው፡፡ ሕይወት ይኸው ዥንጉርጉር ትዕይንት ነው! የሰራተኛዋ ምስር ለቀማ፣ የግድግዳ ተጋሪዬ ዘፈንና የስልክ ወሬ፣ የሌላኛዋ ጎረቤቴ መዝሙር፣ እኔ የማነብባቸው መጽሐፍት ትረካና ጩኸት! ሌላ ምንም የለም፡፡
ከሁሉ ግን ትዝታ ሃያል ነው፡፡ ናፍቆት ሰደድ እሳት ነው፡፡ በሩቅ ይለበልባል፡፡ የኳስ ሜዳ ጨዋታ … ሌባና ፖሊስ … መሀረቦሽ … ቢስክሌት መንዳት … የትምህርት ቤት ፍቅር! የሙሉካን ሰፈር እንደ መሀረቦሽ ጨዋታ … እንደ ታቦት ንግሥ ነበር የዞርኩት፡፡ ሳያት ልቤን ቅልጥ የሚያደርገው፣ እሳት ከዐይኖችዋ ሲነድዱ ሳያይ ጉልበቴ ሲርድ አገኘዋለሁ፡፡ ሳገኛት የምናገረው ሲጠፋኝ፣ ጓደኛዬ ፍቃዱ ሊረዳኝ ይሞክራል፡፡ ለፍቅር መተባበሩ ራሱ ሳስበው ያስቀኛል፡፡ የታላቅ ወንድሜን መፅሐፍ ከቤት ሰርቄ እየመጣሁ “መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ” የሚለውን ግጥም ሳነብብለት በወረቀት ገልብጦ ለብርሃኔ የሰጣት ገርሞኝ ነበር፡፡ ደግነቱ፣ እርሷም ለሙሉካ አንብባለት ሁለቱም ስቀውብናል፡፡
አንድ ቀን ሬዲዮ ላይ “መሸ ደሞ አምባ ልውጣ” ሳዳምጥ፣ ፍቃዱ ትዝ አለኝና፣ እምባዬ ጉንጬን ላሰው፡፡ ሆዴ ተረባበሸ፡፡ ለነገሩ አሁን አሁን በፌስ ቡክ ላይ ስለምንገናኝ ብዙ እናወራለን፡፡ ከብርሃኔ ጋር ተጋብተው፣ ልጆች ወልደዋል፡፡ ካደግን በኋላ በታይፕ የተፃፈ ግጥም አምጥቶ አንብቦልኛል፡፡ የገብረክርስቶስ ደስታ ነበር፡፡ በኋላ ሚካኤል በዜማ አቀነቀነው፡፡፡ እርሱን በልጅነቴ አግኝቼ ለሙሉካ ብልላት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን ጊዜና ዕድል አይገናኙም እንደሚሉት ነው፡፡
የእግዜር ነገር ሆኖ የፀጋዬን ግጥሞች የያዘ ፍላሽ አግንቼ ቤቴ የከፈትኩ ቀን፣ ነፍሴ ልትወጣ ደረሰች፡፡ ትዝታ የልቤን ጀርባ በጅራፍ ሲዠልጣት መቋቋም አልቻልኩም፡፡ ከዚያ የቆየ የልጅነት ደብዳቤ ፍለጋ ወደ ሻንጣዬ ሄድኩ፡፡
“ውዴ ለመፈቀርም ዕድል ያስፈልጋል፣ እኔ እሥረኛ ነኝ፣ እየወደኩህ አጥቼሃለሁ፡፡ ፀባይህን አውቃለሁ፣ ሁለንተናህ ይመቸኛል፡፡ ግን ዕድላችን … ይህንን ጽፋልኝ ከወላይታ ሶዶ ከወጣች ወዲያ ደግሜ አላየኋትም፡፡ ይህንን ደብዳቤዋን ብቻ አላምጠዋለሁ፤ እደግመዋለሁ፣ እደጋግመዋለሁ፡፡
… ፍቃዱና ብርሃኔ ግን ዕድለኞች ናቸው፡፡ “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሰራው” የሚለው የጠቢቡ ቃል በሕይወታቸው ተፈጽሟል፡፡ የኔና የሙሉካ ግን የማይዘንብ ደመና ሆኖ ቀረ፡፡ የከሰመ ተስፋ፡፡ የሎሬትን ግጥም ድምፁን ከፍ አድርጌ ከፈትኩት፡፡ ያላሰብኩት ነገር ነው፡፡ ያልቆለፍኩትን በር አንድ ሰው በርግዶት ገባ፡፡ ድንጋጤዬ ልክ አልነበረውም፡፡ ከማንም ጋር አልግባባም ነበር፡፡
“ይቅርታ!”
“ግድየለም!” አልኩ በይሉኝታ፡፡
“ይህን ግጥም ልታውሰኝ ትችላለህ!?”
“ይቻላል!”
“ግን ለምን እንባ አነቀሽ?”
አፍጥጣ አየችኝ፤ አፍጥጬ አየኋት፡፡ ህልም አይደለም!
ብቸኝነቴን ነው እኔ የማስታውሰው፣
አልጀመርኩም ነበር ፍቅር ከሌላ ሰው፣
ዛሬ በረታብኝ ድንገት ሳላስበው፡፡
“አውቀኸኛል … ሆዴ የሆነ ነገር ነግሮኝ ነበር … ሙሉካኮ ነኝ!”
“ማን ሊያላቅቀን ይችላል …” ሰራተኛዋ ሮጣ መጣች፡፡
“ኧረረረ …” አልኳት ፈርቼ፡፡
“ተወው ከወንድሜ ጋር ነው የምረኖው … ዛሬማ … የሚገርም ቀን ነው፡፡” መብራት ጠፋ … ሻማ … አመጣን!

Read 2466 times