Saturday, 06 April 2019 15:14

ምትሃተኛ መፍትሄዎች - "ውይይት"፣ "ለውጥ"፣ "ዲሞክራሲ"?

Written by  ዮሃንስ. ሰ
Rate this item
(1 Vote)


• ውይይት፣ በጭፍን ሲጋጋል፣ በራሱ ጊዜ፣... እውነትን፣ ሃሳብንና እውቀትን ይወልዳል? የሚወልድ አስመስለነዋል። ለዚህ በሽታ፣ የፕ/ት ሣህለወርቅ ንግግር ፍቱን መፍትሄ ነው።
• ለውጥ፣ በዘፈቀደ ሲቀጣጠል፣ በራሱ እድል፣... ጠቃሚ፣ የሚያዋጣና የሚያዛልቅ ለውጥ ይሆናል? ይዘት ያላቸው የጠ/ሚ ዓብይ እቅዶች ደግሞ አሉ።  
• ዲሞክራሲ እንደፍጥርጥሩ ሲለቀቅ፣ በራሱ መንገድ፣... ሰላምንና የሕግ የበላይነትን ይሆንልናል? ስልጡን ፓለቲካ ውስጥ የዲሞክራሲ ድርሻ ትንሽ ነው - በሕግ የበላይነት ስር እንደ አንዲት ቅርንጫፍ።
                

"ውይይት"፣ በጭፍን ሲጋጋል፣ በራሱ ጊዜ፣... እውነትን፣ ሃሳብንና እውቀትን የሚወልድ አስመስለነዋል። ግን አይወልድም። ከውይይት በፊት፣ እነ እውነት እነ እውቀት ይቀድማሉ።
መረጃ፣ ማስረጃ እና እውቀት፣.... የውይይት ቅድመሁኔታዎች እንደሆኑ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የምሁራን ስራም እውቀትን ማስፋፋት ነው ብለዋል። የአገሪቱን የአንድ አመት ጉዞ ለመገምገምና ለመመዘን በተዘጋጀው ውይይት ላይ፣ ፕ/ት ሣህለወርቅ ያቀረቡት ንግግር አጭር ቢሆንም፣ ሁልጊዜ ልናገናዝበው የሚገባ ትልቅ መልዕክትን የያዘ ነው። ከእውነትና ከእውቀት ውጭ ሌላ የመግባቢያ መንገድ የለም - በጨለማ የመደናበር፣ የመላተምና እንደአውሬ ለመባላት የመናጨት ጥፋትን ካልፈለግን በቀር።   
አሳዛኙ ነገር፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሃላፊዎችና ምሁራን፣.... "ትምህርት፣ መረጃንና እውቀትን ማንቆርቆር አይደለም" እያሉ ሲያጣጥሉ መክረማቸው ነው። አዲስ ለውጥ እያሉ የሚያወሩትም ይህንኑን ነው - መረጃ አልባና እውቀት የለሽ ትምህርትን የማስፋት ለውጥ።
እና.... እንዲህ ይዘቱ ሳይታወቅ፣ "ለውጥ" በደፈናውና በዘፈቀደ ሲቀጣጠል፣ በራሱ እድል፣... ጠቃሚ፣ የሚያዋጣና የሚያዛልቅ ለውጥ ይሆናል? ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ሳይሆን፣ ወደ ከፋ ገደል የሚያወርድ ቢሆንስ? "ለውጥ" እንዲሁ በደፈናው፣ መልካም ለውጥ ማለት አይደለም። አላማውና ፋይዳው፣ ምንነቱና አይነቱ፣ ግቡ እና መንገዱ፣ አቅጣጫውና እርምጃው መታወቅ አለበት። ሦስት ምሳሌዎችን ላንሳ።
ኢህአዴግ፣ ዘረኝነትና ትርምስን የሚጋብዝ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን ትቶ፣ በአስተሳሰብ ላይ የተዋቀረ አገራዊ ፓርቲ ለመሆን እንዳቀደ ጠ/ሚ ዓቢይ አህመድ ተናግረዋል። ይሄ፣ እጅግ የዘገየ ለውጥ ቢሆንም፣ የሚበጅ ለውጥ ነው። ይሄ፣ ይዘት አልባ፣ ድፍን "ለውጥ" አይደለም።
ኢኮኖሚን የሚሸረሽሩ፣ የድሃ አገር ሃብትን የሚያባክኑ የመንግስት የቢዝነስ ድርጅቶችንና ፕሮጀክቶችን፣ በሽያጭ ወደ ግል የማዛወር የጠቅላይ ሚኒስትሩ እቅድም፣ መልካም የለውጥ እቅድ ነው።
ስራ አጥነት፣ ድህነትና ኋላቀርነት የበረታባት አገር እንደመሆኗ፣ ለኢንቨስትመንት በጣም ምቹ ለማድረግ፣ አላስፈላጊና አጥፊ የመንግስት የዘፈቀደ ቁጥጥሮችንና ገደቦችን ለመቀነስ፣ የተንዛዛና የሚያጉላላ የቢሮክራሲ ትብታብን ለማፍታታት፣ የንብረት ባለቤትነት መብትን የሚያስከብርና የኮንትራት ተፈፃሚነትን የሚያረጋግጥ አስተማማኝ የሕግ የበላይነት ስርዓትን ለማስፋፋት.... እንዳቀዱም ጠ/ሚ ዓብይ ተናግረዋል።
"Ease of doing business" በተሰኘው የዓለም ባንክ መመዘኛ፣ ኢትዮጵያ ከመጨረሻው ተርታ ከሚገኙ አገራት መካከል አንዷ ናት። ወደ መካከለኛ ደረጃ፣ ወደ 100ኛ ደረጃ ለማሻሻል እንዳቀዱ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት። ይሄም፣ ይዘቱና ምንነቱ፣ አላማውና ፋይዳው፣ አቅጣጫውና እርምጃው የሚታወቅ የለውጥ እቅድ ነው። የሚቀረው ነገር፣ በብልሃትና በትጋት የማሳካት ጥረት ነው። እነዚህን የመሳሰሉ ለውጦች መልካም ናቸው።
የመንግስት ስርዓትን በተመለከተም፣ ጠ/ሚ ዓብይ እቅዳቸውን ሲገልፁ፣ ስለተቋማት ግንባታ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ይህ የለውጥ እቅድ፣ በደንብ የተብራራ ባይሆንም፣ ቁምነገር ያዘለ የለውጥ ሃሳብ ነው። መንግስታት በተለዋወለጡ ቁጥር፣ ወይም ፓርቲዎች ስልጣን ላይ በተፈራረቁ ቁጥር፣ ተቋማትን እየናዱ ከባዶ የመገንባት ልማድ፣ መቅረትና መለወጥ እንዳለበት ገልፀዋል። ትክክል ብለዋል። ነገር ግን፣ የሚቀሩ ነገሮች አሉ።
አንደኛ ነገር፣ የመንግስት ተቋማት፣ "ዋነኛ፣ አስተማማኝና የሚያዛልቅ ሥረመሠረት"፣ ሌላ ሳይሆን "የሕግ የበላይነት" እንደሆነ፣ ገና በግልፅ ጠርቶና ነጥሮ አልወጣም። ብዙ ጊዜ ሲደጋገም የምንሰማው፣ "ገለልተኛ" የሚለው ቃል ነው። ገለልተኛነት ግን፣ ዋነኛው የተቋማት ባሕርይ አይደለም። ከብዙ ተቀጥላዎችና ቅርንጫፎች መካከል አንዱ ነው። ይልቅስ፣ ማንኛውም የመንግስት ተቋም፣ የሕልውናው መነሻና መድረሻ፣.... "ሕግና ስርዓትን አክብሮ"፣ "የእያንዳንዱን ሰው መብት ለማረጋገጥ" የሚያስችል፣ "ሕግና ሥርዓትን ማስከበር" ነው።
በአጭሩ፣ የሕግ የበላይነትን አክብሮ ማስከበር፣ የመንግስት ተቋማት ዋነኛ ባሕርይ መሆን ይገባዋል። ይህንን የመንግስት ተቋማትን አስኳል በሚያስረሳ ሁኔታ፣.... "ገለልተኛ" የሚለው ቃል፣ እንደ ምትሃተኛ መፍትሄ መግነኑ፣ ብዙም አያዛልቅም። በጊዜ ካልታረመም፣ መጨረሻው አያምርም።
ሁለተኛ ነገር፣ መንግስት ሲቀየርና ፓርቲዎች ሲፈራረቁ፣ ሳይፈርሱ የሚቀጥሉ የመንግስት ተቋማትን ማጠናከርና መገንባት፣.... ተገቢ የመሆኑን ያህል፣ "ከዲሞክራሲ" ጋር እንደሚጋጭ በቅጡ መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህንን በውል አለመገንዘብ፣ ራስን ጠልፎ እንደመጣል ይቆጠራል። ለምን? "ለዲሞክራሲ" ሲባል፣ "የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ" ተብሎ፣ ወይም "ለውይይት" እና "ለአሳታፊነት" በሚሉ ሰበቦች፣ እንደቀድሞው፣ ተቋማትን እያፈረሱ ከዜሮ የመጀመር አዙሪቱ ይደገማል።
አዎ፣ ሳይፈርሱ የሚዘልቁ ተቋማት፣.... "ከሌጣ ዲሞክራሲ" ጋር አይጣጣሙም። ግን፣ የሕግ የበላይነትም "ከሌጣ ዲሞክራሲ" ጋር ይጋጫል። ይሄ፣ የዲሞክራሲን አደጋ ያሳያል እንጂ፣ ተቋማትንና የሕግ የበላይነትን ቸል እንድንል ሊገፋፋን አይገባም። ከዲሞክራሲ በፊት፣ የሕግ የበላይነት ይቀድማል፣ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብሩ ተቋማትም ከዲሞክራሲ ይቀድማሉ። የዲሞክራሲን ድርሻ ለመገደበም ይጠቅማሉ።
በሌላ አነጋገር፣ አብዛኛው መራጭ፣ ወይም በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲ ያሻውን ነገር ማድረግ አይችልም። 99 በመቶ መራጭ ሕዝብም ሆነ በ99 በመቶ ያሸነፈ ፓርቲ፣.... 1 በመቶው መራጭም ሆነ የተሸነፈ ፓርቲ፣.... ሁሉም ሕግን የማክበር ግዴታ አለባቸው። የብዙኃን የበላይነት ወይም የአሸናፊ ፓርቲ የበላይነት ሳይሆን፣ የሕግ የበላይነት ነው ሥልጡን ፓለቲካ።
በአጭሩ፣ ዲሞክራሲ፣.... "ዋነኛ፣ አስተማማኝና ዘላቂ የመንግስት ሥርዓት ሥረመሰረት" አይደለም። ከተቀጥላዎችና ከቅርንጫፎች መካከል አንዱ ነው። ጤናማ ትርጉም የሚኖረው፣ በሕግ የበላይነት ሥርዓት ስር በትንሹ የተገደበ ድርሻ ሲኖረው ብቻ ነው።  የመንግስት ሥርዓት ዋነኛው ስልጡን ሥረመሰረት የሕግ የበላይነት ነውና።               
አሁን አሁን ግን፣ ትልቁ ነገር እየተረሳ፣ ውይይትና ለውጥ ከሚሉ ቃላት ጋር ዲሞክራሲ የሚለው ቃል፣ ከሁሉም በላይ ገንኖ፣ የሁሉም ነገር መፍትሄ እየመሰለብን ነው። ነገር ግን ዲሞክራሲ እንደፍጥርጥሩ ሲለቀቅ፣ በራሱ መንገድ፣... የሰላም አገር፣ የሕግ የበላይነትና መከባበር አይሆንልንም። ይዘት አልባ ለውጥም፣ በድፍኑ መልካም ለውጥ ማለት አይደለም።
እውነት የለሽና እውቀት አልባ ውይይትም፣ መናቆርን እንጂ መግባባትን አይፈጥርም። አዳሜ ግን፣ በደፈናው "ውይይት" ሁሉንም ነገር የሚፈውስ ተዓምር የሚሆንልን ያስመስላል። የትምህርት ሚኒስቴር ሃላፊዎችና ምሁራን ጭምር፣ እውነተኛ መረጃን ማናናቅና እውቀትን ማጣጣል፣ አዲስ የአዋቂነት ምልክት አስመስለውታል። "የመረጃ ችግር የለም"፣ "ትምህርት እውቀትን ማንቆርቆር አይደለም" እያሉ መግለጫ ሲሰጡና ሲደሰኩሩ ነው የከረሙት።
እናስ ትምህርት ምንድነው? "ትምህርት ውይይት ነው"። አስተማሪስ? "አወያይና የውይይት ተሳታፊ" ነው ይላሉ። እንዲያውም፣ አስተማሪው፣ ከምር አስተማሪ አይደለም። ከተማሪዎቹ ጋር እኩል ነው። ይማማራል እንጂ አያስተምርም ብለዋል - የትምህርት ፍኖተ ካርታ አዘጋጆችና መሪዎች። እውነተኛ መረጃንና ቅጥ ያለው እውቀትን የሚያጣጥል፣ "የውይይት አምልኮን" ይበልጥ ለማስፋፋት ነው እቅዳቸው (በዚሁ አቅጣጫ ከእስከዛሬው የከፋ ውድቀትን ለማስፋፋት!)።
ትምህርት ሚኒስቴር፣ መረጃ የለሽና እውቀት አልባ ውይይትን ለሚሊዮን ሕፃናት እለት በእለት ከአመት አመት ያለማቋረጥ እየሰበከና እያስፋፋ፣.... ፕሬዚዳንቷ፣.... "መረጃና ማስረጃ ይቀድማል። የምሁራን ስራ እውቀትን ማስፋፋት ነው" የሚል ሃሳብ አንድ ቀን ቢናገሩ ምን ዋጋ አለው? በነጋታው ይዘነጋል። እናም እንደወትሮው፣ በአዲሱ ፈሊጥ፣ "በውይይት አምልኮ"፣ አገር እየተሳከረ ቁልቁል ይወርዳል።       "አእምሮ ቢስ፣ እውነት የለሽ፣ እውቀት አልባ.... ውይይት".... በራሱ ጊዜ የሁሉም ነገር መፍትሄ ሆኖ እየታያቸው ነው? ወይስ ባይታያቸውም እንኳ፣ እያስመሰሉ? በቃ፣ የሁሉም ነገር መፍትሄ፣.... "ውይይት፣ ለውጥ፣ ዲሞክራሲ" ነው? ሌላው ሁሉ፣ ከንቱ ጭንቀት፣ ከንቱ ልፋት ነው? እንዲህ በቀላሉ፣ ከሃሳብና ከጥረት መገላገል ይቻላል ማለታቸው ነው?
"...If young heads were not too clever
oh, they would be young forever."... የሚሉ ነው የሚመስሉት። መንገዱ ሁሉ አልጋ ባልጋ ነው - ያለአእምሮና ያለ እውነት፣ ያለ ሃሳብና ያለ እውቀት።
Empty heads and tongues a-talking
make the rough road easy walking.

ሃሳብ የለሽ "ውይይት"፣.... አላማ የለሽ "ለውጥ"፣.... ስርዓት የለሽ "ዲሞክራሲ".... የሚሉ መፈክሮችን ወይም የብዥታ ምኞቶችን እንዲሁ እልፍ ጊዜ ስንደጋግማቸው ብንውል፣ በአንዳች ምትሃት ሁሉም ነገር ይሰምራል? አይሰምርም። ለዚህም ነው፣.... በየጊዜው "ውይይት፣ ለውጥ እና ዲሞክራሲ".... ተብለው የሚመጡ "ትግሎችና አመፆች" ወይም "አዋጆችና ሹምሽሮች"፣.... ብዙም ሳይቆዩ፣.... ወደ ተሳከረ የውድቀት ለውጥና ወደ ትርምስ የሚያመሩት።
It will all be well, no need of care,
Though how it will, and when and where,
we can not see, and can't declare.
In spite of dreams, in spite of thought,
it is not in vain, and not for naught,
The wind it blows, the ship it goes
Though where and whither, no one knows.
(Arthur Hugh Clough)
    

Read 6368 times