Saturday, 06 April 2019 15:15

‘መቶ ሰባት የሆነው በምክንያት ነው’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)


"ስሙኝማ…‘የታሪክ ሊቅነት’ ‘የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተንታኝነት’ ምናምን የመሳሰሉ ኒሻኖች እኮ ሁላችንም በዜግነታችን የተሰጠን መብት ነገር ሆኗል፡፡ የምር ግን… አንዳንዴ በምንሰማቸው በምናነባቸው ‘የታዋቂ ሰዎች’ አስተያየቶች መገረም ብቻ ሳይሆን… እየተሳቀቅን ነው፡፡ ወጣቶቻችን “ኸረ ሼም ይያዝህ” የሚሉት እኮ የእውነት ግራ ቢገባቸው ነው፡፡--"

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ከድሮ የሀይ ስኩል ‘ገርልፍሬንድ’ ምናምን ነገር የነበረች እንትናዬ ጋር ድንገት መንገድ ላይ ትገጣጠማላችሁ…ከሁለት አሰርት በኋላ፡፡
“አንተ!”
“አንቺ!”
ቃልአጋኖ ያስፈልጋል፡፡ ልክ ነዋ…ታዲያ ከትዌንቲ ምናምን ዓመት በኋላ “ሁትስአፕ!” ልንባባል ነው!
“አንተ! ብዙ ጊዜ ሆነን አይደል?”
በጣም ብዙ ጊዜ እንጂ!
“በጣም ቆይቷል…እዚህ አገር ያለሽ አይመስለኝምነበር፡፡”
“አስር አስር፣ አስራ አምስት ዓመት አይሆነንም?”
በህግ! በህግ አምላክ! የምን አስራ አምስት ዓመት ነው! እሷዬዋ አስሩን ዓመት ኮማ ውስጥ ነበረች እንዴ! አሁን ሀያ አምስት ትልቅ ቁጥር ሆና ነው አስሩ የሚገነደስላት! ለነገሩ ‘ሎጂኳማ’ ባናውቃትም እንጠረጥራለን፡፡ ለምን መሰላችሁ…እቅጯ ሀያ አምስት ከተጠራች ሌላ ስሌት ሊገባ ነው፡፡ እኔ የምለው…እሷዬዋ ግማሽ ምአተ ዓመት ልትደፍን ጫፍ ሆና፣ እንዲህ ‘ቺክ’ እንደሚሏቸው ቁልጭ ማለት አለ! (ይሄኔ እኮ ጓደኞቿ ኤፍ.ኤም ላይ የሚመርጡላት ዘፈን የማዶና ‘ላይክ ኤ ቨርጂን’ የሚለውን ሊሆን ይችላል፡፡ ለነገሩ ቢመረጥላትም ላይገርም ይችላላ፡፡ “የወሰደ መንገድ ያመጣል መልሶ፣” እንደሚባለው… በዚህ ዘመን ‘የሄደ ነገርዬ’… አለ አይደል… ተመልሶ የማይመጣበት ምክንያት የለም፡፡
“እንዴት ነው ትዳር ምናምን...” ትሉና አራት ነጥቡን ለእሷ ትተዋላችሁ፡፡
“አሁንማ ሦስትልጆች አሉኝ፡፡”
ሦስት! የሀይ ስኩል ‘ሜሞሪ’ እንደገና ብቅ ትላለች… (እኛ፣ ሰፈር እንኳን ጡረታ የወጡት የእንትን ሆስፒታል ሲስተር ምናምን የነበሩት ጩጨዎቹ  ሩጫቸውን ሳይጀምሩ ባያቋርጧቸው ኖሮ፣ እሷዬዋ ይህኔ የአምስት ልጆች እናት ትሆን ነበር፡፡ (ዘንድሮ ‘ሞርኒንግ አፍተር’ ምናምን የሚሉት እንደ ሽምብር ዱቤ የሚቸረቸር ነገር መጣና ጡረታ የወጡ ሲስተሮች ምንቸት ሊወጣ!)
“አንተስ!”…”
አንተስ! የምን አንተስ ነው “እ…”
“ብቻ አላገባሁም፣ አልወለድኩም እንዳትለኝ!”
ሴትየዋ ምን ነካት! የምን ድብልቅ አረፍተ ነገር ምናምን ጥያቄ ነው፡፡ ማግባትና መውለድን አትለይም እንዴ!
“እ…ምን መሰለሽ…”
“ይቅርታ ልትነግረኝ ካልፈለግህ ተወው…”
“ኖ…ኖ…እንደሱ አይደለም፡፡ ትዳር ነበረኝ ግን ተፋትቻለሁ…”
“አፈር በበላሁ!”
እንዴ! እኔ በተፋታሁ የምን ‘አፈር’ ቅብጥርስዮ ነው! አፈር መብላት ከፈለገች ለምን ሰበብ ታደርገኛለች፡፡ በራሷ ሰበብ አትቅመውም!
(የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል….እስቲ ለመጨረሻ ጊዜ “አፈር በበላሁ” የሚለውን ሀረግ የሰማችሁበትን ጊዜ አስታውሱ፡፡ ቀጥሎ “አፈር ብላ!” “አፈር ትብላ!” ምናምን የሚለውን በሳምንት ስንት ጊዜ እንደሰማችሁ አስተውሉ፡፡ “ለውጥማ አለ…” የሚለውን ሀረግ እንድንጠቀም ይፈቀድልንማ!)
አሁን ለምሳሌ በፊት አንድ ‘ቦተሊካ’ ፓርቲ ይመሰረታል…ወይም ተመሰረተ ይባላል፡፡ (‘ቡድን’ ለማለት ተፈልጎ ነው፡፡ ልክ ‘የበራሪ ኮከብ የእግር ኳስ ቡድን’ እንደሚባለው፡፡) እናማ መስራቾቹ አንድ ላይ ይሰነብቱና በሆነ ምክንያት ይጣላሉ፡፡ አንደኛው ቡድን በር ይቆልፍና ለዘበኛው ትእዛዝ ይሰጣል…ወይ ደግሞ በር መቆለፍ ሳያስፈልገው ማህተም ያሠራል…እናላችሁ እኛ ዘንድ የፖለቲካ ቡድኖች ለመፍረስ ወይ በር መቆለፍ ወይ ማህተም ማሠራት ይበቃል፡፡  አናላችሁ…ያለ‘ፖለቲካፕሮግራም’ፖለቲካፓርቲበመመስረትታሪክየሠሩት፣የድራፍትቡድንከሚፈርስበትበቀለለመልኩይፈርሳሉ፡፡
እናላችሁ… የአንድ ‘ቦተሊካ’ ቡድን ፈንጋይና ተፈንጋይ ከጊዜያት በኋላ የሆነ ስፍራ ይገናኛሉ፡፡ እንደ ‘ገርልፍሬንድዬዋና እሱዬው ቃልአጋኖ አያስፈልጋቸውም፡፡
“እዚህ አገር አለህ እንዴ!”
“አለን፣ የት እንሄዳለን ብለህ ነው…”
“እሺ፣ ፖለቲካ እንዴት ነው?”
ምጸት መሆኗ ነው፡፡ ልክ ነዋ…“ኑሮ እንዴት ነው?” ሳይል ምን ‘ቦተሊካ’ ላይ ያንጠለጥለዋል!
“ከፖለቲካ ወጥቻለሁ…”
“ምን! የራሴን ፓርቲ እንኳን አላቋቋምኩም እንዳትለኝ!”
(ይኸው…ይኸዋ! እናማ…እዚህ አገር ፖለቲካ ፓርቲ ከመመስረት ይልቅ እቁብ ማቋቋም  ይከብዳልየሚባለውእኮለዚህነው፡፡)
መቶ ሰባት የሆነው በምክንያት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
 
እናላችሁ… እሱና የጥንት ‘ገርልፍሬንድዬዋ’ ደህና ሲያወሩ ቆይተው ምን ትዝ ቢለው ጥሩ ነው…ሀይ ስኩል የተፈነገለበት! (ቦተሊከኞቻችን እንደሚፈነጋገሉት ማለት ነው፡፡) ቅድመ ማስጠንቀቂያ የለ፣ በትንሽ ልጅ የሚላክ… “ታላቅ ወንድሜ ስለተቆጣ ከአንግዲህ አንገናኝም፣” ብሎ ብጣሽ ወረቀት የለ… ብቻ አንድ ቀን ሲኒማ አምፔር ጥግ ወንበር ላይ ከሌላ ‘ክላስሜታችሁ’ ጋር የ‘ኪሶሎጂ’ የመሰክ ጥናት የሚመስል ሲያደርጉ እጅ ከፍንጅ! (አንድ ሰሞን ከሆነ አለሁ፣ አለሁ ሲልበት ከነበረ ‘የፖለቲካ ስብሰብ’ የጠፋ ሰው ይቆይና ከሌሎቹ ጋር ብቅ ይል ነበር፡፡ “ስዘል ወለም ቢለኝስ!”፣ “አንሸራቶኝ ወገቤ ቢቀጭስ!”፣ “ቡአ ቢወርደኝስ!” የሚል ስጋት ሳይኖር፣ ከአንዱ ወደሌላው የሚዘለልበት የእኛ አገር ፖለቲካ ነው፡፡)
የምር አንዳንዴ እውቅና ያልተሰጠው ጉደኛ ‘ስታንድአፕ ኮሜዲ’ ነገር የሚካሄድባት አገር ናት፡፡ አይደለም በትውልዶች ወደኋላ ሄደን፣ ስለቤተሰባችን ታሪክ መናገር እንኳን ሳንችል፣ ስለ 1880ዎቹ የአገራችን ታሪክ ትንታኔ የምንሰጥ “ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም” የምንል እኮ የብሮድካስት አየር ሰዓቱንና የጋዜጣና የመጽሄት አምዶችን  የተቆጣጠርንበት ዘመን እኮ ነው!
ስሙኝማ…‘የታሪክ ሊቅነት’ ‘የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተንታኝነት’ ምናምን የመሳሰሉ ኒሻኖች እኮ ሁላችንም በዜግነታችን የተሰጠን መብት ነገር ሆኗል፡፡ የምር ግን… አንዳንዴ በምንሰማቸው በምናነባቸው ‘የታዋቂ ሰዎች’ አስተያየቶች መገረም ብቻ ሳይሆን… እየተሳቀቅን ነው፡፡ ወጣቶቻችን “ኸረ ሼም ይያዝህ” የሚሉት እኮ የእውነት ግራ ቢገባቸው ነው፡፡
የምር ግን…ዘንድሮ ፖለቲካው በሉት፣ ምኑ በሉት…ታስቦ የተደረሰበት ወይም የተያዘ ‘አቋም’ ምናምን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ትናንት የሆነ ነገር “አቋሜ እንደዚህ ነው” ብሎ የተናገረውን ሳምንት ሳይሞላው፣ ተቃራኒውን ሀሳብ “አቋሜ እንዲህ ነው” ቢል “እንዴት ሀሳብህን ልትለውጥ ቻልክ?” ብሎ የሚሞግት የለም፡፡ እንተዋወቃለና!
እነ አሜሪካን በመሳሰሉት ሀገራት በስድሳ ዓመቱ ለምክር ቤት መቀመጫ ሲወዳደር፣ የአምስት ዓመት ልጅ ሳለ በኳስ የጎረቤት መስኮት የሰበረው ወሳኝ አጄንዳ ሆኖ ሊመጣበት ይችላል…ሜክ ኦር ብሬክ የሚሉት አይነት፡፡ እኛ ዘንድ የዛሬ ዓመት ከመንፈቅ መንገድ ሊያስለቅቀን ምንም የማይቀረው ሰው፣ ዛሬ ትንፋሽ እስኪያጥረን አንቆ ሲመጨምጨን “ኦንሊ ኢን አወር ካንትሪ” ብለን እናልፈዋለን፡፡
መቶ ሰባት የሆነው በምክንያት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3323 times