Saturday, 06 April 2019 15:42

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(0 votes)

                   ብሩህ ዓለምነህ  (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)

በዛሬው ፅሁፌ፣ ዴቪድ ሂዩምና ኢማኑኤል ካንት የተባሉ የ18ኛው ክ/ዘመን ፈላስፎች፣ የሰው ልጅ አእምሮ ህወስታዎችንና ፅንሰ ሐሳቦችን እንዴት እንደሚያቀነባብር የፃፉትን ሐሳብ በማየት፣ ኢትዮጵያዊው የአእምሮ ጠባይ በዚህ ፍልስፍና ውስጥ ስፍራው የቱ ጋ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡
ፍልስፍና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካበቀላቸው ቅርንጫፎች ውስጥ አንደኛው የሰውን ልጅ ‹‹አእምሮ›› ለብቻው የጥናቱ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ ማምጣቱ ነው፡፡ ይህ ቅርንጫፍ (Philosophy of Mind) በዋነኛነት አእምሮ በህወስታችን ያገኛቸውን መረጃዎች እንዴት እንደሚያቀነባብር፣ እንዲሁም አእምሮ ከአካልና ከአካባቢው ጋር ያለውን መስተጋብር የሚያጠና ነው፡፡ የአእምሮ ፍልስፍና አሁን ላይ ራሱን የቻለ የፍልስፍና ቅርንጫፍ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን፣ የሥነ ዕውቀት ፍልስፍና አካል ተደርጎ ሲካተት ቆይቷል፡፡
በዚህ የፍልስፍና ቅርንጫፍ ውስጥ ከሚጠኑ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ የ‹‹መንስኤ›› ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በነበረው ተለምዷዊ ህይወት ውስጥ፣ ሁለት ክስተቶች በጊዜና በቦታ ተከታትለው ሲከሰቱ፣ አእምሮ የመጀመሪያውን ክስተት በመንስኤነት፣ ሁለተኛውን ክስተት ደግሞ በውጤትነት ይመዘግበዋል፡፡ ይሄንን ልማዳዊ አስተሳሰብ ሳይንሱም ተቀብሎት በርካታ እመርታዎችን አስመዝግቦበታል፡፡
ስኮትላንዳዊው ፈላስፋ ዴቪድ ሂዩም ግን ሳይንስ የቆመበትን ይሄንን ‹‹ተለምዷዊ›› የመንስኤ - ውጤት ማብራሪያ አፈራረሰው፡፡ የሂዩም ዋነኛ ጥያቄ ‹‹ሁለት ክስተቶች በቦታና በጊዜ የተከታተሉት በአጋጣሚ ቢሆንስ?›› የሚል ነው፡፡ እናም ተቃውሞው ‹‹አእምሮ አጋጣሚ የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ ሁለት ክስተቶች ‹በአጋጣሚ› እንኳን ተከታትለው ቢከሰቱ፣ አእምሯችን ክስተቶቹን እውነተኛ መንስኤና ውጤት አድርጎ ነው የሚመዘግበው›› የሚል ነው፡፡ ችግሩ ግን፣ የመጀመሪያው ክስተት ሁለተኛውን ክስተት ‹‹መንስኤ ሆኖ ሲያስገድደው›› በአይናችን ማየት አለመቻላችን ነው፡፡በዚህ የሂዩም ድምዳሜ መሰረት አእምሯችን ለመንስኤ ህወስታ (Sensation) ስለሌለው፣ የሰው ልጅ መንስኤን የማወቅ ተስፋ የለውም፡፡ ይሄ ‹‹መንስኤ በሰው ልጅ አእምሮ ሊታወቅ አይችልም›› የሚለው የሂዩም ድምዳሜ፣ነገሮችን ሁሉ ‹‹ተአምራዊ›› ከሚያደርገው የሀገራችን አእምሯዊ ጠባይ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡
አካባቢያዊ ክስተቶችን በተመለከተ የሀገራችን አእምሯዊ ጠባይ ‹‹ከያሬዳዊው የተአምራዊነትና የብህትውና ባህል›› የወረሰው ሁለት ድምዳሜዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው፣ ክስተቶችን ለየብቻ ነጣጥሎ የሚመለከታቸው መሆኑ ነው፡፡ ክስተቶቹ በቦታና በጊዜ ተከታትለው ቢከሰቱ እንኳን በመንስኤ - ውጤት የተፈጥሮ ህግነት አስተሳስሮ አይመለከታቸውም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ክስተቶችን በመንስኤ - ውጤት የተፈጥሮ ህግ አስተሳስሮ መመልከት አለመቻሉ እያንዳንዱ ክስተት የማይታወቅ መለኮታዊ መንስኤ እንዳለው እንዲያስብ አድርጎታል፡፡ እናም፣ ለሀገራችን የአእምሮ ጠባይ ይሄ ‹‹ተአምራዊነት›› ለክስተቶች ብቸኛው ማብራሪያ ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል፡፡
በዚህ ‹‹ተአምራዊ›› የአእምሮ ጠባይ ላይ ነበር ያሬዳዊውን ሥልጣኔ ለማዘመን አፄ ምኒሊክ የአውሮፓን ቴክኖሎጂ በብዛት ያስመጡት፡፡ በክፍል-15 ፅሁፌ ላይ እንደገለፅኩት፣ ቴክኖሎጂን ከላይ ከላይ ስናየው የቁስ አካል ስብስብ ቢመስለንም፣ ሆኖም ግን ቴክኖሎጂው የሚሰራበት መርህ አመክኖያዊ ነው፡፡ እናም አፄ ምኒሊክ ከቴክኖሎጂው ጋር የአውሮፓን ህሊና (አመክንዮ) አስመጥተው በኢትዮጵያውያን ‹‹የተአምራዊነት›› አእምሯዊ ጠባይ መካከል አስቀመጡት፡፡ እናም፣ ሀገሬው ምን ጉድ መጣብኝ ብሎ ተቸገረ!!
አንድ የአፄ ምኒሊክ ባለሟል መነጋገሪያውን አንስቶ ወደ ንጉሱ ስልክ ደወለ፡፡ በሽቦው ውስጥ የንጉሱን ድምፅ ሰማ፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? ህዝቡ፤ ‹‹ድምፅን በሽቦ ውስጥ አስገብቶ የሚገፋው ሰይጣን ነው›› አለ፡፡ ውሃ በኃይል እየተገፋ በብረት ዘንግ ሽቅብ ወጥቶ ሲፈስ ሀገሬው ሁሉ አየ፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? ለዘመናት በተአምራዊነት ትርክት ሲቀረፅ የኖረው አእምሯችን፤ ይሄንን ክስተት እንዴት እውቀት አድርጎ ይቀበለው? ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የሀገራችን አእምሯዊ ጠባይ ሌሎች ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ክስተቶችን (ዝናብና ጎርፍ፣ ነፋስና ድርቅ፣ ወረርሽኝናበሽታ፣ ውልደትና ሞት፣ ድህነትና ብልፅግና) ሳይቀር ‹‹ተአምራዊ›› አድርጎ ያስባቸዋል፡፡ እናም፣ አፄ ምኒሊክ ያንን ሁሉ ቴክኖሎጂ ያስመጡት ለሁሉም ነገር ‹‹ተአምራዊ ማብራሪያ›› በሚሰጥ ማህበረሰብ ውስጥ ነው፡፡
የአፄ ምኒሊክ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ዋነኛ ግድፈቱ፣ የአውሮፓን ቴክኖሎጂ ከአመክኖያዊ ማብራሪያው ገንጥለው ማስመጣታቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ቴክኖሎጂው ከአውሮፓ፣ ማብራሪያው ደግሞ ከኢትዮጵያ ሆነ፡፡ እናም፣ የአውሮፓ ቴክኖሎጂበኢትዮጵያውያን የተአምራዊነት ማብራሪያ እየታጀበ ሀገር የማዘመን ሙከራውን ተያያዘው፡፡
ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የተአምራዊነቱ ባህል፣ሀገሬው በሙሉ ንጉሱ ባስመጡት ቴክኖሎጂ ከመደነቅ ይልቅ፣ ተጠራጣሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይሄም፣ ቴክኖሎጂው የሚሰራበትን ሳይንስ ለማወቅ ከመጓጓት ይልቅ እንዲርቁትና በሰይጣንነትም እንዲፈርጁት አድርጓቸዋል፡፡ ይህ የሀገራችን ተአምራዊ የሆነ የመንስኤ ፅንሰ ሐሳብ (Mystical Concept of Causation) የካንትን የአእምሮ ፍልስፍና የሚገዳደር ነው፡፡
ጀርመናዊው ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት ለዴቪድ ሂዩም ባዘጋጀው መልስ ላይ፣ አእምሮ አካባቢውን ለመረዳት የሚያልፍባቸውን ሂደቶች በሙሉ ምንም ዓይነት የዘመንና የባህል ተፅዕኖ የማይነካቸው ‹‹ሁለንተናዊ›› (Universal) ክስተቶች እንደሆኑ አድርጎ ፅፏል፡፡ ካንት ለዚህ ድምዳሜው እንደ ማስረጃ አድርጎ የሚያቀርበው ደግሞ የሰው ልጅ አእምሮ መንስኤንና ውጤትን የሚያያይዝበትን መንገድ ነው፡፡
እንደ ካንት አመለካከት፣ ለመንስኤ ህወስታና አመክንዮ ባይኖረንምችግር የለውም፡፡ ምክንያቱም፣ ‹‹መንስኤ›› በውጫዊ ክስተቶች መካከል የሚፈጠር ንክኪ ሳይሆን አእምሯዊ ጠባይ ነው፡፡ ይሄም አእምሯዊ ጠባይ የሚፈጠረው አእምሮ ተፈጥሮን ለመረዳት በሚያደርገው ሂደት ውስጥ ነው፡፡ እናም፣ አእምሮ በቦታና በጊዜ ተከታትለው የሚከሰቱ ክስተቶችን የሚረዳው በመንስኤ - ውጤት ህግ የተሳሰሩ አድርጎ ነው፡፡በካንት ፍልስፍና መሰረት፤ የውጭው ዓለም የአእምሯዊ ጠባይ ነፀብራቅ ነው፤ "we impose the law of cognition on nature"በዚህ አባባል መሰረት፤የተፈጥሮ ህግ ከአእምሮ ጋር የተስማማ ነው፡፡ ይሄም ማለት፣ ተፈጥሮየሚሰራበትህግ (ሎጂክ) እና አእምሯችንህወስታዎችንና ሐሳቦችንየሚያቀነባብርበትመንገድአንድዓይነት ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም፣ የመንስኤ ፅንሰ ሐሳብ አእምሯዊ ቢሆንም በተፈጥሮ ህግነትም ይኖራል፡፡
የካንት ድምዳሜ ከሀገራችን አእምሯዊ ጠባይ ጋር ቅራኔ ውስጥ የሚገባው እዚህ ላይ ነው፡፡ ካንት፣ ‹‹በቦታና በጊዜ ተከታትለው የሚከሰቱ ክስተቶችን በየትኛውም ባህልና ዘመን ላይ የሚኖር አእምሮ ሁሉ በመንስኤ - ውጤት አመክንዮአዊ ህግነት ይተረጉማቸዋል›› ቢልም፣ የሀገራችን አእምሯዊ ጠባይ ግን ተከታታይ ክስተቶችን ነጣጥሎ ስለሚመለከታችው መንስኤያቸውን ተአምራዊ አድርጎ ነው የሚተረጉመው፡፡ እናም፣ የካንት ስህተት፣ አእምሯዊ ጠባይ በባህል ተፅዕኖ ሥር ሊወድቅና ክስተቶችን የሚተረጉምበት መንገድ ሊለያይ እንደሚችል አለመገንዘቡ ነው፡፡
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1021 times