Saturday, 06 April 2019 15:46

የከተማ ወሬ . . .

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

(“ወርቃማ ዘመን” ወ ‘’Go fund me.’’)
         
           ተራርቀን የቆየን ወዳጆች ባጋጣሚ ተገናኝተን አወጋን፡፡ ከሰሞኑ ወሬዎች እየቆነጣጠርን ሰለቅን፤ ሳቅን፤ ተከዝን፤ ተደመምን . . . ለዛሬ ከእጅግ ብዙዎቹ አንዱን በተለይ አለቅጥ የጠነነውን፣ የጠኔውን Poverty አርዕስተ ጉዳይ ብቻ ( ባመዛኙ እንደወረደ ) እነሆ . . .
ስንገናኝ ተሲያት ስለነበር የሰሞኑን አየር ሙቀት መጨመር ጉዳይ አነሳን፤ ‹‹ቀሽት›› ምላሽ ተሰነዘረ፡፡‹‹በየልቦናችን የምናሰላስለው ሀሳብ ስለተጨናነቀ’ኮ ነው አየሩም እንዲህ የሚያስጨንቅ የሆነው›እ ተብሏል፡፡›› ይህን ድንቅ ምልከታ ‹‹ድርቁም የመጣው ማማረር በመጀመራችን curse ነው ተብሏል›› የሚል አከልንበትና መላምቱን ከ1930ው የአሜሪካ ኢኮኖሚ መንኮታኮት - the great depression ጋር አሰናስለን፤ ከዚህ ቀደምም ያንሸራሸርነውን በወቅቱ መላው አሜሪካዊያን ዜጎች ‹‹በኢኮኖሚው ሽባ ሆንን!›› ማለት ሲጀምሩ እንዴት በፖሊዮ የተጠቁ ልጆችን መውለድ እንደጀመሩ፣ በመጨረሻም በተሸከርካሪ ወንበር ላይ የተቀመጠ ያገር መሪን እስከመምረጥ እንደደረሱም አወጋን - በኋላም ፕሬዚደንቱ ፍራንክሊን ሩዝቬልት በባህር ኃይሉ Pearl Harbor ላይ ለተሰነዘረው ጥቃት ምላሽ በፈጸሙት ከባድ ውሳኔ የሚሻ የውትድርና ጀብድ፣ ሀገሪቱ በ‹‹ሁሉም እኩል/አንድ ነው›› All is one የወል አርበኝነት መንፈስ ተነቃቅታ የፖሊዮም ክትባት በዮናስ ሳክ እስኪገኝና በሁለገብ የእድገት እርምጃ መራመድ እስክትጀምር ድረስ፡፡ በዚያ ዘመን የተሰራውን ''One flew over the cooks' nest''ን ፊልምም አብረን አስታወስን ፡፡ ፊልሙ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መቃወስ ዜጋውንም በተቃወሰ የማህበራዊ መስተጋብር መንፈስ እየነዳ የአእምሮ ህሙማን ተቋማት እንዴት በእብድ ዜጎች እንደተጥለቀለቁ ይተርክና በፍጻሜው ላይ ግን ታካሚዎቹ ሳይሆኑ አካሚዎቹ ናቸው ንኮች ሊል ይቃጣዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ጥልቅ ይመስላል፡፡ ከአስር አመታት በፊት ካናዳዊው አንጋፋው የፊልም ባለሙያ ጆን ሉቮፍ የጠየቀንን ጥያቄ አከልንበት - ለጨዋታው ድምቀት ... በፊልሙ መጨረሻ ላይ ‹‹ቀዌ›› ተብዬዎቹ ህሙማኑ ተመካክረው በሌሊት ሲያመልጡ ከመካከላቸው አንዱ፣ ባለ ሉጫ ጸጉረ ረዥሙ ሬድ ኢንዲያኑ፣ ከሩቅ መንገድ ተመልሶ ይመጣና ፤ አካሉን ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ እዚያው አልጋው ላይ ተጋድሞ የቀረውንና ዋነኛው የማምለጥ ሴራ አቀናባሪ ገጸ ባሕርይን (እውቁ ተዋናይ ጃክ ኒኮልሰን ነበር የተጫወተው) በከፍተኛ አክብሮት፣ በሚያንገበግብ ስስትና ጥልቅ ፍቅር አፍኖ ገድሎት ተመልሶ እብስ ይላል፡፡ለምን?!  ‹‹በደንብ አስቡት ተማሪዎች፤ እንዲህ ያለ ታማኝ ወዳጅ ማግኘት ብርቅ ሊሆንም ይችል ይሆናል!›› ማለቱስ ደሞ መምህራችን፡፡
በዚህም አርእስተ ጉዳይ ላይ አወጋን፡፡ ከተሰነዘሩት ሀሳቦች ሁሉ ድንገተኛ የሳቅ ፍንዳታ ያጫረው... ‹‹ከገደለው በኋላ ለቀብር ማስፈፀሚያ ገንዘብ ለማሰባሰብ ይሆን?›› የሚለው ነበር፤ የዘመኑ መንፈስ የፈጠረው ስላቅ! ... ወጣቷ ዝነኛዋ ጓደኛችን ሽሙጡን ተመርኩዛ በቀጥታ ወደ ገደለው ገባች...‹‹ለእሱማ ገና ሳይሞት አይሻለውም ታዲያ፤ ማለት ከመግደል ስቃዩን በማራዘም በቂ እርዳታ' ማሰባሰብ ይችል ነበራ!ድምጽ ማጉያ በጫነ ሚኒ ባስ፣ የምስኪን ታማሚውን የጣር ላይ ፎቶ በደማቅ የባነር ህትመት አሸብርቆ፣ በያደባባዩ እየዞረና በፍቅር እስከ መቃብር ዋሽንት ማጀቢያ በተቀረጸ አንጀት የሚያላውስ የምጽዋት ትረካ አስደግፎ!!! ... - የፊልሙ መቼት’ኮ አሜሪካ ነው ኢትዮጵያ አይደለም እህታችን! ... ከኛ አሁን ጋር ልክክ አለብኛ!... የጦፈ ምልልስ ቀጠለ፡፡ . . . በእርግጥ የአዋጁን በጆሮ ያህል ሊታይ ይችል ይሆናል፤ እዚህ መጻፉ! ያም ሆነ ይህ ግን ወደድንም ጠላንም ይህ ያለንበት ጊዜ መገለጫ ነውና የልመና ሳይንስ "Begiology" መልኩን በመቀያየር፣ ከፍተኛ የተራቀቀ ደረጃ በደረሰበት በዚህ ዘመን፣ በየእለቱ ይህን መሰልና ከዚህም የከፋ ተረብና መራር ቀልድ መስማት እምብዛም አይደንቅምም፡፡ እውነት ነው በታማኝነት ዜጎችን ከመከራ ለመታደግ አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ጥረት ለማድረግ የሚተጉትን ቅን አሳቢ - አድራጊዎችን በአልፎ ሂያጅ ወሬ ሳያረጋግጡ አብሮ መዝለፍ በፍጹም አይገባም፡፡ ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑም የሉላዊ እርዳታ አሰባሰቡን ያስተዋወቀንም ሰው ሊመሰገን ይገባል፤ ችግሩ አሁን አሁን ትንሽ እጦት በገጠመን ቁጥር እንደው ለሽሮውም ለበርበሬውም እንደ ፋሽን የተያያዝነው ይህ የእጃችሁን ዘርጉልን እና ''Go fund me'' መሰል ጊዜያዊ መፍትኄዎች፣ ብቸኛ አማራጭ ሆነው፣ እንደ ሀገር የት ድረስ ይወስዱን ይሆን? ብሎ መጠየቅ ደግሞ ግድ ይላል፡፡ . . . በዚህ አርእስት መነሻ ለተንሸራሸረው ሀሳብ እንደ ምሳሌ የቀረበው የስለት ብር ለመሰብሰብ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የጀመረውና በዚያው ለማኝ ሆኖ የቀረው ሰውዬ ታሪክ ፤ ልመና እንደ ዘበት የሚጀመር ልማድና ውሎ ሲያድር ባሕርይ፤ በመጨረሻም ቋሚ ማንነት ሆኖ የሚቀር ለመሆኑ ጠቋሚና አስረጂ ነበር፡፡
የተከበሩ ለጋሾችንም - ከእርዳታ ጠያቂ፣ ተቀባዮችና አድራሾች እና ‹አከፋፋዮች› ጋር አንስተን ጥለናል፤ እርዳታ ሰጪዎቹስ ምን ያስቡ ይሆን? ...ለምሳሌ ‹‹800 ብር ስለት አገባለሁ ብዬ ተስዬ ነው›› ላለው/ ወይም ለፈለገው - ላስፈለገው ሰው፤ላንዳንድ ነገሩም ይሆነዋል ብሎ በቅንነት 200 ብርም ጨምሮ አንድ ሺህ ብር የሰጠው ለጋስ፤ ባለ ስለቱን ደግሞና ደጋግሞ ሲለምን ሲያየው ምን ይሰማው ይሆን... አልን፡፡ እኮ ባለ ሀብቶቹ ሌላ የተቸገረ ቢመጣም እንዳይሰጡ ያደርጋቸዋል፡፡ግን ይህ ስለሆነ ብለው ልግስናቸውን አልገቱማ፤ ያውም ባደባባይ እዩኝ እዩኝ ሳይሉ ቀኝ እጃቸውን ግራው ሳያየው መስጠታቸውን እንደቀጠሉ ነው! ግን ደሞ እንዴት አፈር ድሜ ቅመው ሀብት እንዳገኙ ያውቁታልና ተረባቸውም አይጣል ነው አሉ! ማንን ነበር ነዳያንን ለፋሲካ ለመመገብ ስፖንሰር አድርጉኝ ብሎ በጠየቀው የተጋነነ የብር መጠን፤"ቁጥር አታውቅምና ልጄ" ያሉት!... "እንዲህ ሀሪፍ ገቢ ካለውማ ከኛም ንግድ ይሻላልና እባክህን ሼር እንስራ ነው" ያሉት አሉ! ሳቅ በሳቅ1... "ይሄ ነገር ግን ለእኛን መሰል መናጢ ድሆቹ አይገባንም!" አለ ትንታጉ ጋዜጠኛ ወዳጃችን፤ "እነሱ ፈልገው ደስ ብሏቸው አምነውበት ሲሰጡ፣ በገንዘብ ከማይተመነው መንፈሳዊ እርካታቸው ባሻገር፣ ያው ላለው ይጨመርለታልና ጠቅጥቆ ይሰጣቸው ይሆናል፡፡"
ማለት?! ሁሉም ባንድ ድምጽ ጠየቁ፡፡ "በቃአ አለ አይደል በቃ . . . ሲሰጡ ለእግዚአብሔር እንዳበደሩት ይቆጠርላቸውም ይሆናል፡፡ አንድ ሚሊዮን ለተቸገረ ሲሰጡ እግዜር መቶ ሚሊዮን  እየለቀቀባቸው ነው አሉ!" ሳ....ቅ! ጭብጨባም! ይመቻቸው! ያርግላቸው አቦ! አስተያየቶች ተደራረቡ..."በተረፈ ባለጸጋዎች ሁሉም ባይሆኑም አብዛኞቹ በአኗኗራቸው ለ‹መረጃ› ቅርብ ስለሆኑ ‹የተፈሳች የተተነፈሰች› ሁሉ አታመልጣቸውምና ማን አስተኳሽ፣ አስወርዋሪ ማን ወዳጅ ቤተኛ መስሎ ወሬ አቃጣሪ፣ቃሪያ ቀርቃሪ አቃቃሪ፣ ማን የምሩን አዛኝ መካሪ፣ሀቀኛ ደፋር ተቆርቋሪ፤ ማን በማን ቁስል ሸሚዝ/ጎማ እንደቀየረ፤ ማን በማን ሞት ውስኪ ጠጥቶ እንደሰከረ፣ረብጣውን መዥርጦ እንደመነዘረ፣ኪሱን ባውንድ ሞልቶኮርቶ ‹‹እንደከበረ››(ክብር ከተባለ!) ልቅም አድርገው ጠንቅቀው ያውቁታል አሉ’ኮ! ከሞላ ጎደል ህዝቡም እንዲሁ! the world is small round. ወንድሞቼና እህቶቼ፤ በዚህ ፈጣን የመረጃ ዘመን የችጋርን ገመና እያሰጡ ለመደለል መሞከርና ለግል ትርፍ እያጋበሱ አይታወቅብኝም ብሎመነሁለልና ንፁህ ሰው መስሎ ባደባባይ መንጎማለል (hypocrisy) ውሎ አድሮ እውነቱ ሲወጣ (መውጣቱም ስለማይቀር ምንም ያህል ይዘግይ እንጂ!)ትርፉ ስምን ማጉደፍ፡ አጉል ውርደትና ከንቱ ጸጸት ብቻ ነው፤ ይኸው አይናችን ስር እንደምናየው! ከነገረ ቀደምኮ ሰው ከራሱ ህሊና ማምለጥ አይችልም!..."
"ወየው ጉድ! አንተ ደሞ፤ ህሊና ሲኖርኮ ነው፤ አስቀድሞ ህሊና ካለህ እንዲህ ያለ አጉል ግብር ውስጥ መች ትገኛለህ እ! ህሊናህን ገድለህ ከቀበርከው ግን ማን እየኮሰኮሰ ይከስስሀል? ስትለምደው ደሞ (ቢዝነሴ ነው ማለት ስትጀምር - ሳቅ!) አዎ በቃ ቀላልnormal ይሆንብሀል"አሉ፤ልክ እንደ ሽንት ቤቱ ተረት ማለት ነው! abnormal condition in abnormal situation is normal. አንዴ እስክትጀምረው ነው እንጂ አንተማ ታዋቂ ስለሆንክ ያዋጣህ ነበር ያለኝ ሰውም አለ!necessity is a mother of invention ይሉሀል ይኼ ነው! ድንቄም!
. . . ወይ ይሉኝታ ማጣት! ይኼ ሁሉ’ኮ የፖቨርቲ ስነ ልቦና ውጤት ነው! የማህበረሰብ ዝገት ልሽቀት በቃ decay መሆን መጀመር!- አገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል እንደሚሉት አይነት! እኔ ከሌላው የተሻልኩ ነኝ ብዬ አይደለም፤ ሁላችንም የራሳችን ድክመት አለብን ግን እንደው በቃ አለ አይደል፤ እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ወላጅ ሆኜ፣ እንደማህበረሰብ ወዴት እየሄድን ነው ብዬ ሳስበው! የእውነት! እና እንዲህ ያለ የጎለደፈ ስነ ምግባር ያንሻፈፋትን ይችን ሀገር ነው ታዲያ በጠፈር ምርምርና በሳይንስና ቴክኖሎጂ...ወዘተርፈገና በለጋ እድሜያቸው በሁለገብ አስደናቂ እውቀታቸው በላቀ ተስፋ ለሚንበለበሉቱ ምስኪን ታዳጊ ልጆቻችን እምናወርሳቸው! እላለሁ፡፡
ኢትዮጵያን መቸም የማይተዋት የሚጠብቃት የሚጸልላት እሱ ፈጣሪ ይታደጋታል! አሜን!! (የጋራ ድምጽ፤ ጓደኛችን እዝን ብላ ቀጠለች) . . .ብቻ እንደው ይብላኝላቸው እንጂ ለአፋሽ አጎንባሽ ተቆርቋሪ ነን ባዮቹ! ከሰው ችግር ለሚያተርፉ! የሞተስ ተገላገለ! በቁም ለሞቱቱ ነው እንጂ ማዘን!
. . . ይህ መራር የዘመን ትዝብት በ‹‹የዘመን ንቅሳት›› ሞጋች ቅንጭብ ስንኝ ታጀበ . . . (ዮሐንስ ገ/መድኅን 2004፡፡)
‹‹...በዕውር ደመ ነፍሱ መሽቶ እስከሚነጋ ለከርሱ ሚተጋ
ማፍረስ ሚቀናው ግብረ አልቦ የሙት መንጋ
እንዲህ ያለው ብኩን ከታጎረበቱ
ከእንዲህ ያለው ሰፈር ከሰፈረ ከንቱ
ከንዲህ ያለው ቀዬ መቃብር መቃብር ከሚሸትበቱ
ሙት ከሰፈረበት ሙትን መለየቱ
ሞት የሚሆንበት ምን ይሆን ምክንያቱ?!››

"መንገድ ላይ የአዱኛ ጊዜ የተድላ ዘመናቸውን ፎቶግራፎች ደርድረው ‹‹እንዲህ ነበርኩ›› እያሉ ምጽዋት የሚለምኑት ግን ያሳዝኑኛል!" አለ አጥረኛው፡፡
"እሱም ያው ምክንያት ፍለጋ ነው ባክህ! የሰው ልጅ እማያልቅ ሀብቱ - ምክንያቱ!"
"አይደለማ! መቸም ባንድ ወቅት እንዲህ ያለ ወርቃማ ጊዜ ነበረኝ ሲሉና ፎቷቸውን ስታይ መቸም ከልብ ታዝናለህ!"
ጓደኛችን አቋርጣ፤ "አንዲት ጓደኛዬ’ኮ የራሷን ፎቶ ከደረደሩት መሀል አግኝታ እሪ...! ብላ ቀውጣው ታውቃለች" አለች፡፡ ሳቅ! ሁለቱ ቀጠሉ . . .
"ወርቃማ ዘመን ማለት በራሱ ምን ማለት ነው’ሱ ባክህ! እናም ደሞ ያንን ወርቃማ ጊዜዬ ነበር ብሎ ያመነውን ዘመኑን ያፋለሰበትን ፍለጋና ጥገና ሰንፎ ቢሆንስ ልመና የጀመረው?"
"ላይሆንም ይችላል፣ ሰው መቸም ፈልጎ አይለምንም!"
"አልሰሜን ግባ በለው አሉ - እንክት! ይለምን! እና ሀገር ምድሩን እሚያምሰው ማን ሆነና፣ ወዶ ለማኝ--- ፀዴ የኔቢጤ ሁሉ አይደለም’ንዴ!"
"እግዜርም ቢሆን ብርሃን ሲሰጥ ጥላንም ፈጥሮኮ ነው፣ ተው እንጂ !"
"አንተው ራስህ ተው እንጂ! ካቅም በላይ ችግር ከገጠመ አማራጭ ከጠፋ፣አዎን እገዛ መጠየቅ መደጋገፍ፣ መረዳዳት ምንም አይደል! ግን አንወሻሻ እየተዋወቅን! አሁን አሁን ሀሪፍ ገቢ ተደርጎ መወሰድ የተጀመረው ምን ሆነና፤አስተዛዝኖ የሀብታምን ልብ አራርቶ እርዳታ መቀበል ነው! ኮሜዲያኑ ያለውን አልሰማህም’ንዴ... "ሁሉም ብልት በሌሎች ቀድሞ ተይዟል፤ እና በየትኛው የሰውነት አካል በሽታ ላይ አስታክኬ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ባዘጋጅ ህብረተሰቡን የተሻለ ለማራራትና አሰተማማኝ ገቢ ማሰባሰብ እችላለሁ?!" . . . (ያላቋረጠ ረዥም ሳቅ፡፡)
"ይልቅ ወርቃማ ዘመን ብለህ ስላነሳኸው ጉዳይ ዘወትር የሚያብከነክነኝ፣ይኼ የየግላችንና ጥቃቅን ወቅታዊ ጉዳያችን ሳይሆን ያጠቃላይ የሀገራችን ‹‹ወርቃማ ዘመን›› መቼ ይሆን የሚመጣው የሚለው ነው!!!››የመጽሐፍ ቀበኛው ወዳጃችን ዙሩን አከረረው፡፡
"ትንሽ ግልጽ አድርገዋ አባዬ!"
"ምኑን ?! አይናችን ስር እየሆነ ያለው ምንድነውና! እሺ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ‹‹ዋ! የዛሬን አያርገውና ጥንት ወርቃማ ዘመን ነበረኝኮ!›› ለማለት ተነሳች እንበል፤ እናም ልክ እንደ መንገድ ዳር ሰዎቹ አይነት ‹ቀን ጥሎኝ› አዲስ አቀራረብ የልመና ፕሮጀክት ብትቀርጽ ማለቴ ነው . . . እሺ የትኛውን ዘመናችንን ነው ‹‹ቀን የጣለብን/ወርቃማ ዘመናችን›› ብለን እምንጠቅሰው እ? ያንኑ አለምን ያጠገብንበት እያልን እምንፎልልበትን የፀሐይ ገበታን የካቻምና አይጨበጤ ጉም ህልምና ቅዠት?!"
አስተያየት ተግተለተለ ፤ በእርግጥ እነዚያው እለት በእለት የማይቀሩቱ ናቸው ሁሉም - አክሱም፤ ላሊበላ፤ ፋሲለደስ፤ ሶፍ ኡመር፤ ጢያ ትክል ድንጋይ፤ ሀረር ግምብ፤ አል ነጃሺ፤ ኮንሶ፤ሀርላ፤ ግዮን ወንዝ፤ ኤርታሌ፤ ሉሲ . . .ወዘተ፡፡
"አልኳችሁኮ! ስለ ሁሉም ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ቅርሶቻችን ያለኝን ክብር ሳልገልጽ አላልፍም፤ ምንም እንኳ ከዛሬያችን ጋር ለማሰናሰል ባንታደልምና አለም በቴክኖሎጂ በተራቀቀበት ዘመን እኛ ዛሬም እነዚያውኑ ብቻ መተረታችን ድግግሞሹ ቢሰለቸኝም፡፡ ግን እነዚህም ቢሆኑ እጅግ በተራራቀ ጊዜ እንጂ ሁሉም በአንድ ወቅት በተቀራራቢ ዘመን የተሰሩ ስላልነበሩ የኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመን ትሩፋቶች ልንላቸው አንችልም! እሺ ጥሩ ለምሳሌ (ያው መቸም እኛም ጥንታዊ ምድርና የቀደምት ስልጣኔ ባለቤቶች ነን እያልን ነጋ ጠባ ስለምንበጠረቅ) የግሪክን ወርቃማ ዘመን እንውሰድ፡- ከክ.ል.በ 6ኛው ክፍለ ዘመን ነው በተለይ የግሪካዊያን ክላሲካል ዘመን - classical period ተብሎ እሚጠቀሰው አይደል፤ እና ታዲያ በዚያ ዘመን’ኮ በፖሊቲካ፡ በሳይንስ፡ ፍልስፍና፡ ኪነጥበብ የላቀ ደረጃ በመንፀባረቁ፤ ማለትም ዴሞክራሲ በአቴና አደባባይ በመንሰራፋቱ፡ ፈላስፋዎቹ እነ ሶቅራጥስና ፕሌቶ የዙሪያቸውን አለም እውነታ ለመፈተሽ ሳይሳቀቁ ከመላው ዜጋ ጋር በነጻነት መወያYት በመቻላቸው፡ሄሮዶቱስ የጥንቱን አለም ታሪክ ከነባራዊው ያገሩ ሁናቴ ጋር መሸመን በመቻሉ፤ የፓይታጎረስ ማቲማቲክስ ጂኦሜትሪ፣ የሂፖክራተስ የህክምና ቃለ መሀላ፣ የየከተማው የኪነ ህንጻ ንድፍ መበልጸግ፣ የቴስፒስ ቴአትር ጥበብ መጀመር ...ይሔ ሁሉና ሌሎችም የትየለሌ የዘመኑ ውብ ጸጋዎች ተደማምረው ነው ለዘመኑ ‹‹ወርቃማ ዘመን›› - golden age of Greek የሚል ስያሜ የተሰጠው፡፡እሺ እኛ ዘንድ መቼ ነበር እንዲህ ተከታታይ የማህበረሰብ አመርቂ እመርታ የተመዘገበበት ወርቃማ ዘመን!? የታል ቅንጣት ታክል የስልጣኔ ፈለግ ቅሪቱስ እ! የአክሱም ሀውልትን ተመልሶ ሲመጣ መትከል አቅቶን የለም እንዴ! የደዌያችንም ሰንኮፍ ሳይነቀል ፤ ለቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ድኩማንነታችን ፈውስ ክትባት ሳይገኝ ይኸው ስንትና ስንት ዘመን ነጎደ! እ! ደርሶ መደገግ! ባዶ ትምክህትና አጉል ጉራ ብቻ! Vain pride! እና እንደኔ እንደኔ ጥቃቅኑን ጉዳይ እንድፈን ካልን መቸም ቆመን አንሄድምና የወል መላ ዘይደን ትልቁን ስእል ለመቀየር መነሳት ነው ቢቻለንስ! እንዴ ዛሬም ‹ሀገራችን በእድገት ጎዳና በመወንጨፍ ላይ ነች!› እያልን በየመገናኛ ቡዙኃኑ ባደባባይ ስንቦተልክ፣ስንቀባጥር፤ በገሀዱ ሀቅ ግን አለሙ ሁሉ ዛሬም እሚያውቀን በዚያው በነባሩ የጆናታን ዲምቢልቢ ጥቁርና ነጭ የ1966ቱ የድርቅ ታሪክ ምስላችንና በአይሰለቼ የተረጂነት መልካችን መሆኑን እንዴት ነው እምታዩት ወዳጆቼ?!"
"አታካብድ ባክህ ››ታሪክ ራሱን ይደግማል!›› ይባላል ከነተረቱም፡፡" ሌላ ሀሪፍ የሆነች ስላቅ! . . . ለረዥ...ም  ሰከንዶች ያላቋረጠ ሳ...ቅ፡፡                                  
"እኔ አልስቅም ባካችሁ! እሺ አንተ እንዳልከው ቀፋፊ ታሪክ እንዳይደገምም ሆነ አጓጉልና ፀያፍ እምንላቸው እንከኖች እንዳይጋርዱን ዋናው ጉዳይ ሁላችንም የየበኩላችንን ግዴታ መወጣታችን መሆኑ ሳይዘነጋ . . . ግን ካነሳነው አርዕስተ ጉዳይ ሳንወጣ፣ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ እያሰለስን በተቸገርን ቁጥር አንጋጥጠን ርጥባን እምንጠብቀው ለምን ይመስላችኋል? በበኩሌ አሣውን ብቻ ስለምንፈልግ ነው! ቶሎ ጠግበን አፍታም ሳንቆይ ወዲያው ደሞ ለመራብ! በቃ አለ አይደል ዘላቂ - Sustainable ሳይሆን ጊዜያዊ- hot cake መፍትኄ ስለምንፈልግ! በእርግጥ ባለቅኔው እንዳለው ‹‹ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል?›› ብላችሁ ትሞግቱኝ ይሆናል ፤ እኔ ግን እላችኋለሁ ‹ከራበው ለጠገበው አዝናለሁ!›"
"እሺ ታዲያ አንተ ለኛ ግድ እሚያስፈልገን ነው እምትለው ምንድነው ?"
"መረቡ! ነዋ - አሣውን ማጥመጃው፡፡ በተረፈማ የፈጣሪ ትዕዛዝ ‹‹ብላ በአፈ ገጽከ›› አይደለም’ንዴ ወገኔ?!"
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!!
አሜን!!

Read 1380 times