Saturday, 06 April 2019 15:48

እኔ የትኛው ነኝ?

Written by  ከዳግማዊ እንዳለ(ቃል ኪዳን)
Rate this item
(1 Vote)



እንደአፍላዉ ጊዜ መናገር ጠፍቶባት
አቧራ ላይ ሊሥል፤ ጣቷ መስታወቱን በሚዳብስበት
እውነት ጎኑ ቆማ፤
እውነትን ፍለጋ ዓይኖቹ ‹መስኮት› ላይ ቀልጠዉ በቀሩበት
ክፍቱን በተተወዉ በነዚያ ምስኪን ቤት
እኔ አለሁ?
ካለሁስ የትኛዉ ነኝ?
መናገር የጠፋብኝ ወይስ ማየት ያቃተኝ?
ፍቅረኛዋ ክዷት ዕንባዋን ልታፈስ ወደቤቷ ‘ምትሮጥ
ምስኪን ሴት ይመስል
ዕንባው ባይኑ ሞልቶ የሚጓዝ ደመና
ከደመናው በታች፤የተቆፋፈረ ገበጣ ጎዳና፤
ከሱ ላይ-ከሱ ዉስጥ
ቄንጠኛ ፍቅረኛ
ወገቧን ካቀፋት ጠይሟ ፍቅረኛው
የበለጠበትን፤ቀዩን ቆዳ ጫማ
አሥሬ ‘ሚቃኘው፤ ሲያሻውየሚያብሰው
ከእርሱ ፈንጠር ብሎ በእራት መብያው ሲጠጣ የዋለ
ቀብራራ ጀብራሬ አጥሩ ጥግ ቆሞ ሽንት እየከፈለ
ከጀብራሬው ጀርባ ሽንት መክፈያዉንየቆሪጥ እያየች
በዝግታ ‘ምታልፍ ቅንዝራም ቂጣም ሴት
ተቀይሯል እንጂ-ስም እንኳን ነበራት እናቷ ያወጡላት
ኧረ ንቀይ በሏት!፤ መንገድሽን እዪ በሏት!
ሰዉጤፉ ‘ሚነዳዉ ስመ-አዲስ መኪና
ገፍትሮ እንዳይድጣት!
ይሄን ሁሉ እያየሁ?
ግና እኔ የታለሁ?
ከደመናው በታች በገበጣው ጎዳና
የታል የእጄ ዳና?
ትልቁን መከፈያ፤ ቀዩን ቆዳ ጫማ
የቅንዝራሟን ቂጥ፤ የሰዉ ጤፉን ጎማ
ሁሉንም አልፌ ቤት የወጋሁበት
የታል የኔ ጠጠር?
ወድቆ አይታይም፤ከተቆፈረው አፈር
መሸታው ቤት ደጃፍ ለኩርማን እንጀራ የሰዉ ዓይን የሚያዩ
ኑሮ ያጎበጣቸዉ አሳዛኝ አዛዉንት
ባለጌ ወንበር ላይ ጡጦ ሳይጨርሱ አልኮል የሚጋቱ
ጊዜ ያበላሻቸዉ አንድ ፍሬ ሕጻናት
በተለየ ቦታ እነባለ ጌታ እነ ባለዲታ
በብዉዝ ቤት-ካርታ በጠይም ሀገር ላይ
ቀይዋን ያየ ሲሉ
አዉራጅ-አርጋጅ ጭፍሮች ጌቶች ላነቃችዉ
ጀርባ እየደለቁ-እነርሱ ሲያስሉ
በ"ነይ ማታ፤ ነይ ማታ"ኑሮ የመሸበት
መረገጥ፣ መገፋትሁሉም ‹ዳንስ› ናቸዉ ብሎ ሲዘባበት
ማንሳትና መግፋት ቅላቸዉ የጠፋበት
ሊያነሳ ሲሰብር በሠካራም ዘበት
በሠካሪያን ብብት፣  በዳንኪረኞች እግር
እየተሽለኮለከ ስባሪ ሚያነሳ፤ ቆርኪ የሚለቅም
ቀይዳማ ልጅ እግር
ቀይዳማዉ ልጅ እግር አዉጥቶ ከደፋዉ የጠርሙስ ስባሪ
ትይዩ አጥር ጥግ 40/60ን ንቆ በላስቲክ ቪላ ዉስጥ
ቅስሙ ተሰባብሮ ‘ሚያለቅስ ዉሪ
ከብላቴናዉ ጎን ከምንድግ አገር ጋር እኩል አልሄድ ብለዉ
ኑሮ እሳት በልቷቸዉ አመድ ስለሆኑ ወጥተዉ የተደፉ
አንዲት ምስኪን ባልቴት የእግዜር ቆብ የደፉ
ብላቴናዉ ያለቅሳል፤ ባልቴት ይጮኻሉ
በጥጋብ አገር ላይ፣እራበን እያሉ
የነሱን ጩኸት ሰምቶ አንድ ተቃዋሚ መንግሥት ይራገማል
ደግሞ ለክፋቱ ራት የበላዉ ቀይ ወጥ ወደላይ ይለዋል
አምስት ብር አዉጥቶ፣ ከአምስት ዓመት ህጻን መሽቲካ ወሰደ
ለመራገም ማግሳት የግዱንይለዋል ጠላም ወይ ወደደ
መስቲካ እየገዛ እንጀራ ከባዕድ ቀላቅላ ምትጋግር
ስንቱን ጤና የነሳች
ሰላም ብላዉ ሄደች
ሥራዋን ቢያዉቀዉም ለምን ይናገራት-መንግሥት እርሷ አይደለች
የሚፈልገዉን-ወንበሩን አልያዘች
በዚህ ሁሉ ቱማታ ግና እኔ የቱ ጋ ነኝ?
እኔ የትኛዉ ነኝ?
ባቀናሁት አገር ጎብጬ ‘ምለምን ያ ምስኪንአዛዉንት?
ወይስ ብላቴናዉ
በናቱ ትከሻ ሽቅብ ተንጠራርቶ ከባለጌ ወንበር እግሩን የሰቀለዉ?
እኒያን ነኝ እንዴ እኔ?
በ'ዳ ደም ባቀሉት የእዳ ካርታቸዉ
ቀይዋን ያየ ሚሉት
ቀይዋ በመጥፋቷ፤ ቀይዋን ካርድ ያላዩት
እላፊ የቆዩት?
እኔ የቱ ጋ ነኝ?
እኔ የትኛዉ ነኝ?
ጎዳና ወድቄ ‘ምታየዉ ጨቅላ? ወይንስ ባልቴቷ
‘ሚጦራቸዉ አጥተዉ ወድቀዉ የቀሩቷ?
ወይስ ተቃዋሚዉ የገዛ ያልገዛዉን ሲነቅፍ የሚኖረዉ
አንዱ በታሠረዉ ሌላዉ በታመመዉ
ሊሸቅል ሚሮጠዉ?
አዎ እዛ ጋ ነኝ! እራሴን አየሁት!
አያችሁኝ? ያዉናኝ!
ከከንቱዎቹ ቤት ክፍቱን ከተተዉ
በወጣዉ አቧራ ቆሜ እያነጠስኩኝ
‹ይማርህ› የሚል ጠፍቶ ‹ይማረኝ› እያልኩኝ?
አያችሁኝ እዛ ጋ‘?
ከሞት የተሻለ ሀሳብ የሚገታመድኃኒት ፍለጋ
አንድ እግሬን ከእግዜር ደጅሌላዉን ካዋቂ
ከፋፍዬ ቆሜ፤መሽቶብኝ ሲነጋ
ደግሞ ተመልከቱኝ!
ሁሉን እረስቼ ያቺን ቅንዝራም ሴት እንዴት እንደማያት?
እግዜር ደጅ ያለዉን አንድ እግሬን አንስቼ እዩኝ ስከተላት!
ገባች ተመልከቷት ከዚያ ጭፈራ ቤት
አገር በአምቦዉሃ እየተበረዘች ከምትጠጣበት
ኧረ ተመልከቱኝእንዴት እንደማስቅ
ቂቂቂቂ……ቂቂቂቂ……ቂቂቂቂ
ባንድ እግሬ እየሮጥኩኝ ተከትያት ገባሁ
ቀይዋን ያየ ሚሉት ቀይዋ ስትገባ  
ምን እንደሚዉጣቸው ሳስብ እጅግ ጓጓሁ
ኤጭ!
እኛ ሽማግሌ ከመሸታዉ ደጃፍ ቆመዉ ሚለምኑት
በሰዓት እላፊ እራቴን እያሉ እይታዬን ጋረዱት!!

Read 1751 times