Saturday, 13 April 2019 12:24

በደቡብ ክልል፤ የዞን መዋቅር ለውጥ ግጭት እያባባሰ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)


            - እስካሁን “7 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በሺዎች ተፈናቅለዋል”
            - “የዞን አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ ከስራ ውጪ ተደርጓል”
            - “መከላከያ ኃይል እንዲገባልን ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል”
                       
                 በደቡብ ክልል በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን፣ ጉማይዴ ወረዳ አካባቢ፣ ከዞን መዋቅሩ ጋር በተያያዘ በተከሰተ ግጭት እስካሁን ሰባት ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ4800 በላይ ሰዎች ደግሞ ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ታውቋል፡፡
በቅርቡ ለኮንሶ ወረዳ የዞን አስተዳድር መዋቅር ሲሰጠው የሌሎቹ እጣ ፈንታ ባለመወሰኑና የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አስተዳደር በልዩ ልዩ ሁኔታ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ እድል ያልተሰጠው በመሆኑ፣ በአዲሱ የኮንሶ ዞን አስተዳደርና በቀድሞው የሰገን ህዝቦች ዞን አስተዳደር መካከል ግጭት መቀስቀሱን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል::  የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማረ ቦሬ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ካለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ጠቁመው፤ በስፍራው ለተከሰተው የፀጥታ ችግር መነሻ ምክንያቱ የመዋቅር ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ ኮንሶ ቀደም ሲል በሰገን ህዝቦች ዞን ስር የሚተዳደር ሆኖ መቆየቱን የገለፁት የዞን አስተዳዳሪው፤ በቅርቡ ኮንሶ ራሱን በዞን መዋቅር እንደሚያስተዳድር ከተወሰነ በኋላ አልፎ አልፎ ግጭቶች ሲቀሰቀሱ መሰንበታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮንሶ የዞን አስተዳደር ሆኖ ሲዋቀር የቀሪዎቹ ወረዳዎች እጣ ፈንታ ባለመታወቁ ምክንያት በአዲሱ የኮንሶ ዞን አስተዳደርና በቀድሞው የዞን አስተዳደሮች መካከል ግጭቱ ተባብሶ በአካባቢው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መከሰቱን አቶ አማረ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ግጭት ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ቁጥር ለመናገር እቸገራለሁ ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪው ከ4810 በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውንና በንብረትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ያለበትን ደረጃና በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የፀጥታ ችግር በመግለፅ፣ ለፌደራል መንግስት ጉዳዩን በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን የገለፁት የዞን አስተዳዳሪው፤ መከላከያ ወደ ስፍራው ገብቶ የአካባቢውን ፀጥታ እንዲያስከብርና የህዝቦችን ህይወት እንዲታደግ ላቀረብነው ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ አላገኘንም፤ በስፍራው ያለው የፀጥታ ችግር ግን ተባብሶ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
በደቡብ ህዝቦች ክልል የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አስተዳደሩ ካለፈው የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሽመደመድ ተደርጓል ያሉት የዞን አስተዳዳሪው፤ በአካባቢው የዘርና የማንነት ጉዳይም ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ፣ ፌደራል መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድና እየጠፋ ያለውን የሰው ህይወት እንዲሁም የሚደርሰውን የንብረት ውድመት እንዲታደግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡
ስፍራው በህግና በስርዓት የሚተዳደርና መንግስት ያለበት አገር እንደማይመስል የገለፁት ነዋሪዎች፤ በአካባቢው ችግር እየፈጠሩ ያሉት “የምንተዳደረው በሲዳማ ክልል ነው፤ ደቡብ ክልል እኛን አይወክለንም” የሚሉ ወገኖች ጥያቄ በማንሳት ለፀጥታ ችግሩ መባባስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አካባቢው በከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እየተናጠ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በተኩስ ልውውጡም ንፁሃንና ሰላማዊ ዜጎች እየሞቱ ስለሆነ መንግስት ይድረስንል ብለዋል፡፡

Read 3461 times