Saturday, 13 April 2019 13:11

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ከስልጣናቸው የተነሱት በችሎታ ማነስ ነው ተባለ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

 - ኮሚሽነሩ ከስልጣናቸው የተነሱት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ነው
                            - በበርካታ የአመራር ችግሮች ተጠያቂ ናቸው ተብሏል
                                        
                የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ኮሚሽነር የነበሩት ሜጀር ጀነራል ደግፌ በዲ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በጡረታ ሳይሆን በችሎታ ማነስ ምክንያት እንደሆነ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
የቀድሞ ኮሚሽነር ይህደጐ ስዩምን በመተካት ከሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ሜጀር ጀነራል ደግፌ በዲ፤ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተፃፈ ደብዳቤ ነው ከኃላፊነታቸው የተነሱት ተብሏል፡፡
በኮሚሽነርነት ሲያገለግሉ በርካታ ስህተቶችን እንደፈፀሙ የሚናገሩት ምንጮቻችን፤ የመንግስታዊ መስሪያ ቤት የግዢ መመሪያን በመጣስ በርካታ ግዢዎችን መፈፀማቸው እንደተደረሰበት ተናግረዋል፡፡
በ9 ወራት ውስጥ የኮሚሽኑ በፖሊስ ኮሚሽነርነት ሲያገለግሉ እና በስሩ ያሉ አስር ክ/ከተሞች በጀት ኦዲት ቢደረግም ከፍተኛ ጉድለት እንደሚያሳይ ግምታቸውን የሚናገሩት ምንጮች፤ አዲስ የሚመደበው ሃላፊ ከመምጣቱ በፊት ኮሚሽኑ ኦዲት ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
ሜጀር ጀነራሉ፤ መዋቅር በሚል ሰበብ በትውውቅና በቲፎዞ ምደባ ከማድረግ ጋር በተያያዘም ስማቸው ይነሳል፡፡ በተለይ በኮሚሽን ደረጃ የሚደረጉ ምርመራዎች ከበድ ያሉ በመሆናቸው በቦታው ልምድ ያለው ሰው እንደሚያስፈልግ እሙን ቢሆንም፣ እሳቸው ግን ልምዱ ያላቸውንና የምርመራ ቡድን ሃላፊዎች የሆኑትን ከቦታቸው በማንሳት፣ በክ/ከተማ ደረጃ የሎጀስቲክ ክፍል እንደ መደቧቸው እነዚሁ ምንጮቻችን ጠቁመዋል:: በምሳሌነትም ከሌብነትና ዘረፋ ምርመራ ክፍል ኃላፊነት የተነሱት ኮ/ር አለማየሁ አያልቄ በቂርቆስ ፖሊስ መምሪያ የሎጀስቲክ ክፍል ሲመደቡ፣ ከልዩ ልዩ ምርመራ ክፍል ሃላፊነት የተነሱትን ኮማንደር አበራ ቡሊናን ደግሞ የአራዳ ክ/ከተማ ሎጀስቲክ ክፍል መመደባቸውን እንደማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
መዋቅር በማለት በምደባ ላይ ችግር የተፈጠረው በኮሚሽኑ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በክ/ከተማም ጭምር መሆኑን የገለፁት ምንጮች ክ/ከተማ የነበሩ ኃላፊዎችን ልምድ በሌላቸውና ማዕረጋቸው ባነሰ አመራሮች እንዲተኩ ተደርጓል ይላሉ፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት በአንድ ወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ፣ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ፣ ችሎት ቀርቦ፣ ዋስትና በማግኘቱ፣ ትዕዛዝ የሰጠውን ዳኛ “አስራችሁ አምጡልኝ” በማለት ትዕዛዝ መስጠታቸውንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሆኑ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡
ጄነራሉ የስንብቱ ደብዳቤ የደረሳቸው ይህንን ትዕዛዝ ካስተላለፉ ከሳምንት በኋላ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡  


Read 7840 times