Saturday, 13 April 2019 13:15

60 የሚደርሱ የመንግስት ኃላፊዎችና ባለሀብቶች በሙስና ተጠርጥረው ታሠሩ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

 በአጠቃላይ 60 የሚደርሱ የመንግስት ኃላፊዎችና ባለሀብቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትላንት ገለፀ፡፡
በዋነኛነት ተጠርጣሪዎች የታሰሩት ከመድኀኒት ፈንድ ኤጀንሲና ከውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሲሆን ከመንግስት የግዢ ሂደት ጋር በተገናኘ ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስትን ማክሰራቸውን የጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጫ ይጠቁማል፡፡
የመንግስት የግዥ መመሪያን ሳይከተሉ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸውን መድኀኒቶች ግዢ በመፈፀም የኢትዮጵያ መድኀኒት ፈንድን ከ79 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳጣታቸው ተመልክቷል፡፡
ከዚሁ ከመድኀኒት ግዥ ጋር በተያያዘም ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ገንዘብ መባከኑ ተጠቅሷል፡፡ ከውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ጋር በተያያዘም ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ያለ ህግ አግባብ ግዢ በመፈፀም፣ የመንግስትና የህዝብ ሀብትን አባክነዋል በሚል ባለስልጣናቱና ባለሀብቶቹ ተጠርጥረዋል፡፡  ከአስመጪዎች ጋር የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር፣ መንግስት ማግኘት የነበረበትን ጥቅም አሳጥተዋል የተባሉ የገቢዎችና ጉምሩክ ኢንተለጀንስ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለፁልን ምንጮች፤ በተለይ ከግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ግብር ከፋይ የሆኑ ነጋዴዎች ግብራቸውን አሳንሰው እንዲያቀርቡ በማድረግ እንዲሁም ያለ ደረሰኝ መስራታቸው እየታወቀ በዝምታ በማለፍ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ የመንግስት ኃላፊዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ታውቋል፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ በመድሃኒት አቅርቦትና ከውሃና ፍሳሽ መ/ቤቶች ጋር በተገናኘ በርካታ የመንግስት ኃላፊዎችና ነጋዴዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለው የፌደራል ፖሊስ፤ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጊዜያዊ ማረፊያ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡


Read 7594 times