Saturday, 13 April 2019 13:18

የእሳት ማጥፊያ ሔሊኮፕተር እንዲገዛ ጠ/ሚኒስትሩ አዘዙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ እሳት በማስነሳት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ታስረዋል

              በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ላይ ተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎ መከሰቱን ተከትሎ፣ ዘመናዊ የበረሃ እሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር እንዲገዛ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ  ማዘዛቸው ተጠቆመ፡፡ በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ላይ ለ3ኛ ጊዜ ሚያዚያ 2 ቀን 2011 ዓ.ም የተከሰተውን ቃጠሎ ለማጥፋት የኢትዮጵያ መንግስት ከኬንያ ሄሊኮፕተር መዋሱ ታውቋል::
በውስጡ ዋሊያና ጭላዳ ዝንጀሮን የመሳሰሉ ብርቅዬ የዱር እንስሳትን የያዘው የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፤ እስካሁን ባጋጠመው የእሳት ቃጠሎ ከ4 መቶ ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍል ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ በፌደራል መንግስት የሚተዳደረው የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ላለፉት 21 አመታት ለአደጋ ከተጋለጡ የጎብኚዎች መዳረሻ ዝርዝር  (Black list) ውስጥ መካቱቱና ከሁለት አመት በፊት ከዚህ ዝርዝር ውስጥ መውጣቱ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ያጋጠመው ቃጠሎ መልሶ  በጥቁር መዝገብ እንዲሰፍር ሊያደርገው እንደሚችል ባለሙያዎች ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
የፓርኩን ቃጠሎ ለማጥፋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በቀጥታ ለኬንያ መንግስት የሄሊኮፕተር እርዳታ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በዘላቂነት ለዚሁ አገልግሎት የሚውል እሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር  በአስቸኳይ እንዲገዛ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ታውቋል፡፡   
ይህ በዚህ እንዳለ፤ በፓርኩ ላይ በድጋሚ  የእሳት ቃጠሎ አስነስተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንን፣ የአማራ ክልል ደባርቅ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምርኩዝ ዋሴ   አስታውቀዋል፡፡

Read 8489 times