Print this page
Saturday, 13 April 2019 13:19

በሰሜን ሸዋ ጥቃት የፈፀሙ ለህግ እንዲቀርቡ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 የአማራ የጸጥታ ሃላፊዎች በጥቃቱ ፈጻሚዎች ማንነት ላይ አልተስማሙም

                  ከሰሞኑ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ከተሞች ከ30 በላይ ንፁሃንን የገደሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐችን ያፈናቀሉ የታጠቁ ሃይሎች በአፋጣኝ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ መንግስትም የዜጐችን ሠላምና ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች አሳሰቡ::  
መንግስት በመግለጫው ያልታወቀ የታጠቀ ሃይል ነው ጥቃቱን የፈጸመው  ማለቱን በጽኑ የተቃወሙት አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፤ መንግስት የደህንነት መዋቅርና መከላከያ ሠራዊት እያለው “ያልታወቀ ታጣቂ” ብሎ መግለጫ መስጠቱ አግባብ አይደለም፤ በአፋጣኝ ጥቃት አድራሽ ሃይሎችን በዝርዝር ይፋ ማድረግ አለበት፤ህጋዊ እርምጃም ሊወስድ ይገባል ብለዋል፡፡  
“ያልታወቁ ታጣቂ ሃይሎች እነማን ናቸው?” ሲሉ የጠየቁት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ከመንግስት የደህንነት ክትትል የተሠወረ የታጠቀ ሃይል አይኖርም ብለዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ አጣዬ፣ ማጀቴ፣ ቆሬ ሜዳ እና አላላ በተባሉ አካባቢዎች የተፈፀመውን ጥቃትም ፓርቲያቸው በጽኑ እንሚያወግዝና ከተጐጂዎች ጐን እንደሚቆም አቶ ሙላቱ ተናግረዋል፡፡
ይህ መሰሉ ጥቃት በወለጋ፣ በጌዲኦና በጉጂ ሲያጋጥም መቆየቱን ያወሱት የፓርቲው ም/ሊቀመንበር፤ በተመሳሳይ ይዘትና መልክ እነዚህን ጥቃቶች የሚያቀነባብረው፣ የሚፈጽመውና የሚያስፈጽመው አካል በአስቸኳይ ተጣርቶ ለፍርድ መቅረብ አለበት ብለዋል፡፡
ከመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ውጪ የታጠቀ ሌላ ሃይል በሀገሪቱ መኖር የለበትም የሚል አቋም ያለው ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፤ ከዚህ ቀደም ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የቆዩና በህዝብ ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩ ሃይሎች በህግ አለመጠየቃቸው ሀገሪቱን ወደለየለት ስርአት አልበኝነት እንዲያመራት ያሰጋል ሲል አስጠንቅቋል፡፡ “የትም ይሁን የትም የታጠቀ አካል ካለ፣ ከመንግስትና ከሀገሪቱ ደህንነት አካል እውቅና ውጪ ሊሆን አይችልም” ያሉት አቶ ሙላቱ፤ “በሰሜን ሸዋ የተከሰተውም  የህዝብ ለህዝብ ግጭት ሳይሆን የታጠቁ ቡድኖች በሠላማዊ ዜጐች ላይ የከፈቱት ጥቃት ነው” ብለዋል፡፡
ለዚህ አይነቱ የጥቃት ሃይሎች እንቅስቃሴ በር የከፈተው ኢህአዴግ በአንድ ሃሳብና በአንድ ልብ ሆኖ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ባለመሆኑ ነው ያሉት የኦፌኮ አመራር፤ ኢህአዴግ አመራሩንና መዋቅሩን አሁንም አጥርቶ መፈተሽ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ኢህአዴግ በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ ያለ አመራሩን አለማጥራቱና መዋቅሩን ሙሉ ለሙሉ አለመቀየሩ በሀገሪቱ ለሚከሰቱ መሰል ጥቃቶችና ግጭቶች መንስኤ ናቸው ያለው ኦፌኮ፤በዚህ ምክንያት ለሚደርስ የሰው ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ድርጅቱ ከተጠያቂነት አያመልጥም ብለዋል፡፡
በአቶ ዳውድ ኢብሣ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በበኩሉ፤ስሙ ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ መነሳቱ አግባብ አለመሆኑን ጠቁሞ፤ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል፡፡ “ጥቃቱን የፈጸመው የኦነግ ታጣቂ ቡድን ነው የሚባለው ጉዳይ እኛን አይመለከትም” ያሉት የግንባሩ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ ኢዳባ፤ መንግስት በድርጊቱ እጃቸው ያለበትን አካላት መርምሮ ይፋ በማድረግ እውነታውን መግለጽ አለበት ብለዋል፡፡
በንፁሐን ዜጐች ላይ ጥቃት ያደረሱ ወገኖች ለፍርድ እንዲቀርቡ የጠየቁት አቶ ቶሎራ፤ ለዚህም ድርጅታቸው አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ሊቀመንበር አቶ ቶሎሣ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ መንግስት የህዝቡን ሠላምና ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበው፣ “ይህን ጥቃት የፈፀሙ የታጠቁ ሃይሎች ማንነት ከመንግስት የተሠወሩ አይደሉም” ብለዋል፡፡ “እነዚህ ታጣቂ ሃይሎች እንዴት ነው ወደ አካባቢው የተንቀሳቀሱት? የት ቦታ ነው የሠፈሩት? ወዴትስ ነው የተሠወሩት?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ቶሎሳ፤ “እነዚህ ሃይሎች ጨረቃ ላይ እስካልሠፈሩ ድረስ መንግስት አፈላልጐ ለህግ ማቅረብ አለበት” ብለዋል፡፡
መንግስትም በአካባቢው በደረሰው ጥቃት ላይ ያለውን ግልጽ መረጃ ለህዝብ ሊያቀርብ እንደሚገባም ያስታወቁት የኦብኮ ሊቀመንበር፤ ይህን እኩይ ድርጊት ፓርቲያቸው በጽኑ እንደሚያወግዝ ገልጸዋል፡፡ ተመሳሳይ ጥቃቶች በኦሮሚያ፣ ደቡብና ሌሎች አካባቢዎች ማጋጠሙን የጠቆሙት ፖለቲከኛው፤ የክልል አመራሮች የህዝብ ደህንነትን የመጠበቅ  ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አስታውቀዋል፡፡  
መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም በአራት የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች የታጠቁ ሃይሎች በፈፀሙት ጥቃት 30 ያህል ዜጐች መገደላቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ ንፁሀንን ከታጠቁ ሃይሎች ሳይለይ በተፈፀመው በዚህ ጥቃት 3 የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አባላት መገደላቸውን፣ ከ25 በላይ የሚሆኑ ዜጐቹ ክፉኛ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ጥቃቱን ሲፈጽሙ የነበሩ አካላት በሚገባ የተደራጁ፣ ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱና ባንዲራና አርማ ያነገቡ መሆናቸውን የሚገልፁት ምንጮች፤ ስለ እነዚህ አካላት ማንነትና ጥቃቱን የፈፀሙበትን አላማ በተመለከተ ከፌደራልና ከክልሉ የተውጣጣ አጣሪ ቡድን ጉዳዩን እያጣራ  መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአጣዬ ከተማ ከጥቃቱ በኋላ በተደረገ ህዝባዊ ስብሰባ፣ ጥቃት አድራሾቹ በግልጽ የኦነግ አባላት መሆናቸውን የሚያመለክት የድርጅቱን አርማና መለያ መያዛቸውን ነዋሪዎች ሲናገሩ ተደምጧል:: ጥቃቱ የተፈጸመባቸው የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች፤ አጣዬ፣ ማጀቴ፣ ቆሬ ሜዳ እና አላላ ሲሆኑ ጥቃት ፈጻሚዎቹ   የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው  ሲደርስ መሸሻቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር ድርጅት ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳባ ጉተማ፤ የአማራና የኦሮሞ ህዝብ አብሮ ብዙ ያሳለፈ፣ ለወደፊትም እልፍ ዘመናትን አብሮ የሚኖር መሆኑን በመግለጽ፣ ጥቃቱን ማንም ይፈጽመው ማን ድርጊቱ በእጅጉ የሚወገዝ ነው ብለዋል፡፡
በሁለት ብሔሮች መሃል ግጭት ለመፍጠር የሚደረገው ሙከራ ተደጋጋሚ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳባ፤ይሄን ጉዳይ መንግስት በአፋጣኝ እልባት ሊያበጅለት ይገባል ብለዋል::  “መንግስት የህግ የበላይነትን ማስጠበቅ አለበት፤ጥቃት ፈጻሚዎችን ለህግ ለማቅረብም በቂ አቅም ያለው መንግስት አለ ብለን እናምናለን” ብለዋል፤ አቶ ዳባ፡፡      

Read 14364 times