Print this page
Saturday, 13 April 2019 13:24

ስለ ሕግ ሳይሆን ስለ ሪፐብሊኩ አምላክ!

Written by  ከሙሼ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)


               የጥላቻ ንግግርን ለማስቆም በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰራጩ መረጃዎችን ማቀብ ላይ ያነጣጠረ ሕግ እየተረቀቀ መሆኑን ተከታትለናል፡፡ ይሁን እንጂ የፌስቡክ ችግር ሁሌም ወቅታዊ ስለሆነ የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት ብቻ የሚፈታ እንዳልሆነ በዓለም ላይ በቂ ተሞክሮ አለ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሕግ ዛሬ የገጠመንን ጊዜአዊ ችግር ከመቅረፍ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሕግ ውሎ አድሮ፣ ጊዜያዊ ችግሩ ተወግዶ፣ ነገር ሲበርድ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ከማፈን ውጭ ሌላ ሚና ስለማይኖረው ወቅታዊና የፍርሃት ውጤት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ፌስቡክን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ማስገባትና ማቀብ ሀገር ውስጥ ያለውንና ለመክሰስ ቅርብ የሆነውን ዜጋ በማሸማቀቅ የማፈን ውጤት እንደሚያስከትል መገመት ሊቅነትን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ በአንፃሩ ከሕግ እይታ የራቀውንና በውጭ ሀገር የሚገኘውን የፌስቡክ ሠራዊት - ሜይን ስትሪም የማህበራዊ መድረክ ተዋናይ ማድረጉም የሚጠበቅ ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም፤ የዜጎችን ሃሳብ በሕግ ከማቀብ በፊት ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ፣ ፌስቡክ ወቅታዊና ኢ-መደበኛ የመረጃ መለዋወጫ አውታር ሆኖ ሳለ ሊታመን በማይችልና እጅግ አስፈሪ በሆነ ደረጃ ተዓማኒነትና ተቀባይነትን እንዴት ሊያገኝ ቻለ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ፌስቡክ በየእለቱ ከፍተኛና የተጠናከረ ውግዘት ቢካሄድበትም ከመንግስትም ሆነ ከግል ሚዲያዎች በላይ ተደማጭና ተነባቢ ከመሆን ያገደው ነገር እንደሌለ እየተመለከትን ነው፡፡ አሁን የሚወጣው ፌስቡክን የሚያካትተው ሕግ የፌስቡክ ተዋናዮችን ይበልጥ ወደ ሕቡዕነት የሚገፋና በሽምቅ እንዲዋጉ የሚያደርግ በመሆኑ ተቀባይነቱን ያጠናክረው እንደሆነ እንጂ መፍትሔ የሚቸር ሆኖ አይታየኝም፡፡
በኔ ግምገማ፣ በአሁኑ ወቅት ፌስቡክ ሜይን ስትሪም ሚዲያ ሆኗል፡፡ አማራጭ ማህበራዊ መድረክ (Alternative Media) መሆን የሚገባው ፌስቡክ ያለ በቂ መነሻና ያለ ምንም ምክንያት ሜይን ስትሪም ሚዲያ ለመሆን እንዳልበቃም በቂ ትንታኔ መስጠት ይቻላል፡፡ ፌስቡክን፤ ሜይን ስትሪም ሚዲያ ወደ መሆን ያሸጋገረው ቀዳሚ መንስዔ በመንግሥት በኩል ያለው የመረጃ አቅርቦት ክፍተት ወይም የተዛባና ያልተጣራ መረጃ ስርጭት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በመንግሥት በኩል ለሕዝብ የሚደርሱ መረጃዎች እጅግ የዘገዩ፣ በቅርጽም ሆነ በይዘታቸው ደካማና አብዛኛውን ጊዜ እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ መሆናቸው፤ አማራጭ የመረጃ ምንጭ የነበሩ እንደ ፌስቡክ ያሉ የማህበራዊ ሜዲያ መድረኮችን ተደማጭ በማድረግ ወደ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭነት አሸጋግሯቸዋል፡፡ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት መፍረስና በሌላ ተመጣጣኝ ተቋም አለመተካት፣ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ውስጥ የተቋቋመው የቃል አቀባይ ቢሮ ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ ተደራሽነቱ ውስን መሆን፣ ያለበት የአደረጃጀት ችግርና የብቃት ማነስ ጉድለቶች ተደማምረው መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በማጣራት፣ በማሳለጥና በሚገባ በተደራጀ መልኩ በማሰራጨት በኩል ትልቅ ክፍተት መፈጠሩ እነ ፌስቡክ ወደ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭነት እንዲሸጋገሩ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
በመንግስት በኩል የሚታየው ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት፣ እጥረትና የመረጃ ፍሰት ችግር ስር የሰደደ መሆኑ የፈጠረው ክፍተት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ራሳቸውን ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ አድርገው የሾሙ፣ ውስጥ አዋቂ ነን የሚሉና በመረጃ የተንበሸበሹ ግለሰቦች በፌስቡክ መድረክ ላይ በስፋት መፍሰሳቸው ፌስቡክን ቀዳሚው ማህበራዊ ሚዲያ (Main stream) እንዲሆን ማድረጉም ይስተዋላል፡፡ ውስጥ አዋቂ ነን ባዮቹና አክቲቪስቶቹ የሚያሰራጩት መረጃ ስፋትና ጥልቀት “ተራ” የሚባልና የሚናቅ ካለመሆኑም በላይ የአንዳንዶቹ ማንነታቸውና የመረጃ ምንጫቸው ጭምር ስለሚታወቅ ከዚህ ዘለግ ሲልም ከዋነኛ የመገናኛ ብዙሃኑ ቀድመው ሰማያዊ ባህርይ አላብሰው፣ ጊዜና ሁኔታን ከግምት ሳያስገቡ ስለሚያሰራጩ ተደማጭነታቸውን እንዲጎላ አድርጎታል፡፡
እንዲህ ያለው ሁኔታ ደግሞ ከሃሳባቸው ጥራትና ጥልቀት ይልቅ በመረጃቸው ሚስጥራዊነት ምክንያት ቁጥር ስፍር የሌለው ተከታይ እንዲያፈሩና ራሳቸውን “በአዋቂነት” መንበር ላይ ሰይመው እንዲኮፈሱ ስላደረጋቸው የማያባራ የመደመጥና የመነበብ ፍላጎታቸው መረጃን ከማጣራትና ከማመሳከር እንዲርቁ አድርጓቸዋል፡፡ በውስጣቸው የተፈጠረው የመሳከር ስሜትም “ጀማሪ አዳኝ ዒላማ መምታቱን እንጂ የሚያጠፋው ነፍስ አይታየውም” እንዲሉ፣ ለወቅቱ ቀድመው መገኘታቸውን ወይም ለስልጣን ቅርበታቸውን ለማሳየት ወይም ሊያዳፍኑት ለፈለጉት አጀንዳ መልስ መስጠታቸውን እንጂ ድርጊታቸው ውሎ አድሮ የሚያስከትለው ጉዳትና መዘዝ እንዳይታያቸውና እንዳይሰማቸው አድርጓቸዋል፡፡
እነዚህ ግለሰቦች ኃላፊነት በማይሰማው መንገድ መንግስታዊ፣ ሀገራዊ፣ ድርጅታዊ፣ ማህበረሰባዊና ግለሰባዊ ሚስጥሮችን እንደዘበት ፌስቡክ ላይ ሲዘከዝኩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የመንግሥት ተቋማት የሰራተኛ ስብጥር፣ ከፍተኛ የባንክ ተበዳሪ፣ የብሔረሰብ ቁጥር፣ የባንክ ተቀማጭ መጠን፣ የመከላከያና የደህንነት የኃይል አሰላለፍ፣… ሳይቀር በፌስቡክ ላይ በመረጃነት ማቅረብ የተለመደ ተግባራቸው ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ ውስጥ አዋቂ ነን ባዮቹ መረጃዎችን የሚቃርሙት ቃለ መሀላ ከፈጸሙ ከፍተኛ ሹማምንትና ባለስልጣናት ጋር በፈጠሩት የዘመድ አዝማድ ግንኙነት፣ ባላቸው የዘርና የብሔር ትስስር፣ በአንድ ፓርቲ ውስጥ በአባልነት የተሳሰሩ በመሆንና በአንድ ቡድን ወይም በሌላ ቡድን ውስጥ የታቀፉ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአንድ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ወይም የፖለቲካ ቡድን የሚሰሩና ለዚህም ከጥግ እስከ ጥግ እገዛ እንዲያገኙ እያደረጋቸው ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የተፈጠረን የፌስቡክ ሠራዊት በሕግ አግባብ አቅባለሁ ማለት ራስን ከማታለል ወይም “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” እንዲሉ ከመሆን አያልፍም፡፡
በሀገራዊ ወይም በመንግስታዊ ሚስጥርና በሕዝብ መረጃ የማግኘት መብት መካከል ያለው ቀይ መስመር ተጥሷል፡፡ መረጃ ለማን፣ እንዴት፣ ለምን፣… እንደሚሰጥ የጠራ አሰራር እንደሌለ በሰፊው ይናፈሳል፡፡ በዚህ መልኩ ፍርሃትና ስጋት በነገሰበት ማህበረሰብ ውስጥ የመረጃ ሞኖፖሊ ይዘው “ውስጥ አዋቂዎች ነን” የሚሉ አክቲቪስቶችና ግለሰቦች የሚያሰራጩት መረጃ ሁሌም ትክክል ሆኖ ባይገኝም በስፋት የሚናኙት መረጃዎች ግን ክፍተት የሚሞሉና ማን እንደሚሾም፣ ከምርመራ በፊት ማን ላይ ምን ዓይነት ወንጀል እንደሚለጠፍ፣ እነማን እንደሚታሰሩና እንደሚታደኑ፣ ምን ዓይነት ግጭት እንደሚከሰት፣ ግጭቱን እነማን እንደሚመሩት፣ የግጭቱ ውጤቱ ወዴት ሊያመራ እንደሚችልና ግጭቱን የሚመሩት ኃይሎች እስከታጠቁት መሳርያ ድረስ… የሚዘልቁ በመሆናቸው የፌስቡክ ውስጥ አዋቂዎችንና አክቲቪስቶችን ተከታዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚገመተው በላይ እንዲጨምርና ፌስቡክ ለኢትዮጵያውያን በቀዳሚ የመረጃ  (Main stream) ምንጭነት እንዲታጭ አድርጎታል፡፡
በበኩሌ እንደ ዜጋ ስጋት አለኝ፡፡ መንግስት ቃለ መሃላ ከገባላቸው ጉዳዮች አንዱ የሪፐብሊኩን ሚስጥር መጠበቅ ነው፡፡ የሀገራችን መረጃዎች፣ የመንግስት ሚስጥሮች፣ በመንግስት መስሪያ ቤት የሚገኙ ሰራተኞችና ከመንግስት ባንክ የተበደሩ ነጋዴዎች ብሔር ስብጥር፣ የመንግስት ሹመኞ ያደረጓቸው የደብዳቤ ልውውጦችና የመሳሰሉት ፕሮቶኮል ያላቸው ሰነዶችና መረጃዎች ከሚመለከተው አካል ውጭ በማንም ቡድን ወይም ግለሰብ ወይም አክቲቪስት መታወቅም ሆነ በእጅ መግባት የማይገባቸው ሰነዶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰነዶች ወይም መረጃዎች በግለሰቦች እጅ እየገቡ የብሔር ግጭት በሚቀሰቅስ መልኩ የፌስቡክ መበሻሸቂያና ቂም በቀል መወጣጫ ሆነው መመልከት ግን ለጥላቻ ንግግር ሕግ ከማውጣትም በላይ ሊያሳስበን ይገባል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረውን ስርዓት (Order) ለመታገል ሲባል ለታማኝ ግለሰቦች፣ ለአክቲቪስቶች፣ ለውስጥ አርበኞችና ለታዋቂ ሰዎች መረጃ በማሾለክ ትግሉን ማጧጧፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ ትግሉ ተደምድሟል፡፡ አሸናፊው ኃይልም የሪፐብሊኩና የክልል መሪ ሆኗል፡፡ እናም ለትግሉ ሲባል ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ መረጃን የማሾለክ አሰራር ከዚህ በኋላ መቆም ይገባዋል፡፡ መንግስትም መንግስት መሆንና ሚስጢሩ የቃለ መሐላ ውጤት ስለሆነ የሕይወት ዋጋ ጭምር በመክፈል መጠበቅ ግዴታ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ አክቲቪስትም አክቲቪስት ነው፡፡ በንክኪ በሚያገኘው መረጃ ላይ ተመስርቶ ሁከትና ብጥብጥ እንዲሁም ልዩነትና ዘረኝት ወይም የአንድ ብሔር የበላይነት እንዲያሰፍን ሊፈቀድለት አይገባም፡፡ በተለይ እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ በተለያየ መንገድ የተገኘን የመንግስትን መረጃ ተጠቅሞ፣ የፌስቡክ ደንበኛ ማሰባሰቢያ አጀንዳው እንዲያደርግ መፍቀድ ከባድ ስህተት ነው፡፡
በኔ በኩል ፌስቡክ ከተመሰረተበት አማራጭ የመረጃ መለዋወጫነት ውጭ ወደ መደበኛ የመረጃ መቀባበያነት እንዳይሸጋገር ተቀባይነቱን ማምከን ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ዜጎች ሁሉ እኩል ስለሆኑ መረጃ ለሁሉም ዜጋ በአግባቡ በመደበኛ ተቋም ሊሰራጭ ይገባል፡፡ ከእንግዲህ የጫጉላ ዘመን ያብቃ! በኢኮኖሚውም በመረጃውም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ ከዚህ ቀደም የነበረው አንዱን ብሔር የራስ አደርጎ የማቅረብና ሌላውን የእንጀራ ልጅ አድርጎ የማራቅ በጊዜ ሊቀጭ ይገባል፡፡ ኢ-መደበኛው ምዕራፍ ይዘጋ፡፡ መደበኛው አሰራር ይጠናከር፡፡ የመረጃ አጠባበቅ ችግር ያለባቸው መስሪያ ቤቶችና ባለስልጣናት ይገሰጹ፣ ይመከሩ፣ ትምህርት ይሰጣቸው፡፡
መረጃ     ኃይል ነው፡፡ በአግባቡና በስርዓቱ መያዝ አለበት፡፡ ልዩነት በሥራ፣ በብቃትና በውጤታማነት እንጂ መረጃ በድብቅ በማቀበል መሆኑ ማብቃት አለበት፡፡ ማንም ዜጋ፣ ማንም ባለስልጣን፣ ማንም አክቲቪስት፣ ማንም ውስጥ አዋቂ ነኝ ባይ ማወቅ ከሚገባውና ከስልጣኑ ወይም ከሹመቱ በላይ መረጃ ሊኖረው አይገባም፡፡


Read 1303 times