Saturday, 13 April 2019 13:47

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

“ሁሌም ስለ ጨለማ ከማውራት አንድ ሻማ ማብራት!!” -ኮንፊዩሸስ-
                                  
                አንድ ንጉስ ነበሩ አሉ፡፡ ከተለመደው መሳፍንታዊ ስርዓት ያፈነገጡ፡፡ … ለተቀናቃኞቻቸውም ፈተና የሆኑ፡፡ … ጠላትም፣ ወዳጅም ‹ሞገደኛ!› እያለ የሚጠራቸው፡፡ ሰውየው በሞቱበት ወቅተ ለህዝባቸው አደራ የሰጡበት ኑዛዜ እስከተነበበ ድረስ ሃሳባቸውንና ድርጊታቸውን መረዳት አስቸጋሪ ነበር፡፡ … ለምሳሌ ከተቃዋሚዎቻቸው ውስጥ አንዳንዳችን ይጠሩና በየተራ! … “ስደበኝ” ይላሉ፡፡ “እንቢ” ካለ ወይም መልስ ካልሰጣቸው እየተበሳጩ “እገድልሃለሁ” ይሉታል፡፡ በአቋሙ ከፀናባቸው እስር ቤት ይልኩታል፡፡ … “እዛው ትሞታለህ” ብለው እየፎከሩ፡፡ ሃሳባቸውን እየቀየሩ የሚለቀቁ ብዙ ናቸው፡፡ … አንዱ ግን ባለመነቃነቁ  እዚያው ቀረ፡፡
“ስደበኝ” ሲሉት “ባይሉኝም አይቀርሎትም” ብሎ ሙልጭ አድርጎ ያስታጠቃቸውን ደግሞ “እግሬ ላይ ወድቀህ ይቅርታ ጠይቀኝ” በማለት ያስፈራሩታል፡፡ “በጭራሽ!” ካላቸው እንደ ፊተኛው ያስሩታል፡፡ ብዙዎች እግር ስመው ተለቀቁ፡፡ አንዱ ግን እዛው ቀረ፡፡ … አሻፈረኝ ብሎ፡፡
“ስደበኝ” ሲባሉ “እሽ” ብለው ተሳድበው፣ ይቅርታ ከጠየቁት ውስጥ አሳማኝና ምክንያታዊ የሆነውን አንድ ሰው አስቀርተው በማሰር ሌሎቹን ለቅቀዋቸዋል፡፡ ብዙዎችን ያስገመረው ግን ንጉሱ እስከሞቱበት ቀን ድረስ ለነዚህ ሶስት እስረኞች የጠየቁትን ሁሉ በማቅረብ የሚያደርጉት እንክብካቤና የሚያሳዩዋቸው ርህራሄ ነበር፡፡ ለመሆኑ ኑዛዜያቸውስ ምን ይሆን?
***
 ወዳጄ፡- “መሻል” ማለት ሌሎች ሰዎች ራሳቸውን ማየትና መረዳት ከሚችሉበት በዘለቀ መንገድ ወደ ውስጥ መመልከት ነው፡፡ “መሻል” ማለት “Average man” ከሚባለው ሰው አንድ ወይም ሁለት እርምጃ ቀደም ብሎ ማሰብና መጭውን መገመት መቻል ነው፡፡ “መሻል” ማለት የራሱን ጥቅም ለብዙሃኑ መስዋዕት ማድረግ ነው፡፡ የሌሎችን ጉድለት ለመሙላት ሲባል እየኖሩ አለመኖር፣ እያወቁ አለማወቅ፣ አንዳንዴም ሳያጠፉ ይቅርታ መጠየቅ፣ የ“መሻል” ብቻ ሳይሆን የአሸናፊነትም ባህሪ ነው፡፡ ደግነት ደግሞ ከሁሉም ይልቃል፡፡ … “Generosity is a mark of superiority!” እንዲሉ፡፡
ወዳጄ፡- “ያለፈ ጊዜ፣ የተወረወረ ጦር፣ የመከነ ፍላጎት (lost desire) እና ከአፍ የወጣ ቃል አይመለሱም” ይላሉ ሊቃውንት፡፡ ነገር ግን ሰው ከስህተቱ ከታረመ፣ በጥፋቱ ከተፀፀተ፣ ከቀደሙ እሱነቱ ያሁኑ ማንነቱ ተሽሏል ማለት ነው፡፡ ጥፋትን ከደገመ፣ ካልታረመና ካልተፀፀተ ግን ከአሁን እሱነቱ ባለማወቅ ያጠፋው የቀድሞ ማንነቱ ይሻላል፡፡ … የለም እንጂ!!
አንድ ግለሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የዕምነት ድርጅት፣ ሆቴል ወይም ምግብ ቤት፣ ት/ቤት ወይም መንግስት ከሱ በፊት ከነበሩት ወይም አጠገቡ ካሉት የሚሻል መሆኑ የሚረጋገጠው ተፎካካሪውን ወይም ተቃራኒውን ስለነቀፈ፣ ደካማ ጎኑን እያጋለጠ፣ ችግሩን እያጎላ ስለተናገረ አይደለም፡፡ እሱ ራሱ የሚሻልበትን ምክንያቶች በተግባር ማሳየት ሲችል ነው፤ ሆኖ ሲገኝ፡፡
“እሻላለሁ” የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት ተፎካካሪውን በማያሳምን ምክንያቶች መንቀፍ ኪሳራ እንጂ ትርፍ አያስገኝም፡፡ ተፎካካሪነት ጥቅም አለው፡፡ ትጋትን ይጨምራል፣ ያነቃቃል፣ ማን አለብኝነትን ይቀንሳል፡፡ “ዕድገት የተቃራኒዎች ውጤት ነው፡፤” ደግሞስ “መጥፎ” ከሌለ “ጥሩ”ው በምን ይታወቃል? … ጥሩውን መፈለግ ደግሞ የሰው ልጆች ሰብዓዊና ስነልቦናዊ ባህሪ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋልና፣ የዚህ ሳምንት ትልቁ ዜና (አሳዛኙ የእሳት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ) ያዩ (ኢሊባቦር) የሚገኘው የማዳበሪያ ፋብሪካ ጉዳይ ነው፡፡ በግንባታ ላይ ከስምንት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ይህ ፋብሪካ፤ “የቀድሞው” ኢህአዴግ ትልቅ ስህተትና የሜቴክ እፍረት መገለጫ እንደሆነ መንግስት አሳውቆናል፡፡ ፕሮጀክቱ ያለ ርህራሄ በመዘረፉና መጠናቀቅ በነበረበት ጊዜ ባለመጠናቀቁ፣ በአገራችን ላይ የብዙ ቢሊየን ብሮች ኪሳራ ደርሷል፡፡ በየአንዳንዷ ቀን 3 ሚሊዮን ብር ወለድ እየተከፈለበት መሆኑም ተዘግቧል፡፡ ፕሮጀክቱን እንዲያጠናቅቅለት መንግስት ከሞሮኮ ኩባንያ ጋር እንደተዋዋለም ሰምተናል፡፡
ወዳጄ፡- አስተዋይነት በጎደለው “የፖለቲካ ውሳኔ” ከግል ኩባንያዎች ተነጥቆ፣ ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣውን ጨረታ ተወዳድረው ማሸነፍ ላቃታቸው እንደ አንባሰልና ዲንሾ ለመሳሰሉት “ፖለቲካዊ” የንግድ ድርጅቶች “እነሆ” መባሉ ትልቅ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ ለድሃው ገበሬ ወገናችን ጉሮሮው ላይ የተሰካ አጥንት ሆኗል፡፡ “Pain on the ass” እንደሚሉት፡፡
ቀደም ሲል የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ የመሸጫ ዋጋ የሚወሰነው በመንግስት ነበር፡፡ ንግዱ ከግሉ ዘርፍ ከተቀማ በኋላ ግን የዋጋ ትመናው ነገር እንደነበር መዝለቁ አጠራጣሪ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምክንያቱም “ንግዱ” በተወረሰበት ጊዜ የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ (urea and DAP) ዘጠናና መቶ ብር ሲሆን አሁን አስር እጥፍ ሆኗል፡፡ ማዳበሪያውን በግድ እንዲገዛ ወይም በብድር እንዲወስድ የሚገደደው ገበሬ፤ ብዙ ጊዜ በእርሻው ወቅት ስለማይደርስለት አበሳው የበዛ ነው፡፡ “የተሻለ ህይወት ለሁሉም” (Better life for all!) የሚል መርህ የነበረው ኢትዮጵያ አማልጋ ሜትድ ሊሚትድ ኩባንያ በተፅዕኖ እንዲፈርስና እንዲዘጋ ከመደረጉ በፊት ከግብዐቱ አቅርቦት በተጨማሪ ለገበሬዎች ትምህርትና ስልጠና መስጠትን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ያግዛቸው እንደነበር ፀሐፊው ምስክር ነው፡፡
የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና በወቅቱ የነበሩት የፓርላማ አባላት ጉዳዩን ለውይይት አቅርበው፣ መንግስት መፍትሄ እንዲፈልግ ቢያሳስቡም “ጆሮ ዳባ ልበስ” ተብለዋል፡፡ .. የፖለቲካ ውሳኔ ነውና!! … እዚህ ጋ ጥያቄው፤ የአገር ልማትና የደሃውን ገበሬ ህይወት ለመለወጥ የሚተጉ በተለያየ የስራ መስክ የተሰማሩ አገር ወዳድ ነጋዴዎችን ማግለል፣ ኩባንያን ማፍረስና ሰራተኛን መበተን፣ የመንግስትን ሚናና ለዜጎቹ ያለውን ኃላፊነት አያሳንሰውም ወይ? … መልካም መሪዎችንስ አያሸማቅቅም? … የማዳበሪያ ጉዳይ “ትሻልን ፍትቼ ትብስን አገባሁ” አያሰኝም? የሚል ይሆናል፡፡ … መልሱን ላንተ ለወዳጄ ትቸዋለሁ፡፡
***
 ወደ ጨዋታችን እንመለስ፡- ሞገደኛው ንጉስ በኑዛዜያቸው ለማሳወቅ የሞከሩት፣ አገር መመራት ያለበት በምክክር መሆኑን፣ እሳቸውን ተክተው አገሪቱን እንዲያስተዳድሩ ያሰሯቸውን ሶስት ሰዎች እንዳዘጋጁ፣ ህዝባቸውም ሰዎቹን እንዲያከብሯቸውና እንዲከተሏቸው ነበር… አደራ ነገር፡፡ ምክንያታቸውም፡- የመጀመሪያው፤ ሰው ለህሊናው ብቻ የሚታዘዝ (ethical) በመሆኑ ለዕምነታቸው ፅናት ምሰሶ እንደሚሆን፣ ሁለተኛው ለክብሩ ከመሞት ወደ ኋላ የማይል (die hard) ስለሆነ የጦር አበጋዝ ሆኖ አገር እንዲከላከል፣ ሶስተኛው ደግሞ ብልህ ስለሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥቅም ያስገኛል የሚል ነው፡፡ … ከእንደ,ኔ ዓይነቱ እነሱ ይሻሏችኋል በሚል መንፈስ፡፡ …. ምንም እንኳ በእስር ቤትና በስልጠና ቦታ ያለው ልዩነት ባይገባቸውም፣ መጭው ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡ ሩቅ የሚያይና ምሳሌ የሚሆን መሪ ደግሞ ይከበራል፡፡ እዚህ ጋ “መሻሻል” ትክክለኛው ቦታ ይመስለኛል፡፡
በነገራችን ላይ ለነገው የፅዳት ዘመቻ ተዘጋጅተሃል? … አገር መውደድ ትንሽ በሚመስሉ ነገር ግን ከፍታ ባላቸው ነገሮች እንደሚገለፅ አትርሳ፡፡ በየመንገዱ አለመፀዳዳትና ቆሻሻ አለመጣል ከስልጣኔ ባለፈ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ … መሻል!!
“ሁሌም ስለ ጭለማ ከማውራት አንድ ሻማ ማብራት!!” ይልሃል ታላቁ አባት ኮንፊዩሸስ፡፡
ሠላም!!

Read 1359 times