Saturday, 13 April 2019 13:45

የገብረክርስቶስ ደስታ ሽቅርቅር ግጥሞች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)


              …ግብሩን ሳያበቃ እንደዛገ ቢላ  ሳይለብስ ጥቀርሻ
ማህፀኑ ሳይነጥፍ፣ ባድማ ሳይበለት የፈጠራው እርሻ
ሳይጐራበተው ምክነት እርግማኔ
ተስፋው ሳይጨነግፍ ይሙት ባለቅኔ፡፡
ተፈሪ አለሙ (የካፊያዎች)
ይህ የመግቢያ ግጥም የሚወስደኝ ወደ ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ነው፡፡ ገብረክርስቶስ በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው፣ በሥራዎቹና የሥራውና የትሩፋቱ አሻራ በነካቸው ዘንድ ሁሌ የሚወደስ የጥበብ ሰው ነው፡፡ ከዘመን አቻዎቹ ጋር ሲነፃፀር በሁለቱም የጥበብ መንደር በናፍቆት የሚወሳ፣ በሥራው የማይረሳ ሆኖ፣ በመገናኛ ብዙሃንም በየሰበቡ ስሙ ብቅ የሚል ባለ ሀውልት ነው፡፡
በተለይ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” በሚል ርዕስ በታተመው መድበል በጥቂቱ ስለ ሰውየውና ስራው መወሳቱ፣ አብሮም የግጥም ሥራዎቹ ለገፀ ንባብ መብቃታቸው፣ የሥራዎቹ ነበልባል እንዳይከስም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ስለ ገብረክርስቶስ ከተወሩትና ከተነገሩት ነገሮች ውጭ በግሌ ያገኘኋቸው አንድ የሃይማኖት መምህር (በዘመኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ የነበሩ) እንዳጫወቱኝ፣ ሰውየው ቆርጦ ለሥራ ሲነሳ  ቤቱን ይዘጋ ነበር፡፡ አንዳንዴ ለአንድ ወር ያህል የሚያስፈልጉትን ነገሮች፣ የጠርሙስ ቢራዎችን ጨምሮ ይሸምትና ክትት ይላል፡፡ ከዚያ ሲወጣ አንዳች ነገር ወልዶ የአራስነት ጊዜው ያበቃል፡፡
ዛሬ ስለ ህይወቱ ማውራት አይደለም - ዓላማዬ፡፡ ከታተሙት ግጥሞቹ ጥቂት ነገር ማየት ነው፡፡ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” የታተመው በ1998 ዓ.ም፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ነው፡፡ መጽሐፉ 251 ገፆች ያሉት ሲሆን፤ ስለ ገጣሚው፣ ግጥሞቹና ሌሎችም ሃሳቦች በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሠፍሯል::
የገብረክርስቶስ ግጥሞች ዘውጋቸው በአብዛኛው ሌሪክ ሲሆኑ ጥቂት ተራኪ ግጥሞችም አካትተዋል፡፡ እውነት ለመናገር በዚህ በሚንቀለቀልና በማይደበቅ ነበልባል ስሜቱ ከሌሪክ ውጭ ሌላ ዘውግ ይጠቀማል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ጊዜ የማይሰጥ ትኩሳትና እርር ድብን ያለ ቆሽት፣ በሰቀቀን እንባ የታጠበ ስሜት፣ ከሌሪክ ቀለሞች ይበልጥ የሚያደምቁት አይኖሩም፡፡ በሀዘን የተወጋ ልብ፣ በትካዜ ፉጨት የተመሳቀለን ድንኳን፣ በፍቅር ፍላፃ የተሰቀሰቀን አንጀት በምን ማስተንፈስ ይቻላል፡፡
በዚህም የተነሳ የገብረክርስቶስ ግጥሞች ከሌሪክም ሙሾን፣ መዲናንና የፍቅር፣ የትዝታ ንዑስ ዝርያዎችን ተጠቅሟል፡፡ ሃሳቡ ድድር ቢሆንም በሞቀ ዜማ የተነከረ ስለሆነ የሣቅና ልቅሶን ድንበር ያፈረሰ ነው፡፡ ከሕያው ሰው እስከ የሙት መቃብር አለፍ ሲልም ባልተለመደ ሁኔታ አጽም የሚያናግሩት ግጥሞች፤ የገጣሚውን ስስነት አንቀው ሌላ የደፋር ኮት ያለበሱት ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ የሚስረቀረቅ ስሜትም ይታይበታል!...እውነትም ግጥሞቹ ውስጥ ይህንኑ ስስነት የሚያግዝ፣ የሰቀቀኑን ድባብ የሚያባብሉ የሙዚቃ መሣሪያዎች ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ ከበሮ ክራር እያለ ከማግባባቱ በስቲያ “ቦጊ” እና የመሳሰሉትን ግጥሞች ዘንቆ የሃሳቦቻችን ክንፎች ሁለት ዓለም እንዲበርሩ አየሩን አሠናድቶልናል፡፡
ለምሳሌ ወደ ሙሾና ግጥሞቹ ስንመጣ “ከሞተች ቆይቷል” አንዳች መንቀጥቀጥ፣ አንዳች መባባት የዋሾነት ዜማ…የገደል ማሚቱ…የእንባ ድምፀት…የደረቀ አበባ…የከሰመች ሰንደል…የተራበች ልብ…የተራቆተች ነፍስ… የባከነች ህይወት… አፍንጫችን ሥር ያስቀምጣል፡፡ ስንኞችን እመዝዛለሁ - (ገፅ 148)
ከሞተች ቆይቷል ብዙ ዘመን ሆኗል
        ብዙ ነበር ጊዜው
ግን ፎቶግራፏ አለ ደብዳቤዋም አለ
በጠጉሯ ጉንጉን  የጠቀለለችው
ምን ቀጠሮ ነው!
    ቀን የቀን ጐደሎ
የቀን ጥቁር መጥፎ!
አበባ ሄድኩ ይዤ
እዚያ አበባ አልጠፋም፡፡
በመቃብሯ ላይ በዙሪያ በጐኑ
በመቃብሯ ውስጥ አበባ ተኝቷል፡፡
ስሜቴ ፈነዳ ገላዬን በተነው
    ነፍሴን ነቀነቃት!
እንባዬ ወረደ ጉንጬን አረጠበው
ለተረሳ ነገር እንዴት ያለቅሳል ሰው
      ለተረሳ ነገር!  
ምን ጊዜው ቢረዝም…
ግጥሙ እንደ ሰዓሊነቱ ቀለም የተቀባ፣ ምሥል የሚፈጥር ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ምሠላ የሚለውን የግጥም አላባ በሚገባ ተጠቅሞበታል፡፡
ይህቺ ገፀ ሰብ በተራኪው ዘንድ ደብዳቤዋን በጠጉራ ጉንጉን ጠቅላላ ሰጥታዋለች፡፡ ፎቶግራፏም እርሱ ዘንድ አለ፡፡ ከትዝታዋ በቀር አሁን በአፀደ ሥጋ የለችም፡፡ ነገር ግን ትዝታዋ ሲከብበው፣ ሠቀቀኗ ሲያላውሰው፣ አበባ ለሰጠችው አበባ ሊሰጣት ሄዷል፡፡ የዚያ ገጠመኝ ትርክት ነው፣ የዚያ ሰቀቀን እንባ ነው፡፡ ስንኞቹ በሀዘን ተዘልዝለው በእንባ ጤዛ የረጠቡ ናቸው፡፡ ገፀ ሰቡ ታምሟል፤ አንባቢንም ያሳምማል! ይሰቀስቃል!
“አበባ ይዤ ሄድኩ!” ይላል፡፡ ግራና ቀኝ አበባ ከብቧታል፡፡ ሌላኛዋ - አበባ ደግሞ መቃብር ውስጥ አለች፡፡ አበባነት ልጅነት ነው፤ አበባነት ውበት ነው፤ አበባነት ተስፋነት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሥዕል እንባውን አፈረጠው፣ ልቡን ቆነጠጠው፡፡ እንባው ጉንጩን ሲያጥበው “ከሞተች ቆይቷል’ኮ!” ብሎ ለራሱ ነገረው፡፡ ግን አልሆነም!...ትዝታዋ እንደ አበባዋ ትኩስ ነው፡፡  “ተረስቷልኮ” አለ፡፡ የማይረሱ ሀውልቶች አሏት:: እናም ስንኞቹ እንባቸውን ሳይጠርጉ ቀጠሉ፡-
ድሮም አውቄያለሁ - ተረድቼዋለሁ
ፀሐይ ጥቁር ስትሆን!
ቀን ቀንን ሲያጠላው …ሌት ሌትን ሲሸፍት፡፡
እረስቼሽ እንደሁ
    እንዴት አንቺን ልርሳ!
ነፍሴ አብሯት የሚኖር የፍቅርሽ ጠባሳ
ፍቅርሽና ፍቅሬ የተወሳሰበው
    አልበጠስ አለኝ
አልበጠስ አለኝ ባስበው ባስበው     
ማን ነበር? ማን ነበር?
ማን ነበር እንደዚህ ብሎ የገጠመው
    ይመስላል ዘላለም…
አንቺ የኔ እመቤት ብያት የነበረ
    አንተ የኔ ጌታ ብላኝ የነበረ
አንተ የኔ ጌታ
አንተ የኔ ጌታ ብላኝ የነበረ
    አንቺ የኔ እመቤት
    ይመስላል ዘላለም…
የረሳት መስሎት፣ ለምን እንዳልረሳት አስቦ፣ ለካስ ሊረሳት አይችልም! ይረሳታል? የፍቅሯ ጠባሳ ውስጡ ተቀምጦ ፍቅሯና ፍቅሩ፣ ተጐናጉኖ፣ ሊፈታና ሊተረተር፣ ሊለያይ አልቻለም፡፡ አስቦታል፣ ሊበጥሰው ስቧል፡፡ ነፍሱ ተፋልማለች፤ ናላው ዞሯል:: ግን ትዝታዋ አሸንፏል፡፡ ስለዚህ ወደ ኋላ ዞር ብሎ የገጣሚውን ግጥም በንቡር ጠቃሽ ዘይቤ ይጠልፍና ያነበንባል፡፡ “ማን ነበር ገጣሚው” እያለ ነፍሱን ይጠይቃል፡፡ ፍቅር ዘላለም ይመስላል፤ ፍቅር ወሰን የለውም! ብሎ የሰበከውን ሰው ሰነድ፣ ከልቡ ገፆች እየገለጠ ያነብባል፡፡ ግን በርግጥም “የኔ ጌታ!...የኔ እመቤት” እየተባባሉ በሚከነፍበት የፍቅር ዓለም፤ ጊዜ መቋጫ፣ ዘመን መግቻ የለውም:: እውነት ነበር፤ እውነት ነው፤ እውነት - ይመስላልም!
ግጥሙ ሲቀጥል፡-
    አውቃለሁ - አውቃለሁ
          አለ ትዝታዋ
አውቃለሁ - አውቃለሁ
በመቃብሯ ውስጥ አበባ ተኝቷል
 በመቃብሯ ውስጥ ጢስ እንጨት ይጨሳል፡፡
    ከርቤ፣ ብርጉድ፣ እጣን - መቃብሯ ሽቶ
    ጣፋጭ መዓዛ አለው አጥንቷ ታቦቱ
    መቅደስ ቤተልሔም ቅኔ ማኅሌቱ
    ዕጣኑ ይጨሳል - ቤቱ ይታጠናል
        ፍቅሬ ሙሽራዬ!
እመቤቴ ፍቅሬ ለኔማ አለኝታዬ
ቤቱ ይታጠናል
ልዩ መዓዛ አላት - ማግሪፍ፣ ዲዩር፣ ቫኔል፡፡
የቆየ መቃብር ውስጥ አበባ አለ፡፡ አጥንቷ ታቦት፣ ሥፍራው መቅደስ ነው፡፡ ለዚያውም ቤተልሔም፡፡ ዕጣን ይታጠናል፣ ሽቶ አለ፣ ማኅሌቱና ቅኔውም ዐውዱን ለውጦታል፡፡ የእንባ ልምጭ በሚገርፈው ጉንጭ፣ እየተላጠ የሚያልቅ በሚመስል ዐይን ስር ይህ ሁሉ ትዕይንት አለ፡፡ ፍቅር ይህንን ሁሉ ትርዒት፣ ይህንን ሁሉ ቅድስና ከተዓምራት ሻንጣ ውስጥ ይመዝዛል፡፡ ትዝታ የየትኛውንም ዐለም ሥዕል መዝዞ ሌላ ቴአትር ይሠራል፡፡
መቃብር ውስጥ ያለች አበባ፣ የገጸ ሰቡ ልቡ ውስጥ ያለች ሙሽራ ናት! እመቤትና የፍቅር ቀንበጥ ሆና ትነበባለች፡፡ መጽሐፉ መቃብሯ ነው፡፡ የተፃፈችበት ብዕር ህይወት ናት፡፡ የፈረሰውን ቀንዋን ሁሉ፣ የነጠፈውን ተስፋ ሃይል መልሶ ያመጣው - ምናብ ነው፡፡
ሥርዓተ ነጥቡ ዘላለምን በነጠብጣቡ ዳና ላይ አሻግረው ለቅቀውታል፡፡ አውቃለሁ እና አውቃለሁ በሚለው መካከል ያለው ክፍተት፣ ገፀ ሰቡ የፈራውን እውነት የሚሸሽበት ቀዳዳ ነው፡፡ ዱሃ ውስጥ ገብቷል፡፡ እየቧጠጠ ነው፡፡ የሚያወጣው የለም፡፡
የገብሬ ግጥሞች ብዙ የዚህ ዓይነት መልኮች አሏቸው፡፡ ብዙ የዚህ ዓይነት ድምፆች ይስተጋባሉ፡፡ የጀግንነት ዋልሴ የታጠቁ፣ በውበት ዘይነው የቆሙ ደመግቡ የስንኝ ሀውልቶችም አሉት፡፡ ብዙ ግጥሞቹ ውስጥ ንፋስ፣ ሙዚቃ፣ ቀለም… የሚሉ ነገሮች ይዘወተራሉ፡፡ንፋሱ በግጥሞቹ ቅርፆች፣ በፍሰትና ተስማሟቸው ላይ አንዳች ተፅዕኖ ያሳደረ ይመስላል፡፡ የሕይወት ማያ መነጽሩም ስልት ነው፡፡ አሠነኛኘቱም ላይ ይግፋል! “ሙዚቃ”ው - የሕይወትና የስንኞቹ ዳንሶች ናቸው፡፡ ቀለሞቹ የሰዓሊነቱ … የሕይወት ቀመሮች አድርገን ልንወስዳቸው እንችላለን፡፡ ብዙ ግጥሞቹ ትዝታ የተሸከሙትም ለዚያ ይመስላል፡፡
ገብሬ ቀልድ አያውቅም፤ ቦክስም ይችላል፤ እነዚህ ምልክቶች ግጥሞቹ ውስጥ ብቅ ይላሉ፡፡ ገብረክርስቶስ ደስታ በሜሎዲ የደመቀ የግጥም ደብር ነው፡፡ አሳዛኝ መዲና ግጥሞቹንም ከእነ ዜማቸው ብናንቆረቁር ትካዜ አይጐርሰንም፡፡ አፋቸው ውስጥ የተጐዘጐዘው ውበት ያጽናናል! “We tend to like poems for what they are,  and what they represent to us” እንዲሉ፡፡

Read 908 times