Print this page
Tuesday, 16 April 2019 00:00

በአለማችን በ2018 ሞት የተፈረደባቸው 690 ሰዎች ተገድለዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ ቻይናን ሳይጨምር በአለማችን 20 አገራት ውስጥ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው 690 ያህል ሰዎች መገደላቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በ2017 በአለማቀፍ ደረጃ የሞት ፍርድ ቅጣት ተጥሎባቸው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 993 እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በ2018 ይህ ቁጥር የ31 በመቶ መቀነስ ማሳየቱን አመልክቷል::
ቻይና በሞት የቀጣቻቸውን ዜጎች ቁጥር በመደበቋ በሪፖርቱ ውስጥ ሊያካትተው አለመቻሉን የጠቆመው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ አገሪቱ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን በሞት ልትቀጣ እንደምትችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡
በ2018 ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሞት የተቀጡባቸው ቀዳሚዎቹ  አገራት ኢራን፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ቬትናምና ኢራቅ እንደሆኑ የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ በአመቱ በአለማችን በሞት ከተጠቁት 690 ያህል ሰዎች መካከል 77 በመቶ ያህሉ በእነዚህ አራት አገራት እንደተገደሉም አመልክቷል፡፡
በ2018 የሞት ፍርድ ተፈጻሚ የተደረገባቸው ሰዎች ቁጥር ኢራን፣ ኢራቅ፣ ፓኪስታንና ሶማሊያን በመሳሰሉ አገራት መቀነስ ማሳየቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ከፍተኛው መቀነስ በተመዘገበባት ኢራን በ2017 ላይ 507 የነበረው ይህ ቁጥር በ2018 ወደ 253 ዝቅ ማለቱን አመልክቷል፡፡ በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር በእነዚህ አገራት መቀነስ  ቢያሳይም በአንጻሩ ደግሞ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ሱዳንና ቤላሩስን በመሳሰሉ አገራት መጨመር  ማሳየቱንም ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ማንኛውም አይነት ወንጀል ቢሰሩ ሰዎች በሞት እንዳይቀጡ የከለከሉ የአለማችን አገራት ቁጥር ባለፈው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ላይ 106 መድረሱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ አግደውት የነበረውን የሞት ፍርድ እንደገና ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩ ታይላንድን የመሳሰሉ አገራት መኖራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 5145 times
Administrator

Latest from Administrator