Wednesday, 17 April 2019 00:00

የሲንጋፖሩ ቻንጊ ለ7ኛ ጊዜ የአለማችን ምርጡ አውሮፕላን ማረፊያ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ስካይትራክስ የተባለው አለማቀፍ የአቪየሽን ዘርፍ ተቋም፣ የ2019 የፈረንጆች አመት የአለማችን ምርጥ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ላለፉት ስድስት ተከታታይ አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የዘለቀው የሲንጋፖሩ ቻንጊ ዘንድሮም በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡ ተቋሙ በአለማችን በሚገኙ ከ550 በላይ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ባወጣው የዘንድሮው የምርጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች ዝርዝር የሁለተኛነት ደረጃን የያዘው ቶክዮ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን፣ የደቡብ ኮርያው ሌንቼን ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነው ስካይትራክስ ባወጣው የአመቱ የአለማችን ምርጥ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ደግሞ የኳታሩ ሃማድ፣ የጃፓኑ ሴንትራል ጃፓን፣ የጀርመኑ ሙኒክ፣ የእንግሊዙ ለንደን ሄትሮው፣ የጃፓኑ ናሪታ እና የስዊዘርላንዱ ዙሪክ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ናቸው፡፡
በዘንድሮው የአመቱ ምርጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች ዝርዝር እስከ አስራ አምስተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ አንድም የአሜሪካ፣ የአውስትራሊያና የአፍሪካ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ አለመካተቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ስካይትራክስ ከ100 በላይ በሚሆኑ የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ ከ550 በላይ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ለማወዳደር ከ39 በላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት መስፈርቶችን ከመጠቀም ባለፈ የደንበኞችን የአገልግሎት እርካታም ለመለኪያነት እንደሚጠቀምም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 3651 times