Monday, 15 April 2019 00:00

የፖለቲካ ቁማርተኞች ያልነገዱበት ኢትዮጵያዊነት!

Written by  ደ.በ
Rate this item
(4 votes)                      “--ሩዋንዳውያን አሁን የብሔር ግጭት ምን እንደሆነ ያውቁታል፡፡ ህመሙ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ አይተውታል፡፡ የሚወዱትን
መነጠቅ፣ እናትና አባት፣ ወንድም እህት ማጣት እንዴት እንደሚዘገንን ተረድተውታል፡፡ እኛስ? እኛ ያንን ሁነት የሩቅ ታሪክ፣ ወይም
የአያት የቅድመ አያት ተረት ያደረግነው ይመስላል፡፡--”
             ደ.በ            የብርጋዲየር ጀኔራል ዋስይሁን ንጋቱ “ዕጣ ፈንታ እና መስዋዕትነት” የተሰኘው መጽሐፍ መግቢያ ላይ ያነበብኩት ሀሳብ ደጋግሞ ውስጤን እንደ ሽንኩርት እየላጠው ቢቸግረኝ፣ ለዛሬ ጽሑፌ አጋዥ አድርጌው ማምጣት እንዳለብኝ አምኛለሁ፡፡
ጄኔራሉ ለ10 ዓመታት በእስር ከቆዩ በኋላ በሚፈቱበት ዕለት በቅጽል ስሙ ወዲ ፊውዳል፣ በተፀዎዖ ስሙ ኃይሉ ነጋሽ፣ ከሚባለው የመቀሌው ማረሚያ ቤት አዛዡ ጋር የተነጋገሩት አንዳች ፍሬ ነገር ለዛሬ ይጠቅመናል  የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዲህ ይላል መጽሐፉ፡-
 “መልኩ ጀኔራል መንግስቱ ንዋይን ከሚመስለው ወደ ፊውዳል ኃይሉ ነጋሽ ጋር ፌት ለፊት ተያየን፡፡ ሥራውን ሁሉ አጠናቅቆ እኔን ብቻ የሚጠብቅ ይመስላል፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ “ስለፈታችሁኝ አመሰግናለሁ!” አልኩት - ከልቤ ነበር፡፡
“ጄነራል ዋስይሁን፣ እኔም በመፈታትዎ ደስ ብሎኛል” አለኝ …
“የአንድ ሀገር ዜጎች ሆነን፣ በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ብቻ በሁለት ጎራ ተከፋፍለን፣ ለ17 ዓመት እርስ በርስ ብንዋጋም ያለ አንዳች ወንጀል 10 ዓመት በመታሰርዎ በጣም አዝኛለሁ” ብሎ አንገቱን ሲያቀረቅር ስሜቴን መቆጣጠር አቃተኝና አቀርቅሬ ማልቀስ ጀመርኩ፡፡ ዓይኔን በመሀረም ጠራርጌ ቀና ስል ግን ያለቀስኩት ብቻዬን አልነበረም፡፡ ወዲ ፊውዳል አብሮኝ እያለቀሰ ነው፡፡ ይሄኔ ነው ያለምንም ገደብ የእምባዬ ዥረት መፍሰስ የጀመረው፡፡ ለዓመታት ጎራ ለይተን ባለመታደል እርስ በርስ ስንጠፋፋ የነበርን ሰዎች፣ የአንድ አገር ልጆች እንደሆንን፣ በዚያች ቅጽበት የተገነዘብን እንመስል ነበር፡፡”
ይህ የጄነራሉ እውነተኛ ገጠመኝ ነው፡፡ እዚህ ቦታ አሳሪውና ታሳሪው የአንድ ሀገር ልጆች ናቸው፡፡ ጉዳዩ ከብሔር ጋር የተገናኘም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከጄኔራሉ ጋር አብረው ከታሰሩት ውስጥ ኮሎኔል ቃለ ክርስቶስ አባይና ሌሎች የትግራይ ተወላጆች አሉ፡፡ ጄኔራል ዋስይሁን ደግሞ የወለጋ ልጅ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ እንደ ሀገር መኖርና ሉዐላዊነቷ መከበር በርካታ ኢትዮጵያውያን ዋጋ መክፈላቸውን ጄኔራሉ ያወጋሉ፡፡ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሞ፣ አማራ ብሎ ነገር የለም፤ ሁሉም ለአንዲት ሀገር ሞተዋል፣ ቆስለዋል፡፡ ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ በክብር እንድትኖር፣ ያለ ልዩነት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ምስራቁን፣ ምዕራቡን፣ ሰሜኑንና ደቡቡን ያኖሩት በገንዘብ ሳይሆን በደማቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት የምንለውም ስለዚህ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ለረዥም ዓመታት የቆየ አንድነት፣ የተጠናከረና ተቀራራቢ ስነ ልቡና፣ እምነትና ባህል የፈጠርነው እንዲሁ አይደለም፡፡ በጋራ ባሳለፍናቸው የችግርና የደስታ ቀናት በሰጡን የጋራ መልክ ነው፡፡ አብረን  ክፉና ደግ በማሳለፋችን፣ በረሀብ ቀን ተካፍለን በመብላታችን፣ አንደኛው ሲጠቃ፣ ሌላኛችን አብረን በመቆማችን ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ብሔራዊ በዐሎቻችንን ስናከብር፣ አብረን ለጋራ ነፃነት መሰዋታችን፣ ለሀገራዊ ድል አብረን መቆማችንም ነው፡፡
በእምነትም አንዳችን የሌላችንን እያከበርን፣ ብሄር ሳንለይ፣ አንድ ደብር እያስቀደስን፣ አንድ መስጊድ እየሰገድን፣ አንድ የአምልኮ ስፍራ ቃለ እግዚአብሄር እየተካፈልን ስለኖርን ነው፡፡ በዓመታዊ ክብረ በዓሎቻችን አብረን የቡሄ ዳቦ እየቀመስን አድገን፣ የመስቀል ደመራ ደምረን፣ አብረን ሆያ ሆዬ ብለን፣ በመኖራችን፣ዘፈኖቻችንና ግጥሞቻችን እንኳ የተለየ ስነ ልቡናዊ ጌጥ እንዲኖረን አድርገውናል፡፡ ይህ የምንኮራበት ክብራችን ነው፡፡
ይህ የኩራት ጌጥ ዛሬም በህዝባችን ልብ ውስጥ አለ፡፡ መኖሩን እንድናውቅ የሚያደርጉን አያሌ ምልክቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የተከሰከሰበት ስፍራ ላይ የተከሰተው ሁኔታ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ የአካባቢው አርሶ አደር በደረሰው አደጋ ደንግጦና አዝኖ በመውጣት አንብቷል፡፡ አርሶ አደሩ ምናልባት የሚያውቀው ነገር ቢኖር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ድንገት ተከስክሶ ሰዎች መሞታቸውን ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪ  ለክፉና ለደግ ቀን የሚረዳዳ፣ አብሮ የሚበላ፣ አብሮ የሚጠጣ፣ አንድ ደብር የሚያመልክ፣ አንድ ላይ የሚኖር ብቻ ሳይሆን በአንድ የቀብር ቦታ የሚቀበር ነው፡፡ ህይወቱ ብቻ ሳይሆን መቃብሩም አንድ ላይ ነው፡፡
ታዲያ ይህ አርሶ አደር የአውሮፕላኑ አደጋ በደረሰ ጊዜ፣ እንባውን ያፈሰሰው ለአማራው ወይም ለኦሮሞው አሊያም ለአንድ ብሔረሰብ ብሎ አልነበረም፡፡ ከኢትዮጵያውያን ውጭ የብዙ አገራት ዜጎች በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው ነበር፡፡ አርሶ አደሩ ያዘነውና ያለቀሰው፣ ለሁሉም የአደጋው ሰለባዎች ነው፡፡ ህይወታቸው ላለፈ ለሰው ልጆች በሙሉ፡፡ የሟቾቹን 12ኛ ቀንም፣ ዳቦ ጋግረው፣ አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ሥፍራ ላይ በመሰባሰብ ዘክረዋል፤እነዚህ ደግና የዋህ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች፡፡ የፖለቲካ ቁማርተኞች ያልነገዱበት ንጹህ ኢትዮጵያዊነት ማለት ይሔ  ነው፡፡
በርግጥ የዘመን ልዩነት አለ፡፡ የአስተሳሰብ ወሰንም ይለያያል፡፡ ዛሬ አንዱ ለሌላው ደመኛ እንደሆነ ሲተረክለት ነው የሚያድገው፡፡ አንዱ ያንዱ ጠላት እንደሆነ እየተማረ ነው ነፍስ የሚያውቀው፡፡ በአንድ ሀገር ላይ በፍቅርና በይቅርታ ከመኖር ይልቅ ለመጠፋፋት ብዙ ተለፍቷል፡፡ በፈጣሪ ሃይል እስካሁን ከታቀደውና ከተደገሰልን ከፍተኛ የእርስበርስ ጥፋት  ድነናል፡፡ ነገር ግን ዛሬም አደጋው በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ አንዣቧል፡፡
ብዙዎቻችን እንደምናውቀው በቅርቡ የዚህ ጥላቻና ቁማር ግለት ሰማይ ነክቷል፡፡ ግን እውን ይህ የህዝቡ ሀሳብና ፍላጎት ነው? .. በፍፁም! ሰሞኑን አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ነገር ለዚህ  ብሩህ ማሳያ ነው፡፡ ወዳጄ ኮዬ ፈጬ የሚባለው ቦታ ኮንዶሚኒየም ደርሶታል፡፡ ይሁንና በአንዳንድ የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞች፣ የተነሳውን ንትርክ ሁላችንም እናስታውሳለን፡፡ በዚያ ላይ ህዝቡ እሳት ልሶ እሳት ጎርሶ፣ ሜንጫ ይዞ እየጠበቀ ነው ተብሎ ተወርቶ ነበር፡፡ ወዳጄም ዘግየት ብሎ ወደ ኮንዶሚኒየሙ ሲሄድ በዚያ ፍራቻ ውስጥ ሆኖ  ነበር፡፡ እውነት ለመናገር ወዳጄ፣ ከማንም በላይ የኦሮሞ ህዝብ ተቆርቋሪና ታጋይ ነው፡፡  እዚያ ሄዶ ያጋጠመውን ሲነግረኝ ፈፅሞ የተለየና አንጀት የሚበላ ነው፡፡ እርሱ እንደነገረኝ የአካባቢው  ወጣቶች፣ በታላቅ ፍቅር፣ በማይታመን ሁኔታ ነበር አቀባበል ያደረጉላቸው፡፡ እንዲያውም “እናንተ ብትመጡ ደስታችን ነው፤ ቢዝነስ እንሰራለን!” ብለውታል፤ወዳጄ እንዳጫወተኝ፡፡ ይህንን መዋደድና  መፋቀር የማይሹ የብሄር ጽንፈኞች ግን አሉ፡፡ ብሔርን ከብሔር በማጋጨት የራሳቸውን እንጀራ የሚጋግሩ፤ የራሳቸውን ሆድ የሚሞሉ!
እውነት ለመናገር ለህዝቡ በእውነት የሚቆረቆር ማነው? … የኦሮሞ ወጣት ደረቱን ለጥይት ሰጥቶ፣ ለለውጡ የከፈለውን ዋጋ ትሩፋት አግኝቷል ወይ? … ይልቅስ ትናንት ከዚያኛው ኢሕአዴግ ጋር ተለጥፈው ሆዳቸውን ይሞሉ የነበሩ ሰዎች አይደሉ፣ መሰንቆ ይዘው እንደ ታጋይ የሚዘፍኑት? ለግል ጥቅማቸውና ምናልባትም በስልጣን ጥም ለሰከሩ ሰዎች ትልቁ መንገድና ዕድል የዘውግ ፖለቲካው ነው፡፡ ህዝብን ከህዝብ ጋር በማናጨት፣ የተሻለ ኑሮና ወንበር መጎምዠት፣ ዋነኛው የፅንፈኞች መሹለኪያ በር ነው፡፡ ይሁንና አደገኛነቱ የትየለሌ እንደሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ በጉልህ የታየ እውነታ ነው፡፡ ሰው በደሙ ማሰብ ከጀመረ፣ ሰው ዘር ቆጠራ ከገባ ሀገር ትበላሻለች፣ ትውልድም ይጠፋል! አባቶች ከእነ ድክመቱ የገነቡት መሰረት  ሲናድ፣ ሀውልቶቻችን ፈርሰው ጠጠር ለቀማ እንገባለን፡፡
ምኒልክ አስፋው የተባሉ ፀሐፊ በ1999 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፋቸው ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላሉ ፡-
“-- ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ጀርመኖች ያሰሙት የነበረው መፈክር ለዚህ ጥሩ አብነት ይሆነናል፡፡ ጀርመኖቹ ደማችን ንፁህ መሆን አለበት፤ በጀርመኖች ደም ስር ውስጥ መመላለስ ያለበት የጀርመኖች ደም ብቻ ነው፤ በመሆኑን ደማቸው ከቆሸሸበት ነገር ሁሉ መጽዳት አለበት” ይሉ ነበር፡፡ የጀርመኖቹ አካሄድ አንድ ህዝብ፣ አንድ ባህል፣ አንድ ቋንቋ፣ ብሎም አንድ ዓላማና አንድ አገር ለመመስረት ነበር፡፡ ከእነርሱም በኋላ የተነሱ ህዝቦችም የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት፣ ጀርመኖቹ ያራምዱት የነበረውን ርዕዮተ ዓለም  ሲያራምዱት ታይቷል፡፡ ለምሳሌ ሰርቦች፤ ምድራችን ንፁህ መሆን አለበት ይሉ ነበር፡፡ የሰርቦች ምድር የሚገባው ለሰርቦች ብቻ ነው፤ በመሆኑም ምድራችን ከእኛ ወገን ወይም ዘር ካልሆኑትና ከሰርጎ ገቦች መጽዳት አለባት በማለት ብዙ እልቂት አድርሰዋል፡፡--”
የመጽሐፉ ደራሲ ምኒልክ ያስነበበን፣ ራቅ ያሉትን አገራት ቅዠትና የገጠማቸውን ጥፋት ነው፡፡ እኛ ደግሞ ከዚህ የቀረበና ሰሞኑን ሃያ አምስተኛ ዓመቱን ያከበረው የሩዋንዳው አሰቃቂ እልቂት አጠገባችን አለ፡፡ ጥፋቱ የጀመረውም በተአምር አይደለም፤ አሁን እኛ እምናራግበው ዓይነት እሳት ተነስቶ ነው የእሩብ ሚሊየን ህዝብ ህይወት የቀጠፈው፡፡ ያለ ኪሳራ መዳን፣ ያለ ጥፋት መመለስ ይቻል ነበር፡፡
ሩዋንዳውያን አሁን የብሔር ግጭት ምን እንደሆነ ያውቁታል፡፡ ህመሙ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ አይተውታል፡፡ የሚወዱትን መነጠቅ፣ እናትና አባት፣ ወንድም እህት ማጣት እንዴት እንደሚዘገንን ተረድተውታል፡፡ እኛስ? እኛ ያንን ሁነት የሩቅ ታሪክ፣ ወይም የአያት የቅድመ አያት ተረት ያደረግነው ይመስላል፡፡ ስለዚህም “እንታረቅ፣ እንነጋገር፣ እንወያይ!” የሚል የለም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች ግርግሩን ለስልጣን መወጣጫ ለመጠቀም ሌት ተቀን ለጥፋት ይባዝናሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የመቶ ዓመታት ትርክት እያነሱ፣ አዲሱን ትውልድ፣ የጥላቻ  ክኒን ያቅሙታል፡፡
በተለይ ማህበራዊ ሚዲያውን መሳሪያ በማድረግ፣ የፖለቲካ ቁማር ይጫወታሉ፡፡ እኛ ተጠቃሚዎቹም ክትትላችን ግልብና ስሜታችን በብሔር የተቃኘ ስለሆነ፣ ከመመርመር ይልቅ ስድብን በስድብ ለመመለስ እንተጋለን፡፡ ሌላው ቀርቶ በእውኑ አለም ከምናውቀው እጅግ በተለየ ሁኔታ ነውረኛ የብሔር አዋራጅ ስድብ ሲሳደቡ፣ “ማን ሊሆን ይችላል?” ብለን አንፈትሽም፡፡ ስለዚህ እንደ ልባቸው ሜዳውን ተቆጣጥረው፣ እየሳቁ በሁላችንም ላይ ጎል ያገባሉ፡፡ እኔ በግሌ ባለፉት ወራት፣ ዘግናኝ የብሔር ስድብ የሚሳደቡትን ሰዎች ለመከታተል ሞክሬ ያገኘሁት ውጤት፣ አማራ መስለው፣ ኦሮሞን የጥላቻ ስድብ የሚሳደቡ፣ አማራ አይደሉም፡፡ ኦሮሞ መስለው፣ አማራን የሚሳደቡ፣ ኦሮሞ አይደሉም፡፡ ለምሳ “ጫልቱ” በሚል ስም የሚጠቀም ሰው፣ የአማራን ብሔር በእጅጉ ይዘልፋል፣ የሚያበሳጩ ቃላትን ተጠቅሞ ጠብ ያጭራል፡፡ ተጠራጥሬ ፈተሽኩት፡፡ የተለያዩ ሰዎች በቁቤ የፃፉትን መልዕክት ፖስት ያደርጋል እንጂ ራሱ በቁቤ አይፅፍም፡፡ በዚያ ላይ በአማርኛ የሚፅፈው ጽሑፍ የእንስት ስነ ልቦናዊ ማንነትን ይቃረናል፡፡ ስለዚህ መልስ ሰጠሁት፡፡ “አንተ ሴትም፣ ኦሮሞም አይደለህም፣ ከሆንክ አሁን አንድ ዐረፍተ ነገር በዚህ ቅፅበት ፃፍልኝ” አልኩት፡፡
“የማልችል መስሎህ ነው!” አለኝ፡፡
“ፃፍና አሳየኝ!”
ብሎክ አድርጎኝ ጠፋ፡፡ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ የፖለቲካ ቁማርተኞችን በመከታተል ማጋለጥ ጀምሬያለሁ፡፡ ሰሞኑን እንደዚሁ የአማራ ስም ለጥፎ፣ ኦሮሞን ሲሳደብ ያየሁትን ሰው፣ ውስጡን ገብቼ መረመርኩት፡፡ በእርሱ ግድግዳ ላይ፣ የአፄ ቴዎድሮስ ፎቶ ተዘቅዝቆ ተሰቅሏል፡፡ ወረድ ብሎ ደግሞ እስልምናን ፀያፍ ስድብ ይሳደባል፡፡  የአማራን ፓርቲ እንደዚሁ!
ይህ አሳዛኝ ቁማር ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ብዙ ሰዎችን አግኝቼ፣ አምስት ሺ ለሚሆኑ የፌስ ቡክ ሽርኮቼ እያጋለጥኩ ነው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መጣዳችን ካልቀረ፣ እነዚህ የሀገር ጠላቶችን እናጋልጥ! ባለፈው ሰሞን አቶ ለማ መገርሳ፤ “ብሔራችን ተጠቅሶ መሰደብ ከህዝቡ የመጣ ጥላቻ አይደለም፡፡ ለዚህ ስራ የተቀጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ ደህንነት የሚባለው የከተማ አውደልዳይ ይህንን ስራ እንኳ ቢሰራ ምናለ?” ብለዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን፡፡ ራሳችንንም ሆነ አገራችንን ከአክራሪ ብሄርተኞች የጥፋት መንገድ መጠበቅ ይገባናል፡፡ መንግስትም ቀዳሚ ሃላፊነቱ፣ ህዝብን ከአደጋና ከስጋት  መጠበቅ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡
 ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!     

Read 1939 times