Saturday, 20 April 2019 13:33

በቀጣይ 3 ወራት ለተፈናቃዮች ከ300 ሚ. ዶላር በላይ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 2.4ሚ ዜጐች ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል ችግሩ አገሪቷን ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ሊከታት ይችላል ተብሏል

             በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ተፈናቃዮችን ለቀጣዮቹ ሶስት ወራት ለመመገብ ከ300ሚ. ዶላር በላይ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ ለሚያዚያ፣ ግንቦትና ሰኔ ወር ለተፈናቃዮች እርዳታ ለማቅረብ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የ332.9 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ የማይገኝ ከሆነ በሀገሪቱ የሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል  ጽ/ቤቱ አስጠንቅቋል፡፡ “ችግሩ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፤ አፋጣኝ ድጋፍ ያስፈልጋል” ያለው ጽ/ቤቱ፤ አሁንም 2.4 ሚሊዮን ዜጎች በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂዎች ናቸው ብሏል፡፡
በአጠቃላይ በሃገሪቱ 8.3 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ፈላጊዎች መሆናቸውን ያወሳው የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ለአንድ ዓመት ከሚያስፈልገው 1.314 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ እስካሁን 29 በመቶ ብቻ መገኘቱን በመጠቆም የእርዳታ ግኝቱ አበረታች እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡ ይህም በሃገሪቱ እርዳታ ጠባቂ ዜጎች ላይ ስጋትን የሚደቅን ነው ብሏል - ጽ/ቤቱ፡፡ ለቀጣዮቹ 3 ወራት ለተፈናቃዮች ለማቅረብ የሚያስፈልገው የ332.9 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ሙሉ ለሙሉ ተፈናቃዮችን ለመመገብ የሚውል መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የተፈናቃዮችና የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር አሁንም አለመቀነሱ ከሃገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ እንዳይከሰት ያሰጋል ብሏል -የተመድ ሪፖርት፡፡

Read 6143 times