Saturday, 20 April 2019 13:45

የፋሲካ ዕለት የተወለደች ሁልጊዜ ፋሲካ ይመስላታል

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በገጠር የሚኖር የናጠጠ ሀብታም ልጅ፤ የንጉሡን ልጅ ለማግባት ፈልጎ፤ ወደ ንጉሡ ከተማ ሽማግሌዎች ይልካል፡፡ የፋሲካ ማግሥት ነው ዕለቱ፡፡ ሽማግሌዎቹ ተፈቅዶላቸው ግቢ ይገባሉ፡፡
ንጉሡን ጨምሮ ልዑላኑና መኳንንቱ ተቀምጠዋል፡፡
ሽማግሌዎቹ ገብተው ከፊት ለፊት ቆሙ፡፡
‹‹ተቀመጡ እንጂ›› አሉ ንጉሡ፡፡
‹‹የለም፡፡ ጥያቄ አለንና፣ ጥያቄያችን ሳይመለስልን አንቀመጥም›› አሉ
‹‹መልካም፤ ጥያቄያችሁን እንስማ!›› አሉ ንጉሡ፡፡
ከሽማግሌዎቹ ጠና ያሉት ተነሱና፤
‹‹የመጣነው ልጃችሁን ለልጃችን ለጋብቻ ለመጠየቅ ነው፡፡ ፈቃዳችሁ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡››
‹‹ከየት ነው የመጣችሁት ከማንስ ቤተሰብ ነው የመጣችሁት?››
ሽማግሌው፤
‹‹ቤተሰባችን ጨዋ፣ የደራ የኮራ፣ ልጃችን የታረመ የተቀጣ፣ ምሁር ነው፡፡ የቤተክህነት ትምህርት  ጠንቅቆ ያቃል፡፡  የደጃች እከሌ ቤተሰብ ነን፡፡ ከሩቅ ገጠር ከለማው ቀዬ ነው የመጣነው፡፡ በማናቸውም መንገድ ከእናንተ ቤተሰብ ምንም ዓይነት ዝምድና እንደሌለ አጥርተን አውቀናል››
ንጉሡ፤
መልካም፡፡ ከሩቅ አገር መምጣታችሁን ገምተናል፡፡ ስለዚህ ብዙ አናመላልሳችሁም፡፡ እዚህ አካባቢ ቆየት ብላችሁ ተመለሱ፡፡ ልጃችንን እናናግራት፡፡ ዘመድ አዝማዱንም እናማክርና ጥያቄም ካለ ይቀርብላችኋል፡፡ እንደሚታወቀው ልጃችን ጠቢብ ናትና የምትጠይቀው አታጣም›› አሉ፡፡
ሽማግሌዎቹ እጅ ነስተው ወጡ፡፡ ከሰዓት በኋላ ተቀጥረዋል፡፡ ሽማግሌዎቹ በየዘመድ አዝማድ ዘንድ እህል ውሃ ሲሉ ቆይተው፣ በተቀጠረው ሰዓት ተመልሰው መጡ፡፡ አሁን ጠርቀም ያለው የቤተሰብ ዘርፍ እልፍኝ ተሰባስቧል፡፡
ንጉሱ፤
‹‹አገር ሽማግሌዎች አጣደፋችሁንኮ፡፡ ዋናው ጉዳይ የእኛ ፈቃደኝነት ብቻ ሳይሆን የልጃችንም መቀበል ነው፡፡ ልጃችን ጥያቄ አቅርባለች፡፡ ጥያቄዋም፡- ‹እኔ ላገባው የምችለው ወንድ፣ ለእኔ ያለው ፍቅር፤
1ኛ/ እንደ እናቴ መቀነት
2ኛ/ እንደ አባቴ ጥይት
3ኛ/ እንደነብስ አባቴ ማተብ
ከሆነ ነው፡፡  የዚህን ፍቅር ፍቺ በወጉ ከተረዳ እሺ ብላለች በሉት” ብላናለች፡፡
እንግዲህ የዚህን ፍቺ በሁለት ቀን ውስጥ ከላከና የገባው ከሆነ ታገባዋለች” አሉ ንጉሡ፡፡
ሽማግሌዎቹ፤ “በሁለት ቀን መልስ ይዘን እዚሁ እንገኛለን” ብለው ሄዱ፡፡
በሁለተኛው ቀን ቤተ - መንግስት ቀረቡ፡፡
ንጉሡ፤
 “እህስ ሁነኛ መልስ ይዛችሁልን መጣችሁ?”
ሽማግሌ፤
“አዎን፤ ንጉሥ ሆይ!”
ንጉሥ፤
“በሏ እንስማችሁ?”
ሽማግሌው ተነስተው፤
“ልጃችን ለአንደኛው ጥያቄ ያለው መልስ፡- የእናቴ መቀነት ማለቷ - የእናት መቀነት ተፈትሎ፣ ተከሮ፣ ተሸምኖ ነውና መቀነት የሚሆን ሥራ ወዳድ መሆኑን ፈልጋለች፡፡
አንድም ደግሞ እናት ሁሉን ዋጋ ያለው ነገር የምታኖረው መቀነቷ ውስጥ በመሆኑ ገንዘብና ንብረት ያዥና ቆጣቢ መሆን ያለብኝ መሆኔን ማመላከቷ ነው፤ ብሏል፡፡
ሁለተኛው ጥያቄዋ አዳኝ መሆኔን፣ ተኳሽ መሆኔን፣ ጀግና መሆኔን እንደምትወድ ስትገልፅልኝ ነው፡፡
ሶስተኛው ጥያቄዋ፤ ለትዳራችን ሁለታችንና ሁለታችን ብቻ ወሳኝ መሆናችንንና አንዳችን የአንዳችንን ምስጢር እንደነብስ አባት መጠበቅ እንዳለብን መንገሯ ነው፡፡
እኔ ደግሞ ሶስቱንም አክባሪ ነኝ” ብሏል አሉ፡፡
ንጉሡ ደስ አላቸው፡፡
“በቃ ልጃችንን ለልጃችሁ ፈቅደናል፡፡ ወደ ገበታው እንቅረብና የምስራቹን፣ ቤት ያፈራውን እንቅመስ!” አሉ፡፡
 ፋሲካው ደመቀ፡፡
***
በየትም ጊዜ፣ በየትም አገር ከውጣ - ውረድ ነፃ የሆነ ነገር የለም፡፡ ያለ ሥራ፣ ያለ ቁጠባ፣ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ያለ አላሚ - ተኳሽና ጀግና፣ ቤቱን አስከባሪ፣ ድንበሩን አክብሮ - አስከባሪ፤ በመጨረሻም የአገሩን ምሥጢር አክባሪ መሆን፤ ትዳርን በሀገር ለመተርጎም ለቻለ ሁሉ ወሳኝ ነው! እንደ ምን ቢሉ - የሀገር ምሳሌ ቤተሰብ ነውና!
ቤተሰብ በፍቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ይጀመርና እንደ ባህሉ በህግ ይታሰራል፡፡ እንደ ባህሉ ተከባብሮ፣ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብሎ፣ ግጭት ቢፈጠር ተወያይቶ፣ ችግርን ፈቶ፣ በእኩልነት የመተዳደርን ባህል አዳብሮ በፍቅር ይዘልቃል፡፡ ልጆች ቢወለዱም በዳበረው ልማድና ባህል ውስጥ መተዳደሪያቸው ተቀምሮላቸው፣ በግብረ-ገብነት ታንፀው እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡ ለአቅመ-አዳም ወይም ለአቅመ - ሄዋን ሲደርሱ ከቤተሰብ ወጥተው  ቤተሰብ ይመሰርታሉ፡፡ የራሳቸውን ደምብና ሥርዓት አበጅተው ህይወትን ይቀጥላሉ:: የመተዳደሪያ ደምብ፣ የኢኮኖሚ ይዞታ፣ የልጅ አስተዳደግና ሥነ ምግባር ደምብ፣ የኢኮኖሚ ይዞታ፣ የልጅ አስተዳደግና ሥነ ምግባር፣ ከጎረቤት ጋር ያለ ባህላዊ ግንኙነት፣ የጤናና የትምህርት ሁኔታ፤ ወዘተ-- በቤተሰብ ውስጥ የምናያቸው ሥርዓተ-አኗኗሮች ሁሉ የአንድ አገር መንግሥት መዋቅር መሰረት ናቸው፡፡ በተለይ የኢኮኖሚ ሁኔታው እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን በቅርብ ተከታትሎ መሰረቱ እንዳይናድ፣ እንዳይመዘበር፣ ሥርዓት እንዳያጣ ተጠንቅቆ መምራት የአስተዳደሩ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ አስተዳደሩ የፖለቲካው ዋና መዘውር ነው፡፡ ፖለቲካ የኢኮኖሚው አቅም ጥርቅም ገፅታ ነው (politics is the concentrated form of the economy) እንዲሉ ፈረንጆቹ:: ቀለል አድርገን ብናየው “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንደምንለው ይሆናል፡፡ ኢኮኖሚው ሲበላሽ ፖለቲካው መናጋቱ፣ ህዝብ ጥያቄ ማንሳቱ፣ አመራሩ ሁነኛ መልስ ካልሰጠ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ፣ የመሰረታዊ ለውጥ አስፈላጊነት (Radical change) እየጎላ መምጣቱ አይቀሬ እየሆነ ይሄዳል፡፡ በታሪክ እንደታየው ማንኛውም አመራር አካል በቸገረው ሰዓት፤ ሰዎችን ከመዋቅር መዋቅር ለመለወጥ ይሞክራል፡፡ ያ ካልተሳካ የመዋቅሩን ደም-ሥር እንዲመረምር ይገደዳል፡፡ ፍትሐዊ ሂደት መኖር አለመኖሩን ያጣራል፡፡ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ መኖር አለመኖሩን ይፈትሻል፡፡ መልካም አስተዳደር ሰንሰለታዊ ባህሪ አለው- hain Reaction እንዲል መጽሐፍ፡፡ ለምሳሌ የመልካም አስተዳደርን ጉዳይ ብቻ ነጥለን እንመታለን ብሎ ማሰብ፣ ከደን ውስጥ አንድ ዛፍ መፈለግ ዓይነት ነው፡፡ ፍትሕ፣ ዲሞክራሲ፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ ተቋማዊ ብቃት፣ ባህላዊና ልማዳዊ አካሄድ፣ የአገር ሉአላዊነት፣ የአዕምሮ ውጤቶች አያያዝ፣ ማህበራዊና ሥነ ምግባራዊ ዕድገት ወዘተ ሁሉ በስፋትና በጥልቀት ሲኬድባቸውና ሲታዩ የመልካም አስተዳደር መጋቢ መንገዶች ናቸው፡፡ ድርና ማግ ናቸው፡፡ አንዱ ያለ አንዱ ፍሬ አያፈሩም፡፡ ወንዝ አያሻግሩም፡፡ እነዚህን ሁሉ በወግና በሥነ ሥርዓት ቀንብቦ ለመያዝ በህግ የበላይነት አምኖና ተማምኖ መመራት ያስፈልጋል፡፡ “በህግ አምላክ” የማይባልበት አገር ዜጋ ተከባብሮና ሥርዓት ይዞ ለመኖር ያዳግተዋል፡፡ ሰላሙን በቀላሉ አያገኝም፡፡ የህግ የበላይነት የእኩልነት መቀነቻ ነው፡፡ የተገነባው እንዳይጠቃ፣ ዘራፍ - ባይ ቆራጭ ፈላጭ እንዳይፈጠር፣ ቀና ብለን የምናየው የህግ የበላይነት መኖር አለበት፡፡
መኖሩን የሚያሳይ ተግባርም መታየት አለበት፡፡ የህግ የበላይነት በሥራ ተተርጉሞ ካልታየ ባዶ ነው፡፡
ከላይ ያነሳናቸው ፍሬ - ጉዳዮች እየተሟሉ ሲሄዱ የአገር ተስፋ ይለመልማል፡፡ ሆኖም ልምላሜው የሚገኘው በወርቅ አልጋ በእርግብ ላባ ላይ ተተኝቶ አይደለም፡፡ መንገዱ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ ውጣ ውረድ፣ አቀበት ቁልቁለት የበዛበት እሾሃማ መንገድ ነው፡፡ አንዴ ልምራው ተብሎ ከተገባ እሾኩን እየነቀሉ፣ አበባውን እየጠበቁ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ የነብርን ዥራት ከያዙ አይለቁም ነው ነገሩ፡፡
በመሰረቱ ለዘመናት በችግር የተተበተበችን አገር ውስብስብ ህልውና፤ በአንድ ጀንበር ማቅናት አይቻልም፡፡  ስኬታማነት ሊኖር ይችላል፡፡ ግን መሰናክሎችም አብረውት አሉ፡፡
“ችግር አለ፡፡ ችግሩንም ለመናገር ችግር አለ” በሚባልበት አገር፣ ስኬት ብቻ ነው የሚታየኝ ማለት ወይ ሆነ ብሎ ዐይንን መጨፈን ነው፡፡ አሊያም “የፋሲካ ዕለት የተወለደች ሁል ጊዜ ፋሲካ ይመስላታል” የሚለውን ተረት ውስጠ - ነገር አለመገንዘብ ነው፡፡ ከችግሩ ሁሉ ወጥተን ትንሳኤ እናገኝ ዘንድ እንመኛለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ውድ አንባቢያን፤ እነሆ አዲስ አድማስ ተመሥርታ ለአንባቢያን መድረስ ከጀመረች ድፍን 20 ዓመት ሊሞላት ጥቂት ወራት ነው የቀራት፡፡ በመጪው ዓመት ታህሳስ 29 ቀን 2012 ዓ.ም የምስረታ  በዓሏን በተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ታከብራለች፡፡ ይሄን ምክንያት በማድረግም፣ ባለፉት ዓመታት ከታተሙ የጋዜጣው ጽሁፎች እየመረጥን፣ ለትውስታ ያህል እናቀርባለን፡፡ ከላይ የተነበበው  ርዕሰ አንቀጽም በዚህ መንፈስ ካለፈው ዕትም የተመረጠ ነው፤ አፕሪል 21, 2012  በአዲስ አድማስ ድረ ገጽ ላይ ፖስት ተደርጓል፡፡

Read 11915 times