Print this page
Saturday, 20 April 2019 13:47

የህወሓት መግለጫ በአረና መነፅር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

· መግለጫው፤ በትግራይ ማንም ህውሓትን መቃወም አይችልም የሚል ነው
                      · በመቀሌ ለፅዳት ዘመቻ የወጡ ወጣቶች እስርና ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል
                      · ኢህአዴግ የፈረመውን ቃል ኪዳን ስላላከበረ በም/ቤት እንከሰዋለን
                      · በትግራይ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የለም

          ህውሓት ከሰሞኑ ያወጣው መግለጫ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በዚህ መግለጫው ካነሳቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የኢህአዴግ ውህደት የማይታሰብ መሆኑ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲና ህገመንግስቱ አሁንም ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሔ እንደሆኑ፣ በትግራይ “ባንዳዎች” እና “ተላላኪዎች” የህዝብ አንድነት ለመሸርሸር እየሠሩ መሆናቸው እንዲሁም የኢህአዴግ የተሃድሶ እንቅስቃሴ አለመሳካቱ --- ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ህውሓት በተጨማሪም ቀጣዩ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለበት ሲል አቋሙን አስታውቋል፤ በመግለጫው፡፡ በትግራይ ብቸኛ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው የአረና ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ ደስታ እንደሚሉት፤ ህውሓት ከእንግዲህ የሚቃወመውንና የሚተቸውን በዝምታ እንደማያልፍ ባለፈው እሁድ ለፅዳት ዘመቻ የወጡ ወጣቶች ላይ የወሰደው እርምጃ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ህወሓት ተቃዋሚዎቹን ባንዳና ተላላኪዎች በሚል መፈረጁንም አቶ አብርሃ ደስታ ይኮንናሉ፡፡ ኢህዴግን ለመክሰስ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉአላዊነት ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ ደስታን  አነጋግሯቸዋል፡፡

               ጠ/ሚኒስትሩ ያቀረቡትን የጽዳት ዘመቻ ተቀብለው፣ ለጽዳት የወጡ ወጣቶች መታሰራቸውን ተናግራችኋል፡፡ በምን ምክንያት ነው የታሰሩት?
በመቐሌ ከተማ ኪዊሃ በሚባል ክፍለ ከተማ እሁድ ጠዋት፣ የጽዳት ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ ነዋሪዎች ወጥተው ነበር፡፡ በርካታ ወጣቶች ነበር  የወጡት፡፡ ጽዳቱን ከጨረሱ በኋላ ሲሰባሰቡ ነው ወዲያው ፖለሶች መጥተው ወጣቶቹን መደብደብ የጀመሩት፡፡ የተወሰኑት  በሩጫ አመለጡ፡፡ ከ10 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ተያዙ:: በመኪና ጭነዋቸው እየደበደቡ ወዳልታወቀ ቦታ ወሰዷቸው፡፡ የአይን እማኞች እንደነገሩን፤ ልጆቹ እየተደበደቡ የተወሰዱት “ለምን በጽዳት ተሳተፋችሁ? ወደ ጽዳት ዘመቻው ለምን ገባችሁ?” ተብለው ነው፡፡ የተወሰኑት ሆስፒታል ገብተው ነበር፡፡ በኋላ ሲጣራ ደግሞ ከሆስፒታል ተወስደው መታሠራቸው ታውቋል፡፡
በወጣቶቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ አንደምታው ምንድን ነው?
ህወሓት በሰሞኑ መግለጫው “ከእንግዲህ የሚቃወሙኝ ባንዳዎች ናቸው፣ በገንዘብ የተገዙ ናቸው አልታገሳቸውም፣ ተቃውሞ አንቀበልም” የሚል የፖለቲካ ምህዳሩን የሚዘጋ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ይሄን መግለጫ ካወጣ ከ1 ቀን በኋላ ነው እስርና ድብደባው የተፈፀመው:: ስለዚህ በወጣቶቹ እንቅስቃሴ ደስተኛ አለመሆኑን እርምጃው ያሳያል፡፡ ከወር በፊት የኢህአዴግ መንግስት “የፖለቲካ ምህዳሩን አሰፋለሁ፤ በሠላማዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ እንቅፋት አልሆንም፤ በራሴ መንገድ ተወዳድሬ ማሸነፍ እችላለሁ” ብሎ በመሪው (በሊቀ መንበሩ) ዶ/ር ዐቢይ በኩል የቃል ኪዳን ሰነድ መፈረሙ ይታወቃል፡፡ አሁን ግን ህወኃት አባል የሆነበት የኢህአዴግ መንግስት፣ አፈናውን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የፈረመውን ቃል ኪዳን አላከበረም ማለት ነው፤ በዚህም እንከሰዋለን:: ለፓርቲዎች ም/ቤት ክሣችንን ሠሞኑን እናቀርባለን:: ኢህአዴግ በቃሉ አልተገኘም፡፡ አሁንም በትግራይ የፖለቲካ እስረኞች አሉ፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንደታፈነ ነው፤ ይሄ የሚያሳየው ኢህአዴግ አሁንም ለፓርቲ ፖለቲካ ፍቃደኛ አለመሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ክሣችንን  ለም/ቤቱ እናቀርባለን፡፡
በእርስዎ አመለካከት የህወሓት የአቋም መግለጫ ዓላማው ምንድነው?
መግለጫው የሚናገሩትን ያጠናከረ ማስፈራሪያና ዛቻ ነው፡፡ ባንዳ፣ ተላላኪ ሲሉ ማንን እንደሚሉ በግልጽ ባይጠቅሱም የሚቃወማቸውን በሙሉ ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የመሬት ካሣ ጉዳይን አንስተው የነበሩ አርሶ አደሮችንም ይጨምራል ማለት ነው፡፡ በወቅቱ ለእነሱ “ባንዳ” የሚል መልዕክት ነበር ያስተላለፉት፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ መግለጫቸው፣ በትግራይ እነሱን የሚቃወም ሁሉ ባንዳ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡ “ተላላኪ ባንዳ” የሚል አፀያፊ ቃል ተጠቅመው፣ ለማስፈራራት ነው የሞከሩት፡፡ በአጠቃላይ መግለጫው ሲታይ፤ “ማንም በትግራይ ህወሓትን መቃወም አይችልም” የሚል መልዕክት ነው የሚያስተላልፈው፡፡ ማንም አካል እኛን ሊቃወም ውይም ሊተች ከሞከረ እርምጃ እንወስዳለን ነው ያሉት፡፡ በዚያ መግለጫ መሠረት ነው አሁን ወጣቶችን እያሠሩ እየደበደቡ ያሉት፡፡ አጠቃላይ መግለጫው ሲታይ፤ “አፈናዬን አጠናክሬ እቀጥላለሁ፤ በዚህ መሃል የሚቃወመኝ ካለ እርምጃ እወስድበታለሁ” የሚል ነው፡፡ እርምጃው ምንድን ነው የሚለውን እንግዲህ፣ ከወዲሁ በወጣቶቹ ላይ እያሳዩን ነው፡፡
በትግራይ አሁን ያለው የህዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ምንድን ነው? የህዝቡስ አንድነት ምን ያህል ነው?
አሁን በትግራይ ህዝቡ ጋ ያለው ጥያቄ ተመሳሳይ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ አልተከፋፈለም፤ አሁንም አንድነቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ በዚያው ልክ የአርሶ አደሩም፣ የከተማ ነዋሪውም ጥያቄ ተመሳሳይ ነው:: ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ዋነኛ ጥያቄ ነው:: አሁን ጥያቄዎች በየቦታው በተለያየ ጊዜ እየተነሱ ነው:: ህዝቡ በህወሓት ላይ ከፍተኛ ግፊት እያደረገ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ተገቢው የመሬት ካሣ ሊሰጠን ይገባል የሚል ጥያቄ ይዞ ነው የተነሣው፡፡ እነሱ ግን ይሄን ጉዳይ ህዝቡ እንደተከፋፈለ አድርገው በመግለጽ፣ በራሣቸው የፖለቲካ ስትራቴጂ እየተጠቀሙበት ልዩነቱን ከፈጠሩ በኋላ፣ ፀብ በሌለበት አስታራቂ ሆነው በመግባት፣ የፖለቲካ ጨዋታ ለመጫወት ነው የፈለጉት፡፡ እንጂ ህዝቡ በፍፁም አልተከፋፈለም፤ ጥያቄው ተመሳሳይ ነው:: ሁሉም ህዝብ ተባብሮ ከስልጣን እንዳያባርራቸው ስለሰጉ፣ ህዝቡን በተለያየ መንገድ ለመከፋፈል ጥረት እያደረጉ ነው:: በሚቃወማቸው ላይም የመጨረሻ የሃይል እርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡
ህወሓት ውስጡ ተከፋፍሏል፤ ጥንካሬውን አጥቷል የሚሉ ወገኖች አሉ፤ እናንተ ምን ትላላችሁ?
ህወሓት አሁን ጠንካራ ነው ማለት አይቻልም::  እንደተባለውም በውስጡ በተፈጠረ ችግርና በሌሎች ምክንያቶች በህይወት አለ ለማለትም ያስቸግራል:: እርግጥ ነው የፖሊስ ሃይል አለው፤ ስለዚህ አርሶ አደሮችንም ሆነ ወጣቶችን መደብደብ ይችላል፡፡ ይሄን ማድረግ ደግሞ የፓርቲ ጥንካሬን አይፈልግም:: ለማፈን ለመግደል የፓርቲ ጥንካሬ አያስፈልግም:: ጥያቄው በዚህ ሊቀጥል ይችላል ወይ? ከሆነ፣ መቀጠል አይችልም፡፡ አሁን ጥንካሬያቸው ጠመንጃቸው ብቻ ነው፡፡
ህወሓት በዚህ መግለጫው ኢህአዴግ መዋሃድ አይችልም ብሏል፡፡ ይሄን እንዴት አያችሁት?
እንደኔ ኢህአዴግ አንድ ፓርቲ ቢሆን ጥሩ ነው:: ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ እንዲጠራጠር ያደረገው የእነሱ መከፋፈል ነው:: ስለዚህ አንድ መሆኑ ለሀገሪቱ ጥሩ ነው፡፡ ምንም እንኳ ኢህአዴግ የኛ ተፎካካሪ ቢሆንም፣ ሃገር እንዳትከፋፈል የፓርቲውን አንድ መሆን እንሻለን፡፡ ከህዝብ ደህንነት አንፃር ባይለያዩ ጥሩ ነበር፡፡ ግን ውህደት አንፈልግም ካሉ የራሳቸው ጉዳይ ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የሚዋሃደውን ፓርቲ ማንኛውም አላማውን የተቀበለ ድርጅት ሊቀላቀለው ይችላል ብለዋል፡፡  አረና ምናልባት ይሄን ውህድ ፓርቲ ይቀላቀል ይሆን?  
እኛ እንኳ በዚህ ደረጃ እስከ ዛሬ ውይይት አላደረግንም፡፡ እንደ ተቃዋሚ ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር እንጂ ከኢህአዴግ ጋር ለመዋሃድ አስበን አናውቅም፡፡ በዚህ ጉዳይም መክረንም አናውቅም፡፡ ነገር ግን በቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው አይታወቅም:: ምክንያቱም ኢህአዴግ ከኛ ጋር ያለው ችግር የርዕዮት አለም ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በፍፁም አንቀበለውም፡፡ እነሱ አብዮታዊ ዲሞክራሲን የሚቀይሩ ከሆነ ግን ስለ ብዙ ነገር ማሰብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ይዞ እኛ ልንቀላቀለው አንችልም፡፡
ህወሓት በመግለጫው “ምርጫው መራዘም የለበትም” ብሏል፡፡ ይሄን ሃሳብ ትጋራላችሁ?
ኢህአዴግ ከኛ ጋር በተፈራረመው የቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት፤ ፀጥታ በማስከበር፣ ምርጫ የሚያደርግ ከሆነ እኛ እንሳተፋለን፤ ተሳትፈንም እናሸንፋለን ብለን ነው እየተዘጋጀን ያለነው:: ነገር ግን በአሁኑ ሰአት ህዝቡ አልተረጋጋም፤ በጦርነት ተከበሃል እየተባለ ነው ያለው፡፡ ኢህአዴግም ሀገሪቱን ማስተዳደር አልቻለም፤ የተለያዩ ችግሮች አሉ:: ስለዚህ በአሁኑ ሰአት ኢህአዴግ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ያካሂዳል ብለን አንጠብቅም፡፡  ይሄን ማድረግ ከቻለ ግን እኛ ለመወዳደር አንቸገርም፡፡ የምርጫ ዝግጅት ደግሞ መጀመር ያለበት ከአሁኑ ነው፡፡ ይሄ ካልሆነ ምርጫ እንዲራዘም ተፈልጓል ማለት ነው፡፡
ምርጫውን በትግራይ ለማካሄድ  ምቹ ሁኔታ አለ ማለት ይቻላል?
አይቻልም፡፡ እነሱም በመግለጫቸው የተለየ ሃሳብና አመለካከትን አናስተናግድም ብለዋል፡፡ ተቃውሞ አንፈልግም ነው ያሉት፡፡ ታዲያ ከማን ጋር ነው ምርጫ የሚወዳደሩት? በሌላ አባባል “ምርጫ የለም” እያሉን ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለበት ሲሉ እኮ፣ በፌደራል መንግስቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እየገለፁ ከመሆን የዘለለ አይደለም:: ኢህአዴግም ፀጥታ ካላስከበረ፣ ለምርጫ የመዘጋጀት ፍላጐት የለውም ማለት ነው፡፡

Read 1819 times