Saturday, 20 April 2019 13:53

‘አሻቅቦ ወጥቶ ወደታች መውረድ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)


              “--የሰለጠኑ የሚባሉት በጣም እርቀውን የሄዱት አንድም በዚህ ነው፡፡ ግለሰብም ሆነ ተቋም ላይ እንደፈለጉ መዛት አይችሉም፡፡ ተጠያቂነት ይኖራላ! እኛ ዘንድ ነው እንጂ ለምንም ነገር ተጠያቂነት የሌለበት ዘመን ላይ የተደረሰ የሚመስለው! ያውም በየጓዳውና በየጎድጓዳው ሳይሆን በአደባባይ፣ ሲብስም በመገናኛ ብዙኃን!--”
             
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንዴት ያለው ሩቅ ምን ያለው መንገድ
አሻቅቦ ወጥቶ ወደታች መውረድ
--የሚሏት ነገር አለች፡፡ እውነትም ‘አሻቅቦ ወጥቶ ወደ ታች መውረድ!’
እሱዬው የሆነ አጉል፣ ሰው የሚያስከፋ ነገር አደረገ እንበል፡፡ እናላችሁ…
“እንዴት እንዲህ አይነት መጥፎ ነገር ያደርጋል!” ይባላል፡፡ መልሱ ምን መሰላችሁ…
“እሱ አስቦ ያደረገው አይደለም፣ ሰይጣን አሳስቶት ነው፡፡”
እኔ የምለው የ“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…” ማሳበቢያ ባይኖር ኖሮ ስንታችን ጉድ ሆነን ነበር! ስንታችን እየተፋቅን ጉዳችን ይፈላ ነበር! እናላችሁ… “ሰይጣን አሳስቶት ነው፣”  ከተባለ… አለ አይደል…“እሱ እንዴት እሺ ብሎ ይሳሳትለታል!” የሚል ‘የማፋጠጫ’ ጥያቄ ብሎ ነገር የለም፡፡ ታዲያማ…ጥፋት ከተፈጸመበት ሰው ይልቅ ለጥቃት ፈጻሚው ይታዘንለታል:: አሀ… ሰይጣን አሳስቶት ነዋ! እንጂ…እሱ አስቦ የወዳጁን እጮኛ አላማገጠም፣ ከጓደኛው ገንዘብ ተበድሮ  “ዓይኔን ግንባር ያድርገው!” ሲል አልካደም፣ ጠጥቶ ሲያሽከርክር ሰው ላይ ጉዳት አላደረሰም…ብቻ ምን አለፋችሁ ከሁሉ አጉል ድርጊቶቹ ጀርባ  ያ ‘ነገረኛ’ አለ፡፡
እናማ…አሁን ያለንበት ጊዜ ያው፣ የምንገልጽበት ቅጽል እንኳን እያጠረን ነው፡፡ በቀደም የሆኑ ‘የሚቀራረቡ ሰዎች’ ስለምንሰማቸው አንድ ሺህ አንድ መጥፎ ነገሮች እያወሩ ነው፡፡ ታዲያላችሁ…የቃላት ልውውጡ… አለ አይደል… በብዙ ነገሮች ላይ እየተለመደ እንደመጣው ወደ ‘አካባቢ’ ወረደ፡፡ የ‘ሰናይ’ነትና የ‘እኩይ’ነት ብያኔ የሚሰጠው በሰዎች ባህሪይ ላይ ተመስርቶ ሳይሆን በትውልድ አካባቢ ሆነ፡፡ ከመሀላቸው አንዱ እንደ ምንም ብሎ ስብስቡን በትኖ ሁሉም ወደ ጉዳዩ ባይሄድ ኖሮ፣ የሚያስጠላ ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ነበር ተብሏል፡፡
እንዴት ያለው ሩቅ ምን ያለው መንገድ
አሻቅቦ ወጥቶ ወደታች መውረድ
--የሚሏት ነገር አለች፡፡ እውነትም ‘አሻቅቦ ወጥቶ ወደ ታች መውረድ!’
ታዲያላችሁ…ምን ነገር አለ መሰላችሁ፣ ለማንኛውም ክፉና እኩይ ተግባር የሚላከክበት፣ “እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው፣” የሚባልበት አይጠፋም፡፡ እናማ… እነኛ ከሀይለ ቃል ወደ ዘለፋ እየተሸጋገሩ ከነበሩት ጋር ‘የሚቀራረቡ’ ሰዎች… “አንተ እንዴት እንዲህ አይነት ነገር ትናገራለህ?” ቢባሉ ከአስሩ ሰባቱ… “ሰይጣን አሳስቶኝ ነው፣” ባይሉ ነው! ልክ ነዋ! አጅሬው እኮ አስበን፣ እቅድ አውጥተን፣ ጊዜ ወስደን ላደረግነው አጉል ነገር ሁሉ መሸፈኛነት የምንመዘው ‘ጆከር’ ሆኗል!
“እንጀራ ውስጥ ጄሶን የሚያህል አደገኛ ነገር ጤፍ ውስጥ መክተት ምን የሚሉት ጭካኔ ነው! እንደው ትንሽ እንኳን አይከብዳችሁም!»
“እኛ ምን እናድርግ!”
“ምን እናድርግ ብሎ ነገር ምን አይነት አማርኛ ነው…በእናንተ ምክንያት የስንት ሰው ህይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አይታያችሁም?”
“አስበን ያደርግነው እኮ አይደለም፣ ሰይጣን አሳስቶን ነው፡፡”
‘ይቺ ናት ጨዋታ’ ብሎ መዝፈን ይሄኔ ነው:: የሰይጣን ‘ማሳሳት’ ነገር…አለ አይደል… “ጉዳዩ ሲፈጸም የተመለከተ የዓይን ምስክር ማቅረብ ትችላላችሁ?” ምናምን ተብሎ መስቀለኛ ጥያቄ አይቀርብበት ነገር! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…“ሰይጣን አሳስቶኝ ነው፣” ካላችሁ ይታዘንላችኋል እንጂ… “ለትንሹም ለትልቁም እሱ ላይ መንጠልጠል ምንድነው?” ብሎ የሚሞግት የለም፡፡ ነግ በእኔ ነዋ!
እንደውም ምን ይመስለኛል…እንደ ዘንድሮ ሁኔታችን፣ እንደ ዘንድሮ ነገረ ሥራችን አንድዬ ዘንድ ሄዶ አቤቱታ የሚያቀርብ ይመስለኛል፡፡
“አንደኛውን እዚሁ ድረስ መጣህልኝ!”
“እኔ አሁንስ አልቻልኩም፣ በቃ ምርር ነው ያለኝ!”
“ጭራሽ አንተ የምትማረርበት ዘመን መጣ! አንተው ተናዳጅ፣ አንተው ተበሳጭ ሆንክና አረፍከው!”
“እነኚህን ሰዎችህን አንድ ትልልኝ እንደሁ አንድ በልልኝ!”
“የትኞቹን ሰዎች?”
“እነኚህ አፍሪካ ቀንድ ነው ምናምን የሚሉት ቦታ ያሉት፣ እነሱ ተተራምሰው እኔን እኮ በቃ ፉዞ ሊያደርጉኝ ነው!”
“ጉድ እኮ ነው፣ አንተም አቤቱታ አቅራቢ ሆንክና አረፍከው?”
“ምንም ላደርግ አልቻልኩም፤ ሁሉም ነገር ከአቅሜ በላይ ሆነብኝ!”
“ምን አደረጉኝ ነው የምትለው?”
“የእኔን ሥራ ሁሉ ወስደውብኝ ሲያበቁ፣ አሁን ጭራሽ ከእኔ ሦስት እጥፍ ብሰው እኔንም እያስፈሩኝ  ነው፡፡”
“ይሄንን ታዲያ ሂድና ከእነሱ ጋር ተነጋገራ! አንሰማም ካሉህም፣ ይሄ ኮፒራይት ነው ምን የምትሉት ነገር አለ አይደል… በእሱ አንቀጽ ጥቀስና ክሰሳቸው፡፡”
“እኔ ክስም አልፈልግም፤ አሁን የምፈልገው ቦታ እንድታለዋወጥን ነው፡፡”
“ምን አልክ?”
“በቃ፣ እኔ ሌላ ምንም አልፈልግም፣ ቦታ አለዋውጠን፡፡»
“አንተ ልጄ ደልቶሀል፡፡ እኔ ከዛሬ ነገ ዙፋኔን ሊነቀንቁብኝ መሞከራቸው አይቀርም ብዬ ሀሳብ ገብቶኛል፤ ጭራሽ ከእነሱ ጋር ሌላ ጣጣ ውስጥ ልትከተኝ ነው፡፡”
“ቆይ፣ ቆይ… አንተም እንደኔ ፈራኋቸው እንዳትለኝ!”
“አልልህም፤ምክንያቱም ብዙዎቹ አሁንም ከልባቸው የእኔ ልጆች ናቸው፡፡ ግን የአንዳንዶቹ ነገረ ሥራ ስላላማረኝ ነው፡፡ ስለዚህ ሂድና ጣጣህን እዛው ጨርስ፡፡”
እናላችሁ…ዘንድሮ፣ “ኤኒቲንግ ካን ሀፕን” ከሚባልላቸው ስፍራዎች አንዷ የእኛዋ አገር ሳትሆን አትቀርም፡፡ እኔ የምለው… በቋጥኙም፣ በጠጠሩም ፉከራ የበዛብን… እሱም ነገር…የ‘ሰይጣን ሥራ’ ይሆን እንዴ!
እንዴት ያለው ሩቅ ምን ያለው መንገድ
አሻቅቦ ወጥቶ ወደታች መውረድ
--የሚሏት ነገር አለች፡፡ እውነትም ‘አሻቅቦ ወጥቶ ወደታች መውረድ!’
የምር ግን፣ እኔ ምለው…ከታች እስከ ላይ ሁሉም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ “ወዮልህ!” ባይ፣ ሁሉም “በጭንቅላትህ እንዳላቆምህ!” ባይ… ሁሉም “ነብር አየኝ በል!” ባይ፣ ሁሉም ፎካሪ ሆነብን እኮ! አለ አይደል…እዚህ አገር ነገሮች ያለማስፈራራት መስራት አይቻልም ማለት ነው!
የሰለጠኑ የሚባሉት በጣም እርቀውን የሄዱት አንድም በዚህ ነው፡፡ ግለሰብም ሆነ ተቋም ላይ እንደፈለጉ መዛት አይችሉም፡፡ ተጠያቂነት ይኖራላ! እኛ ዘንድ ነው እንጂ ለምንም ነገር ተጠያቂነት የሌለበት ዘመን ላይ የተደረሰ የሚመስለው! ያውም በየጓዳውና በየጎድጓዳው ሳይሆን በአደባባይ፣ ሲብስም በመገናኛ ብዙሀን!
እንዴት ያለው ሩቅ ምን ያለው መንገድ
አሻቅቦ ወጥቶ ወደታች መውረድ
--የሚሏት ነገር አለች፡፡ እውነትም ‘አሻቅቦ ወጥቶ ወደታች መውረድ!’
ስሙኝማ…በዚህ በበዓል ሰሞን ምንም እንኳን እንደ ወትሮው ፈገግታ በፈገግታ ሆነን የማክበር ሞራላዊ ጥንካሬ ባይኖረንም፣ ቢያንስ መጪውን ጊዜ የተሻለ ያድርግልን ብለን ልንመኝ እንችላለን:: ቀደም ባለው ጊዜ በዓል ጥሩ ‘አኔስቴዚያ’ ምናምን ነገር ነበረች፡፡ የወራት ብስጭትና ንጭንጭ ገታ ይልና ለአንድና ለሁለት ቀን ሁሉም ነገር ይረሳል፡፡ ዓመቱን ሙሉ “ይሄ ኑሮ እንደው ብን ብለሽ ከአገር ጥፊ እያሰኘኝ ነው!” ስንል ከርመን፣ በዓል ሲመጣ ግን ምንም ነገር ያልተፈጠረ ይመስላል፡፡ ዘንድሮ ግን በዚህ ደረጃ ራሳችንን ማደንዘዙ ሳያስቸግር አይቀርም!
ለከፉም ለደጉም የተሻለውን ዘመን ያምጣልንማ! በዚህ ዘመን አሻቅቦ ወጥቶ ወደታች ከመውረድ የባሰ ሽንፈት አይኖርም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3401 times