Saturday, 20 April 2019 14:56

‹‹ውጊያ በቃኝ!››

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

ንጉሥ አሶካ፤ ታላቅ ወታደር ነበረ፡፡ እልፍ አዕላፍ ሠራዊት ያንበረከከ፡፡ ዛሬ ገድሉን እምንዘክረው ግን ስለ አይበገሬ ጦረኝነቱ ብለን አይደለም፡፡ ይልቅስ አሶካ ታላቅና እጅግ መልካም ሰው ስለመሆኑ እንጂ፡፡ምክንያቱስ - ‹‹ውጊያ በቃኝ!›› ብሎ ጦርነትን እርግፍ አድርጎ በመተዉ ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነበር . . .
ክንደ ብርቱው አሶካ፤ የጦረኝነት ገድሉ ከታላቁ እስክንድር የሚተካከል ነው፡፡ በዘመተባቸው የጦር አውድማዎች ሁሉ ድል የሚነሳ፡፡ መላውን የህንድ ምድር ጠቅልሎ እስከ መግዛትም ደርሶ ነበር፡፡ አንድ ቀን ከቡድሂስት ባህታዊ ጋር ተገናኘ፡፡ ካህኑም ለአሶካ ከእርሱ በፊት ንጉሥ ስለነበረው ቡድሀ ጉተማ ህይወትና አስተምህሮዎቹ አወጋው፡፡
አሶካ፤ በሰማው ጥዑም ወግ ልቡ ተነካ፤ እናም ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ የቡድሂስት እምነት ተከታይ ሆነ፡፡ ከዚያም ባሻገር እርሱ ራሱም ቀሪውን የህይወት ዘመኑን ስለ ቡድሀ እምነት ለህንድ ህዝብ እያስተማረ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔን አደረገ፡፡ ቡድሀ በአስተምህሮው ሲሰብክ የኖረው ደግሞ ሰላምንና ሰላምን ብቻ ነበር፡፡
ስለዚህም፡ በመጀመሪያ አሶካ አንዳችም አይነት ጦርነት ከማድረግ ታቀበ፡፡ እርሱም እንደ ቡድሀ፤ ታላቅ ሀገረ ገዢ ከመሆን ይልቅ መልካም ሰው መሆን እንደሚሻል አስተማረ፡፡ ቀጥሎም፡ በእርሱ ግዛት ያሉ ባሮች ሁሉ ነጻ ይወጡ ዘንድ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ለህሙማኑ መታከሚያም ሆስፒታሎችን ገነባ፡፡ እናም ጎበዛዝቱን በመላው የህንድ ምድር እየተዟዟሩ፣ የቡድሀን አስተምህሮ እንዲሰብኩ አሰማራቸው፡፡
በቡድሀ የትውልድ መንደር፣ የቡድሀን ቤተ መቅደስ አቆመ፤ አሶካ፡፡ እንዲሁም ቡድሀ ከቤት ወጥቶ መኖር በጀመረበት ቀዬም ሌላ ቤተ መቅደስ፡፡ ሦስተኛውን ቡድሀ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህንድ ህዝብ ማስተማር በጀመረበት እናም አራተኛውን ቤተ መቅደስ ቡድሀ ባረፈበት ስፍራዎች አሰራ፡፡
እኒሁም የቡድሂስቶች ቅዱሳን መካናት ናቸው፤ ህዝቡ እነርሱን ባየ ጊዜ ሁሉ ቡድሀንና አስተምህሮዎቹን የሚያስታውስባቸው፡፡
አሶካ ግን አሁንም አልረካም፡፡ ማንኛውም ሰው ደስተኛና መልካም እንዲሆን ጽኑ መሻት አደረበት፡፡ ሰዎች ደስተኛና መልካም ይሆኑም ዘንድ የቡድሀን አስተምህሮዎች መከተል ይገባቸዋል ብሎ አመነ፡፡ በዚያን ዘመን ደግሞ ይህን ሀሳብ ማስፋፋት ለመቻል መጻሕፍት መታተም አልጀመሩም ነበር፡፡
ይህን እቅድ በሌላ መልኩ ለመተግበር ለአሶካ መላ የሆነው፣ የቡድሀን አስተምህሮዎች በትልልቅ ጥርብ ድንጋዮች ላይ እንዲቀረፁ ትዕዛዝ መስጠት ነበር፡፡ ቋጥኝ ድንጋዮቹ በመላው የህንድ ግዛት ዙሪያ ስለሚገኙ በነዚያ ላይ የተቀረፀውን የቡድሀን አስተምህሮ ህዝቡ ሁሉ ለማየትና ለመረዳት፣እምነቱንም ለመከተል ይቻለዋልና ነው፡፡
አንድ ማረጋገጥ የሚያስፈልገን ጉዳይ አሶካ ጦርነትን እርም ብሎ በመተዉ ቅንጣት ታክል ጸጸት እንዳልተሰማው ነው፡፡ የመጨረሻው ጊዜ ሲደርስም፤ በህይወት ዘመኑ፣ ሰዎች አንዳቸው ሌላቸውን መውደድ እንዲቻላቸው የበኩሉን ማድረጉን ያውቅ ነበር፡፡ መልካም ይሆኑ ዘንድ፡፡ ይህም ሰዎችን በጦረኝነት ከመግደልና በባርነት ከማንበርከክ ብዙ ሺህ እጥፍ የተሻለ መሆኑን፡፡
ማን ያውቃል፤ አንድ ቀን ሁላችንም እንደ አሶካ ማሰብ ጀምረን ፤ ጦርነት እስከ መቼውም ያከትም ይሆን? ይሆናል . . .
ሰላም ለሰው ልጆች!!

Read 995 times