Saturday, 20 April 2019 14:58

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)


                                “የእውነተኛ እምነት መሰረት ራስን ማሸነፍ ነው”
                                    

             ጋዜጦች ያስጮሁት የከተማው ወሬ ስለነበር ፍ/ቤቱ ተጨናንቋል፡፡
ዳኛው ለሁለተኛ ጊዜ ጠየቁ፡-
“ለባለቤትህ ታማኝ ነህ አይደለም?
ተከሳሽ፡- “ነኝ”
የተከሳሿ ሚስት፡- “ውሸቱን ነው” አለች ጣልቃ ገብታ፡፡
ዳኛ፡- “አንቺን አይደለም የጠየኩት” ካሉ በኋላ የቆንጆ ሴት ምስል ያለበት ጉርድ ፎቶግራፍ ብድግ አድርገው፡-
“ይቺን ታውቃታለህ?” ሲሉ ተከሳሹን ጠየቁ:: ፕሮፌሰሩ ህግ ፊት የቆመው በ“አደስተር” ተጠርጥሮ ነው፡፡
ተከሳሽ፡- “አውቃታለሁም አላውቃትምም”
ዳኛው እየተገረሙ፡- “ማ‘ናት?”
ተከሳሽ፡- ዝም
ዳኛው፡- አንድ ላይ የታሰሩ ብዙ ደብዳቤዎችን እያሳዩት፡-
“እነዚህን የፃፍካቸው አንተ ነህ? … አይደለህም?”
ተከሳሽ፡- “እኔ ነኝ”
ዳኛ፡- “ለማ‘ነው የፃፍከው?”
ተከሳሽ፡- “ለሷ”
ዳኛ፡- “እኮ እሷ ማ‘ናት? የት ናት ያለችው?”
ተከሳሽ፡- ዝም፡፡
ዳኛው ግራ ገባቸው፡፡ የቀረበላቸውን የሃኪም ማስረጃ እንደገና ተመለከቱ፡፡ ሰውየው የጤና እንከን እንደሌለበት ተረጋግጧል:: በዚህ ላይ የስነ ህይወት ተመራማሪ ነው፡፡ ለማስረጃ የቀረበው ፎቶግራፍ ትክክለኛና በራሱ ካሜራ የተነሳ ነው:: በቴሌቪዥንና በጋዜጦች “ትፈለጋለች” ተብሎ ማስታወቂያ ቢነገርም፣ “እኔ ነኝ” የምትልም ሆነ “አውቃታለሁ” ባይ ብቅ አላለም፡፡ ባህሩ ዳር ካለው ቤትም ፕሮፌሰሩ ለፃፋቸው ደብዳቤዎች የተሰጠ ምላሽም ሆነ የሴት አልባሳት፣ መጫሚያዎችም ሆኑ የመዋቢያ መገልገያዎች አልተገኙም፡፡ ፖሊስ በየአቅጣጫው ባደረገው ምርመራም ፍንጭ ሊያገኝ እንዳልቻለ ለፍ/ቤቱ አስረድቷል፡፡ ዳኛው ወረቀቶችን እያገላበጡ ለረዥም ጊዜ ሲያስቡ ቆይተው፣ እንደገና ፎቶግራፉን በማንሳት፡-
“ለመጨረሻ ጊዜ ልጠይቅህ … ይቺን ሴት ገድለሃታል? አልገደልካትም?” ብለው ጠየቁ፡፡
ተከሳሽም፡- “አልገደልኳትም፣ አልሞተችም … አለች” በማለት መለሰ፡፡ ፍ/ቤቱን የሞላው ታዳሚ ማጉረምረም ጀመረ፡፡ ዳኛው መዶሻውን አንስተው ጠረጴዛቸውን “ግው!” አደረጉ፤ ፀጥታ ለማስከበር፡፡ በዚህን ጊዜ አጠገባቸው ከነበረው መደርደርያ ላይ የነበረ፣ ሁለት የጌጥ አሳዎች የሚኖሩበት የመስታወት ሳጥን (Aquarium) ወለሉ ላይ ወድቆ ተሰበረ፡፡ ታዳሚው ፀጥ፣ እረጭ አለ፡፡ የዳኛው ፊት ወዲያውኑ ተቀየረ … ፈገግ አሉ፡፡ ወደ ሰውየው ተመለከቱ፤ ሳቀ:: ቀጥሎ ወደ ሚስቱ ተመለከቱ፡፡ እንባ እየተናነቃት ነበር፡፡
“ክሱ ተዘግቷል፣ ነፃ ነህ!!” አሉ፤ እንደገና ጠረጴዛውን እየመቱ፡፡ … ባልና ሚስቱ ተቃቀፉ:: ጉዳዩን ለመከታተል የመጣው ህዝብና የሚዲያ ሰዎች ግን አልገባቸውም፡፡ … ምን ተፈጠረ …?
***
ወዳጄ፡- አንዳንዴ የምናስበውን ሰው በደቂቃዎች ውስጥ በአካል እናገኘዋለን፡፡ ወይም ስልክ ይደውልልናል፡፡ እኛንም ለሚፈልጉ እንደዚያው ነን፡፡ የአእምሮአቸውን ተፈጥሯዊ ሃይል ለዝባዝንኬ ወይም ለክፋት ተግባር የማያባክኑ ሰዎች ለበጎነት ቅርብ ናቸው፡፡ ምንም ዓይነት ግንኙነትና ትውውቅ ከሌላቸው መሰሎቻቸው ጋርም በመንፈስ ይሳሳባሉ:: (Spiritual communication እንደሚሉት) የሚገፈትራቸውንም መንፈስ (energy) በቀላሌ መረዳት አያስቸግራቸውም:: ህፃናትና እንስሳትም ሶስተኛ ኃይል ጣልቃ እስካልገባ ድረስ እንደዚያው ናቸው፡፡ እውነተኛ አማኞችንም ይጨምራል፡፡ ምክንያቱም የእውነተኛ እምነት መሰረት ሌላውን ማሸነፍ፣ ሌላውን መግፋት ሳይሆን በመጀመሪያ እራስን ማሸነፍ፣ ራስን መግራትና ሌላውን መውደድ መቻል በመሆኑ ነው፡፡ እውነተኛ አማኞች እንኳን ሰውን የሚያክል በምንክንያትና በአምሳል የተሰራን ፍጡር መጉዳትና ማሳዘን ቀርቶ ትንኝ እንኳ ያለ አግባብ እንድትሞት ሰበብ መሆን አይፈልጉም:: ለምሳሌ የሂንዱ ጄኒስት መነኮሳት ትንኝ አፋቸው ውስጥ ገብታ እንዳትሞት ሁሌም አፋቸውን በጨርቅ (Mukha) ይሸፍናሉ፡፡ እነሱ (እንስሳት) ባይኖሩ የሰው ልጅ የለም ይላሉ፡፡
በሳታ - ፓታ ብራህማና (Indian mytheology) ሳንስክሪት፣ የሰው ልጆችን ከጥፋት ውሃ (the great flood) የታደጋቸው “ማትሲያ” የተባለው ዓሳ መሆኑን ይተረካል፡፡ ይኸውም፡- ማትስያ ከስምንት ትውልድ በኋላ እንደገና የተወለደላቸው የነፍሳቸው ጠባቂ (Life preserver) የሆነው አምላክ ቪሽኑ ራሱ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ማትሲያ ለሰው ልጆች ህገ ትዕዛዛትን የሰጠው የመጀመሪያው አባት “ማኑ” ፊቱን እንዲታጠብ ከቀረበለት የገበቴ ውሃ ውስጥ ብቅ ብሎ፡-
“ላድንህ ነው የመጣሁት” አለው፡፡
ማኑም … “ከምንድነው የምታድነኝ?” በማለት ሲጠይቀው፣ ታላቅ ጎርፍ እየመጣ ስለሆነ መርከብ እንዲሰራ ነገረው፡፡ በተከታይም ማድረግ የሚገባውን ሌሎች ነገሮች በቅደም ተከተል አስረዳው፡፡ ማኑም እንደታዘዘው አደረገ፡፡
ማትሲያ ጎርፍ ከቀነሰ በኋላ መርከቡን እየመራ ወደ ሰሜን ተራሮች ጫፍ በማድረስ እንደተሰናበተው ይነበባል፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- የፕሮፌሰሩ ሚስት ባሏን የተጠራጠረችው በምክንያት ነበር:: ደብዳቤዎችና ፎቶግራፍ በማግኘቷ ብቻ ሳይሆን ሰውየው ለረዥም ሰዓታት በጥልቅ ሃሳብ ውስጥ የመቆየቱ ጉዳይ እረፍት ስለነሳትም ጭምር ነው:: ባለቤቷ በበኩሉ ሚስጢሩን ለፍርድ ቤቱም ሆነ ለማንም ለማስረዳት የጥናቱ ፀባይ አልፈቀደለትም:: ከብዙ ዓመታት ድካም በኋላ አግኝቶ ጓደኛ ያደረጋትን ፍጡር ጉዳይ አደባባይ ማውጣት አልፈለገም፡፡ አሁን የተፈጠረው ውጥረትና የፍርድ ቤት ግርግር “የተሰማት” ወይም “sense” ያደረገችው “እሷ” ግን በመኖሪያዋ ሆና መንፈሷን (ኢነርጂዋን) ላከች፡፡ አኳሪየሙ እንዲሰበርና ሰዎቹ ስለ ዓሶች እንዲያስቡ በማድረግ፣ የሰውየውን ሚስትና የፍርድ ቤቱን ዳኛ አባነነቻቸው፡፡ … ውቧ መርሜይድ!!
ወዳጄ፡- መርሜይድ ማ‘ናት? እንዳትለኝ:: ዓለም Vegetarian እየሆነ በመጣበት በዚህ የስልጣኔ ዘመን፣ በፋሲካ ስለሚጨፈጭፋቸው እንስሳት ለሚያስብ እንዳንተ ዓይነት “ሃይማኖተኛ” ይኸንን መንገር “ለውጥ ከማደናቀፍ” የሚተናነስ አይመስለኝም፡፡
ይልቁንስ አንድ ነገር ልጠይቅህ … የመንፈስ ነገር ከተነሳ አይቀር፡፡
“ሁለትና ሶስት በሆናችሁበት ሁሉ አለሁ” ያለው ማን ነበር? … ምርጫ ልስጥህ፡-
ሀ) ክርስቶስ
ለ) ዲያቢሎስ
ሐ) ጌታቸው
መ) ጎሃ
ረ) ከ “ሀ” በስተቀር ሁሉም አንድ ናቸው፡፡  
ሰላም!!

Read 606 times