Saturday, 02 June 2012 09:11

የኑሮ ውድነት ግንቦት 20ን አይፈራም!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(0 votes)

የፖለቲካ ተቃውሞ ከተማ ያቆሽሻል ! (ፑቲን)

ወዳጆቼ … የግንቦት 20 ሃያ አንደኛ ዓመት የድል በዓል እንዴት ነበር? እኔ ከሁሉም የተመቸኝ ቴሌኮም በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለደንበኞቹ ያደረገው የአጭር መልዕክት (ቴክስት ሜሴጅ) ታሪፍ ቅናሽ (ዲስካውንት) ነው፡፡ የገባው ነጋዴ እኮ ነው! ምናለ እንደቴሌኮም ዓይነት አንድ ሁለት ቢኖረን፡፡ እኔ የምለው… አገር ውስጥ ገቢ ለታክስ ከፋይ ዜጎች ማበረታቻ ወይም ሆሊዴይ ታክስ አሊያም የሆነ የታክስ ዲስካውንት ነገር የለውም እንዴ? (ግብር አይደለም እዳ… ብቻ ምን ይሰራል?) በግንቦት 20 (ቢያንስ በዓመት አንዴ) እንዲቀንስልን የምንፈልገው ብዙ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ፋሲካ  ከ90 ብር ተተኩሶ 120 ብር ላይ ቂብ ብሎ የቀረው ጥሬ ስጋ በግማሽ ዋጋ  ቢቀንስልን  እንመርቀው ነበር - ዘላለም እንዲነግስ! በእርግጥ መንግስት አቅም ላይኖረው ይችላል (ከየት ያመጣል?) እነ IMF እና ዎርልድ ባንክ ግን ሊያግዙን ሊደጉሙን ይችላሉ … የአሁኑማ አለፋ… ለመጪው ካሁኑ ይታሰብበት! ከምሬ ነው … በግንቦት 20 ሽሮ መብላት ሙድ ያበላሻል፡፡ (እንዴ ቤቱ በዓል በዓል ሳይሸት?) እኔ የምለው ግን …የኑሮ ወድነቱ ላይ ዲስካውንት የሚደረግልን መቼ ነው? ይኸው ተስፋ የጣልንበትም ቀን እኮ አለፈ! (ግንቦት 20!)

እስቲ አስቡት … መንግስት ባለሁለት ዲጂቱን የኢኮኖሚ እድገት ወደ ዳቦ ለውጦ ያመጣል ብለን ስንጠብቅ ስንት ጊዜያችን! (ረሳው መሰለኝ) አንዱ ሽማግሌ ምን ነበር ያሉት? “መንገዱም ግድቡም መሰራት ያለበት እኛ እየኖርን ነው” እውነታቸውን እኮ ነው! እኔ የምለው ግን… የኑሮ ውድነቱን የሚመለከተው መንግስታዊ መስሪያቤት የቱ ነው? የኑሮ ውድነት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴስ… እስካሁን የለም ማለት ነው? ኮሚቴው ከሌሎቹ ቅሬታ ሰሚኮሚቴዎች የተለየ ተዓምር እንደማይፈጥር እኮ አሳምረን እናውቃለን፡፡ ቅሬታችንን የምንተነፍስበት ሲኖር ግን ምንም ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ ይሄን መቼም ለኢህአዴግ አልነግረውም፡፡ የዛሬ 21 ዓመት “ብሶት የወለደው…” ብሎ አይደል ራሱን ያስተዋወቀን! (ጊዜው እንዴት ይከንፋል ባካችሁ?) በነገራችን ላይ ሳልረሳው ለኢህአዴጎች አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ግን ሃቀኛ (Honest) መልስ ነው የምፈልገው (ለመመረቂያ ወረቀት ስለሆነ)  በትግል ላይ እያላችሁ ከ20 ዓመት በላይ እንገዛለን ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? (ልብ አድርጉ ድብቅ አጀንዳ የለኝም!)

እናላችሁ … የኑሮ ውድነት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ባለመኖሩ ሰዎች ቅሬታቸውን በቴክስት ሲላላኩ ዋሉ - ቴሌኮም ባደረገልን ቅናሽ (ይሞታል እንዴ ታዲያ?) እስቲ እኔ የደረሰኝን መልዕክት ላጋራችሁ (መረጃ መደበቅ ያስጠይቃል!)

ርዕሱ ምን ይላል መሰላችሁ? “የግንቦት 20 ፍሬዎች”

ጤፍ - ከ120ብር ወደ 1600ብር

በግ - ከ150ብር ወደ 2500ብር

ስጋ - ከ10ብር ወደ 120ብር

ጫት - ከ10ብር ወደ 100ብር

ውሃ - ከ0ብር ወደ 10ብር

ዶላር - ከ5ብር- ወደ18ብር

ነዳጅ - ከ5ብር - 20ብር

ጫት - ከ10ብር - 100ብር

እውነቱን ልንገራችሁ አይደለ … ይሄ ሜሴጅ እንደደረሰኝ በጣም ብሽቅ ብዬ ነበር…ለምን መሰላችሁ? የሸቀጦች መናር የሚፈጠረው ኢኮኖሚው ሲያድግ እንደሆነ ስንቴ ነው የተነገረን! ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ በፓርላማ ስንቴ ነው ያስረዱት (የኢኮኖሚ ሀሁ አለማወቅ ችግሩ ይኼ ነው!)  እንደሚነገረን ከሆነ እኮ… የሸቀጦች ዋጋ አሁን ካለው በእጥፍ እንዲጨምር ሁሉ መመኘት አለብን፡፡ ለምን መሰላችሁ … ዋጋ ናረ ማለት ኢኮኖሚው ተመነደገ ማለት እኮ ነው! (ኪስ ባይሞላም)

ዝም ብዬ ሳስበው ግን ይሄን ሜሴጅ ያረቀቁት “መርዶ ነጋሪዎች” እንደሆኑ ጠርጥሬአለሁ፡፡ እኔማ ምን አደረኩኝ መሰላችሁ… አሰብኩ አሰብኩና ሌሎች የግንቦት 20 ፍሬዎችን ቸክችኬ ላኩላቸዋ (በቴክስት)  እንዲህ ይላል -  ዲሞክራሲ (ከነገደቡ) “ የፖለቲካ ምህዳሩ (ከነጥበቱ)” የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ (ከነወከባው)” የኢኮኖሚ ዕድገቱ (ከነግነቱ)”ኮንዶሚኒየም (ከእነጉድለቱ)” የ1ለ5 አደረጃጀት ስትራቴጂ (ከነትችቱ) “የመሬት ሊዝ አዋጅ (ከነተቃውሞው)” የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ (ከእነዓለማቀፍ ውግዘቱ)  ወዘተ… የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው አልኩዋቸው  (ዋሸሁ?)

እንዲህ ሽንጤን ገትሬ የተከራከርኩለትን አውራ ፓርቲ ሰሞኑን እንዴት እንደታዘብኩት አልነግራችሁም፡፡ ምን መሰላችሁ… የታዘብኩት? ዛሬም ከ20 ዓመት በሁዋላ  ከደርግ ጋር ልፊያ ተው …እኩያ አይደላችሁም… ቢባል አሻፈረኝ ማለቱ ነው፡፡ እንዴ… በየግንቦት 20ው እኮ ደርግን ከማውገዝ አልተላቀቀም (ፈረንጆቹ stuck in time እንደሚሉት)  አንዳንዴ ምን እንደማስብ ታውቃላችሁ? አሁን የደርግን ስም ማንሳት ክልክል ነው ቢባል ኢህአዴግን ምን ይውጠዋል? (የስነልቦና ምሁራን ይሄን አባዜ ስም አያጡለትም!)  እንደው ፈርዶበት ነው እንጂ የልማት ትሩፋቶቹ እኮ  ለፌሽታው በቂ ነበሩ! በዚያ ላይ እኛን የመሰለ የዋህ ህዝብ ሰጥቶታል!

በሉ እኛም ኢህአዴግን በችኮነት እየወቀስን ችኮ እንዳንሆን ወደሌላ አጀንዳ እንለፍ፡፡ በነገራችሁ  ላይ በግንቦት 20 በዓል ኢቴቪ ችክ ብሎ ነው የዋለው (የ20 ዓመት አርካይቭ በግድ ተጋትን እኮ !) እኔማ ትንሽ የሚያዝናና ወይም በአል በአል የሚሸት ፕሮግራም ይኖራል ብዬ ሁለት ሰዓት ሙሉ አፌን ከፍቼ ስጠብቅ ቆዩኝና… ነገሩ ስላላማረኝ… ስንት ወር የተውኩትን ድራፍት ልጨልጥ ወጣሁ - (በኢቴቪ ከምደበር እራት ይቅርብኝ ብዬ) ድራፍትና እራትማ በማን አቅም?   (የኑሮ ውድነት እኮ ግንቦት 20ን አይፈራም!)

ወደ ድራፍት ቤቱ ስገባ ገና በጊዜ ጢም ብሎ መሙላቱ ገርሞኝ አሳላፊውን ጠየቅሁት “ግንቦት 20 እኮ ነው ጋሽዬ” አለኝና ጃምቦዬን ሊያመጣ ሮጠ -  በጠባብዋ ግሮሰሪ ውስጥ፡፡ አጠገቤ ተቀምጦ አልኮል የሚስበው ጎልማሳ ወደእኔ እያየ “የግንቦት ልደታ መሰለው እንዴ?” በማለት በሌለበት በቁጣ ገላመጠው፡፡ ሰውየው ከእኔ ጋር ጨዋታ የፈለገ ይመስላል፡፡ እኔ ደግሞ ባዶ ሆዴን ነኝ - ቢያንስ አንድ ጃምቦ መጠጣት አለብኝ፡፡ ሰውየው ጂኑን እንደክኒን ነው ወደ ጉሮሮው የሚወረውረው፡፡

ጃምቦዬ እስኪመጣ የያዝኩትን ጋዜጣ ማገላበጥ ያዝኩኝ፡፡ አንድ ጥግ ላይ በጉልህ የሰፈረው ጥቅስ  ትኩረቴን ሳበው “የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን መንግስት በቀጥታ ያስተላለፈልን መልዕክት አፋችሁን ዘግታችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ የሚል ነው”  ይሄን የተናገሩት  “ጀስት” የተባለው የሩስያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ናቸው - ጋዜጣው እንደሚለው፡፡ እኔን የገረመኝ አፍሪካም… አውሮፓም… መካከለኛው ምስራቅም … አንታርቲካም ወዘተ  የገዥ ፓርቲዎችና የተቃዋሚዎች ውዝግብ ተመሳሳይ መሆኑ ነው (የአምባገነኖቹን ማለቴ ነው!)  በቅርቡ ምርጫ አሸንፌአለሁ ብለው የለመዱት ስልጣን ላይ የተፈናጠጡት ፑቲን፤ ምርጫ አጭበርብረዋል በሚል ተቃውሞ ሲሰነዘርባቸው የቆየ ሲሆን የተቃዋሚውን ጫጫታ ጭጭ ለማሰኘት የመጣላቸው ግሩም ሃሳብ  አዲስ ህግ ማውጣት ብቻ ነው (አምባገነኖች አዋጅና ህግ ይወዳሉ ልበል)  እናላችሁ …ፑቲን በፓርላማ ባፀደቁት አዲሱ የሩሲያ ህግ መሰረት” በተከለከሉ ሰልፎች ላይ የሚሳተፉ ሰዎች፤ ከ160 ዶላር እስከ 32ሺ500 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ሲጣልባቸው፤ የሰልፍ አስተባባሪዎች ግን ተጨማሪ ቅጣት ይጠብቃቸዋል - ሰልፍ የተደረገበትን ስፍራ በመጥረጊያ ሙልጭ አድርጎ ማፅዳት! (በተቃውሞ ያቆሸሹትን ማለት ነው) በሌላ አነጋገር ፑቲን እያሉ ያሉት… የፖለቲካ ተቃውሞ ከተማ ያቆሽሻል ነው፡፡ (ዘይገርም ነው!)

በፑቲን አምባገነንነት እየተገረምኩና እያዘንኩ… ፊትለፊቴ በአረፋ ተሞልቶ የተቀመጠውን ድራፍት አነሳሁኝና ወደጉሮሮዬ ላክሁት (ደፋሁት ብል ይሻላል) በአንዲት ትንፋሽ ያጋመስኩትን ድራፍት ሳስቀምጥ እንዲህ የሚል በጥያቄ የተጠቀለለ ሃሳብ ከአዕምሮዬ ጉዋዳ ድንገት ብቅ አለብኝ “ሩሲያኖች… ግንቦት 20 የላቸውም እንዴ!?”  በነገራችሁ ላይ አዲስ ዘመን እየተባለ በሚጠራው ጋዜጣ ላይ “የግንቦት 20 ዓለማቀፋዊ ዳራዎች” የሚል ፅሁፍ ማንበቡን አንድ ወዳጄ ነግሮኝ ትንሽ ሙድ ያዝንበት፡፡ እኔ የምለው… አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሄራልድ  ጋዜጦች የመንግስትና የህዝብ ናቸው አይደል (እንደ መሬት ማለት ነው!)

ከግማሽ ሰዓት በፊት እዚች ድራፍት ቤት ስገባ ጢም ብላ የሞላች መስሎኝ ነበር …  (ተጠራጠርኩት ዓይኔን) እሺ የቅድሙም ይቅር …  ይኸው አሁን ራሱ የታለ መፈናፈኚያ! ግን አንድም የሚመለስ ሰው የለም፡፡ ይገባል ይገባል… ይጠጣል ይጠጣል! የዚህንማ ምስጢር ማወቅ አለብኝ ብዬ ዛትኩኝ (ምን ዓይነት ተዓምረኛ ቤት ናት!) ምስጢሩን ለማወቅ ግን ትንሽ መቆየት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ሁለት… ሶስት …አራት… ጃምቦዎች ያህል መቆየት … መታገስ ይፈልጋል፡፡ እኔ የምለው …  የግንቦት 20 ድል የተገኘው በመታገስ ነው በመታገል? የድል አጥቢያ አርበኛ ሳይሆን በትክክል የታገለ መልስ ቢሰጥበት ደስ ይለኛል፡፡

የድራፍት ማሽኑን ተደግፎ የሚጠጣው … ሁለመናው ከስጋ የተሰራ የሚመስል ጎልማሳ “ድምፅ ስጠው! ድምፅ ስጠው! አንተ” አለ ግድግዳው ላይ ወደተሰቀለው የቲቪ ስክሪን አፍጥጦ፡፡ የዜና እወጃ ሰዓት ነበር… ሰውየው ዜና ያደንቃል ማለት ነው አልኩኝ - በሃሳቤ፡፡ ብዙ የግንቦት 20 ፍሬዎች… ብዙ የግንቦት 20 ድሎች… ብዙ የግንቦት 20 ልማቶች…ብዙ የግንቦት 20 ትራንስፎርሜሽኖች…ተወሩ ተነገሩ ተበሰሩ …

ትኩረቴን ከቲቪው ዜና ላይ መንጭቄ የነቀልኩት አጠገቤ የተቀመጠው ጠጪ ሲናገር ነው “በቃ አይለቀንም …እቺን ሰበብ አግኝቶ ነው …ግንቦት 20 ሲል መክረሙ ነው!” አንዴ ወደ ኢቴቪ” አንዴ ወደ እኔ እያየ ነው የሚያወራው፡፡ ማዶ በግሩፕ ሆነው የሚጠጡት ጎረምሶች ከጣራ በላይ ሲያስካኩ ሰውየው ከሚያወራው ተናጠበና በርቀት አፍጦ እያያቸው፤

“ኢህአዴግ ይሄን 1ለ5 አምጥቶ ጉድ አፈላብን እኮ” አለኝ ትክ ብሎ እያየኝ

“እንዴት?” አልኩት ተረብ እንደሆነ በመጠርጠር

“ለኮብልስቶን ተደራጁ ሲላቸው ድራፍት ቤት ተደራጅተው ይመጣሉ”

ሳቅ አልኩኝና ወደ ግሩፑ አሻግሬ ተመለከትኩ - አምስት ናቸው፡፡

“ወንድሜ… ለሰፈሩ እንግዳ ነህ መሰለኝ?” ሲል ጠየቀኝ - ጂኑን እየቆነደደ፡፡

“ለሰፈሩ ሳይሆን ለቤቱ ነው እንግድነቴ” መለስኩለት፤ ድራፍቴን እየተጎነጨሁ፡፡

“እንኩዋን ወደ ግንቦት 20 ግሮሰሪ በደህና መጣህ” አለኝ ተዋናይ ብቻ የሚችለውን ፈገግታ እያሳየኝ፡፡

“ ወንድሜ ሙት ከምሬ ነው…ግብር ላለመክፈል ሲል ታፔላ አልሰቀለም እንጂ… ”

ፈገግ አልኩኝ - በተናገረው እንደተስማማሁ ዓይነት፡፡

“ይገርምሃል” አለና ጂኑን ፉት አለ “ሚስት ያገባሁት በግንቦት ወር ነው… ሁለት ልጆቼም የተወለዱት በግንቦት ወር ነው… በቃ የግንቦት ቤተሰብ ነን… አደራ ግን ምስጢር ነው …ለማንም ተናግሬው አላውቅም”

ግራ ገባኝና ትክ ብዬ አየሁት - ሰውየውን፡፡

“ምን መሰለህ…  የኢህአዴግ ሰዎች እንዲያውቁ አልፈልግም…” አለ ዙሪያውን እየተገላመጠ፡፡

“ምኑን?” አልኩት ነገሩ ስላልገባኝ

“በግንቦት ማግባቴን… በግንቦት መውለዴን …”

“የኢህአዴግ ሰዎች ቢሰሙ  ምን ችግር አለው?” ጠየኩት

“ትቀልዳለህ…  ልጆቼን የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው ብሎ… ቢቀማኝስ?”

ልስቅ አልኩና ሰውየው  ኮስተር ማለቱን ስመለከት ሳቄን ዋጥኩዋት፡፡ “የኔ ወንድም ነገ ብቅ በላ… እጋብዝሃለሁ” ጂኑን  ጨለጠና ከተቀመጠበት ተነሳ “ሶስት ደብል ናት…ሃንድል አድርጋት” አለኝ ወደ ብርጭቆው እያሳየኝ፡፡

ከዛ ለመናገር እድል ሳይሰጠኝ ቀጥ ብሎ ወጣ - ከግንቦት 20 ግሮሰሪ፡፡ ሰውየው የጫነብኝ ዕዳ ዱብዕዳ ቢሆንም  አልተበሳጨሁም፡፡ (የግንቦት 20 ፍሬ ነው ብዬ ግን አይደለም)

 

 

Read 3944 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 09:25