Saturday, 20 April 2019 14:59

የሰው አገር ገነት!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ /አተአ/
Rate this item
(2 votes)


                       “…አሁን እኔ እንደዚያ ነኝ፡፡ ድሮ ሁሉን የጨበጥኩት የመሰለኝ ወቅት ነበር፡፡ ደስተኛ ህይወት ነበረኝ፡፡ ከተራራው ማዶ የሚጨስ ጭስ እኛ መንደር የሚደርስ አይመስለኝም ነበር፡፡ በመንደራችን አደባባይ የተሰቀሉ የሌላ ጎሳ አባላት ሰቆቃ እንደ ራሳችን አልሰማ ብሎን በማዘን ብቻ አልፈን ነበር፡፡ ጥላቻና ዘረኝነት ግን እንደማይድን ቁስል ነው፡፡ የደረቀ ሲመስልህ እንደገና እየነፈረቀ ያስለቅስሃል፡፡… ››
                    

              ሜትሮ ለመሳፈር /የምድር ውስጥ የከተማውን ባቡር/ ከመሬት ወደ ውስጥ  /ወደ ጣቢያው/ ቁልቁለቱን በተሽከርካሪ ደረጃ እየወረድኩ እያለ የእስካሌተሩ ፍጥነት ያልማረካቸው ተጓዦች ‹እስኪ እባክዎ ያሳልፉኝ!› እያሉ በጎንና በጎኔ እየተራመዱ መውረድ ሲጀምሩ ነበር ከደረጃው ቀኝና ግራ ጎን የተፃፉትን እንግሊዝኛ ፅሁፎች ያነበብኩት:: ‹ቆመው መውረድ ከፈለጉ በስተቀኝ ይቁሙ! … እየተንቀሳቀሱ መጓዝ ካስፈልገዎ በግራ በኩል ይጠቀሙ!› ይላል፡፡ ወይ አለማወቅ! በተቃራኒው ቆሜ መንገዱን ሁሉ ዘግቼው ኖሯል፡፡ ተገታሪ ፖለቲከኞችም እንዲህ ሚናቸውን ስለማይለዩ’ኮ ነው በህዝቡ መንገድ ላይ የሚነደቀሩት፡፡
እንደ ምንም ወርጄ ከጣቢያው የቆመው ባቡር ሊነሳ መሆኑን ተረድቼ፣ ተንደርድሬ ወደ ባቡሩ በር ስደርስ መሳሳቴ ገባኝ፤ እግር ፍሬን ቆንጥጬ ቆምኩ፡፡ ከፉርጎ ውስጥ ከሚታዩኝ በዛ ያሉ ሴቶች ውስጥ ሰውነቷን ሁሉ የሸፋፈነች አንዲት ሴት በፍጥነት ወደ ውስጥ እንድገባ በእጅ ምልክት ብትሰጠኝም ተገትሬ ቀረሁ፡፡ ነገሩን ከማሰላሰሌ በፊት ኮምፒውተራይዝድ የሆነው የባቡሩ አስተናጋጅ ሰውዬ ንግግር፣ በአረብኛና በእንግሊዝኛ በስፒከሩ ውስጥ ተሰማኝ፡፡  
‹‹Al abwab Toghlaq …. Doors closing!››  /በሩ እየተዘጋ ነው!/
ለነገሩ ምን የሚያስቸኩል ነገር አለና ነው የምሮጠው! ከ 2 ደቂቃ በኋላ ሌላው ባቡር መምጣቱ አይቀርምና ትንሽ መንጎራደዱን መረጥኩ፡፡ ስህተቴ ምን ነበር! የመረጥኩት መግቢያ ልክ አልነበረም፡፡ ከፊት ያሉትና ከደረጃው ወዲያው ወርጄ ያገኘኋቸው የባቡሩ መግቢያዎች ቅድሚያ የሚሰጥባቸው ናቸው:: የመጀመሪያው ለወርቃማ ካርድ ባለቤቶች፣ የሚቀጥሉት ደግሞ ለሴቶችና ህፃናት ብቻ የተሰናዱ ነበሩ፡፡ ከዚያ ለጥቆ በሚገኘው መግቢያ ነው መግባት የነበረብኝ፡፡
***
በደቂቃ ልዩነት በሚቀጥለው ባቡር ተሳፈርኩ:: የተጨናነቀ አልነበረም፡፡ ሙቀት አይታሰብም፡፡ ኸረ እንዲያውም  በየሄድኩበት የሚከተለኝ /ሙቀት ማብረጃ ኤሲ/ አስጠልቶኛል፡፡ በርግጥ ወደ ውጪ ወጣ ሲባል ከአስፋልቶቹ ላይ እየነጠረ እንደ እሳት ወላፈን የሚጋረፈው ሙቀት ያስበረግጋል፤ ቢሆንም ቅዝቃዜው ደግሞ ቤት ውስጥ ስገባ ኮት እንድደርብ እያደረገኝ ነበር፡፡ ምግብ ቤት፤ ሱቆች፣ ትልልቅ የገበያ ማዕከሎች ሁሉ ይቀዘቅዛሉ፡፡ ዱባይን ሳይሆን የቀዝቃዛ አገር አየር ያስታውሳሉ፡፡  
ከዱባይ ሞል ተሳፍሬ ወደ አል-ሪጋ ነበር የምሄደው፡፡ ባገኘኋት ወንበር ላይ ተቀመጥኩና ዙሪያዬን መቃኘት ጀመርኩ፡፡ ለጥቆ ድምፁ እንዲህ ሲል አወጀ፤
‹‹Al abwab Toghlaq …. Doors closing!››  /በሩ እየተዘጋ ነው!/
ዘዋሪ /አሽከርካሪ/ አልባው ሜትሮ መንቀሳቀስ እንደጀመረ አናውንሰሩ እንዲህ ሲል በድጋሚ አወጀ /እንግሊዝኛው ድምጽ የእንግሊዛዊው ጆን ስትሪክላንድ ነው/፣
‹‹Al Mahatta Al Qadima Heya – Emirates Towers! ….. The next station is – Emirates Towers!›› /የሚቀጥለው ጣቢያ - ኢሚሪየትስ ታወር!/ በመስኮት እያንጋጠጥኩ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ለማየት መንጠራራት ያዝኩ፡፡
አገሪቱ ገነት መሳይ የመጤዎች ከተማ ናት:: በየሄድኩበት የማየው አገሬውን ሳይሆን መጤውን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሰው እንዲህ ተከባብሮ እንዴት ሊኖር እንደቻለ ግራ የገባኝ እኔ ብቻ ከሆንኩ ይገርመኛል፡፡ ህንዶች፣ ፓኪስታኖችና ፊሊፒኖች ይበዛሉ፡፡ በተለይ በየሰው መሃል በሳይክል የሚሽሎከለኩ ህንዶች ትንሽ ቢያጨናንቁኝም ከተማው የነጻነትና የሰላም ከተማ ነው፡፡ ብቻዎን 24 ሰዓት በፈለጉበት ቦታ ቢንቀሳቀሱ ዞር ብሎ የሚያዎት የለም፤ ሰላም ይሰማዎታል፡፡ ለአገርዎና ለከተማዎ ይመኙታል፡፡
ሸገር በየሰልፉ ላይ የሚተሻሸኝና ሲደብረው ክንዱን እላዬ ላይ እያስደገፈ፣ ሲሻው በማያገባኝ ወሬ ልቤን የሚያደክመኝ የሀገሬን ሰልፈኛ ስንቴ አሰብኩት፡፡ እዚህ የተነካኩ ሲመስልዎ ቀድመው ይቅርታ መጠየቅ አለብዎ፡፡ ሰዎች የሌሎችን ግላዊ ህይወት በጣም ያከብራሉ:: እንደኔው አገር ሰው የኤቲኤም ሰልፍ የሚጠብቁ ሰዎች ከተጠቃሚው በሜትሮች ርቀው ይቆማሉ፡፡ ይህንን ሳይ በአናቴ ላይ አሻግሮ ማሽኑ ላይ የምሰራውን የሚመለከትና ሲፈልግ ‹‹ፓስ ወርዱን ድጋሚ አስገባ ትክክል አይደለም … ካንስል በለው … ›› የሚል የአገሬ ሰው (ከኋላዬ የተሰለፈ ተረኛ) ትዝ ብሎኝ ፈገግ ሳልል አልቀረሁም፡፡
***
ባቡሩ ውስጥ ብዙ ሰው ስላልነበረ በሩ አካባቢ ከሚገኝ ወንበር ላይ ተቀምጫለሁ:: ብዙም የቆመ ሰው አይታየኝም፡፡ በመሃል ከአሁኑ ፌርማታ የተሳፈሩ ፀአዳ የለበሱ ጢማም ሽማግሌ፣ አጠገቤ ያለውን ብረት ይዘው ቆሙ:: ትንሽ ዞር ዞር እያልኩ የተቀመጡ ሰዎችን አስተዋልኩ፡፡ ብዙዎቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ግማሾቹ በባቡሩ ዋይፋይ ኢንተርኔት የሚጠቀሙ፣ ጥቂቶቹ ኢርፎን ጆሮአቸው ላይ ሰክተው የሚያዳምጡ (ሙዚቃ ወይም ሌላ ነገር… ምን አውቃለሁ!) በመሆናቸው በየራሳቸው ተጠምደዋል፡፡ ለሽማግሌው ቦታ ለቀቅኩና እንዲቀመጡ ጋበዝኳቸው፡፡ ፈገግታ ካሳዩኝ በኋላ ተቀመጡና ጎብጠው በማጎንበስ አመሰገኑኝ፡፡ /እናም በደስታም በሃፍረትም ዞር ዞር እያልኩ የሚያየኝ ሰው እንዳለ ብመለከት አንድም ሰው እያየኝ አልነበረም፡፡ተመስገን፡፡/
ጥቂት ቆይቶ ሽማግሌው ያወጉኝ ጀመር፡፡
‹‹ግን ከየት አገር ነህ? በርግጥ አፍሪካዊ መሰልከኝ!!››
‹‹አልተሳሳቱም ከኢትዮጵያ ነኝ!…  እርስዎስ?››
‹‹እኔ ከአፍጋኒስታን ነኝ፡፡ ከአገሬ ከወጣሁ አስር አመት ሊሞላኝ ነው፡፡ እዚህ ሶስት አመቴ ነው፡፡ ምግብ ቤት አስተናግዳለሁ፡፡ አንተ ምን ትሰራለህ? (ስራህ ምንድነው?)››
‹‹እኔ እንኳ የመጣሁት ለስራ ነው፡፡ ጥቂት ቀናት ቆይቼ እመለሳለሁ፡፡››
በመስኮት ወደ ውጪ ትንሽ ካተኮሩ በኋላ በረጅሙ ተነፈሱና፤  … ‹‹…ዕድለኛ ነህ! ወደ አገርህ ትመለሳለህ፡፡ እኔ አገር አልቦነት ከተሰማኝ ቆየ፡፡ ዘመዶቼን፣ አገሬንና ህዝቤን (ህዝቦቼን!) ካየሁ ቆየሁ!…›› እጀ ጠባብ በመሰለው የሹራብ እጄታቸው፣ በምንጭሮቻቸው ጫፍ ላይ ያጤዙ ዘለላዎችን ጠራረጉና ፈገግ አሉ፡፡
‹‹አየህ አገር መጠለያ እንጂ የራሱን ዜጎች አሳዳጅ ሲሆን ዓለም ይጨልማል፡፡ የራስህ ሰፊ መሬት አልበቃ ብሎህ እርስ በርስ ስትጫረስ፣ እንደዚህ በጠባቧ መሬት ላይ እጁን ዘርግቶ ተቀብሎ የሚያኖር አለም ባይኖር ኖሮ፣ ምን እንሆን ነበር?! መቼም አላህ ይመስገን እየሰራሁ እኖራለሁ!…››
‹‹… ቤተሰብ አለዎት?…››
የፈገግታና የሀዘን ማኪያቶ ፊታቸው ላይ ሲቀላቀል ይታወቃል፡፡ በትኩረት እያስተዋሉኝ… ‹‹…ቆንጆ ሚስትና ስድስት ልጆች ነበሩኝ፡፡ አንድ ቀን በትራንስፖርት አውቶብስ ላይ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ አለቁ፡፡ እኔ ትምህርት ቤት እያስተማርኩ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሒሳብ አስተማሪ ነበርኩ፡፡ የዚያን ዕለት ሁለት ልጆቼ ሲተርፉ (እነሱ ትምህርት ቤታቸው ነበሩ!) ሌሎቹ ቤተሰቦቼ በሙሉ ወደ ምንምነት ተበታተኑ፤ ሁለቱ ጎረምሳ ልጆቼ ደግሞ ወደ ፓኪስታን ጠፉ፡፡ እኔም ተሰደድኩ፡፡…››
በዝምታ ውስጥ፣ በስደትና በሰው ልጅ ጥላቻ የሚቆስሉ ህዝቦች ታወሱኝ፡፡ የምወዳት አገሬን’ኳ ስንቱን ህዝብ ከኖረበት ቤት እየነቀለች ደም እምባ ታራጨው አይደለምን፡፡
‹‹…አየህ አሁን አባቶች እንደሚሉት፤ ከትልቅ ዛፍ ላይ ተበጥሳ እንደወደቀች ቅጠልነት ነው የሚሰማኝ፡፡ ቅጠሏ ምን ሊሰማት ይችላል! ታማርራለች ወይስ ታለቅሳለች፡፡ ታዝናለች ወይስ ትፅናናለች፡፡ አሁን እኔ እንደዚያ ነኝ:: ድሮ ሁሉን የጨበጥኩት የመሰለኝ ወቅት ነበር፡፡ ደስተኛ ህይወት ነበረኝ፡፡ ከተራራው ማዶ የሚጨስ ጭስ እኛ መንደር የሚደርስ አይመስለኝም ነበር፡፡ በመንደራችን አደባባይ የተሰቀሉ የሌላ ጎሳ አባላት ሰቆቃ እንደ ራሳችን አልሰማ ብሎን በማዘን ብቻ አልፈን ነበር:: ጥላቻና ዘረኝነት ግን እንደማይድን ቁስል ነው፡፡ የደረቀ ሲመስልህ እንደገና እየነፈረቀ ያስለቅስሃል:: እግርህ ጣት ላይ የወጣች ቁስል ሃይለኛ ራስ ምታት ታስከትላለች አይደል!…››
‹‹እውነት ነው… !›› የሚል ቃል አወጣሁ፡፡
‹‹እናንተ አገር ሰላም ነውን?! ›› ሲሉ ጠየቁኝ::
‹‹…ሰላምም ነው ሰላምም አይደለም! …›› ስል ተነፈስኩ፡፡ አገሬ ምን ላይ ነበረች? …. ሳስበው አገሬ በተስፋ ክር ላይ ተንጠልጥላለች፡፡ ክሩን ደግሞ ለመበጠስ የምንታገል ብዙዎች ነን፡፡ በአለም ላይ የተለዩና የተመረጡ ህዝቦች የሉምና እኛም የሌሎቹ ዕጣ ፈንታ ውስጥ ስንወድቅ በህይወት እያለሁ እንዳላይ ፀለይኩ፡፡
አገር በሽማግሌዎችና በጎልማሶች አመራር፣ በወጣቶች ሸክም ስር ትኖራለች፡፡ ሸክሙን እንዲወጡትና እንዲኮሩበት የሚያደርጋቸው የታላላቆች ትምህርትና ተስፋ ነው፡፡ ወጣቶች በወደፊታቸው ውስጥ የመኖር ተስፋ ካላዩና በፍቅር ካላደጉ ሸክሙን አሽቀንጥረው ይጥላሉ:: አገር ትፈርሳለች፡፡ የአገራችን አባቶችና አያቶች ደግሞ መቆጣትና መምራት አቁመዋል:: ስለዚህ ወጣቶች በፍቅር አላደጉም:: መካሪም የላቸውም፡፡ በጥላቻ ተኮትኩተዋልና አገራቸውን አሽቀንጥረው ለመጣል ቸኩለዋል፡፡  
‹‹…ያቺ ያልኩህ ከዛፍ የወደቀች ቅጠል ምን ሊሰማት ይችላል፡፡ ማዘን አይገባትም፡፡ ለዘመናት የተሸከማት ዛፍም አያዝንም፣ ቅጠሊቱም አታዝንም፡፡ በርግጥ አልተሸከማትምና፡፡ በእርሷ ህይወት አግኝቶ ነበርና ሙሉ ነበር፡፡ ቅጠል ተዘርግታ በምትወስደው ፀሃይ ነበር ዛፍ ዛፍ የሚሆነው፡፡ ዛፍም አይሸከማትም፤ እርሷም የራሷን ሃላፊነት ትወጣለች፡፡ ቀጥሎ መውደቅ ሲመጣ ሌላኛው የህይወት መንገድ ማለት ነውና የመጣውን በደስታ መቀበል ነው፡፡ በዚያው መጓዝ፡፡ መንሳፈፍ፡፡
“ቤተሰቦቼ ያለቁ ሰሞን ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ነበር፡፡ በኋላ በተስፋ መቁረጥ መሃል ሆኜ አንድ ማለዳ እግሬ እንደመራኝ ከቀየዬ ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ ከአመታት በኋላ ራሴን እዚህ አገኘሁት፡፡ አየህ እዚህ ከ200 አገራት በላይ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ይኖራሉ፤ ተከባብረውና ተቻችለው፡፡ የአገሪቱ ዜጎች ከሃያ በመቶ ያንሳሉ ግን እስካሁን ቅሬታ የላቸውም፡፡ አላህ የተመሰገነ ይሁን ሰርተን እንገባለን፡፡ የወደፊቱን አናውቅም፤ አሁን ግን ብዙ አለም ያሳደዳቸው ህዝቦችን ጨምሮ ሚሊዮኖች ውለው ይገቡባታል፡፡ ጥሩና ተስፋ ያለው መሪ አላቸውና ለሁሉ የሚበቃ አገር ሰርተዋል፡፡››
‹‹እኛም ጥሩ መሪ ነበረን … ግን … ሰላም የለም፡፡››
‹‹ጥሩ መሪ ካለህ ሰላም መኖር አለበት፡፡ ጥሩ መሪ ማለት የሚወደድና የሚፈራ መሆን አለበት፡፡››
‹‹የሚወደድ መሪ አለን፣ የሚፈራ ግን አልመሰለኝም፡፡››
ጣቢያ አስተዋዋቂው /አናውንሰሩ/ የመድረሻዬን ድምፅ ሲናገር እየሰማሁ ነበር፡፡
‹‹Al Mahatta Al Qadima Heya – Al Rigga! ….. The next station is – Al Rigga!…›› .. /የሚቀጥለው ጣቢያ - አል ሪጋ!/ ወደ መውረጃዬ እየደረስኩ ቢሆንም የሰውዬውን ወግ መቋጨት አላስቻለኝም፡፡ ዝም ብዬ ማዳመጥ ፈለግሁ፡፡
ደብዘዝ ባለ  እይታ እያጤኑኝ፤ ‹‹መሪ መፈራት አለበት፡፡ አንድ ተረት አለ፡፡ በአንድ ወቅት በርሃብ የተነሳ እንስሳት አልቀው አንበሳ፣ ነብርና አህያ ብቻ ቀርተው ነበር አሉ፡፡ እናም በጣም በመስማማትና በመወያየት ኖሩ፡፡ ግና አብረህ የምትኖራቸውን ማጤን ይገባሃል:: ችግር ሲመጣ በየት እንደምትወጣ ለማወቅ ይጠቅምሃል፡፡ አንዴ በጣም በመራባቸው የተነሳ ተቀምጠው ሲወያዩ አንበሳ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ ‹ይህንን ያህል ስቃይ እየደረሰብን ያለው ሃጢያት ሰርተን መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ በአምላካችን ፊት በአደባባይ እንናዘዝና ይቅርታ እንጠይቅ::› …በዚሁ ሃሳብ ተስማምተው መናዘዝ ጀመሩ አሉ፡፡
አንበሳ፤ ‹‹ሃጢያተኛው እኔ ሳልሆን አልቀርም፤ አንድ ጊዜ አንድ ወደል ወይፈን አገኘሁና ወገቡን ሰብሬ በላሁት፡፡››
ሁለቱም እንሰሶች ተያዩ፡፡ አንበሳ የሚያከብሩት ብቻ ሳይሆን የሚፈሩትም ነበርና እየተሽቀዳደሙ ይመልስሉት ጀመር::  ‹‹አንተማ ያደረከው ሃጢያት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር እንድታደርግ የፈቀደውን ነው፡፡›› ሲሉ ተስማሙ::
ቀጥሎ ነብር ተናዘዘ፤ ‹‹ አንድ ጊዜ ከአንድ ገበሬ የፍየል መንጋ ውስጥ አንዲቱን ሰርቄ በልቻለሁ፤ ሃጢያተኛው እኔ ሳልሆን አልቀርም::››
ሁለቱ ተያዩ፤ ነብር ፈጣን አዳኝ ነው፡፡ እናም በቀስታ ሁለቱም ተናገሩ፤ ‹‹እንዲያውም ጨምረህ መብላት ነበረብህ፡፡ ትክክለኛ ነህ፡፡››
በመጨረሻም አህያ ተናገረ፤ ‹‹አንድ ጊዜ ከነጋዴ ሰውዬ ጋር መንገድ ስንጓዝ፣ ሰውየው ወዳጁን አግኝቶ ቆሞ ሲያወራ፣ ወደ መንገዱ ጠርዝ ወጣ ብዬ አንዲት ጭብጥ ሳር ነጭቼ በልቻለሁ፡፡ ሃጢያቱ ይህ ሣይሆን አይቀርም፡፡››
ሁለቱ በፀጥታ ተያዩ፡፡ አህያን አይፈሩትም ነበርና ወዲያውኑ ይዘነጣጥሉት ጀመር፡፡ ሃጢያቱ አብረህ የምትኖራቸውን አለማወቅ ነው፡፡ አየህ ለዚህ ነው መከበርና መወደድ ብቻ ሳይሆን መፈራትም ወሳኝ የሚሆንበት ጊዜ የሚኖረው፡፡ ጉልበተኞች በሚበቅሉበት አገር፤ ጉልበተኛና የሚፈራ መሪም ያስፈልጋል:: የሚያታልል ሳይሆን የሚፈራ፣ የሚወደድና የሚከበር፡፡ ፍቅርን ለሚሹ ፍቅር የሚሰጥ፣ ጉልበት ሲያስፈልግ የሚደቁስና የሚፈራ መሪ፡፡ አሁን ግን እኔን ብትጠይቀኝ አላህ ሰው ሳይሆን ወንዝ አድርጎ ቢፈጥረኝ እመርጥ ነበር፡፡››
የቀረችውን ፌርማታ በዝምታ ተረቷን አላመጥኳት፡፡
***
አል ሪጋ ስንደርስ ሁለታችንም ወረድን:: ሰውየው የሚሰሩት ከባቡር ጣቢያው ወጣ ብለን መቶ ሜትር ሳንጓዝ በፊት በሚገኝ ካፌ ነበርና ቁጭ ብዬ ከካፊያቸው ተስተናገድኩ፡፡ ደስ የሚል የአፍጋኒስታን የምጣድ ቂጣ በወጥ:: እናም አገሬ ሳልሄድ በፊት ተመልሼ መጥቼ እንደምጎበኛቸው ቃል ገብቼ ወጣሁ፡፡
የቀትሩ ሙቀት ከአስፋልቱ ላይ ሲነጥር ሚራጁ እንደ እሳት ነበልባል ይርገበገብ ነበር:: አቤት ጌታዬ ሆይ ምርጥ አገር ሰጥተኸን ስታበቃ፣ እኛ ግን በሰው እሳት የሆነ አገር ቅናት ያንገበግበናልሳ፡፡ አስፋልቱን ለመሻገር አረንጓዴ እስኪበራ ድረስ የጠበኳት ጥቂት ሰከንድ እንደ ዝንተ ዓለም ረዘመችብኝ፡፡ የአዲስ አበባ ፀሃይ አስመረረን ስንል፣ እዚህ ያለው ደግሞ እንደ ጦር አናት የሚበሳ ነው፡፡ ኸረ ተመስገን በል፣ የሰው አገር ገነት ለማየት ስናንጋጥጥ፣ የራሳችንን ረስተነው ኖሯል፡፡ ግንባሬ ላይ መዳፌን እንደደገንኩ የጋሽ ይርጋ ዱባለን ዘፈን መዝፈን፣ ከአገሬም መገኘት አማረኝ፤
... የሰው የለው ሞኝ የሰው የለው ሞኝ
ካገሩ ከቦታው ከስፍራው ሲገኝ ....

Read 854 times