Saturday, 27 April 2019 10:09

ልደት፣ ህይወት፣ ሞት፣ ትንሣኤ (The Aztec. - Ancient Legacy, Modern Pride.)

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

ልደት  -  አምስቱ ዘመናት
‹‹በመጀመሪያ ሰው ትቢያ ነበረ፡፡›› ብሎ ይጀምራል፤ የአዝቴኮች የስነ ፍጥረት ድርሣን:: የሰው ልጅም ዛሬ ከደረስንበት አምስተኛው የፀሐይ ዘመን በፊት አራት ጊዜ ተፈጥሯል:: በውኃ፣ መሬት፣ ነፋስና እሳት ፈረቃ:: በመጀመሪያው የፀሐይ ዘመን ከአመድ የተፈጠሩትን ሰዎች ውኃ አንሳፍፎ ወስዶ አሣ አደረጋቸው፡፡ በሁለተኛው የፀሐይ ዘመን የተፈጠሩቱ ግዙፋን ቢሆኑም ውሽልሽል ነበሩና የሌት አናብርት እንዳይቀራመቷቸው በፍርሀት እየተንዘፈዘፉ፣ ገና ለራሳቸው መቆም ሳይችሉ፣ ሌሎችን ቀስ ብላችሁ ተራመዱ! እንዳትወድቁ! እያሉ ሲያስጠነቅቁ፣ ሁሉም እየተፈጠፈጡ አለቁ:: በሦስተኛው የፀሐይ ዘመን የሚዘንበው እሳት ነበርና ሰዎቹ ሁሉ ተቃጥለው እርር ኩምትር ብለው ከሰሙ:: የአራተኛው የፀሐይ ዘመን ሰዎች ደግሞ ነፋስ ሲጠራርጋቸው ወደ ጦጣነት ተለወጡ፤ ወደ ተራራም ሸሹ፡፡ በመጨረሻም፣ ቸርነቱ ለማይነጥፍበት አምላካችን ኩዬትዛልኮትል ምስጋና ይሁንና፤ በአምስተኛው የፀሐይ ዘመን የአራቱን ነባር ዘመናት ቅሪቶች አሰባስቦ እኛን ፈጠረ፤ እነሆ መቁኑናችንን በቆሎ እየመገበም ያኖረናል፡፡
ህይወት  -  እባብና ሰው
በ13ኛው ክፍለ ዘመን ገደማ ሦስተኛው የሜክሲኮያዊያን ታላቅ ስልጣኔ ከፍ ብሎ ወጣ:: አዝቴኮች ዋና መዲናቸው ቴኖቺቲላንን፣ ያሁኒቱ ሜክሲኮ ከተማ በቆመችበት የባህር ዳርቻ ላይ ቆረቆሩ፡፡ ራሳቸውን ሜክሲካ ብለው የሚጠሩት አዝቴኮች ከቀድሞ ቀያቸው ወደ መካከለኛዋ ሜክሲኮ በዘላንነት ነበር የመጡት:: ወዲያውም ባስደናቂ ሁኔታ ዙሪያ ገባውን ለመቆጣጠርና የገዢነቱን እርካብ ለመቆናጠጥ በቁ፡፡ በተለይ በእንጨት ስራ፣ ሽመና ሙያና አንድ ጊዜ ብቻ ይመረት የነበረውን እርሻ መስኖ ተጠቅመው፣ በአመት አራት ጊዜ የበቆሎ ምርት በገፍ ለማከማቸት ቻሉ:: ጥብቅ በሆነው ማህበራዊ መስተጋብራቸው ተጠቅመውም፣ የራሳቸውን ዘር ወደ ከፍታ አመጠቁት፡፡ ፀጋና በረከታቸው ለሌላውም እስኪተርፍ በእድገትና ስልጣኔ ተመነደጉ:: አይበገሬ ጦረኝነታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው አይካድም፡፡ እንጂ ቀድመው በምድሪቱ ሰፍረው የነበሩቱ ነዋሪዎች አዝቴኮችን ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› ብለው ለመቀበል ከቶም ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ በወረርሽኝ እንዲጠፉ ሴራ ደግሰውላቸው ብዙዎች ረግፈው የተረፉት ቀጠሉ፡፡ በየደረሱበት ከጥፋት እያዳነ ለሚመራቸው አምላካቸው ሁዪትዚሎፖትቺሊ ቤተ መቅደስ እየገነቡና መስዋእት እየገበሩ፣ እየተጠናከሩ፣ አይነኬ ሆኑ፡፡ የሜክሲኮያዊያኑ ሀገረ ገዢ ካልኋካን በትህትና ላቀረቡት የሰፈራ ጥያቄ የተሰጣቸው ምላሽም በሴራ ጥንስስ የተጠመቀ ነበር፡፡ ገዢው ለ‹‹መጤ›› ተብዬዎቹ መስማማቱን ባደባባይ ካጸደቀላቸው በኋላ፤ ይሰፍሩበት ዘንድ የመራቸው ስፍራ ሆን ተብሎ የተመረጠ መርዛማ እባቦች የታጨቁበትን ቦታ ነበረ፡፡ ነቄዎቹ አዝቴኮች ምን አደረጉ ታዲያ፤ ሰፈሩበት፤ እናም እባቦቹን እየቀቀሉና እየጠበሱ ቅርጥፍጥፍ አድርገው በሏቸው፡፡ ያን ጊዜ ‹‹ነባር ነን›› ባዮቹ ለ‹‹መጤ›› ዎቹ እጅ ሰጡ፡፡ አዝቴኮች ንጉሳቸውን ቀብተው አነገሡ፡፡
በአዝቴክ ጥንታዊ አምልኮ መሰረት፤ እያንዳንዱ አዲስ ንጉሥ በአንዲስ ተራራ ላይ በንግሥና ሲቀባ፣ መለመለ እርቃኑን ዘይት ተነክሮ፣ መላ አካሉን ጥፍሮቹ፣ ሽፋሽፍቱና ከብብቱ የሚፈልቀው ላብ ሁሉ በወርቅ ዱቄት ተደምድሞ እያብረቀረቀ፣ ወደ ጓታቪያ ሀይቅ ዳርቻ ወርዶ ለአምላካቸው ካስለመዱት ግብሩ ጋር የወርቅና ጌጣጌጦች ገጸ በረከት አቅርቦ ቃለ መሀላ ይፈጽማል፡፡ ለአምላካቸው የሚገብሩት ለመስዋዕትነት ከቀረበ ሰው ደረት ተቦትርፎ የሚወጣ ህያው ልብ ነበር፡፡
ሞት - ‹‹ከሞቱ ያሟሟቱ››
በአዝቴኮች ዘንድ ሰው ከሞተ በኋላ በህይወቱ ሳለ ለሌላው ባደረገው ክፉና በጎ ምግባሩ አይመዘንም:: በእንዴት መልኩ ሞተ በሚለው እንጂ:: ለምሳሌ ወንጌል ‹‹ጌታ ከሞት በኋላ በግራና በቀኝ ፍየልና በግ አድርጎ አቁሞ ‹ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ተጠምቼ አጠትታችሁኛል፣ ታስሬ ጠይቃችሁኛልን› ሲል፤ ‹ጌታ ሆይ አንተ መች ተርበህ፣ ተጠምተህ፣ ታስረህ ታውቅና› ሲሉት፤ ‹ከነዚህ ከታናናሾቼ ላንዱ ያደረጋችሁት ለኔ እንዳደረጋችሁት ነው› ይላል፡፡ በአዝቴኮች ዘንድ ግን የአንድ ሰው እጣ ፈንታ በራሱ በሰውየው እጅ ነው የሚል ጽኑ ህግ አለ፡፡ በውርደት ወይስ በክብር አለፈ የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ ለአምላክ ግብር ለመሆን ራሱን ወደ መሰዊያው እሳት ወርውሮ ቢያቃጥል ክብር ነው፡፡ የክብር ሞት ሁሉ ሀገርን ከማዳን፣ የውርደት ሞት ሀገርን ከመክዳት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በዚህ ቁርጠኛ የሀገር ወዳድነት ገድልም ነው ሉአላዊነታቸውን አስጠብቀው መዝለቅ የቻሉት (ምናልባት)፡፡ የመጨረሻው ንጉሣቸው ግን ለዚህ አዝቴካዊ ክብር አልታደለም ... ‹እምጵፅ!›
አዝቴኮች የገናናነትን ጫፍ በነኩበት በ1519 ገደማ፡ በጀብደኛው ሄርማን ኮርቴዝ የተመሩ 500 የስፓኒሽ ወታደሮች ድንገት አዝቴኮችን ወረሩ:: ንጉሡ በብርሀን ፍጥነት በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮቹን ጠርቶ ማሰለፍና መከላከል ይቻለው ነበር፡፡ ንጉሥ ሞንቴዙማ ግን ህዝቡን ለማዳን አንድም ሙከራ ከማድረግ ታቅቦ ፉዞ ሆነ:: ምክንያቱም በጦር አዝማቹ ኮርቴዝ በሰው ተመስሎ ሊያጠፋኝ የመጣው ራሱ አምላክ ኩዬትዛልኮትል ነው ብሎ ራሱን አሳምኖና ያለቅጥ ተንጰርጵሮ ነበር፡፡ ስፔንያርድስ በቀላሉ አዝቴኮችን መማረክና ምድሪቱን መቆጣጠር ቻሉ፡፡ (ያገር ሰው ወገኔ በጨነቀው ጊዜ ‹እንዲህ ያደረግክልኝ እንደሁ ህይወትህን/ነፍስህን እንደሰጠኸኝ ነው እምቆጥረው!› ማለቱን ስናስብ... ‹ ምናለ አምላኩስ መጣ ብሎ ካመነ ያስለመዱትን ግብሩን ልቡን አውጥቶ ሰጥቶ፣ እሱ ሞቶ ሌላውን ቢያድን?› ወይ ‹ኤዲያ! እንደ አጤ ቴዎድሮስ ራሱን ቢያጠፋና በክብር ቢሰናበት ኖሮስ?› ይል ይሆናል፤ አዎን...እንግዲህ አዝቴኮች ‹እጣ ፈንታ/ክብርና ውርደት በራሱ በሰውየው እጅ ነው!› ማለታቸው ይህን ይሆን (ምናልባት....)? እነሆ አሁንም ‹‹ነባሮቹ ለመጤዎቹ›› ስፍራቸውን ሲለቅቁ ያሳየናል፤ የህይወት ዑደት፡፡
ትንሣኤ -  ነፍስ ወ ውርስ ቅርስ
በአዝቴኮች ‹‹ትንሣኤ ዘ ሙታን›› ድርሣን፤ የአንድ አዝቴካዊ ለአማልእክቱ ግብር መሆን የአዝቴኮችን ህይወት የማስቀጠል በጎ ምግባር ነውና ለነፍሱ ዘላለማዊ ብርሀንነት፤ ፀሐይ ወይ ጨረቃነትን ያጎናጽፈዋል፣ እንደ ደሙ መጠን፡፡ የመሰዊያው እሳት የሚቃጠል ስጋ እንዳያልቅበት ጆሮውን ቆርጦ ቢወረውርም እንዴት ያለ መታደል ነው፡፡ ለአምላክ የሚሰዋው የደም ግብር ነዋ በየሄዱበት ለሚገጥማቸው ጦር በጨለማ እንዳይደናበሩ ብርሀን በመሆን የሚነድደው፡፡ ልክ ኩራዝ ለመብራት ጋዝ እንደሚያሻው ሁሉ ለአምላክ በሚገበረው የደም ነዳጅ ነው በሌት የጨረቃ፣ በቀን የፀሐይ ብርሀን ለመቸር የሚያስችላቸው:: የጨረቃና ፀሐይ ብርሀን መድመቅና መፍዘዝ ልዩነቱም ከደሙ ግብር/‹‹ላምባው›› ማነስና መብቃት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡›› ብለው ያምናሉ አዝቴኮች፡፡ (ለፀሐይ በነዳጅነት ተሰውቶ ራሱ ፀሐይ ለመሆን ደሙን ለማንዘቅዠቅ፣ ደረቱን አስነድሎ ልቡን ለመገበር በጉጉት እሚቁለጨለጭ ወፈ ሰማይ አዝቴኬ የወረፋ ግፊያ . . .!)
የዚህ ዘመን የምድሪቱ ነዋሪዎች የቀደምት ስልጣኔያቸውን የብርሀን ሰበዝ ለመምዘዝ የኋላቸውን ታሪክ መጎድፈሩን ተያይዘውታል:: ባለንበት ዘመን በመንግሥት ደረጃ የተቀረፀ ነባሩን ስልጣኔ የማንቃት ማህበራዊ እንቅስቃሴ ተቀጣጥሏል፡፡ ይኸው ሜክሲኮያዊያን ከነባሩ ሀገር በቀል ቅርሳቸው በመነሳት በወል የሀገራዊ አርበኝነት የቀደመውን የአዝቴክ አሻራ በዘመናዊው አለም ለማስቀጠል (living tribute to México’s noble indigenous past) በዙሪያቸው ካሉ ህዝቦች ሁሉ በጋራ ለእድገት የሚተጉበት መርሐ ግብር የተነደፈው Realism and Utopianism በተሰኙ ሁለት አበይት ተያያዥ ንኡስ ስያሜዎች ስር ነው፡፡ Realism ቁጥራቸው የሚበዙትን ህንዳዊያንና ሌሎችንም ወደ ሜክሲኮ የሚመጡን ህዝቦች ሁሉ ከመገፋፋት ይልቅ በእኩልነት የመኖር መብት የሚያረጋግጥና ‹‹ነባር፤ መጤ›› ሳይል የወል ሁኔታዎችን በጋራ የሚያመቻች ሲሆን፤ Utopianism ደግሞ ነባሩን የአዝቴክ ስልጣኔ ውርስና ቅርስ ወደዚህ ዘመን ማሸጋገር ነው:: በባህል፡ ኢኮኖሚ፡ ፖለቲካ፡ ቋንቋና የተተዉ የተረሱትን ጥንታዊ የአዝቴክ አምልኮአዊ ክብረ በአላትን ዳግም ማስቀጠልንም ያቀደ ነው፡፡ ... እንግዲህ ጠፍተው ካልቀሩትና ካሸለቡበት ከተቀሰቀሱቱ ካንሰራሩቱ ከጥንታዊ የግሪክ ስልጣኔና መሰሎቹ አንዱ ሊሆን የትንሣኤ እድል አገኘ ማለት ነው፤ጥንታዊው አዝቴክ፡፡ The Modern Aztec Legacy.
በተለይ Utopianism ቃሉ ካገራችን Ethiopia ጋር መመሳሰሉ እናም አንዳንድ ምሑራንም ተወራራሽ-ተሰላሳይነቱንም ጭምር በማስረዳት ላይ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለውና፤ እንኪያስ የኛዋስ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ትንሣኤ መች ይሆን...? የሚል ሀሳብ ብቅ ከማለት የሚከለክለው የለም... ትንሣኤው መምጣቱ እንደማይቀር (የራሳችን እጣ ፈንታ ወሳኝ ስንሆን ምናልባት? ‹ነባርና መጤ› መባባል ሲቀር...በቁርጠኝነት ‹‹ልብን›› ለወገን መገበር ሲቻል...ወዘተ.) ተስፋ በማድረግና አለቅጥ መዘግየቱን ግን በጽኑ በመቃተት፣ የባለቅኔውን (ጸገመ) ቁጭት ተውሰን እናንጎራጉራለን . . .
‹‹እሳት አንሆን ወይ አበባ
በህቅ እንቅ ስንባባ
ባከነች ልጅነታችን እየቃተትን ስናነባ፡፡››
ፈጣሪ ሀገራችንን ይባርክ!!

Read 606 times