Saturday, 27 April 2019 10:09

ያሬዳዊው ሥልጣኔ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

ክፍል - ፲፱ ማጠቃለያ
                                                
            ካለፈው ዓመት (ሰኔ፣ 2010 ዓ.ም) ጀምሮ ላለፉት አስር ወራት ‹‹ብህትውናና ዘመናዊነት›› እንዲሁም ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ›› በሚሉ ትልልቅ ርዕሶች ሥር 26 መጣጥፎችን (7 በመጀመሪያው፣ 19 ደግሞ በሁለተኛው ርዕስ ሥር) ሳቀርብ ቆይቻለሁ:: በሁለቱም ርዕሶች ሥር ያቀረብኳቸው ፅሁፎች የሐሳብ ዝምድና ያላቸው ናቸው፡፡
ፅሁፎቹን በመጀመሪያ ያዘጋጀሁት በ2010 ዓ.ም ‹‹Ascetic-Mysticism: Its Cultural Traces and Challenges to the Ethiopian Modernization Projects›› በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ነበር፡፡ ፅሁፉም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ፍልስፍና ትምህርት ክፍል ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ለማስተርስ ዲግሪ መመረቂያ ያዘጋጀሁት ጥናት ነው፡፡ በኋላ ላይ ግን፣ ‹‹ፅሁፎቹ ሙሉ በሙሉ የሀገራችንን ሥልጣኔና የባህል ታሪክ የሚመለከቱ ስለሆነ ለአንባቢ በሚሆን መልኩ ቢዘጋጁ በርካታ ሰዎች በአትኩሮት ሊያነቧቸው ይችላል›› ከሚል ሐሳብ በመነሳት በአማርኛ ተርጉሜ አቅርቤያቸዋለሁ፡፡
ፅሁፎቹ የተዘጋጁበትን የእንግሊዝኛ ርዕስ ‹‹ብህትውናና ተአምራዊነት፡- የባህል አሻራዎቻቸውና በኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ውስጥ የፈጠሩት ተግዳሮት›› በሚል አቻ የአማርኛ ርዕስ መተርጎም እንችላለን:: ለዚህም ነው እስከ ዛሬ ድረስ ባቀረብኳቸው ተከታታይ ፅሁፎች ውስጥ ሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ሲከተሉን የነበሩት - ብህትውና፣ ተአምራዊነት እና ዘመናዊነት፤ በተለይም ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ፡፡
ፅሁፎቹን በአማርኛ እየተረጎምኩ በማቀርብበት ወቅት ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የባህል ምንጮቹ ብህትውናና ተአምራዊነት ከሆኑ፣ ኪነ ጥበቡስ ከየት ነው የመጣው?›› የሚል ጥያቄ መጣብኝ፡፡ ፅሁፎቹ ውስጥ ‹‹ሠሞነ ሕማማት›› የሚል ሐሳብ ያስገባሁት በዚህ ወቅት ነበር፡፡ በዚህም፣ ባጠቃላይ ፅሁፎቹ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የዲበ አካል፣ የሞራልና የኪነ ጥበብ አምዶች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህም ሦስት አምዶች በቅደም ተከተል ተአምራዊነት፣ ብህትውናና ሠሞነ ሕማማት ናቸው›› የሚል መደምደሚያ አለው፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ አራት ርዕሰ ጉዳዮች (ተአምራዊነት፣ ብህትውና፣ ሠሞነ ሕማማትና ዘመናዊነት) የፅሁፎቹ ዋና የማስተንተኛ ፅንሰ ሐሳቦች ሆነው ቢያገለግሉም፣ በውስጡ ግን ፅሁፎቹ በይነ ዲሲፕሊናዊ የሆነ አቀራረብ የሚታይባቸው ናቸው:: በዚህም፣ ፅሁፎቹ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የባህልና የሥነ መለኮት ሐሳቦችን በአንድነት አጣምረው የያዙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡  
ፅሁፎቹ፣ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ በመንፈስ መንገድ የተገኘ ነው›› በማለት ቀንጭቦ የሰጠንን ሐሳብ ለማብራራት የሚሞክሩ ናቸው፡፡ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በሚለው መፅሐፉ ዶ/ር እጓለ ‹‹የሰው ልጅ ህይወት ሁለት መንገዶች አሉት - አንድም የመንፈስ፣ ሌላም የህሊና:: ያሬዳዊው ሥልጣኔ የመጀመሪያውን መንገድ መርጧል›› ይላል (2003፡ 64)፡፡
ሆኖም ግን፣ ይህ የመንፈስ መንገድ እንዴት ያለ ነው? አነሳሱና ዕድገቱ ምን ይመስላል? ምን ዓይነት ባህሪዎችና ይዘቶች አሉት? ታሪካዊና ባህላዊ ዕድገቱ፣ አሻራዎቹስ እንዴት ያሉ ናቸው? ለሚሉት ጥያቄዎች ዶ/ር እጓለ ከእሱ በኋላ ለሚመጣው ትውልድ የቤት ሥራ ሰጥቶን ነው የሄደው፡፡ እነዚህ ተከታታይ ፅሁፎችም ይሄንን የቤት ሥራ ለመስራት የሞከሩ ናቸው፡፡
ዶ/ር እጓለ እንደሚለው፤ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ ለብዙ ዘመናት ብቻውን ዘግቶ በኖረበት ጊዜ ከገዛ መንፈሱ በተገኙት የሥልጣኔ ሐብታት ተደስቶና ረክቶ ሌላ መኖሩን ባለማወቅ የራሱን የመጨረሻ አድርጎ ኖሯል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ግን የሌላ ህዝብ (የምዕራባውያን) የሥልጣኔ መንፈስ ገባበት›› (2003፡ 77)፡፡ የኢትዮጵያ ነገስታት የሥልጣኔ ንፅፅር ውስጥ መግባት የጀመሩት በዚህ ወቅት ነበር:: ይሄም የንፅፅር ሐሳብ አፄ ቴዎድሮስ ላይ አደረና ‹‹ኢትዮጵያን ማዘመን›› የሚለውን የዘመናዊነት ፕሮጀክት ወለደ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ እስኪመጡ ድረስ ያለው ‹‹የያሬዳዊው ሥልጣኔ›› ታሪክ ‹‹ተአምራዊነት፣ ብህትውናና ሠሞነ ሕማማት›› በሚሉት ሦስት ፅንሰ ሐሳቦች የሚተነተን ነው፡፡ ከ19ኛው ክ/ዘ አጋማሽ ጀምሮ ግን የያሬዳዊውን ሥልጣኔ የወደፊት የታሪክ ጉዞ በአራተኛነት የሚወስን ሌላ አዲስ መስተፃርር ከውጭ ሰርጎ ገባ - ‹‹ዘመናዊነት››፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ከ19ኛው ክ/ዘ አጋማሽ ጀምሮ ያለው የሀገራችን ታሪክ ያሬዳዊው ሥልጣኔ (ተአምራዊነትና ብህትውና) ከምዕራባዊው የዘመናዊነት ሐሳብ ጋር በሚያደርገው መስተጋብር የሚወሰን ሆነ:: ከክፍል-12 ጀምሮ ያቀረብኳቸው ፅሁፎች ይሄንን የታሪክ ዳይናሚክስ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ያሬዳዊው ሥልጣኔ እንደዚህ ዓይነት የታሪክ ዳይናሚክስ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ያሳለፈው ታሪክ ልሙጥና ቀጥ ያለ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ምንም ዓይነት ጠንካራ መስተፃርር ከውጭም ሆነ ከውስጥ ሳያጋጥመው 1450 ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ይህ ቀጥ ያለ የታሪክ ጉዞ ሥሩ የሚመዘዘው ደግሞ ከጥንታዊ ግሪክ ፍልስፍና ነው፣ በተለይም ከፕሌቶ የብህትውና ፍልስፍና፡፡ መቼም የጥንታዊ ግሪክ ፍልስፍናን ያህል በዓለም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረ ሌላ ፍልስፍና ማግኘት ይከብዳል፡፡ የብህትውና አስተምህሯቸው ከግሪክ አልፎ በክርስትና ውስጥ ማህበራዊ ንቅናቄን የፈጠረ ሲሆን፣ ይሄም ንቅናቄ መካከለኛው ምስራቅን አዳርሶ የሰሜኑና የመካከለኛው የሀገራችን ክፍል ላይ የሚገኙ ህዝቦች ላይ እስከ አሁን ድረስ የባህልና የማንነት ምንጭ እስከ መሆን ደርሷል፡፡
በዚህም የተነሳ፣ በሰሜኑና በመካከለኛው የሀገራችን ክፍል ላይ የሚኖረው ህዝብ ፖለቲካው፣ ታሪኩ፣ ባህሉ፣ ሥነ ልቦናው፣ ኪነ ጥበቡ፣ ኪነ ህንፃው …ላይ ሁሉ ይሄንን የተአምራዊነትና የብህትውና አሻራዎች አሁን ድረስ በስፋት እናገኘዋለን፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› እና ‹‹የኢትዮጵያ የዘመናዊነት ፕሮጀክት›› የመጡት ይሄንን ሥር የሰደደ የተአምራዊነትና የብህትውና ባህል በመገዳደር ነው፡፡
ባጠቃላይ፣ በእነዚህ ተከታታይ ፅሁፎች ውስጥ ተአምራዊነትና ብህትውና ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔነት ተሻግረው አካዳሚያዊ ተዋስዖን ተላብሰዋል፡፡ ይሄም መሆኑ በኢትዮጵያ ጥናት ላይ አምስት ዋና ዋና አበርክቶዎች ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው፣ ከ6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ የተፀነሰውን የያሬዳዊውን ሥልጣኔ የሐሳብ ሥረ መሰረቱን (genealogy) ለመረዳት የሚጠቅመን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ከሌላ መዓዘንና መነፅር ለማየት አዲስ ዕድል ይሰጠናል:: ሦስተኛ፣ የኢትዮጵያን ፍልስፍና በይዘት፣ በቀጣይነት፣ በተያያዥነትና በዕድሜ ያበለፅገዋል:: አራተኛ፣ የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች በተደጋጋሚ ያጋጠማቸውን ክሽፈቶች መንስኤውን በተመለከተ እስከ ዛሬ ከነበሩት ምልከታዎች የተለየ አዲስ እይታ ያቀብለናል:: አምስተኛ፣ ፅንሰ ሐሳቡ ለኪነ ጥበባዊ ሒስ ያለው አበርክቶትም ትልቅ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን በኢሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 556 times