Saturday, 27 April 2019 10:33

ትንሿ … ደፋሯ … ውቅያኖስ ጠላቂ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ኢዛቤላ ቴዎድሮስ የ10 ዓመት ታዳጊና የ5ኛ ክፍል የሊሴ ገ/ማርያም ተማሪ ናት፡፡ ገና በ10 ዓመቷ በዓለም ላይ ትንሿ “እስኩባ ዳይቨር” ወይም ውቅያኖስ ጠላቂ ለመሆን በቅታለች፡፡ “ስኩቫ ዳይቪንግ” ምን ማለት ነው ለምትሉ፣ የትኛውም ውሃ ያለበት አገር ከ10 ዓመት በላይ ያለ ሰው የሚያደርገውና በግልፅ ውሃ (ኦፕን ዋተር) ውስጥ ለምሳሌ ጥርት ባሉና ግልፅ በሆኑ ውቅያኖሶች ውስጥ የሚከወን ዋና የሚመስል ግን ከዋና ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ሰዎች በውቅያኖስ ውስጥ ዳይቭ ሲያደርጉ ፍፁም የተለየ ዓለም፣ በምድር ላይ የማይታዩ፣ ህብረ ቀለማትና አሳን ጨምሮ የተለያዩ ፍጥረታት የሚታዩበት ፍፁም ሰላማዊና ከፈጣሪ ጋር የመገናኛ መንገድ ነው ይላሉ - 40 ሜትር ያህል ጥልቀት ዳይቭ ያደረጉ ሰዎች ሲናገሩ፡፡
የዳይቭ ትምህርትና ስልጠና ከ10 ዓመት በታች ስለማይሰጥ፣ ህፃን ኢዛቤላም 10 ዓመት እስኪሞላት ስትጠብቅ መቆየቷን አጫውታኛለች፡፡ ልክ 10ኛ ዓመት የልደት በዓሏን እንዳከበረች ነው የዳይቪንግ ትምህርት ለመማር በዓለም ወደ እውቁና በዚህ ዘርፍ ስልጠና በሚሰጠው “Padi Organization” የተመዘገበችው፡፡ መጀመሪያ የፅሁፍ ፈተና፣ ከዚያም የሶስት ቀን ስልጠና ይሰጣል፡፡
ኢዛቤላም በፖዲ ኦርጋናይዜሽን ተመዝግባ፣ የቃል ፈተና አልፋና ስልጠናዋን አጠናቅቃ፣ በራሷ ብቃት በጅቡቲው ውቂያኖስ ውስጥ 15 ሜ. ጥልቀት ዳይቭ አድርጋ ነው - በዓለም ትንሿ እስኩባ ዳይቨር የተባለችው፡፡
“ለመሆኑ ምን አስደናቂ ነገር አየሽ?” ብያት ነበር - ኢዛቤላን “15 ሜትር ዳይቭ ባደረግኩ ጊዜ የሰመጠ መርከብ አይቼ በጣም ገረመኝ። መርከቡ በጣም ያምራል” አለችኝ፡፡ መርከቡ በጣም ከማማሩ የተነሳ መግባት ፈልጋ እንደተከለከለች ከነገረችኝ በኋላ፣ ያ መርከብ የብዙ አሳዎች መኖሪያ ሆኗል። ብታይው ይገርምሻል” እያለች በሚጣፍጥ የህፃን አንደበቷ አጫወተችኝ “አንቺም ዳይቭ አድርገሽ ብትሞክሪ እንዴት እንደምትወጂው ብታይ” በማለትም ገፋፋችኝ፡፡
“ለመሆኑ በዳይቪንግ ፍቅር እንዴት ወደቅሽ?” ስል ኢዛቤላን ጠየቅኳት፣ እናቴ ለረጅም አመት ዳይቭ ስታደርግ ስለነበር፣ መቼ ነው ዳይቨር የምሆነው እያልኩ ነበር የምጠብቀው፡፡ አሁን የምፈልገው ሆኖልኛል፤ በእኔ ዕድሜ የሚፈቀደውን 15 ሜትር ጥልቀት ዳይቭ አድርጌያለሁ፤ በ15 ዓመቴ ደግሞ አድቫንስ ዳይቨር እሆናለሁ” በማለት አስረዳችኝ፡፡
ዳይቭ ስታደርግ የተቀረፀችውን ቪዲዮ ላፕቶፕ ላይ እያሳየችኝ ከሰመጠው መርከብ ቀጥሎ ያስደነቋትን ግዙፍ የአሳ አይነቶች አሳየችኝ። ስማቸውን እየዘረዘረች የሚመርዙና የማይመርዙትን ነገረችኝ፡፡ ዳይቭ አድርጋ በቅርብ ርቀት የቀረበችውን አሳ አሳየችኝ። በጣም ያስፈራል። አፉ በጣም ሰፊ ነው። ያለማጋነን አንድ ወፍራም ሰው መዋጥ ይችላል፡፡ “አልፈራሽውም?” አልኳት “መጀመሪያ ፈርቼው ነበር። ሆኖም ጥርስም ምንም ስለሌለው መብላት አይችልም። ቢውጠኝ እንኳን መልሶ ነው የሚተፋኝ” በማለት አብራራችልኝ፡፡ ሌላ አንድ አሳ አሳየችኝ። በጣም ብዙ ቁጥር ባላቸው ትንንሽ አሳዎች ተከብቧል፡፡ “እነዚህ አሳዎች ለምን ትልቁን ከበው እንደሚዞሩ ታውቂያለሽ? ይሄ የምታይው ትልቁ አሳ ስለሚፈራ ሌሎች አሳዎች እንዳይበሏቸው ነው፡፡  ብቻ በዳይቪንግ ብዙ ምድር ላይ የማታያቸው አስገራሚ ነገሮችን ታያለሽ። ደስ ይላል ግን በደንብ መተንፈስ የምትችይ መሆን አለብሽ። ያለበለዚያ ችግር ውስጥ ትወድቂያለሽ” እያለች ስለ ዳይቪንግ አስደናቂነት ተረከችልኝ፡፡
ትንሿ ደፈሯና ጎበዟ ስለ ኢዛቤላ ወደፊት ዕቅዷ ስትነግረኝ፤ “የሚፈቀድ ከሆነ እስከ መቶ ሜትር ጥልቀት ዳይቭ ማድረግና በውቂያኖሱ ውስጥ ያለውን ማንኛውም ህይወትና ተፈጥሮ ማየት መመራመርና ታዋቂ ዳይቨር መሆን  ነው፡፡ እስካሁን ጅቡቲና ሲሼል ደሴት ሀይቅ ላይ ዳይቭ ያደረገች ሲሆን በመጪው መስከረም የጅቡቲ ሀሩር በረድ ሲል ወደዚያው አቅንታ ተጨማሪ ዳይቮችን በማድረግ፣ ብቃቷንና አቅሟን የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገልፃለች - በዓለም ትንሿ እስኩቫ ዳይቨር ኢዛቤላ ቴዎድሮስ፡፡  


Read 1476 times