Print this page
Saturday, 27 April 2019 10:55

የፋሲካ በዓልና አርቲስት ታደሰ አለሙ

Written by  በስንታየሁ አለማየሁ
Rate this item
(2 votes)

 ዓውዳመትን ዓውዳመት ሲመጣ በዓል ከሚያስመስሉልን የሙያ ሰዎች ዋነኞቹ አርቲስቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም ደግሞ ድምፃዊያን ለዚህ አይነተኛ ሚና እና ድምቀት እንዳላቸው ለዘመናት እያየን ዛሬ ላይ ደርሰናል:: ዘፈን አንዱ የጥበብ ቅርንጫፍ ነው፤ ይህንን የሚከውኑት ከያኒዎቹ ድምፃዊያንም እንዲሁ፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ከተለመዱ በአላት መካከል አብዛኛዎቹ ሃይማኖታዊ በአላት ናቸው፡፡ ከነዚህ በአላት ውስጥ ደግሞ በክርስቲያን ሀይማኖት ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የፋሲካ በአል ወይንም የእየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በአል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህንን በአል በእምነቱ ስር ያሉ ሊቀ-መዘምራን በመዝሙር እንደሚያደምቁት ሁሉ አለማዊ ድምፃዊያንም በኪነታቸው ያደምቁታል፡፡ በተለይም ከዚህ ከፋሲካ በአል ጋር ተያይዞ በምርጥ ስራው የሚታወቀው ታደሰ አለሙ ነው፡፡ ነፍሱን ይማረውና! ታደሰ አለሙ በዋናነት በሰርግ ዘፈኖቹ የሚታወቅ ቢሆንም ቅሉ ከዚህ ከፋሲካ በዓል ጋር ደግሞ ከሌሎች ድምፃዊያን ለየት ባለ መልኩ ቁርኝት አለው፡፡ ታዴ በእንደዚህ ያለ በዓል አይረሴና ዘመን ተሻጋሪ ለመሆን ሲል፣ ከእለቱ በአል ጋር በተቆራኘ መልኩ እንዲሁም ከባህላዊ ትውፊት ጋር አስተሳስሮ ”ሚሻሚሾ” ሲል ሸጋ የጥበብ ውጤት አበርክቶልን አልፏል፡፡ በበአል ቀን በደረቁ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ከማለት እስቲ አንዳንዴ በአሉን ስናከብር፣ እግረ መንገዳችንን በአሉን ካደመቁልን ባለውለታዎች  ጋር በአካልም ይሁን በምናብ አብረናቸው በመሆን እናክብረው፡፡ ዛሬ በፋሲካ በአላችን ላይ ምርጡን ድምፃዊ ታደሰ አለሙንና በተለይም ደግሞ ከዚሁ በአል ጋር የተቆራኘ ምርጥ ስራውን ”ሚሻሚሾ”ን በማንሳት በአሉን እያከበርን፣ እሱንም ለመዘከር ብንወድ ደስ ይለኛል፡፡ በእርግጥ ታደሰ አለሙ “አውዳመት” የሚል ሌላ በዓል ተኮር ዘፈንም አለው፤ ነገር ግን ይህ ስራው እንደማንኛውም የአውዳመት ዘፈን “ብሉልኝ ጠጡልኝ” ወይንም “አብረን ስንበላው አብረን ስንጠጣው” የሚል ሃሳብ ብቻ ስለያዘ እምብዛም የተለየ ማራኪነት የለውም፡፡ ሚሻሚሾ ግን ማንም ባላየበትና ባላሰበበት መልኩ ልክ እንደ መዝሙርም እንደ ቅኝትም ያለች ፣ ሸጋ መልዕክትን ያዘለች ፣ ከትውፊትና ከእለቱ ሃይማኖታዊ ጭብጥ ጋር በሚገባ የተሰናሰለች ምርጥ ስራው ናት:: በአመት አንዴ ለዚህ በአል ብቻ የምንሰማት ብትሆንም ቀኑን በሚገባ የዋጀች በመሆኗ ዕለት ተዕለት ከምንሰማቸው የአዘቦት አቲካራዎችም ላቅ ብላ ትገኛለች፡፡  
(ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ)
በቀራኒዮ ላይ ታዬ
ታዬ ታዬ
በጎለጎልታ ላይ ታዬ
ታዬ ታዬ
የአለም መድሃኒት የጌታ ትንሳኤ
የጌታ ትንሳኤ
በለተ ፋሲካ በጌታ ትንሳኤ
በጌታ ትንሳኤ
.....ሲለን በቀጥታ የትንሳኤውን ዜና እያበሰረን ነው ፣ ሀይማኖታዊ ትርክቱም እንዲሁ ተመሳሳይ እውነታን ነው የሚሰብከን፡፡ የድምፃዊውም ስራ መቼት ከሀይማኖቱ ጋር ያልተጣረሰ ነው ማለትም - ቀራኒዮና ጎለጎልታ ነው፡፡ የአለም መድሃኒት መሆኑን፣ በቀራኒዮ ላይ መታየቱን ፣ መነሳቱን... ከእውነተኛ ሀይማኖታዊ ትርክቱ በመነሳት በጥሩ ዜማና ቅንብር ብሎም ክሊፕ አሳምሮ አቅርቦታል፡፡ ይህን እንዲህ አድርጎ ጠቅለል ያለውን የትንሳኤ ሃሳብ ከነገረን በኋላ ቀጥሎ ባለው ስንኙ ደግሞ ዝርዝር የስቅለት ጉዳዮቹን ያስረዳናል......
አርባ ቀን አርባ መአልት ገዳመ ቆሮንጦስ ጌታ
ተፈትኖ
ለፈጠረው ፍጡር ተወግሮ ተሰቅሎ የአለም ቤዛ
ሆኖ
ክርስቶስ ታጅቦ እየበተኑለት የዘንባባ ለምለም
ሆሳዕና በአርያም በአህያ ሁርንጫ ገባ እየሩሳሌም
ከደቀ መዝሙራት በ30 ዲናር ይሁዳ ሽጦት
በፀሎተ ሀሙስ ስጋ ደሙን ሰጠን ለኛ ድህነት(4)
....በዚህ ገለፃው ውስጥ በተለይ ከዕለተ እሁድ ጀምሮ በሀይማኖቱ ውስጥ ሰሞነ ህማማት ተብለው በሚጠቀሱት ቀናት ውስጥ የተከናወኑትን ሁነቶች የሚዳስስና የሚገልፅ ነው፡፡ ክርስቶስ በአህያ ሁርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ እየሩሳሌም መሄዱን ፣ በሃዋርያው ይሁዳ በ 30 ዲናር መሸጡን ፣ በዕለተ ሀሙስ ወይንም ደግሞ በፀሎተ-ሃሙስ ደግሞ ይህ “ነገ የሚፈሰው ደሜ ነው...ይህም ነገ የሚቆረሰው ስጋዬ ነው” ተብሎ በሀይማኖት መጽሐፍ እንደተፃፈ ሁሉ፣ ታደሰም በዚህ ዘፈኑ ..... በፀሎተ ሀሙስ ስጋ ደሙን ሰጠን ለኛ ድህነት...በማለት ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ አድርጎ አኑሮታል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ታዴ ከዋናው ጥቅል ሃሳብ ወደ ዝርዝር ሃሳቡ በመግባት (deductive approach) የሚከተሉትን ስንኞች ደግሞ ከዕለተ-ስቅለቱ ከአርብ እስከ ዕለተ-ትንሳኤው እሁድ ድረስ ያሉትን ሀይማኖታዊ እውነታዎች በመግለፅ እንኳን ደስ አላችሁ ሞትን ድል አድርጎ ጌታችን ተነሳ....በማለት ያሳርጋል፡፡ ተመልከቱት እስቲ፡-
.....አስራሶስት ህማማት ግርፋት ስቃዩን
 በአምላክነት ችሎ፣
በጊዜ ስድስቱ አይሁድ ቸንክረውት ጌታችን
ተሰቅሎ፣
ኤሎሄ ኤሎሄ አባት ሆይ አደራ እንካ ነፍሴን
አድን፣
በጊዜ ተስአቱ አሳለፈ እራሱን በመስቀል ላይ
ዋለ፣
ዲያብሎስ ታሰረ አዳም ነጻ ወጣ ከሰራው
አበሳ፣
እንኳን ደስ አላችሁ ሞትን ድል አድርጎ
ጌታችን ተነሳ (4)
......ይሄንን ሀይማኖታዊ ጉዳይ በሚገባ ተርኮ ካሳየን በኋላ ከእለቱ ባህላዊ ትውፊት ጋር ነው ሚሻሚሾ በማለት በጨዋታ የሚደባልቀን እንየው እስቲ..........
ኦ ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ (4)
ከብረሽ ቆይኝ ከብረሃ በ30 ጠምደሃ
ከብረሽ ቆይኝ ከብረሽ በ30 ጠምደሽ
የጌታዬ ሰቀላ ተሸልሟል በአለላ
የእመቤቴ አዳራሽ ተሸልሟል በሻሽ
...በማለት የቡሄ በሉ ዘይቤ አይነት በመጠቀም፣ የቡሄ ጨዋታን የመሰለ ባህላዊ ጭፈራን በማስከተል፣ በሚገርም አቀራረብና ለዛ ሲያቀነቅን ይታያል፡፡ ይህ አይነት ጭፈራ በተለይ በአገው አካባቢ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ እንደ አሸንዳ ያለ ጭፈራ ነው......ወንዶችም በሴቶችም  ሊጫወቱት የሚችሉት ነው - ሚሻሚሾ ማለት፡፡
ኦ ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ (4)
እምዬ ይነሱ ይንበሳበሱ (2)
እማ ከድፎው ቢሰጡኝ ቢቆርሰው
እማ ከጉልባኑ ይዝገኑ ይዝገኑ
እማ ከዱቄቱ ትንሽ በወጭቱ
ማጣፈጫ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
መሰልቀጫ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ትንሽ ቅቤ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ለወገቤ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ትንሽ ጨው
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ቆንጥረው
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ከቅመሙም
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ጣል አርገው
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
በርበሬውን
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ቀላቅለው
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ማጣፈጫ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
መሰልቀጫ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
...እያለ በማዜም ታደሰ አለሙ ይህ በአል ዘወትር በየአመቱ በልዩ ሀይማኖታዊም ኪነታዊም ከፍታ ተከብሮ እንዲውል የላቀ ውለታ ውሎልን አልፏል:: እናም ታዴን የበአሉ አንድ አይረሴ ሰው በማድረግ፣ በስራው እየተዝናናን ዘክረነው እንውል ዘንድ ይህንን አስታወስን፡፡ በድጋሚ ለመላ የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች እንኳን ለፋሲካ በአል በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ!!

Read 9096 times