Saturday, 27 April 2019 11:13

“ወላይትኛ የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን እታገላለሁ” - ወብን

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)


           በወላይታ ተወላጅ ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን የተመሠረተው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) ወላይታ ራሱን የቻለ ክልል፣ ወላይትኛ ቋንቋም የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን የቅድምያ ትኩረት አድርጌ እታገላለሁ አለ፡፡
ባለፈው ሳምንት በወላይታ ሶዶ ከተማ መስራች ጉባኤውን ያደረገው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን)፤ በወላይታ ህዝብ ላይ የደረሱ ታሪካዊ በደሎችና እየደረሱ ያሉ ነባራዊ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ መታገልን አላማው አድርጐ መመስረቱን ም/ሊቀመንበሩ አቶ ኃይሚካኤል ለማ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ንቅናቄው ቀዳሚ ትኩረት አድርጐ የሚሠራውም የወላይታ ተወላጆች ከሀገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ እኩልና ፍትሃዊ ተጠቃሚ ማድረግን፣ የወላይታ ህዝብ የራሱ የክልል አስተዳደር እንዲኖረው ማስቻልንና ሠፊ ተናጋሪ ያለውን የወላይትኛ ቋንቋ የክልልና የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን መታገል መሆኑን አቶ ኃይለሚካኤል አስረድተዋል፡፡ ከፖለቲካ አንፃር በዋናነት የወላይታ ህዝብ ራሱን በራስ የማስተዳደር ታሪክ ያለው መሆኑን በማስገንዘብ፣ አሁንም ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር እንጠይቃለን ያሉት ም/ሊቀመንበሩ፤ የደቡብ ክልል ውስጥ የተካተተው ያለ ፍላጐቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የወላይታ ህዝብ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት የራሱ ክልል እንዲኖረው የሚታገለውም ከዚህ አንፃር ነው ይላሉ - አቶ ኃይለሚካኤል፡፡
በሌላ በኩል ፓርቲው የኢኮኖሚ ጥያቄም ይዞ መነሳቱን ም/ሊቀመንበሩ ይገልፃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የወላይታ ተወላጅ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ መገፋት እየደረሰባቸው በመሆኑ ፍትሃዊ የኢኮኖሚና ሃብት ክፍፍል እንዲሰፍን እንታገላለን ብለዋል፡፡
የወላይታ ቋንቋም የፌደራል የስራ ቋንቋና የመገናኛ ብዙኃን ቋንቋ እንዲሆን በዋነኛነት ትግል እናደርጋለን ብለዋል - አቶ ኃ/ሚካኤል፡፡
በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ አቅዶ ከወዲሁ እየተዘጋጀ የሚገኘው “ወብን” መስራች አባላቱ በአመዛኙ የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ የፌደራልና የክልል መንግስት መስሪያ ቤት ሠራተኞችና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሰሩ የብሔረሰቡ ምሁራን መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የንቅናቄው የፖለቲካ ፕሮግራም በቅዳሜው ጉባኤ በሙሉ ድምጽ የፀደቀ ሲሆን፤ ዶ/ር አበባየሁ ቶራ በሊቀ መንበርነት፣ አቶ ኃይለሚካኤል ለማ በም/ሊቀመንበርነት መመረጣቸው ተነግሯል፡፡

Read 7968 times