Saturday, 27 April 2019 11:18

የኦሮ-ማራ ህዝቦች ጥምረት ለፖለቲካ ፍጆታ እየዋለ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ‘‘ጥምረቱ ከሁለቱ ህዝቦች ተሻግሮ ኢትዮጵያውያንን ማቀፍ አልቻለም ˝ ፖ ለቲከኞች‘‘ የኦሮ-ማራ ህዝቦች ግንኙነት ኢትዮጵያን የታደገ ነው ˝ አዴፓ
             
          የኦሮሞና አማራ ህዝቦች ግንኙነት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ መሆን እንዳለበትና ሌሎች ህዝቦችንም በማካተት ወደ ኢትዮጵያዊነት ማደግ እንደሚገባው ፖለቲከኞች ተናገሩ፡፡ በሁለቱ ክልል መሪዎች ደረጃ ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ በአምቦ የተካሄደውን የኦሮሞና አማራ ህዝቦች የግንኙነት መድረክ ተከትሎ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡ ፖለቲከኞች መድረኩ አቅጣጫውን እየሳተ ነው ብለዋል፡፡
“ኦሮ-ማራ” የሚል ሃሳብ በማህበራዊ ገፃቸው በማቀንቀን ከሚታወቁት  ምሁራን አንዱ የሆኑት የዩኒቨርሲቲ መምህርና አክቲቪስት ስዩም ተሾመ፤ የሁለቱ ብሄሮች ለህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ታስቦ የተጀመረ ቢሆንም አሁን ግን የፖለቲከኞች ግንኙነት እንደሆነና መነሻ አላማውንም እንደሳተ ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል “ኦሮ - ማራ” በሚል በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተጀመረው ግንኙነት አሁን ለተገኘው ፖለቲካዊ ለውጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ያሉት አቶ ስዩም፤ ጥምረቱ ግን ከሁለቱ ህዝቦች ተሻግሮ ኢትዮጵያውያንን ማቀፍ ያልቻለ፣ ከመሆኑም በላይ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ እየዋለ ነው ብለዋል፡፡
“የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች እርስ በእርስ የተዋለዱ”፣ “ሁለቱ ግዙፍ የኢትዮጵያ ብሔሮች” ወዘተ እየተባለ በየመድረኩ የሚቀርቡ ጥናቶች በራሳቸው ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን ዘረኝነትን የሚያጐሉ ናቸው የሚሉት አክቲቪስቱ፤ “ከዚህ በኋላ የሁለቱ ህዝቦች ጥምረትና ግንኙነት ብቻውን ይሄን ሀገር አያድንም፤ ወደ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ያለ ፕሮጀክት መሆን ይገባዋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በሁለቱ ህዝቦችም ሆነ በሌሎች ህዝቦች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ከፖለቲከኞችና ከፖለቲካ ተጽእኖ ነፃ መሆን እንዳለበት የተናገሩት መምህሩና አክቲቪስቱ፤ በቀጣይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ተቋማዊ በሆነ መልኩ በምሁራን መመራት አለበት ብለዋል፡፡
የቀድሞ የ “ሰማያዊ ፓርቲ” አመራር መምህር አበበ አካሉም፤ ጥምረትና ግንኙነቱ ከህዝብ ለህዝብነቱ ይልቅ የፖለቲካ ፍጆታው እያመዘነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በኦሮሞና በአማራ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ብቻ ማቀንቀን ለሀገሪቱ ጉዳት እንጂ ጥቅም አያመጣም ባይ ናቸው፡፡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተጀመረው ግንኙነት ሌሎችን የመገፋትና በአናሳነት የመታየት ስነልቦና ውስጥ እንዳያስገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ሲሉም ይመክራሉ - አቶ አበበ፡፡
የብሔር ፅንፈኛ አክቲቪስቶች ግራና ቀኝ መጓተታቸውን እስካላቆሙ ድረስ የመሪዎቹ መገናኘትና “ኦሮ - ማራ” እያሉ መዘመር የሚያመጣው ለውጥ የለም የሚሉት ፖለቲከኛው፤ አክቲቪስቶችን በህግም ሆነ በሞራል የማነፅ ሥራ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ሌላው አክቲቪስትና ፖለቲከኛ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) በበኩላቸው፤ ከ80 በላይ ብሔሮች ባሉበት ሀገር “ኦሮ-ማራ” ብሎ የሁለቱን ብሔሮች ጥምረት ብቻ ማራመድ ለኢትዮጵያዊነት እንደማይጠቅም ይናገራሉ፡፡ የኦሮ-ማራ ጥምረት ሠፍቶ ወደ ኢትዮጵያዊነት ህብረት ማደግ ይኖርበታል ያሉት አቶ ክንፈ ሚካኤል፤ ከዚህ በኋላ ዘር ከመቁጠር ወጥተን የጋራችንን ኢትዮጵያ ማሰብ አለብን ብለዋል፡፡ “ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ወዳቀፈና ሁሉም ህዝብ የሃገሩ ባለቤት ነው ወደሚል ንቅናቄ መሸጋገር አለበት” ሲሉም አክለዋል - አክቲቪስቱና ፖለቲከኛው፡፡  
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑትና በንቁ ፖለቲካዊ ተሳትፎአቸው የሚታወቁት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ግን የተለየ ሃሳብ ያንፀባርቃሉ፡፡ “የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ሁለቱ ትላልቅ ህዝቦች ላይ ያተኮረው ሌሎችን ለማግለል ሳይሆን ለረዥም ጊዜ ትልቅ ፕሮፓጋንዳ የተሰራው በኦሮሞና አማራ ህዝብ ላይ በመሆኑ ነው” ብለዋል - ከኤል ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፤ የኦሮሞ አማራ ግንኙነትን አስመልክቶ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ “የኦሮሞ ብሔር፣ ከአማራም ሆነ ከሌላው ህዝብ ጋር የፖለቲካም ሆነ ሌላ ችግር የለበትም፤ ጥምረቱ በሁለቱ ህዝቦች ብቻ ሳይገደብ በሁሉም ህዝቦች መካከል መጐልበት” አለበት ብሏል፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ሲፈራረቁ የነበሩ ስርዓቶች የኢትዮጵያን ህዝብ እርስ በእርስ ሲያጋጩ ነበር ያለው ኦነግ፤ አሁንም ከተመሳሳይ ዝንባሌ መላቀቅ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል፡፡
የኦሮሞና አማራ ህዝብን ግንኙነት ለማጠናከር የተሠራው ስራ ትልቅ ፖለቲካዊና ህዝባዊ ድል አስገኝቷል ያለው የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በበኩሉ፤ ይህ መሰሉ ግንኙነት ከሌሎች ህዝቦችም ጋር እየሠፋና እየተጠናከረ መሄድ ይኖርበታል ብሏል፤ ከአምቦ መድረክ በኋላ ባወጣው የአቋም መግለጫው፡፡ የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ግንኙነት ኢትዮጵያን ከጥፋት የታደገ መሆኑን ያስታወሰው አዴፓ፤ የማህበራዊ ሚዲያ አራማጆች ሂደቱን ለማንኳሰስ መሞከራቸው ተገቢ አይደለም ሲል ተችቷል፡፡     

Read 9527 times