Saturday, 04 May 2019 15:04

ዶ/ር ነጋሶ ያሳደጓት ልጅ ምን ትላለች?

Written by 
Rate this item
(8 votes)

*ከ8 ዓመቴ ጀምሮ አባታዊ ፍቅራቸው አልተለየኝም
*የቤተዘመድ ማህበራቸው ውስጥ አባል አድርገውናል  
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ሁለት ልጆችን አሳድገውና አስተምረው ለቁምነገር እንዳበቁ ከሰሞኑ ሰማንና፣ አንደኛዋን አፈላልገን አገኘናት፡፡ ማህሌት ይርጉ ትባላለች፡፡ ከ8 ዓመቷ ጀምሮ
የዶ/ር ነጋሶ አባታዊ ፍቅርና ድጋፍ እንዳልተለያት የምትናገረው ማህሌት፤ዛሬ የባንክ  ሰራተኛ ሆናለች፡፡ ወንድሟም የራሱን ቢዝነስ እንደሚሰራ አውግታናለች፡፡ በሁለቱ ወንድምና እህት ህይወት ውስጥ ደግሞ ዶ/ር ነጋሶ አሉ፡፡ እንዴት? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ወጣት ማህሌትን በአጭሩ አነጋግሯታል፡፡ እነሆ፡-
ዶ/ር ነጋሶን እንዴት ነው  ያወቅሻቸው?
እሳቸው ፕሬዚዳንት በነበሩ ጊዜ እናታችን ቤተ መንግስት ትሰራ ነበር፡፡ ዶ/ር፤ ሁሉንም ሰው በእኩል የሚያዩ፣ በቤተ መንግስቱ ለነበሩ ሰራተኞች በሙሉ እኩል ፍቅር የነበራቸው
 ሰው ናቸው፡፡ እናታችንን በህመም ካጣናት በኋላ፣ እኔና ወንድሜ፣ የእናታችንን ሞት እንድንረሳ አጽናንተውናል፡፡ እንዳናዝን ተንከባክበውናል፡፡ አብረናቸው እንድናሳልፍ ያደርጉ ነበር፡፡ ሁሉንም በዓላት አብረናቸው ነበር የምናሳልፈው፡፡ እንደ ቤተሰብ ነው  ግንኙነታችን፡፡ እርግጥ ቤተሰቦችና አያቶች አሉን፤ ነገር ግን ዶ/ር እና ባለቤታቸው ለትምህርት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ያሟሉልን ነበር፡፡ ማንኛውንም ነገር ያደርጉልናል፡፡ በጣም ይንከባከቡን ነበር፡፡ በቁስ ከሚያደርጉልን በላይ የአባትነት ፍቅር ይለግሱን ነበር፡፡ ከቤተ መንግስት ከወጡ በኋላ ለራሳቸው ምንም ሳይኖራቸው፣ እኛን ይንከባከቡን ይደግፉን ነበር፡፡ እኛ ቤተሰባቸው ነን፡፡ እናታችንን ካጣናት ቀን ጀምሮ አባት ሆነው፣ ባለቤታቸውም እናታችን ሆነው አሳድገውናል፡፡ በጣም ነው የምንዋደደው፡፡ ይሄን ፍቅራቸውን ከቤተ መንግስት ከወጡ በኋላም አላቆሙም፡፡ ቤተሰቦቻቸው እንደ ቤተሰቦቻችን፣ እንደ እህት ወንድም ሆነው ነው የኖርነው፡፡ አሁንም የምንኖረው እንደዚያው ነው፤ ያለን ቅርርብ በጣም ጥብቅ ነው፡፡ የቤተ ዘመድ ማህበር አላቸው፡፡ በዚያ ማህበር ውስጥ እኛም አባል ነን፡፡ አባል አድርገው አስመዝግበውን፣ የቤተሰቡ አባል ሆነናል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ላንቺ ምን አይነት ሰው ነበሩ?
ዶ/ር ሰውን አይለያዩም፡፡ ሁሉንም በእኩል አይን ነው የሚያዩት፡፡ ባህሪያቸው በጣም የሚደንቅ ነው፤ ተምረን እንድንለወጥ ነበር የሚፈልጉት፡፡ በእሳቸው ስም እንኳ ተምረን ስራ
እንድናገኝ አይፈልጉም ነበር፡፡ በራሳችን ጥረት፣ ራሳችንን እንድንችል ነው ሲመክሩን የነበረው፡፡ ጠንክረን በራሳችን እንድንለወጥ ነበር የሚፈልጉት፡፡ አሁን እግዚአብሔር ይመስገን፣ እኔም ወንድሜም ተምረን፣ መልካም ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡ ከዶ/ር እና ባለቤታቸው ጋርም እንደ ቤተሰብ አብረን ነን፡፡ እንደ አባቴ ነው የማያቸው፡፡
ከስንት ዓመትሽ ጀምሮ ነው ከእሳቸው ጋር የተቀራረብሽው?
የ8 ዓመት ወይም የ9 ዓመት ልጅ እያለሁ ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አባታዊ ፍቅራቸው አልተለየኝም፡፡ አሁን ተመርቄ የራሴ ስራ አለኝ፡፡ የእሳቸውን መልካምነት ለመግለፅ
ይከብደኛል፡፡ እሳቸውም ባለቤታቸውም ከልባቸው መልካም ሰው ናቸው፡፡ እኛን ሳይሆን እናታችንን ነበር የሚያውቋት፡፡ እሷ እዚያ በምታገለግልበት ሰዓት በመልካም ባህሪዋ
ይወዷት፣ ያከብሯት ነበር፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ እንኳ የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸው ሳይገድባቸው፣ በቀብር ሥነ ስርዓቷ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ይሄን ፍቅራቸውን አሁን በቃላት መግለፅ አልችልም፡፡
በቅርቡ አግኝተሻቸው ነበር?
አዎ፤ከህልፈታቸው አስራ አምስት ቀን በፊት ተገናኝተን ነበር፡፡ በቤተ-ዘመድ ማህበራችን ላይ ተገናኝተን፣ አብረን ነበር ያሳለፍነው፡፡  
የጤንነታቸው ሁኔታ እንዴት ነበር?
እኔ እንዲህ ለሞት የሚያበቃ ህመም አላስተዋልኩባቸውም፡፡ መሞታቸውንም ማመን አልቻልኩም፡፡ ለሞት የሚያደርሳቸው ህመም አለባቸው ብዬ በፍፁም አልጠበቅሁም፡፡
አሁን አንቺና ወንድምሽ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያላችሁት?
ያው እኔም ባንክ ተቀጥሬ እየሰራሁ ነው፣ ወንድሜም የራሱን ቢዝነስ እየሰራ ነው፡፡ እኛ እዚህ እንድንደርስ የሳቸው አስተዋፅኦ መተኪያ የሌለው ነው፡፡
ህልፈታቸውን የሰማሽበት አጋጣሚ እንዴት ነበር?
ስራ ቦታ ነበርኩ፡፡ የሰሙ ሰዎች ሊነግሩኝ አልፈለጉም ነበር፡፡ ያለንን ቀረቤታ ስለሚያውቁ በጣም ታመዋል ነበር ያሉኝ፡፡ መንገድ ላይ ሆኜ ነው ወንድሜ ድንገት መስማቷ
አይቀርም ብሎ "ሳትደናገጭ ወደ ቤት ነይ፤ ዶ/ር አርፈዋል፤ተረጋጊና ነይ" አለኝ፡፡ በወቅቱ በድንጋጤ የማደርገውን አላውቅም ነበር፡፡ ዶ/ር በጣም ነበር የሚወዱኝ፡፡ ልጄን
ሳይቀር “አያቱ መሆኔን እየነገርሽ አሳድጊው፤ “አካካ” (አያቴ ማለት ነው) እያለ ይደግ" ይሉኝ ነበር፡፡ ልጄ አሁን “አካካ” ነው የሚላቸው፡፡ ሃዘኑ መቼም ቢሆን ከውስጤ
አይወጣም፡፡ ዶ/ር፤ በማንኛውም አጋጣሚ እኛን "አሳደግኋቸው፣ ረዳኋቸው" ብለውም አያውቁም፡፡ ግን በሚያስፈልገን ነገር ሁሉ፣ ያውም ከቤተ መንግስት በወጡበት ጊዜ፣ ምንም
ሳይኖራቸው ረድተውናል፡፡

Read 5067 times