Print this page
Monday, 06 May 2019 11:51

ቃለ ምልልስ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ - በወዳጆቻቸው አንደበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


“ በ50 አመት የፖለቲካ ህይወታቸው ከተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪነት እስከ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት፤ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት እስከ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነት የዘለቁት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ብዙዎች “ለህሊናቸው የኖሩ የመርህ ሰው” ሲሉ ያደንቋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሚዛን እንደሆኑ የሚነገርላቸው ዶ/ር ነጋሶ፤ ከብሔርተኛው “ኦነግ” እስከ አንድነት አቀንቃኙ “አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ” በአመራርነት አገልግለዋል፡፡  
እኚህ ጉምቱ ምሁርና ፖለቲከኛ ከሰሞኑ ለህክምና ወደ ጀርመን ሀገር ሄደው ድንገተኛ ህልፈታቸው መሰማቱ ለብዙዎች አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ ለመሆኑ የፖለቲካ ባልደረቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ህልፈታቸውን እንዴት ተቀበሉት? ዶ/ር ነጋሶ ምን ዓይነት ሰው ነበሩ? የፖለቲካ ህይወታቸው እንዴት ይገለጻል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ዙሪያ የተሰጡ ምስክርነቶችንና አስተያየቶችን እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡“


         “በጣም ጠንካራ የሥራ ዲሲፕሊን ነበራቸው”
አቶ ተመስገን ዘውዴ
(የቀድሞ “አንድነት” አመራር)
እኔና እሳቸው በ“አንድነት” ፓርቲ ውስጥ በአመራርነት አብረን ሰርተናል፡፡ እሳቸው ፕሬዚዳንት ሲሆኑ እኔ የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ነበርኩ፡፡
ዶ/ር ነጋሶ በሚሰጡኝ አመራርና ባላቸው ራዕይ፣ ሙሉ እምነት ኖሮኝ ነው አብሬያቸው ስሰራ የነበረው፡፡ ከዚህ ግንኙነታችን ልታዘብ የቻልኩት፣ ዶ/ር ነጋሶ፣ የመርህ ሰው መሆናቸውን ነው፡፡ ሃቀኛ ናቸው፤ ለሃገር አሳቢ ናቸው፡፡
በጣም ጥንካሬ ያላቸው ሰው ናቸው፤ ጥንካሬያቸው የሚመጣው ደግሞ ከዲሲፕሊን ነው፡፡ በጣም ጠንካራ የስራ ዲሲፕሊን አላቸው፤ ሰርቶ የማሰራት ብቃት ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ ከሳቸው የሚደንቀኝ የመርህ ሰው መሆናቸውና ሃቀኝነታቸው ነው:: በዚህ የሚወዳደራቸው የለም፡፡
በሳቸው ህልፈት ክፉኛ ነው የደነገጥኩት፡፡ እሳቸውን ማጣት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በሃቀኝነትና በመርህ ህይወት ላይ ክፍተት የሚፈጥር ነው የሚሆነው፡፡ መሞታቸውን እንኳን የሰማሁት በቴሌቪዥን ነው፡፡ ለኔ በእጅጉ አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡  
“ኦሮሞነታቸውና ኢትዮጵያዊነታቸው ተጣልተውባቸው አያውቁም”
 ዳንኤል ተፈራ
(“ደንዲ የነጋሶ መንገድ” መፅሐፍ ደራሲ)
ለኔ ህልፈታቸውን መስማት በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከሁለት ወር ወዲህ በስልክ ተገናኝተናል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትንታኔ ላይ አንድ መፅሐፍ እየጨረሱ ነበርና በዚያ ጉዳይ ስለማግዛቸው እንገናኝ ነበር፡፡ እኔ የማውቀው ለህክምና እንደሚሄዱ ነበር፡፡ ግንቦት መጀመሪያ አካባቢ ህክምናዬን ጨርሼ እመለሳለሁ ነበር ያሉት፡፡ በዚህ መልኩ ህይወታቸው ያልፋል ብሎ መገመት ከባድ ነው:: ምክንያቱም ከዚህ በፊት በብዙ ችግር ውስጥ አልፈዋል፡፡
የመድሃኒት መግዣ እስከ ማጣት ደርሰዋል፣ ብዙ ተጎሳቁለዋል:: ነገር ግን ቢያንስ ካለፈው ዓመት ወዲህ፣ ያ ችግራቸው ተቀርፎላቸዋል፡፡
እንደ ቀድሞ የሃገር ፕሬዚዳንትነታቸው፣ ተገቢውን ክብርና ጥቅም ባያገኙም፣ ቢያንስ እነ ዶ/ር ዐቢይ ከመጡ በኋላ የተሻለ ነገር እያገኙ ነበርና አጋጣሚው በጣም የሚያስቆጭ ነው፡፡ ቅዳሜ እለት ወሬው ሲሰማ ማመን አልቻልኩም፡፡ በጣም ደንግጫለሁ፡፡ በጣም ነው ሞታቸው የቆጨኝ፡፡ አሳዛኝ ነው፡፡
ዶ/ር ነጋሶ በጣም የተለየ ሰብዕና ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ ዶ/ር ነጋሶን እንደ ሰው ስናያቸው፤ በማህበራዊ ህይወታቸው ሰው ወዳድ፣ በጣም ተግባቢ፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚወድዱ፣ ለምድራዊ ቁሳቁስ ብዙም ቦታ የማይሰጡ፣ ለብልጭልጭ  አለም የማይንበረከኩ፣ በራሳቸው እምነት የሚጓዙ አይነት ሰው ናቸው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ የቀናነት የሃቀኝነት ልክ ማሳያ ናቸው፡፡
ከ50 ዓመት በላይ በቆዩበት የፖለቲካ ህይወት፣ በመርህ የተጓዙ፣ በየትኛውም የፖለቲካ ትግል ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ሰው ናቸው፤ ከኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መጠነ ሰፊ ፖለቲካዊ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚወዱ፣ በዚያው ልክ ኦሮሞነታቸውም የሚወዱ ሰው ነበሩ፡፡ ኦሮሞነታቸውና ኢትዮጵዊነታቸው ተጣልተውባቸው አያውቁም፡፡ ጥሩ ኦሮሞ፤ ጥሩ ኢትዮጵያዊ መሆን ይቻላል ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡
ከመለያየትና መነጣጠል አንድ መሆን ይሻላል ባይ ነበሩ፡፡ በተደጋጋሚ አንድ የሚናገሩት ነገር ነበር፡- “እኛ እንደ ጉንጉን አበባ ነን” ይላሉ “አንድ አበባ ብቻውን ውበት የለውም፤ ከሌላው ጋር ሲጎነጎን ውበት ይሰጣል፡፡” ዶ/ር ነጋሶ ሲነገርላቸው ቢዋል ቃላት አይገልፃቸውም፤ ሰብዕናቸው አስተማሪና ዘመን ተሻጋሪ ነው፡፡

 “በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጠንካራ አቋም ነበረው”
አቶ አስራት ጣሴ
(የቀድሞ የ“አንድነት” አመራር)
ዶ/ር ነጋሶ፣ እኔ እስከማውቀው፣ ከዚህ በፊት የልብ ቀዶ ጥገና አድርጓል፡፡ ይሄን ስለማውቅ እንዲህ ድንገት ህልፈቱ ይሰማል ብዬ አልጠብቅም ነበር፡፡ በጣም አስደንጋጭ ነበር የሆነብኝ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ፣ ከፕሬዚዳንትነቱ በገዛ ፈቃዱ ከለቀቀ በኋላ የመንግስት ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ነው ያጎሳቆሉት፡፡ ሁለት መኪና ነበረው፤ እሱን በአንድ ጊዜ ወሰዱበት፣ የደህንነት ጠባቂዎች፣ የቤት ምግብ አብሳዮች በሙሉ በአንድ ጊዜ ተወሰዱ፤ ደሞዝ ከለከሉት:: በአንድ ወቅት ከባለቤቱ ደመወዝ በቀር ምንም ዓይነት ገቢ አልነበረውም፡፡ እንደውም ያለውን ሁሉ ከማጣቱ የተነሳ ህክምና እንኳ ለመታከም ተቸግሮ ነበር፡፡ ህክምናው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ስለነበር በጊዜው ሳይታከም ቀርቷል፡፡ ብዙ ነው የተጎሳቆለው፡፡ እንደ ምንም በአሜሪካን ሃገር የልብ ቀዶ ጥገና ካደረገ በኋላ እንኳ ተመልሶ ሄዶ፣ በቀጠሮው መሰረት ቼክአፕ ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡ ይሄ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ማንም ይረዳል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ በአጠቃላይ በተወሰደበት የቂም እርምጃ ብዙ ተጎድቷል፡፡ መኖሪያ ቤቱ ያፈስ ነበር፡፡ ጠግኑልኝ ሲላቸው ጭራሽ ቤቱን ለቀህ ውጣ ነበር ያሉት፡፡ እሱ ደግሞ ጥቅም በህይወቱ ውስጥ ቦታ ስለሌለው፣ ሚኒስትር በነበረ ጊዜ እንኳ ጓደኞቹ መሬት ሲወስዱ፣ እሱ ግን የመጣሁት ለማገልገል እንጂ  ቦታ ልወስድ አይደለም ብሎ አልወሰደም፡፡ ከቤት ውጣ ሲሉት መሄጃ አልነበረውም፤ ስለዚህ የሚያፈሰውን ቤት ላለመልቀቅ ነው የታገለው፡፡ በዚህ መጠን ነው ያጎሳቆሉት፡፡ በጣም ተቸግሮ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ይሄን ችግሩን ተረድተን እርዳታ ልናደርግለት ኮሚቴ አቋቁመን ነበር:: እሱ ግን በፍፁም ምንም እንድታደርጉ አልፈቅድም ነው ያለው፡፡ እንዲህ አይነት ሰው ነበር - ዶ/ር ነጋሶ፡፡ በእኔ እምነት በዚህ ጉስቁልና ምክንያት ህመሞቹ ስር ሰደዋል፡፡ አሁን መታከም በሚችልበት ሰዓት ደግሞ የማይመለሱበት ደረጃ የደረሱ ይመስለኛል፡፡
ዶ/ር ነጋሶን እኔ የማውቀው ገና ከልጅነት ነው:: ከ12ኛ ክፍል ጀምረን በልኡል በዕደ ማርያም ት/ቤት አብረን ነው የተማርነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ፣ ለአራት አመት የታሪክ ትምህርት አንድ ክፍል ነው የተማርነው፡፡ ስራ ስንመደብም እኔ ነቀምት ሲደርሰኝ፣ እሱ አይራጎሊስ ነው የሄደው፡፡ እኔ ከነቀምት ወደ ጊምቢ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ዳይሬክተር ሆኜ ስመደብ በቅርበት እንገናኝ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያስተዋልኩት፣ ዶ/ር ነጋሶ የተረጋጋ ሰው መሆኑን ነው፡፡ አስተዳደጉም በጠንካራ ስነ ምግባር ነው፡፡ መልካም ሰብዕና ያለው፣ ትህትናን የተላበሰ፣ በስራ ላይ ታታሪ የነበረ ሰው ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ፣ አኗኗሩ በከፍተኛ ፕሮግራም የሚመራ ነው፡፡ የፖለቲካ ተሳትፎን የጀመረው ገና ተማሪ ሆነን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት ከፍተኛ ተሳትፎ ነበረው:: የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረትን (ዩዝዋ) በመመስረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ሰው ነው፡፡ የመሬት ላራሹን መፈክር ይዞ ከሌሎች ተራማጅ ተማሪዎች ጋር ታግሏል፡፡ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድን በመቃወም፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ሰልፍ ሲያደርጉ፣ ዶ/ር ነጋሶ ከፍተኛ ተሳትፎ ነበረው፡፡ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የነበረው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡
ዶ/ር ነጋሶ፣ ያመነበትን ሃሳብ ለማራመድ ችግር የለበትም፡፡ ከዚህ ወገን ተቃውሞ ይመጣብኛል፤ ይሄን አስከፋለሁ ብሎ አያስብም፡፡ ያመነበትን ሃሳብ ይሰጣል፡፡ ባመነበት ሃሳብ በመርህ ላይ ተመስርቶ ይከራከራል፡፡ ጠንካራ የመርህ ሰው ነበር፡፡ ዶ/ር ነጋሶ የመጫና ቱለማ ህብረት አባል ነበር፡፡ በኋላም የ“ኦነግ” አመራር አባልም ነበር:: ከዚያም ኢህአዴግ ሆነ፤ ኢህአዴግ ውስጥ ልክ ያልሆነ ነገር ሲያይ፣ ስልጣንና ጥቅሙን ትቶ ተቃዋሚ የሆነ ሰው ነው፡፡ የ አንድነት” አመራር ነበር፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ወደ አንድነት ፓርቲ በመጣበት ወቅት መቼም የማትዘነጋኝ አንድ ንግግር አድርጎ ነበር፡፡ “የብሔርን እንቁላል ሰብሬ ወጥቻለሁ” ነው ያለው፡፡ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ሲሆንም “የአገሪቷ አንድነትም ሆነ ሉአላዊነት አይነጣጠሉም፤ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበርና ነፃነት ዋጋ ከፍሏል” ብሏል፡፡ ይሄ ጠንካራ አቋሙ ነበር:: በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጠንካራ አቋም ነበረው፡፡ በዚያው ልክ የብሔሮች መብት ይከበር የሚልም ጠንካራ አቋም አለው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በግልፅ ፊት ለፊት ሃሳቡን የሚያራምድ ሰው ነበር፡፡ ያመነበትን ይዞ ጥቅሙን እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ ለአቋሙ የሚታመን ሰው ነበር፡፡

“ፍፁም ቀና፣ ፍፁም ግልፅ፣ ፍፁም የዋህ ነበሩ”
አቶ አንዷለም አራጌ
(የቀድሞው “አንድነት” አመራር)
የዶ/ር ነጋሶን ማለፍ እስካሁን ማመን ተስኖኛል፣ በጣም ነው ግራ የተጋባሁት፡፡ አስደንጋጭ ሆኖብኛል፡፡ ካለን ቀረቤታ አንፃር የማውቀው በጥሩ ጤንነት ላይ እንደነበሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ረድቶኝ ከእሳቸው ጋር በሰራሁ ጊዜ ከእሳቸው ብዙ ተምሬያለሁ፡፡ ስገልፀው እንዳላሳንሰው ፈራሁ እንጂ እኔ እስከ ዛሬ ከእርሳቸው በላይ ቀና ሰው አላገኘሁም፤ ከእርሳቸው በላይ ቀጥተኛ ሰው አላገኘሁም፡፡ ፊታቸው ላይ የሚታየውን ነገር ከአንደበታቸው መስማት ይቻላል፡፡ የተደበቀ ነገር የላቸውም፡፡ ፊት ለፊት ናቸው፡፡ በውስጣቸው ቂም የለም:: ፍፁም ቀና፣ ፍፁም ግልፅ፣ ፍፁም የዋህ ሰው ነበሩ፡፡ ሌላው ሰው የማያውቀው፣ እኔ ከሳቸው ተምሬ በህይወቴ ውስጥ እተገብረዋለሁ ብዬ የማስበው ሌላው ነገር፣ ሰአት አክባሪነትና መረጃን በጥንቃቄ የመያዝ ልምድ ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በጣም ሰአት አክባሪ ናቸው። እያንዳንዷን ሰዓት በስርአቱ የሚጠቀሙ፣ በዋዛ ፈዛዛ ሽራፊ ሰከንድ ማጥፋት የማይፈልጉ ታታሪ ሰው ነበሩ:: እያንዳንዷን ጉዳይ በማስታወሻ ደብተር የሚከትቡ፣ ያንን ማስታወሻ በጥንቃቄ ሰንደው የሚይዙ ሰው ነበሩ፡፡ ይሄ ከሳቸው የተማርኩት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሌላው የሰው አክብሮታቸው ነው፡፡ በሳቸው ደረጃ ለሰው አክብሮት ያለው ሰው አላጋጠመኝም፡፡ ሁሉንም ሰው በእኩል የሚመለክቱና በእኩል የሚቀርቡ ሰው ነበሩ:: በስልጣናቸውና በትምህርት ደረጃቸው መታበይን የማያውቁ ሰው ናቸው፡፡ እሳቸው 150 ብር ይዘው ለታክሲ የምትሆናቸውን ብቻ አስቀርተው፣ ሰውን ለመደገፍ ይታትሩ ነበር፡፡ ለገንዘብ፣ ለቁስ ደንታ የላቸውም፡፡ እንደውም አንድ ጊዜ ከቤት ሊያስወጧቸው ሲሉ፣ ባለቤቴን ወደ ሃገሯ ሸኝቼ እኔ መንገድ ላይም ቢሆን በድንኳን እኖራለሁ እንጂ ሃገሬን ትቼ የትም አልሄድም ያሉ ሰው ናቸው፡፡   
ዶ/ር ነጋሶ፤ አንተ ማንም ሁን ማን፣ የሚከተሉት የሃሳብ መስመርን ነው፡፡ በጣም ሃሳባዊ የሚባሉ ሰው ናቸው፡፡ የሃሳባዊነት ሰው ለኔ ነጋሶ ናቸው፡፡ እኔ በእስር ላይ እያለሁ ፍርድ ቤት እየተመላለሱ፣ እያንዳንዷን የኔን ችሎት ይከታተሉ ነበር፡፡ በደላችን እንዲሰማ የተደራጀ ስራ ይሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡ እኔ ዶ/ር ነጋሶን በቃላት ብቻ ለመግለፅ እቸገራለሁ፡፡

የማህበራዊ ድረ-ገፅ
“ዶ/ር ነጋሶ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይ ደግሞ ለኦሮሞ ህዝብ እጅግ በሚያስፈልጉበት ጊዜ እረፍተ ህይወታቸውን መስማቱ ትልቅ እጦት ነው፡፡”
አቶ ሙሼ ሰሙ
(የፖለቲካ ተንታኝ)
“ስሜቴን የምገልፅበት ቃል የለኝም፡፡ ከግል ጥቅምና ፍላጎት ነፃ የሆኑ፣ አብሬ በመስራቴ ኩራት የሚሰማኝ ወዳጄ ዶ/ር ነጋሶ አረፉ መባሉን ስሰማ አላመንኩም። ግን እውነት ነው፡፡ መልካም ሰው፤ በልዩነት ፍቅር የማይነሱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ!”
አቶ ግርማ ሰይፉ
(የቀድሞ የፓርላማ አባል)
 “የራሱ ሰው፣ ትሁት፣ ከምላሱ ይልቅ ለጆሮው ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ታታሪ፣ እምነትህን ልትጥልበት የምችል ታማኝ፣ ከዘመቻ ጫጫታ ይልቅ የአንድ ነገር ቀጣይነትና ትክክለኛነት የሚታየው፣ ከልቡ የቆረበ ኢትዮጵያዊ፡፡”
ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን

Read 1344 times