Monday, 06 May 2019 12:17

ቃለ ምልልስ 11 ልጆች ከወለዱ በኋላ ወደ በረሃ ትግል የገቡት እናት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 በኢትዮጵያ ሴቶች ትግል ውስጥ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ጥቂት ሴቶች አንዷ ናቸው፡፡ በደርግ ዘመን 11 ልጆች ከወለዱ በኋላ ልጆቻቻን ጥለው ለትግል ወደ በረሃ ገብተዋል፡፡ የኢህአፓ ሠራዊት አባል በመሆንም ለ17 አመታት ታግለዋል፡፡ ከልጆቻቸው ይልቅ ለህዝብ መብት መታገልን የመረጡት እኚህ እናት፤ ከ42 አመታት የበረሃ ትግልና የስደት ኑሮ በኋላ ከሰሞኑ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ልጆቻቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የ87 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉነሽ አደራ፤ ስለ ትግል ህይወታቸው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

         - ለ17 ዓመት የኢህአፓ ሠራዊት አባል ሆኜ በበረሃ ታግያለሁ
         - ላለፉት 42 ዓመታት ከልጆቼ ጋር አልተገናኘሁም
         - ትግል ያሰለጠንኳቸው ልጆቼ ናቸው አሜሪካ የወሰዱኝ
         - አሁን የሚያስፈልገው ወደ ሰውነት ከፍታ መውጣት ነው

           እስቲ ከውልደትዎና እድገትዎ እንጀምር ----
እዚሁ አዲስ አበባ ነው የተወለድኩት:: እድገቴ ደግሞ አብዛኛውን አዲስ አበባ፣ ለተወሰነ ጊዜ ደግሞ ጅማ አድጌያለሁ፡፡ ስራ የጀመርኩት የቼኮዝሎቫኪያዎች ጥይት ፋብሪካ ውስጥ ነው:: እርሳስ፣ ጥይትና ባሩድን አገጣጥሞ ጥርት አድርጐ የሚያወጣ ማሽን ላይ ነበር የምሠራው፡፡ እዚህ ማሽን ላይ ሦስት አመት ከአምስት ወር ሠርቻለሁ:: እዚያ እየሠራሁ ሳለ አንበሳ አውቶቡስ ሴቶች ይቀጥራል ሲባል፣ እዚያ አመልክቼ በ60 ብር ደመወዝ ተቀጠርኩ:: እንግዲህ አንበሳ አውቶቡስ መስሪያ ቤት 20 አመት ሠርቻለሁ፡፡ 10 አመት በገንዘብ ተቀባይነት (ቲኬት ሽያጭ)፣ ቀሪውን አስር ዓመት ግን በቢሮ ውስጥ ነበር የሠራሁት፡፡
አንበሳ አውቶቡስ እያሉ፣ ሠራተኞችን ለፖለቲካ ትግል ያነሳሱ ነበር ይባላል፡፡ ስለሱ እስቲ ይንገሩን?
አዎ! በአንበሳ አውቶቡስ ውስጥ ማህበር መስርተን ነበር፡፡ እንደ መረዳጃ ማህበር ነበር የመሠረትነው፡፡ ማህበሩ ሠራተኞች ሲታመሙ የምንረዳዳበት፣ ሠራተኞች ያለ አግባብ ከስራ ሲባረሩብን በጋራ የምንጮህበት ነበር፡፡ የሹፌሮች መረዳጃ ማህበር ብለን ነበር የመሰረትነው፡፡ በኋላ በ1957 ዓ.ም የሠራተኞች አንድነት ማህበር ተቋቁሟልና እዚያ እንድትገቡ ተባልን፡፡ እኛም የመሰረትነውን ማህበር እንደያዝን የሠራተኞች አንድነት ማህበሩን ተቀላቀልን፡፡ በዚህ ማህበር በኩል የደመወዝ ጉዳይ፣ የሠራተኞች መባረር ሲያጋጥም ድምፃችንን እናሰማለን፡፡ በዚህ የመብት ማስከበር እንቅስቃሴ፣ ከጃንሆይ ፊት ቀርበን ድምፃችንን እስከ ማሰማት ደርሰን ነበር፡፡ በዚህ የሠራተኛውን መብት የማስከበር እንቅስቃሴያችን ከስራቸው የተባረሩትን ተሟግተን ወደ ስራቸው የማስመለስ፣ የማስመለስ ጥረቱ ካልተሳካልን ደግሞ  በሌሎች መስሪያ ቤቶች የማስቀጠር እንቅስቃሴ እናደርግ  ነበር፡፡ ከፍተኛ የመተባበር መንፈስ የነበረው ማህበር ነው፡፡ ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ እኔ እስከለቀቅሁበት 1968 ዓ.ም ድረስ ማህበራችን ጠንካራ ነበር፡፡
እርስዎ በሴቶች ትግል ውስጥ የነበርዎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል፡፡ እስቲ ስለዚያ ትግል ያስታውሱን?
እንደውም ድርብ ታጋይ ነበር የሚሉኝ:: የሴቶች ትግልን በፊት ለፊት የጀመርነው በአንድ አጋጣሚ ነው፡፡ አንበሳ አውቶቡስ ውስጥ ስንሰራ በመውለዳችን ከስራ ያባርሩን ነበር:: ሴቶች እየወለዱ አስቸገሩ ሁሉ ተብለናል፡፡ ድርጅቱ ከሠረ ብለው ነበር በአንድ ላይ ከስራ ያሰናበቱን:: እንደውም በ1968 ዓ.ም በዚህ ጉዳይ ላይ ቲያትር ሁሉ ሠርተንበት ነበር፡፡ ሴቶች ወለዱ ተብለን ነው እንግዲህ ከአንበሳ አውቶቡስ ተጠራርገን እንድንወጣ የተፈረደብን፡፡
ምን ያህል ነበራችሁ የተባረራችሁት?
ከ15 በላይ እንሆናለን፡፡ ሁላችንም እየወለዳችሁ ስራ በድላችኋል በሚል ነበር የተባረርነው፡፡
እናንተ ታዲያ ምን አማራጭ ተከተላችሁ?
ወዲያው የድርጅቱ አስተዳዳሪ፣ እኛን አስወጥተው፣ የራሳቸውን ዘመዶች ሊቀጥሩ ነው የሚል ክስ ነበር ለበላይ ኃላፊዎች ያቀረብነው:: ኃላፊው አቶ ተፈሪ ሻረው ነበሩ:: እሣቸው፤ “ልጆቼ እኔ ምን ላድርግላችሁ፣ መስሪያ ቤቱ ከሠረ ነው የሚሉን፤ መስሪያ ቤቱ እንዲከስር ማድረግ የለብኝም” የሚል ምላሽ ሰጡን:: እኛም በዚህ ሳናበቃ በወቅቱ የሀገር ግዛት ሚኒስትር የነበሩት ራስ አበበ አረጋይ ጋ ሄድንና አቤቱታችንን አቀረብን፡፡ ከብዙ ምልልስ በኋላ ነው እሣቸው ጋ የደረስነው፡፡ እሣቸውም ቀጥታ እኔን “ልጆች አሉሽ?” የሚል ጥያቄ ነው ያቀረቡልኝ፡፡ አዎ ስላቸው፤ “ታዲያ ችግሩ እሱ አይደል” የሚል መልስ ነው የሰጡን፡፡ በኋላም በቃ የ6 ወር ደመወዝ እየሰጣችኋቸው አሰናብቷቸው የሚል ትዕዛዝ ተሰጠልን፡፡ መስሪያ ቤቱም የ6 ወር ደመወዝ እንዲከፍለን ተደረገ፡፡ ያንን ብር ይዘን ወጣን፡፡ በኋላ አመለወርቅ ኢዴኤ የምትባል ጓደኛዬ ነበረች፡፡ አሁን እንኳ እሷን አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር የመጣሁት፡፡ መሞቷን ሰምቼ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ እሷ ለራስ አበበ አረጋይ፣ እኔ ደግሞ ለራስ ስዩም አመለከትን፡፡ በኋላ ሁላችንም ወደ ስራችን መመለስ ችለናል፡፡ ለመመለስ ግን ከፍተኛ ትግል ነበር ያደረግነው፡፡ እንዲህ ያለ ትግል ነው ስናደርግ የነበረው፡፡
ሠላማዊ ሠልፍም አስተባብረው ይመሩ ነበር  ይባላል?
አዎ፤ በ1968 “ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ” የሚል መፈክር ይዘን ወጥተን ነበር:: “ልጃገረዶች ት/ቤት ይግቡ፣ ይማሩ” የሚል ሠልፍም አካሂደናል:: “ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ” የሚለውን ንቅናቄ የጀመርንበት መነሻ፣ ወንድና ሴት ሠራተኞች እኩል እየሠሩ ክፍያ ላይ ግን ከወንዶቹ በግማሽ ያህል ያንሱ ነበር፡፡ ወንዱ 4 ብር ሲከፈለው፣ ሴቷ 2 ብር ነበር የሚከፈላት:: ይሄ ከፍተኛ በደል ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ በወቅቱ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ገና ታዳጊ ልጃገረዶች መማር ሲገባቸው፣ ቡና ለቀማ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር:: አሠሪውም እነዚህን ልጃገረዶች በአነስተኛ ዋጋ እየቀጠረ፣ ጉልበታቸውን ይበዘብዝ ነበር:: ይሄ ለምን ይሆናል በሚል ነበር ሠላማዊ ሠልፍ የወጣነው፡፡
ይህ ተቃውሟችሁና ጥያቄያችሁ ምን ምላሽ አገኘ?
በወቅቱ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ በኛ ላይ ጥርስ መንከስ ጀምሮ ነበር፡፡ “የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች፤ ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች” ተባለ፡፡ ወዲያው የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ሠራተኞች ኃላፊ የነበረችውንና ልትወልድ 15 ቀን ብቻ የቀራትን ዳሮ ነጋሽን ገደለ፡፡ ከሷ ጋር ስምንት የብርሃንና ሠላም ሠራተኞች ናቸው ተገድለው በአንድ ቀን የተቀበሩት፡፡ ያኔ እኔም ይህ እስኪገጥመኝ ቆሜ መጠበቅ የለብኝም ብዬ ነው፣ ወደ በረሃ ትግል የገባሁት፡፡ ዝም ብዬ ከምሞት አንድ ለአንድ ተናንቄ ለምን አልሞትም ብዬ ወደ ትግል ገባሁ:: እኔ ወደ አሲምባ 11 ልጆቼን ትቼ የገባሁት በዚህ መነሻ ነበር፡፡
ወደ አሲምባ ለትግል የገቡት ከእነማን ጋር ነበር?
ከሴቶች ጋር ነበር ወደ ትግል የገባሁት፡፡ እነ ፀዳለ፣ ሠላማዊት ዳዊት፣ ትርሲት (የተፈሪ በንቲ ልጅ)፣ ንግስት፣ ፍቅርተ ገ/ማርያም፣ ፀዳለ (የብርሃኑ እጅጉ እህት) እና ሌሎችም አብረውኝ ነበሩ፡፡
ልጆችዎን ትተው በረሃ ለመግባት መወሰን አያስቸግርም?    
ብኖርም እኮ አላሳድጋቸውም ነበር፡፡ ዳሮ ነጋሽ እኮ ልጆቿን አላሳደገችም፡፡ ህፃናት ልጆቿን ሜዳ ላይ በትና ነው የሞተችው፡፡ እኔ ብሞት ግድ የለኝም ነበር፣ ነገር ግን ለምን ታግዬ አልሞትም ብዬ ነው ልጆቼን ትቼ በረሃ የገባሁት፡፡ እኔ በረሃ ስገባ አንደኛዋ ልጄ በደርግ ተገድላለች፡፡ የ17 አመት ታዳጊ ተማሪ ነበረች፡፡ “የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች” ብሎ ስም ዝርዝራችንን ደርግ አውጥቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ልጆቼን ትቼ ወደ ትግል ከመውጣት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረኝም፡፡
የአሲምባ ቆይታዎስ ምን ይመስላል?
አሲምባ አንድ አመት ነበር የቆየነው፡፡ ከህወሓቶች ጋር በምንነጋገርበት ወቅት “እኛ ለትግራይ ነፃነት ነው የምንታገለው፤ እናንተ አማራ ናችሁ፣ ለአማራ ነው የምትታገሉት” በማለት “መሬታችንን ለቃችሁ ውጡ” አሉን፡፡ በኛ ላይ ጦርነት ከፈቱብን፡፡ ወያኔዎች ሁልጊዜ  ጦርነት የሚከፍቱት ህዝቡ ውስጥ፣ ት/ቤት ውስጥ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ነው:: እኛ ለእነሱ የመልስ ተኩስ ስንሰጥ የምናጠፋው የተከለሉበትን አካል እየሆነ ተቸገርን:: በመጨረሻ እኛ መሬቱን ለቀንላቸው ወደ በጌምድር ወጣን፡፡ በዚያም ትግላችንን ቀጠልን::
እርስዎ በየትኞቹ ጦርነቶች ላይ ነው የተሳተፉት?
በዚህ ቦታ ማለት አልችልም፡፡ ለ17 አመታት በረሃ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ በተመደብኩበት ቦታ ሁሉ ተሳትፎ አድርጌያለሁ፡፡ ከ1969 እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የኢህአፓ ሠራዊት አባል ሆኜ በበረሃ ቆይቻለሁ፡፡
ወደ በረሃ ሲገቡ የመጨረሻው ልጅዎ እድሜው ስንት ነበር?
አንድ ዓመት ከ7 ወር የሆነውን ልጄን ነው ትቼ የሄድኩት፡፡
ከዚያ በኋላ ከልጆችዎ ጋር ተገናኝተዋል?
ላለፉት 42 አመታት አልተገናኘንም:: ምክንያቱም ደርግ ሲወድቅ ስልጣን የያዘው ወያኔ ነው፡፡ ወያኔ ባለበት እንዴት ወደዚህ ሀገር እመጣለሁ? እንደውም ልጆቼ እንዳይታወቁብኝና ጥቃት እንዳይፈፀምባቸው በሚል በምንም መንገድ አላገኛቸውም ነበር፡፡
እርስዎ ወደ አሜሪካ እንዴት ሊሄዱ ቻሉ?
ያሳደግኋቸው፣ ትግል ያሰለጠንኳቸው ልጆቼ ናቸው መንገዱን አመቻችተው የወሰዱኝ:: በነገራችን ላይ የኢህአፓ ህዋስ በበርካታ የአለም ሀገራት አለ:: አውስትራሊያ፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ የመሳሰሉ ሀገራት የኢህአፓ ታጋዮችን የተቀበሉ ሀገራት ናቸው፡፡ ቀድመውኝ የወጡ ልጆቼ የምላቸው የትግል አጋሮቼ ናቸው የተቀበሉኝ፡፡
በ42 አመታት የበረሃና የስደት ቆይታዎ ልጆችዎን ለማግኘት ምንም ጥረት አላደረጉም?
የልጆቼ ደህንነት ያሳስበኝ ነበር፡፡ ስለዚህ እኔ የእነሱ እናት እንደሆንኩ እንዲታወቅ አልፈልግም ነበር፡፡ አሁን‘ኮ ዶ/ር ዐቢይ ሲመጣ ነው የመጣሁት::
ከእነዚህ አመታት በኋላ አሁን ልጆችዎን ማግኘት ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥራል?
በጣም አስደሳች ነው፡፡ የሞቱትም ሞተው ያሉትም ኖረው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ሶስት ልጆች ሞተውብኛል፡፡ አልቅሼ ለመቅበር እንኳ አልታደልኩም፡፡ አሁን ስምንቱ በህይወት አሉ:: ሶስቱ እኔ ጋ አሜሪካ መጥተዋል፡፡ አንዱ ጀርመን ነው ያለው፡፡ ቀሪዎቹ አራቱ እዚህ ነው ያሉት:: አላሳደገችንም ብለው አኩርፈው ሊያገኙኝ ያልፈለጉ ልጆቼም አሉ፡፡ አናውቃትም፤ አላሳደገችንም ብለው አኩርፈው ሰላም እንኳ አላሉኝም፡፡ እኔም ያሉበት ቦታ ሄጄ ሠላም እንኳ እንዳልላቸው ፈርቼ ቀረሁ፡፡ በዚህ መልኩ ያጣኋቸውም ልጆቼ አሉ፡፡
ባለፉት ከ50 አመታት በላይ እልህ አስጨራሽ ትግል ተደርጐ አሁን የለውጥ ተስፋ መጥቷል የሚሉ ወገኖች  አሉ፡፡ እርስዎ የታገልንለት አላማ ግቡን እየመታ ነው ብለው ያምናሉ?
ትልቅ ተስፋ ነው የተፈጠረው፡፡ ግን ህዝቡ ደግሞ አሁን ራሱን መግዛት፣ ራሱን መቆጣጠር፣ አርቆ ማስተዋል አለበት፡፡ ሰው ራሱን ይመልከት፤ እኔ ለሀገሬ ምን ላድርግላት ማለት አለበት፡፡ ይህ የለውጥ ተስፋ ፍሬያማ የሚሆነው ወደዚህ መንፈስ ካመራን ብቻ ነው:: ዋናው ነገር ሰው፣ ሌላው ሰው ላይ ከማተኮር ይልቅ  ራሱ ላይ ያተኩር፡፡ በ42 ዓመት ውስጥ የተፈጠረው ትውልድ ማድረግ ያለበት፤ ሰው ለመሆን መሞከር ነው፡፡ በብሔር ጐሣና ዘር መከፋፈል ከሰው በታች መውረድ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ወደ ሰውነት ከፍታ መውጣት ነው፡፡ እኔ ድሮ የማውቀውን የኢትዮጵያን ህዝብ ስነ ልቦና አይደለም አሁን እያየሁ ያለሁት፡፡
የሴቶች ትግልስ በኢትዮጵያ ፍሬ እያፈራ ነው ማለት ይቻላል?
አይ አይመስለኝም፡፡ እንዲሁ ልባስ ነው ያለው እንጂ ትክክለኛው የሴቶች ጥያቄ ጐልቶ አልወጣም፡፡ አሁን ያለው የመታያ ነገር ነው፡፡ ለውጭ ሀገር ሰዎች ለማሳየት የሚደረጉ ነገሮች ናቸው የሚበዙት፡፡ ዛሬም ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ የለም፡፡ ሴት ህፃናት በቤት ውስጥም በሌላም ቦታ ያለ እድሜያቸው ኃላፊነት ወስደው፣ ለጉልበት ብዝበዛ እየተዳረጉ ነው፡፡ እኩል የትምህርት እድል እያገኙ አይደለም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ግማሽ ካቢኔያቸውን ሴቶች አድርገዋል፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንትም ሴት ናቸው:: ይሄንንስ እንዴት ያዩታል?
እነሱ በስራቸው የሚመዘኑ ይሆናል፤ ለህዝብ ሠርተው ማሳየት አለባቸው፡፡ በተግባር የሴቷን ህይወት መቀየር ካልቻሉ፣ አሁንም መታያ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡
ልጆችዎን ትተው በረሃ በመግባትዎ የሚፀጽትዎት ነገር አለ?
ፈጽሞ የለም፡፡ ትቻቸው በመውጣቴ ምንም አይቆጨኝም፡፡ በአቅሜ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ 17 አመት በበረሃ ታግያለሁ፡፡ ለኔ ይሄ ለሀገሬ ያበረከትኩት አስተዋጽኦ ነው፡፡ ስለዚህ ባደረግሁት ሁሉ አልፀፀትም፡፡ ባደረግሁት ትግል እኮራለሁ፡፡
አሁን ላለው መንግስትና ህዝብ ምን ይመክራሉ?
ሹመት ማለት እዳ እንጂ ክብር አይደለም:: ሹመት ማለት ህዝብን የማስተዳደር ኃላፊነት ነው:: የተበላሸውን ስርአት ማቃናት ያስፈልጋል:: ላለፉት 40 ዓመታት የተበላሸ ስርአት ነው የነበረው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከመጣ በኋላ ህዝቡን ማረጋጋት ችሏል፡፡ ይሄን መረጋጋት ተጠቅሞ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል:: ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያዋጣው አንድ ላይ መቆሙ ነው፡፡ ኢህአፓ ሲታገል ከ14ቱም ክፍለ ሀገር በተውጣጣ ሠራዊት ነው፡፡
የልጅ ልጆች አግኝተዋል?
አዎ፤ በጣም ካስደሰተኝ ነገር ዋነኛው ይሄ ነው:: እዚያ በረሃ ሆኜ ተርፌ ልጆቼን አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ አሜሪካ ከገባሁ በኋላ ግን ፈጣሪን እድሜ እየለመንኩ፣ እንደው አንድ ቀን የልጅ ልጆቼን ሰብሰብ አድርጌ፣ መሃከላቸው ሆኜ፣ ፎቶግራፍ ለመነሳት እመኝ ነበር፡፡ ያ ምኞቴ ሠምሮ፣ አንድ ቀን ማታ፣ ከልጅ ልጆቼ ጋር ሆኜ ፎቶ ተነስቻለሁ፡፡    

Read 2122 times