Monday, 06 May 2019 12:31

“የተማረ አይራብም” … “የተማረ የት ደረሰ?”

Written by 
Rate this item
(2 votes)


                  ከአዘጋጁ፡-
   ጋዜጣችን አዲስ አድማስ የተመሰረተችበትን 20ኛ ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ታከብራለች:: የመጀመሪያው የአዲስ አድማስ ዕትም፣ ቅዳሜ ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር ለአንባብያን የደረሰው፡፡ ወደ 20ኛው ዓመት በዓላችን በሚያዳርሱን ጥቂት ወራት “የአድማስ ትውስታ” በሚል በሰየምነው በዚህ አዲስ ዓምድ፤ ከቀድሞ ዕትሞች እየመረጥን ጊዜውንና ጋዜጣችንን እናስታውሳችኋለን፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍ በመጀመሪያዋ  የአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ (ቅዳሜ ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም በቅፅ 1፣ ቁጥር 1 እትም) በ“ትምህርት” ዓምድ ላይ የታተመ ነበር፡፡ በትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ዙሪያ የሚያጠነጥን ፅሁፍ ነው:: ለትውስታ ብቻ ሳይሆን ለንፅፅርም ይሆናል፡፡ መልካም የትውስታ ጊዜ!!

      • “ሀ” ብለው ከጀመሩ 1000 ተማሪዎች መሀል ዩኒቨርሲቲ ገብተው ከዛም ለመመረቅ የሚበቁት ቢበዙ 2 ናቸው፡፡
      • ለትምህርት የሚመደበው በጀት በየዓመቱ እያደገ ነው፡፡ የ1992 በጀት በ1986 ተመድቦ ከነበረው በጀት በእጥፍ ይበልጣል፡፡
      • 1986 … 1.1 ቢሊዮን ብር
      • 1992 … 2.2 ቢሊዮን ብር
    
      በአንፃሩ ትምህርት በየጊዜው ከድጡ ወደ ማጡ ጥድፊያ ተያይዞታል፡፡ ወቅቱ የተማሪዎች የግማሽ ዓመት ፈተና ጊዜ ነው፡፡ ግን ስለ ፈተና ማውራት “ወገኛ” የሚያስብል ነው፡፡ “ሐምሌ ነሐሴ መጣ እየገሰገሰ ምንም ሳላጠና ፈተና ደረሰ” ድሮ የቀረ አባባል ነው፡፡ “ዓመት ከመልፋት የአንድ ቀን የአይን ጥራት” ማለት “ፋራነት” ወይም የዛሬ ተማሪዎችን ሁኔታ በወጉ ካለመገንዘብ የሚመጣ ስህተት ነው:: ለፈተና ደንታ የላቸውም፡፡ እንደ ድሮ “ለመኮረጅ” የሚፈፀም ጀብድ የለም፡፡ መኮረጅ ከተቻለ ተቻለ፣ ካልሆነ ደግሞ አልሆነም፡፡
“ዘመድ እስከ አክስት፣ ትምህርት እስከ ስምንት” የሚል አመፅም ጊዜው አልፎበታል:: አሁን የሰፈነው ግድ የለሽነትና ደንታ ቢስነት (Resignation) ነው፡፡ መውደድም፣ መጥላትም የለም፡፡ “እማራለሁ” የሚል ወኔ የለም፣ “አልማርም” የሚል አመፅም የለም፡፡
ተማሪና ወላጅ ትምህርት እንደሚመኙት ወይም መሆን እንደነበረበት እንዳልሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ሁኔታውን መለወጥ የሚቻል ግን አይመስላቸውም:: “የተማረ የት ደረሰ?” ወይም “የዘንድሮ ትምህርት፣ የዘንድሮ ተማሪ” ሲሉ ምሬታቸውንና ተስፋ መቁረጣቸውን ይገልፃሉ:: የአስተማሪው ስሜትም ይብስ እንደሆነ እንጂ የተሻለ አይደለም፡፡
“የእንጀራ ነገር ሆኖ ነው እንጂ አስተምረህ ለውጥ ስለማታመጣ መምህርነት ያስጠላል” ይላል፤ አንድ የ11ኛ ክፍል የሂሳብ አስተማሪ፡፡ ማስተማር ከጀመረ ገና አራተኛ ዓመቱ ቢሆንም፣ ጎበዝ አስተማሪ ነው እየተባለ በተማሪዎች የሚደነቅ ቢሆንም ከ4 ዓመት በፊት የነበረው ወኔ አሁን የለም፡፡ አስተማሪዎችም በትምህርት ሁኔታ እንደ ሌላው ሰው ግራ ተጋብተዋል፡፡ ለ31 ዓመታት ያስተማሩ አንድ መምህር፣ በየዓመቱ የተማሪዎች ጉብዝና እየቀነሰ፣ ስንፍና እየባሰ ሲሄድ መታዘባቸውን የገለፁት በግርምት ነው:: ዕድገት ያዩት በት/ቤቶች አጥር ላይ ብቻ ነው:: ልክ እንደ እሥር ቤት በየጊዜው በግንብ፣ በስብርባሪ ጠርሙስና በሚዋጋ ሽቦ የት/ቤቶቹ አጥር ሲረዝምና ሲጠናከር ይታያል፡፡
የትምህርት ዝቅጠት ላይ የሚሰማው ቅሬታ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይዘልቃል:: በርካታ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች፣ ከድሮ ጋር እያነፃፀሩ በዛሬዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድክመት ያዝናሉ፣ ይማረራሉ፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ረዳ እንደሚሉት ከሆነ፤ ተማሪዎች መፃህፍት ማንበብን እስከ መጥላት ድረስ ሄደዋል፡፡ እንደ ምንም ፈተናን ለማለፍ እንጂ ለማወቅ አይፈልጉም፡፡
ግን በእርግጥ እንደሚታመነው ትምህርት ዘቅጧል? ትምህርት ሚኒስቴር በየዓመቱ ትምህርት ነክ በሆኑ ጉዳዮች መረጃ አሰባስቦ ያሳትማል:: በመረጃው መሰረት፣ ከአብዮቱ በፊት 1ኛ ክፍል ተመዝግበው ትምህርት ከሚጀምሩ 1000 ተማሪዎች መሀል፣ በአማካይ 172ቱ 12ኛ ክፍል ድረስ ይማሩ ነበር፡፡ ከአብዮቱ በኋላ ይህ ቁጥር በፍጥነት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በ1978 ዓ.ም ትምህርታቸውን ከጀመሩ 1000 ተማሪዎች፣ 12ኛ ክፍል መድረስ የቻሉት 56 ብቻ ናቸው፡፡ በ15 ዓመት ውስጥ 12ኛ ክፍል ድረስ ለመማር ብቃት ወይም ትዕግስት ያላቸው የተማሪዎች ቁጥር በሶስት እጅ ቀንሷል ማለት ነው፡፡ ከ1ሺ ተማሪዎች 172 የነበረው ወደ 56 ዝቅ ብሏል፡፡
ከዚህ ጋር፣ ሦስትን በአራት ማባዛት የማይችል የ12ኛ ክፍል ተማሪ ለማግኘት አለማስቸገሩ ይጨመርበት፡፡ ዶ/ር ልዑልሰገድ አለማየሁ እንደሚሉት፤ ማንበብና መፃፍ እንደ ነገሩ የለመዱ መሃይም የ12ኛ ክፍል ምሩቃንን ነው እያየን ያለነው:: ከ56ቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ውጤት የሚያገኙት 4 ወይም 5 ብቻ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ዲግሪያቸውን ለመቀበል የሚበቁት ቢበዛ ሁለት ናቸው፡፡ 1ኛ ክፍል “ሀ” ብለው ከጀመሩ 1ሺ ተማሪዎች፣ ዲግሪ የሚያገኙት አንድ ወይም ሁለት ናቸው፡፡
የት/ሚ አሃዝ፣ የአስተማሪዎች አስተያየትና በየአጋጣሚው የምናየው የተማሪዎች ዝቅተኛ አቅም፣ በትክክል ትምህርት አይወድቁ አወዳደቅ እንደደረሰበት ያመለክታሉ፡፡ ከዓመታት የገንዘብ ወጪ እንዲሁም የጉልበትና የአዕምሮ ድካም በኋላ፣ ተማሪዎች የሚያገኙት አንዳንድ እንግሊዝኛ ቃላትን ብቻ ነው፡፡ የኔታ ደህና አድርገው ካስቆጠሯቸው ፊደልና ቁጥር በተጨማሪ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ከትምህርት ቤት ከሚገኙ የእንግሊዝኛ ቃላት ይልቅ ከቪዲዮ ፊልም የሚለቃቀሙ ይበዙ ይሆናል፡፡
እያንዳንዱ የትምህርት ዘመን፣ የተማሪውን የመኖር አቅምና ችሎታ የሚያዳብር እውቀትና የማሰብ ክህሎት መስጠት ነበረበት፡፡ “ትምህርት ያገኘ የሚሰራውን አያጣም” እንደሚሉት ዶ/ር ልዑልሰገድ፡፡ አሁን ግን ለጥቂት ጠንካራ ልጆች ካልሆነ በቀር ትምህርት ለኑሮ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ያለ አይመስልም፡፡ 12ኛ ክፍልን ከጨረሰ ተማሪ ይልቅ የት/ቤትን በር ያልረገጠ ገበሬ፣ የበለጠ የመኖር ብቃት፣ ለመኖር የሚያስችል እውቀት አለው፡፡ አርሶና ኮትኩቶ ራሱን ያኖራል፡፡
ተማሪ ከክፍል ክፍል ሲሸጋገር እውቀቱ እየሰፋ፣ የማሰብና የመፍጠር ችሎታው እየጨመረ መሄድ ነበረበት፡፡ እያወቀ፣ እየበሰለ ሲሄድ ራሱን የቻለ፣ በራሱ የሚተማመን ስለዚህም ደግሞ ደስተኛና ሰውን አክባሪ ይሆናል፡፡ እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ነው:: ጭራሽ በመጀመሪያ የትምህርት ዓመታት ያወቃቸው መሰረታዊ የሳይንስ ፅንሰ ሃሳቦች ዓመታት ባለፉ ቁጥር እየደበዘዙበት ይሄዳሉ፡፡ የተካነው የማሰብ ብልሃት ይሳሳል፣ ይጠፋል፡፡ ከዓመታት የት/ቤት ምልልስ በኋላ አዕምሮው በውዥንብር የተዋጠ. በራሱ የማይተማመን፣ ደስታን ማጣጣም የማይችል፣ ስነ ምግባር የጎደለው ወጣት ብቅ ይላል:: “የተማረ የት ደረሰ?” ሲባል መልሱ ይህ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሃገሪቱ የትምህርት ፖሊሲም እንደሚያምነው፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁምነገር ያለው ምርምርና ጥናት የሚያካሂዱ “ችግር ፈቺ ምሁራን”ን ለማፍራት አልቻሉም:: በአብዛኛው ከተቋማቱ የሚወጡ ምሁራን፣ የመንግስት ቢሮክራሲ ምቹ ዕቅፍን የሚመኙ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ትምህርት የቅርብ ጊዜ ታሪክ “የውድቀት ታሪክ” ሊባል ይችላል፡፡
ማን ተሻለ? የመላ ያለህ
የ31 ዓመት የማስተማር ልምድ ያካበቱት አስተማሪ፣ የተማሪዎች አቅም ከዓመት ዓመት እየተመናመነ እንደሆነ ቢገልፁም “ለምን ይሆን? ምን ይሻላል?” ተብለው ሲጠየቁ፣ እርግጠኛ መልስ አልነበራቸውም፡፡ ጥያቄዎቹ ሁሌም ግራ የሚያጋቧቸውና የሚያስጨንቋቸው እንደሆኑ ነው የገለፁት፡፡ ይሁንና የትምህርት ቤት አጥር ማስረዘም ዋጋ እንደሌለው ጠቁመው፣ ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን ከባህል ጋር የተያያዘ የስነ ምግባር ትምህርት ለመስጠት ቢሞከር ይሻላል ብለዋል፡፡
ሥነ ምግባር
 ስለ ትምህርት ውድቀት ሲነገር የተማሪዎች ስነ ምግባርም አብሮ ይነሳል፡፡ የተማሪዎች ለትምህርት ደንታ ቢስ መሆንና ጠቅላላ የስነ ምግባር እጦት ለትምህርት ውድቀት አስተዋፅኦ እንዳደረገ የሚያምኑ አሉ፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትምህርት ሚኒስቴር፣ ስነ ስርዓትን በተመለከተ ጠንካራ ዕርምጃዎችን ወስዷል፡፡ የት/ቤቱ አጥሮችን ከማጠናከር ጀምሮ በዓመት ከ20 ቀን በላይ የቀረ ተማሪን እስከ ማባረር፣ ተማሪዎች ዩኒፎርም እንዲለብሱ፣ በትምህርት ቤቶች የወላጅ፣ የዲሲፕሊን እንዲሁም የተማሪ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ማድረግ ወዘተ …፡፡ የተሰራው መጥፎ ነው ባይባልም፣ መፍትሄነቱ ግን ሲበዛ አጠራጣሪ ነው፡፡
ታላቋ የትምህርት ሰው ማሪያ ሞንቴሶሪ፤ “ሰው በተፈጥሮ የማወቅ ፍላጎት ስላለው፣ ልጆች እንዲማሩ፣ እንኳን ቅጣት … ሽልማትም አያስፈልጋቸውም” ትላለች፡፡ መጠነኛ እገዛ ካገኙና ሁኔታዎች ከተመቻቸላቸው፣ ልጆች ከምንም በላይ በትምህርት፣ በእውቀት፣ በምርምር የሚደሰቱና የሚመሰጡ እንደሆኑ ዶ/ር ሞንቴሶሪ ትገልፃለች:: በተግባርም ሰርታ በማሳየት፣ በመላው ዓለም ታዋቂነትንና አድናቆትን አግኝታለች፡፡ ልጆች ትምህርት ካገኙ ደስተኛና መልካም ስነ ምግባር የተላበሱ ይሆናሉ ነው፣ እሳቤው፡፡ ዶ/ር ልዑልሰገድ በዚህ ይስማማሉ፡፡ ወጣቶች ለእንዝህላልነትና ለምግባረ ብልሹነት የተጋለጡት ትምህርት ስላላገኙ ነው ይላሉ፡፡ ዶ/ር ልዑልሰገድ፣ ወጣቶች ትምህርት አላገኙም ሲሉ ት/ቤት አጥተዋል ማለታቸው ሳይሆን ት/ቤት ሄደው የሚያገኙት ነገር የላቸውም ማለታቸው ነው፡፡
ማንም ሰው ጥቅም የሌለውን ነገር እንዲወድ ወይም እንዲያከብር አይጠበቅም፡፡ ተማሪዎች ከት/ቤት ይገኛል የሚባለው ጥቅም እንደሌለ ሲያዩ፣ ት/ቤትን እንደ እስር ቤት ቢመለከቱ፣ አስተማሪን ቢንቁና ቢያላግጡበት አያስገርምም፡፡ በተለይ የመምህራን ስድብ፣ ግርፍያና ምክንያት አልባ ባህሪይ ሲታከልበት:: የትምህርት ውድቀት ከተማሪዎች ስነ ምግባር ጉድለት የመጣ አይደለም፡፡
በተገላቢጦሹ፣ የትምህርት ውድቀት፣ የተማሪዎቹ ምግባረ ብልሹነትን አባብሷል:: በባህሪያቸው መጥፎ የሆኑ ጥቂት ተማሪዎች ይኖሩ ይሆናል፡፡ አብዛኞቹ የስነ ምግባር ጉድለት የሚታይባቸው ተማሪዎች ግን ትምህርት ስላጡ እንጂ በባህሪያቸው መጥፎ ስለሆኑ አይደለም:: ከዚህ በተጨማሪ የተማሪዎች ስነ ምግባር ጉድለት የተጋነነ ነው፡፡ የመጨረሻ አስቸጋሪ የሆነው ተማሪ ሳይቀር ጎበዝ አስተማሪን ያከብራል፡፡ ለነገሩ የአንደኛና የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ የትምህርት ድክመት፣ እንዴት በስነ ምግባር ጉድለት ሊሳበብ ይችላል?
ሥርዓተ ትምህርት
ት/ሚኒስቴር ይበጃል ያለውን አዲስ ስርዓተ ትምህርት ቀርፆ፣ ከ1ኛ እስከ 9ኛ ክፍል ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በሚቀጥሉት 3 ዓመታትም በተቀሩት ክፍሎች በየደረጃው እንዲሰራበት ታቅዷል:: የሥርዓተ ትምህርት ዋነኛ መገለጫ መማሪያ መፃህፍት ናቸው፡፡ ለዚህም አዳዲስ መፃህፍት ተዘጋጅተው ታትመዋል፡፡
በቀድሞው ስርዓተ ትምህርት መሰረት በፖለቲካ፣ ታሪክ፣ እንግሊዝኛና አማርኛ መፃህፍት ውስጥ ታጭቀው የነበሩት ኢ-ሳይንሳዊ የማርክሲዝም ቀኖናዎችና ፕሮፓጋንዳዎች እንዲወጡ ተደርጓል:: ሌላው ለውጥ የትምህርቱ ደረጃ ከፍ መደረጉ ነው:: ለምሳሌ የ9ኛ ክፍል ትምህርት የነበረው የ7ኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲማሩት ተደርጓል፡፡ ለትምህርት ጥራት እንደሚያግዝ በት/ሚኒስቴር የታመነበት የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ከሞላ ጎደል ተጠናቋል፡፡
ሥርዓተ ትምህርት፣ ለትምህርት ጥራት ወሳኝ እንደሆነ ብዙዎች የትምህርት ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለዚህ ወሳኝ ሚና ብቃት ይኑረው አይኑረው ግን ብዙዎችን ያከራክራል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ ህዝቦች ክልል፣ ከ1990 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች 27 በመቶ ያህሉ ነበር የወደቁት፡፡ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በ8ኛ ክፍል ተግባራዊ በሆነበት በ1991 ዓ.ም ግን ከ50 በመቶ በላይ ወድቀዋል፡፡
ትምህርቱ፣ ካላቸው የማስተማር አቅም በላይ ሆኖ፣ መምህራን ለት/ሚኒስቴር ቅሬታ ማሰማታቸውን በማስረጃነት ጠቅሰው “አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የኢትዮጵያን ሁኔታ ያላገነዘበ ነው” ይላሉ ምሁራን፡፡ በፖሊሲ ደረጃ የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን ቢያንስ የዲፕሎማ ምሩቃን መሆን አለባቸው፡፡ ሆኖም በት/ሚኒስቴር መረጃ መሰረት፣ ወደ 110 ሺ ከሚጠጉ የ1ኛ ደረጃ መምህራን መሃል መመዘኛው የሚያሟሉ 7ሺ አይሆኑም፡፡
መመዘኛውን ከሚያሟሉት መምህራን ውስጥ ደግሞ 20 በመቶ የሚገኙት አዲስ አበባ ነው፡፡ ያም ሆኖ፣ ባለፈው ዓመት፣ በ8ኛ ክፍል ፊዚክስና ኬሚስትሪ ለማስተማር አቅም ያለው አስተማሪ ባለመሟላቱ፣ ለወራት ሳይማሩ ለፈተና የተቀመጡ ተማሪዎች አሉ፡፡ በክልሎች ሊኖር የሚችለውን ሁኔታ መገመት ይቻላል፡፡
ሌላው አስቸጋሪ ሁኔታ በአዳዲሶቹ መፃህፍት የሚታየው የማስተማሪያ ዘዴ ነው፡፡ እንኳን ተማሪዎች አስተማሪዎችም መፃህፍቱን አንብበው ለመረዳት ተስኗቸዋል፡፡ አዳዲሶቹ መፃህፍት ግንዛቤና ዕውቀትን ሳይሆን ሽምደዳ - በቃል መያዝና ማነብነብን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የአሲድ ምንነትን ሳያውቁ፣ የተለያዩ የአሲድ ዓይነቶችን አስቸጋሪ ስሞች እንዲሸመድዱ ያደርጋል፡፡
ጎበዙ ተማሪ በቃሉ ሊይዛቸው ቢችልም፣ ፈተና አልፎ ዓመቱ ሲያልቅ ተጠራርገው ከአእምሮው ይጠፋሉ፡፡ ባይጠፉም ምንም አይፈይዱለትም፣ አያውቃቸውምና፡፡
ዶ/ር ሞንቴሶሪ እንደምትለው፤ የትምህርት ዋነኛ ዓላማ፣ ተማሪዎች አንዳንድ ነገሮችን ሲያውቁ፣ በዛውም በጣም አስፈላጊ የሆነውን የማሰብ፣ የመመራመር ክህሎት እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው:: ተማሪዎች ራሳቸው እየሞከሩ፣ ቢያንስ ቢያንስ ሙከራዎችን ከመፃህፋቸው እያነበቡ ካልተማሩና መሸምደድ ላይ ካተኮሩ፣ ምንም ሳያውቁ፣ የማሰብና የማገናዘብ ክህሎት ሳይካኑ ይቀራሉ፡፡ በዚህ መመዘኛ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አሳሳቢ የሆነውን የትምህርት ዝቅጠት ያቃልላል ተብሎ አይታሰብም:: ሥርዓተ ትምህርቱ ጥሩ ቢሆን እንኳ የትምህርት ጥራት ይሻሻላል ማለት አይቻልም፡፡ ት/ቤቶቻችንን እኮ እናውቃቸዋለን፡፡
የግል ት/ቤቶች
የአሜሪካ መንግሥት ለትምህርት የሚመድበው በጀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በ1960 ሲያወጣ ከነበረው 345 ዶላር፣ በ1996 ለአንድ ተማሪ በዓመት ወደ 6 ሺ ዶላር እስከ ማውጣት ደርሷል (World Almanac ‘97):: የአገሪቷ የትምህርት ጥራት መመዘኛ ፈተና (SAT) የሚያመለክተው ግን ከ1963 እ.ኤ.አ ጀምሮ ያለማቋረጥ የተማሪዎች አቅም እየቀነሰ መምጣቱን ነው፡፡ የአሜሪካ ህዝብ በሁኔታው እጅጉን ከመጨነቁ የተነሳ ሮናልድ ሬገን ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ፣ ለትምህርት ዝቅጠቱ መፍትሄ እንደሚሰጡ በምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ያነሱት አብይ ነጥብ ነበር፡፡ ሬገን፣ የትምህርት ሚኒስቴር መ/ቤት እንዲፈርስና ለትምህርት የሚመደበው በጀት ለእያንዳንዱ የተማሪ ወላጅ እንዲሰጥ ነበር ሃሳባቸው፡፡
አንድ ተማሪ በግል ት/ቤት ለመማር በአማካይ በዓመት ከ2 እስከ 3ሺ ዶላር ይበቃዋል፡፡ ለምሳሌ ለሁለት አመት የኮሌጅ ትምህርት የሚከፍለው 6,316 ዶላር ነው (World Almanace ‘97):: በፕሬዚዳንት ሬገንና በደጋፊዎቸው ሃሳብ መሰረት፣ ለትምህርት ውድቀት ዋነኛ ምክንያት የመንግስት ት/ቤቶች ናቸው፡፡ የመንግስት ት/ቤቶች፣ ወላጆች፣ የልጆቻቸውን የትምህርት ሁኔታ እንዳይከታተሉ እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ ብዙ ሰው ሃሳቡን በመንግስት ላይ ይጥላል፡፡ የልጆቻቸውን ትምህርት በጥብቅ የሚከታተሉ ጠንካራ ወላጆች እንኳ ልጆቻቸውን ራሳቸው ካላስተማሩ እምብዛም ለውጥ አያመጡም:: ት/ቤት ድረስ ሄደው በአስተማሪው ወይም በትምህርቱ አይነት ላይ ቅሬታና አስተያየት ለመስጠት ቢፈልጉ የሚሰማቸው አይኖርም:: ደካማና ባለጌ አስተማሪን የሚያባርር ወይም ትጉህና ጎበዝ አስተማሪን የሚንከባከብ የመንግስት ት/ቤት አይኖርም፡፡ ካባረረም በግል ቂምና ጥላቻ እንጂ ለትምህርት ጥራት በመጨነቅ አይሆንም:: ለትምህርት ጥራት የሚጨነቅ፣ ተጨንቆ ለውጥ ለማስገኘት የሚያስብ፣ ያሰበውን የሚተገብር ወይም ለመተግበር የሚችል ሰው፣ የመንግስት ት/ቤት ውስጥ አይገኝም፡፡
የትምህርት ጥራት እንዲኖር ት/ቤቶች ባለቤት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የሚሰጠው ትምህርት ጥራት ከሌለው ደንበኞቼ ይሸሹኛል ብሎ የሚጨነቅ፣ የትምህርትን ጥራት ይበልጥ ባሳድግ ደንበኞቼ ይበዙልኛል ብሎ የሚያቅድ ባለቤት ያስፈልጋቸዋል:: ፕሬዚዳንት ሬገን፣ ት/ሚኒስቴርን የማፍረስ ሃሳባቸው በተለያዩ ምክንያቶች አልተሳካላቸውም:: ይሁን እንጂ ትምህርት ሚኒስቴር ለአንድ ተማሪ ከሚያወጣው 6 ሺህ ዶላር ግማሹ እንኳ ለወላጆች ቢሰጣቸው፣ ልጆቻቸውን በጥሩ የግል ት/ቤት ማስተማር ይችላሉ፡፡ ይህ ያልተሳካ የሬገን ሃሳብ፣ ዛሬ በተለያዩ የአሜሪካ ስቴቶች እየተሞከረ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የግል ት/ቤቶች ብዛት በጣም ጨምሯል፡፡ ትምህርት ከገባበት አዘቅት የሚወጣበት ተስፋ ካለ፣ ትልቁ ተስፋ በእነዚህ ት/ቤቶች ነው፡፡ ወላጆች፣ የልጆቻቸውን ትምህርት እለት ተእለት የመቆጣጠር ባህል እንዲያዳብሩ ያደርጋል፡፡ መምህራንና ዳይሬክተሮች ከምር - የማሳወቅ ስራ ላይ መሰማራታቸውን እንዳይዘነጉ ያስገድዳል፡፡ ጠያቂ፣ ተቆጣጣሪ ወላጅ አለና፡፡
ይህ አሰራር በትንሹም ቢሆን ወደ መንግስት ት/ቤቶች ሊገባ የሚችልበት ዕድልም ይፈጠራል፡፡ ወላጆች ብዙ ብር ስለከፈሉ ብቻ ቁጥጥራቸውን፣ ክትትላቸውን ቸል ካሉ ግን ያው የግሎቹም እንደ መንግስት ት/ቤቶች ይሆናሉ፡፡

Read 6132 times