Monday, 06 May 2019 12:57

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)


                     “ቅን አስተሳሰብ ለባለቤቱ መኖሪያ ገነት ነው”
                    
            ረቡዕ ዕለት የሰራተኞች ቀን (May Day) ተከብሯል፡፡ ነገ ደግሞ ዳግማዊ ትንሳኤ ነው፡፡ ሁለቱም ከትግልና ከመስዋዕትነት የተወለዱ የረዥም ጉዞ ስንቅ፣ የአዲስ ተስፋ ብስራትና የመጪው ብሩህ ዘመን ወጋገን ናቸው፡፡ በአንድ አጋጣሚ ክርስቶስና ማርክስ የልብ፣ የልባቸውን እየተጨዋወቱ ይስቃሉ፡፡
“ጌታ ሆይ” አለ ማርክስ፡፡
“ጌታ ሆይ አትበለኝ አላልኩህም?”
“ይቅርታ! ያውም በሜይዴይ ሰሞን…እ?”
“የጌታና የባሪያ ስርዓት አልፏል ለማለት እንጂ እኔ ሌኒን አይደለሁ እንደፈለግህ ልትጠራኝ ትችላለህ”
“ሞተህ ከተነሳህ ሁለት ሺ ዓመታት አለፉ፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል?...ሞተህ በሶስተኛው ቀን ተነስተሃል የሚባለው ዕውነት ነው?”
“ትጠራጠራለህ እንዴ?”
“በስጋማ እንዴት ይሆናል?...በመንፈስ ብርሃን እንጂ፡፡ እንደዛማ ቢሆን አይሁድ ‹መሲሃችን ገና ይመጣል› እያሉ አይዝናኑም ነበር፡፡”
“መቃብርህ ሲከፈት አስከሬንህ መች ተገኘ ታዲያ?”
“መች ተገኘ?...እንዴት ይገኛል?...በሶስተኛው ቀን ይነሳል ብለው ስለፈሩ በተሰቀልኩ ዕለት ሌሊት ላይ ነው ከሳሾቼ ያቃጠሉት፡፡ ለነገሩ ‹ካፈርኩ አይመልሰኝ› ሆኖባቸው እንጂ መስቀሌ ብቻውን ሲያርግ አይተዋል፡፡”
“መስቀሉንማ ወደ ምድር መልሰኸዋል አሉ፡፡ እንደገና ልትሰቀልበት ነው እንዴ? አሁንም ህዝቦችህ ‹ናልኝ ሰቆቃ በዝቶብናል› እያሉ ያለቅሳሉ፡፡
“ሞኛችሁን ፈልጉ በላቸው፡፡ በራሴ አካልማ እንደገና አልገለጥላቸውም፡፡ ጋንዲን ሆኜ ብመለስ ገደሉኝ፣ ስፒኖዛን ሆኜ ብወለድ አስቀየሙኝ፣ ማንዴላን መስዬ ብሔድላቸው አሰሩኝ፣ በፀጋዬ ገ/መድህን በኩል ዕውነቱን ብነግራቸው አላከበሩኝም:: ማዘር ቴሬዛን የሆንኩላቸው ጊዜ ትንሽ ተሽሏቸው ነበር፡፡ በራሴ ገላማ ያንን መስቀል እንደገና አልሸከምም፡፡ ዕድሜ ለቤንኸር (Benhour)!...ያኔም ከጐልጐታ የደረስኩት እሱ ስላገዘኝ ነው”
“አሁን መስቀሉ የት ነው ያለው?”
“አዲስ አበባ”
“አዲስ አበባ?...ያውም አፍሪካ?” በማለት ከጠየቀ በኋላ መልሶ፤ “አዎን፣ አዎን፣ ልክ ነው ሰምቻለሁ” በማለት አስታወስ፡፡ ማርክስ ቀጥሎም “መስቀል ከሰማይ ወረደ” ተብሎ ጉድ ሲባል ነበር፡፡ እዛ እንዲሆን ለምን ፈለግህ?”
“የናቴ ቅደመ አያት የሰለሞንና የሼባ የልጅ ልጆች እንዲሁም ወደፊት እኔ የምገለጥባቸው ሰዎች የሚገኙት እዛ ስለሆነ ነዋ!፡፡ ደግሞም…”
“ደግሞ ምን?”
“ዘመዶቼ እስከዛሬ ድረስ ማንነታቸውን ለማወቅ የተቸገሩበትን ሚስጢር ለመፍታት፣ እንዲሁም በዳግማይ ትንሳኤ ስም የራሳቸውን መንግስት እንዲያቋቁሙ ለመርዳት የተላከ ምልክት ነው፡፡”
“ምን የሚባል መንግስት ነው የሚያቋቁሙት?”
“ዮቶፒያ (UTOPIA)!”
“እ?...የኮምዩኒስቶቹን ዓይነት?”
“አትቀልድ!”
“እሺ፡፡ የመስቀሉ ሚስጢር ምንድነው?” ነገረው:: ማርክስ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ምን ብሎት ይሆን?
***
ወዳጄ፡- ዕውቀት የስልጣኔ ማበልፀጊያ፣ ያዲስ ነገር ማፍለቂያና የአውሬነት ባህሪያችንን ገርተን ትሁት የምንሆንበት ፀጋ መሆኑ ቀርቶ ሌሎች ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን የምንገፋበት አጋርነት የምንነፍግበት ወይም ራስ ወዳድነትን የምናዳብርበት መሳሪያ ካደረግነው አላወቅንም:: መንገድ ስተናል፡፡ ምናልባትም ሞተናል፡፡ ነገ የሚከበረው የዳግማይ ትንሳኤና ባለፈው ረቡዕ የተከበረው የሰራተኞች ቀን (May Day) በዓላትን ስናስብ ግን እንደገና የመወለድ፣ እንደገና የመንቃት፣ እንደገና የመነሳትና እንደገና የመኖር ተስፋ አለ፡፡
ወዳጄ፡- “ሰው ሁለት ጊዜ ይወለዳል” ይባላል፡፡ አንድም በአካል፣ አንድም በዕውቀት፡፡ አሟሟቱም ሁለት ዓይነት ነው፡፡ በአካልና በአእምሮ፡፡ ሰው ከተወለደና ካደገ በኋላ ለምን እንደሚኖር፣ እንዴት እንደሚኖር ካላወቀ፣ በአካባቢው ስላሉት የተፈጥሮ በረከቶች አነሳስና አወዳደቅ ወይም መጀመሪያና መጨረሻ ካልተረዳ፣ ካልተወለዱት ወይም ጨርሶ ከሌሉት አይሻልም፡፡ መልካም ፍሬ ከማያፈራ፣ አበባው ከማያምር “ጥቅም አልባ” ዛፍ ወይም ሲቀምሱት ከሚመር፣ ሲበሉት ከሚመርዝ ፍሬ ወይም የተዘሩ እንዳይበቅሉ፣ የበቀሉት እንዳያድጉ ማነቆ ከሚሆን አረም በምን ይለያል?
ወዳጄ፡- በአካል የሞተ ሰው። በአእምሮውና በዕውቀቱ ሊኖር እንደሚችል፣ አእምሮው ሞቶም አካሉ ሊቆይ ይችላል፡፡ መልካም ሰዎች፤ ሊቃውንትና ተመራማሪዎች፣ ደራሲዎች፣ ሰዓሊና ቀራፂያን፣ ሙዚቀኞችና ሌሎች አርቲስቶች፣ ማሰብና መፍጠር የቻሉ ሁሉ “ዘለዓለም” ይኖራሉ፡፡ የስልጣኔ ፋና ወጊ ናቸውና፡፡
እንደ ግብፅ ፈርዖኖች አዕምሯቸው ሞቶ፣ አካላቸው እንደ ዕቃ ተሞሽሮ “የሚኖሩ” አስከሬኖችም አሉ፡፡ በኬሚካል Preserve የተደረጉ፡፡ “በቁም የሞቱ ወይም በሌሎች ሳንባ የሚተነፍሱ” የሚባሉም ብዙ ናቸው፡፡ አካላቸው እየተንቀሳቀሰ፣ እየበሉ እየጠጡ፣ በትክክል ማሰብ የማይችሉ፤ ማንነታቸው ወይም የኑሮ ከፍታቸው በአስተሳሰብ ልቀት የተገኘ ሳይሆን በሌሎች ራስ ላይ በመቆማቸው እንደሆነ ያልገባቸው ከንቱዎች!
ወዳጄ፡- ቅን አስተሳሰብ ለማህበራዊ ኑሮ ዋነኛ መሰረት ብቻ ሳይሆን ለአሳቢው ወይም ለባለቤቱ መኖሪያ ገነትም ነው፡፡ ጥልቅ እፎይታና ሰላም እዛ ውስጥ ይገኛል፡፡ “አንዳንድ ጊዜ” ግን በእንደዛ ዓይነት ስሜት (mood) ከሚብሰለሰል ሰው ጊዜን መስረቅ መሞከር ላያስደስተው ይችላል፡፡ ፈጠራው የሚፀነሰው በዛ መንፈስ ስለሆነ ፈቃደኛነቱን ሳንገምት የምናደርገው ጣልቃ መግባት፣ ፍቅራችንን ለመለገስና ብቸኝነቱን ለመጋራት በማሰብ ቢሆንም “ችላ” ቢለን ወይም ቢሸሸን ግር ልንሰኝና ልንቀየም አይገባም፡፡ ምክንያቱም ለብቻ መሆን መፈለግ (to be alone) እና ብቸኛ (lonly) መሆን ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸውና፡፡
“As a rule a man is socialble just in the degree in which he is intellectually poor and generally vulgar” በማለት የሚያረጋግጥልን ታላቁ ሾፐን ሃወር ነው፡፡
በነገራችን ላይ “Space” በሚለው የእንግሊዘኛ ቃል “S” በካፒታል ሌተር ስትፃፍ ትርጉሙ ከአካልና የባዶ ቦታ ዝምድና ማሳያነት በዘለለ የአእምሮና የሃሳብ መጨናነቅንና የነፃነት ፍላጐት መገለጫ እየሆነ ይነበባል፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- መስቀል አዲስ አበባ ላይ ከሰማይ የመውረዱ ሚስጢር ክርስቶስ ሲጠየቅ የመለሰው፤ “ስማቸው በ “ተ” ፊደል የሚጀምር ሰዎች ከላይ ለተጠቀሰው “Clan” መሪነት የተመረጡ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው” በማለት ነበር፡፡ እውነቱን ከሆነ፣ እኔም በበኩሌ “ተመስገን” የሚለው “የብዕር ስሜ” ወደ ዕውነትነት እንዲቀየርልኝ ለፍ/ቤት አመለክታለሁ፡፡ አንተም ወዳጄ፡- “ዩቶፒያ” የቅዠት አገር ነው” እያልክ የምታወራውን ነገር አልወደድኩትም፡፡ ክልል የሌለን ዜጐች የት እንኑር ታዲያ?
ሠላም!!

Read 952 times