Monday, 06 May 2019 12:58

ከስብሃት ትዝታ፤ ጠብታ

Written by  መኮንን ሽፈራው
Rate this item
(10 votes)


      “--እዚህ ጋ አንድ ታክሲ ወደ እግረኛው መስመር እጅግ ተጠግቶ፣ ስብሃት መሄድ የፈለገበትን አቅጣጫ ጠራ። ጋሼ ስብሃት ከተደገፈበት ግንብ ተላቅቆ፣ ፌስታሉን አንጠልጥሎ፣ ወደ መኪናው በኩል ተራመደ። ተከትዬው ወደ ታክሲው ተጠጋሁ። ዞሮ አቀፈኝ። ፈረንሳዮቹ የሚወዱትን ሰው ሲሰናበቱ እንደሚያደርጉት
አንገቴን በእጁ እቅፍ አድርጎ፣ ጉንጮቼን እያፈራረቀ ሳመኝ። በጆሮዎቼም አንሾካሾከ--”
    
           የአዲሱ ሚሊኒየም የመጀመሪያ ዓመት። እኔና ጓደኛዬ ሄኖክ፣ የአንድ የሌላ ጓደኛችን ሰርግ ላይ አምሽተን ወደ ቤታችን እናዘግማለን። አራት ኪሎ። እኛ ልንገባበት ከነበረበት የሚኒባስ ሆድ ገናናው ደራሲ ወጣ። እኔ አላየሁትም ነበር። ሄኖክ ነው እንጂ ስሜን ጠርቶ ሲያበቃ፣ “ስብሃት! ስብሃት!” ያለው። ዞርኩኝ። ስብሃት! ከመኪናው ጋቢና  ወረደ። ዓይኔን ጨፍኜ ገለጥኩ። ያ! ጉርምስናዬን ሙሉ ሳወድሰው የኖርኩት የምንጊዜም ምርጥ መምህሬ ከፊቴ ለፊቴ ቆሟል። እንዴት አርጅቶ  ኖሯል?! ዕድሜ እንደ ሎሚ የጨመቀው ኮስማና ሽማግሌ። ልቤ እዚያው በዚያው ተሰበረ።
“የጠሉት ይወርሳል፣ የፈሩት ይደርሳል” የሚለው አባባል ውስጤ ገነነ። በ“ሌቱም አይነጋልኝ”፣ በ“ትኩሳት” እና በሌሎቹም ልቦለዶቹ ደራሲው ተጎፍንኖና ተፀይፎ የገለፀው እርጅናን አሁን እንደ ቡልኮ በአሜን ተጎናፅፎ፣ ወጣት መዓዛውን ጊዜ ወስዶ፣ የእርጅና ሽታ ሲለጥፍበት ተቀብሎ፣ የማይቀርልህን እንግዳ አጥብቀህ ሳመው ብሎ፣ ከእርጅና ጋር ተቃቅፎ፣ እፊቴ ቆሟል - ሽማግሌው።
ስለ እሱ ስናገር መጥቶብኝ የማያውቅ፣ ከዚያ በኋላም ቢሆን ያልተጠቀምኩበት፣ አንቱታ ወዲያውኑ አፌን ሞላው።
“እንደምን አመሹ ጋሼ ስብሃት?” አልኩት።
እጄን ለሰላምታ ዘረጋሁ። በአፀፋው የተጨበጠ ቡጢ ሰደደልኝ። ለአፍታ ግራ ተጋባሁ። ለእሳት የላሰው ትውልድ የተዘጋጀ ዘመነኛ ሰላምታ  መሆኑን ገመትኩ። እጄን መልሼ እንደ እሱው ቆልምሜ ቡጢውን ገጨሁት። ይህ ሰው የሚባለውን ያህል ግልፅ ደራሲ አይመስለኝም። በስነ-ፅሁፍ ስራዎቹ ውስጥ፣ አያሌ ሚስጥራትን ሸሽጎ፣ ላይ-ላዩን በሳቅና በፈገግታ ሊሸውደኝ ሲሞክር፣ ብዙ ጊዜ ሚስጥራቱ ድንገት ብልጭ እያሉብኝ፣ ተደንቄአለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንዳንድ ቃለ-መጠይቁና በአንዳንድ የፅሁፍ ስራዎቹ መግቢያ ላይ እንደጠቀሰው፤ ይሄንን ትውልድ  “እሳት የላሰው ትውልድ” በማለት ይጠራዋል። ምክንያቱንም አብራርቷል። እኔ በግሌ ግን፣ ስለዚህ ትውልድ (በተለይ እሱ የ‘Naturalism’ ዘውግን/ይትበሃልን ተከትሎ ከሰራቸው ልቦለዶቹ ዘመን አንጻር) የሚሰማውን የአያዎ ስሜት የገለፀበት ሀረግ ይመስለኛል። በአንድ ወቅትም ስለዚሁ ስሜቱ “እሳት የላሰው ትውልድ” በሚል ርዕስ ስር  የሚከተሉትን ስንኞች አኑሬአለሁ።
አንተ ታላቅ ጠቢብ - እውነት ተናግረሃል
እሳት የላሰው ነው - ትውልዱን ብለሃል
ብቅ ሲል ካንገቱ - እሳት እየላሰው
እንደ በልግ ጀምበር - ጉም እየወረሰው
ከበጎው ጋር ሁሉ፣ መርገም ተለግሶት፣
መምከን መች ይነሰው
የደስታው ሰንሰለት - ሃዘን ከጎተተ
ለመውለድ ተኝቶ  - ሲነሳ ከሞተ
በብዙ ሲያበቅል - ብዙ ካሳጨደ
ፈክቶ መክሰም እንጂ - ሌላ መች ለመደ
አሁንም  ሰላምታው ቅኔያዊ ሆነብኝ። ግራ መጋባቴን አስተውሎ አጉተመተመ።
“ያዝ ባክህ! እንትህን ባራገፍክበት እጅህ....”
ከሰላምታው በኋላ እኔና ሄኖክ መንገዳችንን ትተን፣ እሱን እያዋራን ወደ ኋላ ተመለስን። እሱ በሚሄድበት የሜክሲኮ አደባባይ ታክሲ ተሳፈርን። እያጫወተንና እያጫወትነው ሜክሲኮ ደረስን። ከዚያም ሌላ ታክሲ መያዝ ነበረበት። እኛም ሰዓታችን ሄዷል። ከምንጊዜም ምርጥ ሰውዬዬ ጋር ያለኝ ቆይታ አጠረብኝ። ሌላ ቀን አግኝቼው በሰፊው ልናወራበት የምንችልበት ዕድል ይኖረን ዘንድ የመጨቅጨቅ ያህል ወተወትኩት። እሱ ግን ተስፋ በቆረጠ ስሜት “የእኔን ነገር ተወው። የፃፍኳቸውን ካነበብክ ይበቃሃል።” አለኝ።
ደግሜ ለመንኩት።
“እባክህን ተወኝ፡፡ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ተገናኝተን ቢሆን ይሆን ነበር:: አሁን እኔም እራሴ ነገ የት እንደምሆን አላውቅም።”
የፍቅሬን ያህል ልመናዬ በረታ።
“እባክዎትን?”
ቀጥሎ የሆነው ፈፅሞ ያልጠበቅኩት ነበር። ፊቴ በሃይለኛ ጥፊ ሲነረት ተሰማኝ። የጋሼ ስብሃት መዳፍ በሚያስደንቅ ፍጥነት ተወርውሮ ጉንጬ ላይ አርፏል። ካንገቴ አጎነበስኩ። ፊቴን ወደ እሱው አቀረብኩለት። ሌላኛውን ጉንጭ አዙሮ የመስጠት አይነት ነበር። ምን ማለቴ እንደሁ እንጃ። እርሱ ግን እጁን ዳግም ሰድዶ፣ በድጋሚ ጥፊ ፈንታ፣ አንገቴን አቀፈኝ። ምን ያህል አስጨንቄው እንደነበር  ዘግይቶ ታወቀኝ።
Dilemma በተሰኘው የአሜሪካኖች ዘፈን ውስጥ ሴቷ Kelly ለወዳጇ Nelly በምትጠቀመው ውብ ቋንቋ “you don’t know what you mean to me” አልኩት።
ትከሻዬን ይዞ ከእርምጃዬ አቆመኝ። የመኪና መንገድ መሃል ላይ ነን። በግራና በቀኛችን ዕድሜ-ጠገብና ዘመናዊ መኪኖች በአስፋልቱ ወደ ኋላና ወደ ፊት ሲፈስሱ ይሰማናል። እግረኞች መንገዱን ሲያቋርጡ አንገታቸውን እየቆለመሙ ወደ እኛ ይገላመጣሉ። ወጣቶችና ቆንጆ፣ ቆንጆ  ሴቶች “ስብሃት!” እያሉ ከርቀት ሲጠቋቆሙ ይታዩናል። ኩርማን ጨረቃ ፍዝ ብርሃኗን ትወረውርብናለች። እጅግ ከወደድኩት “ሌቱም አይነጋልኝ” ከሚለው ድርሰቱ ውስጥ፣ መነሻ ሃሳብና ብዙ ቃላት ሰርቄ  የፃፍኳት ሚጢጢ ግጥም እውስጤ ሰረፀች።
በምሽት፣ አንድ ሃምሳ ከዋክብት ለቅሜ ከሰማይ
በማለዳ፣ አንድ ወርቃማ ጮራ መዝዤ ከፀሀይ
እና ከዋክብቱን በጮራው ቀጣጥዬ
ልስራልሽ ሀብል ውድዬ
ከእሱ ጋር ዝም ብሎ መተያየቱ ሲረዝምብኝ፣ ቀና ብዬ ጨረቃዋን ተመለከትኩ። ቁራጭ ናት፤ እሷም በፊናዋ፣ አጮልቃ ተወዳጁን ደራሲ የምትመለከት መስላለች። በአንድ ወቅት “እኔ አፈጣጠሬ እንደ ንጉስ ነው። በየሄድኩበት ፍቅር እንደተነጠፈልኝ ነው” ያለው ታወሰኝ።
ሌላ ምን ታወሰኝ?
በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ግማሽ አመታት ከነበሩት ስመ-ጥር ደራሲዎች አንዱ ነው። ሩድያርድ ኪፕሊንግ። ከእንግሊዛዊ ቤተሰቦች በህንድ አገር ተወልዷል። አያሌ ተወዳጅ ረዣዥምና አጫጭር ልቦለዶችን ፅፏል። ዘመን ተሻጋሪ የግጥም ስራዎች አበርክቷል። “If” የተሰኘች ግጥሙ ለምሳሌ፣ በእንግሊዝ አገር በተሰራ “Public Opinion Poll” መሰረት፣ ባገሬው ህዝብ ምንጊዜም ከሚወደዱ ምርጥ አምስት ግጥሞች ውስጥ አንዷ ሆና ተካትታለች። በፈረንጆቹ 1989፣ የመጀመሪያ ስራው የሆነውን የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ፣ ገና በ23 ዓመት ዕድሜው አሳትሞ ዝነኛ መሆን ከጀመረ በኋላ፣ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ተጓጉዞ ነበር፤ ለሽርሽር። እግረ መንገዱን ታዲያ፣ ወደ ኒው ዮርክ ከተማ አቅንቶ፣ የዕድሜ ዘመን ኮከቡን፣ አንጋፋውንና ስመ ገናናውን Samuel Clemens (ማርክ ትዌይን)፣ በገዛ ቤቱ ተገኝቶ የመጎብኘት ብርቅ ዕድል ገጥሞት ነበር። ለሁለት ሰዓታት፣ ሲጋራ እየተቀባበሉ ጭምር እያጤሱ፣ ይወያያሉ፡፡ An Interview with Mark Twain በምትል መለስተኛ መጣጥፉ፣ ኪፕሊንግ፣ ለማርክ ትዌይን ያለውን ጥልቅ ስሜትና ፍቅር “man I had learned to love and admire fourteen thousand miles away” ሲል መቼም በማይዘነጋ መልክ ይገልፃል፡፡ “እጅ ለእጅ ተጨባበጥን….ትከሻዬን ተደገፈኝ” ይለናል፡፡
ስብሃት ጉሮሮውን ጠራርጎ ተናገረ። ድምፁ ከሆዱ ግድም አቋርጦ የሚመጣ ይመስላል። ሸካራና ዘገምተኛ ነው። ጆሮ ውስጥ የመሰንበት፣ ልብ ላይ የመክረም፣ ከአዕምሮ የመጣበቅ ፀጋ አለው።
“ሁላችንም የግዜር ትንፋሾች ነን።” አለ
“እውነት ልንገርዎት?” አልኩት “ደራሲ መሆን እፈልጋለሁ። የእርሶ የአፃፃፍ ስልት ይመስጠኛል። እርስዎን አግኝቼ ትምህርት ለመቅሰም መፈለግ ከጀመርኩ ዓመታት ተቆጥረዋል።”
“ይኸውልህ ስማኝ” አለኝ “ሁለት ነገር እነግርሃለሁ። ልብህ ንፁህ እስከሆነና  ሰው መውደድ እስከቻልክ የምትፅፈው ሁሉ ጥሩ ሆኖ  መውጣቱ አይቀርም።”
“ይሄ በቂ ነው?”
“ንባብ ጨምርበት”
“እሺ፣ እርስዎ የሚያደንቁት፣ እኔን እንዳነበው  የሚመርጡልኝ፣ እና እርስዎን የማስታውስበት መፅሐፍ ይጠቁሙኝ?”
“አደፍርስ!”
“ከውጪስ?”
“ሼክስፒር። ማንኛውም ስራው። እንግሊዝኛው ካልከበደህ”
ይሄን ብሎኝ ወደዚያ በኩል ዞረ። አብሬው ዞርኩ። ከፊታችን፣ ነጭ ሱሪ ምጥን ገላዋ ላይ የተለጠፈባት፣ ቅርፀ ሸጋ ወጣት፣ መንገዱን ታቋርጣለች። የስብሃት ጉልህ ዓይኖች የልጅቱ ለግላጋ ሰውነት ላይ ተንከባለሉ። ተከትለናት:: አስፓልቱን ስንሻገር፣ ስብሃት አጉተመተመ። “እዚህ ስታደርቁኝ ስንትና ስንት ቆንጆ አስመለጣችሁኝ።”
መአት ታክሲዎች ተደርድረው ወደ ቂርቆስ የሚጭኑበት ተራ ደረስን። መንገዱ ዳር አንድ የግንብ አጥር ተደገፍን። ሄኖክ ፈንጠር ብሎ  ቆሞ ያየናል። ስብሃት ከቅድሙ በተሻለ  አሁን መለያያችን ሲደርስ ሊያወራኝ የጓጓ መሰለ። ሄኖክ በስልኩ ለማስታወሻ የሚሆን  ፎቶ እንዲያነሳን ጠየቅኩት። ስብሃት ወደ እኔ ስር ተጠጋ። የካሜራው ብርሃን ግን የአካካቢውን ጨለማ ማሸነፍ አቃተው። ስብሃት እራሱ “ቆይ! መኪና ሲያበራብን ጠብቀህ አንሳን” አለው። ያም ሊሆን አልቻለም። ዝም ብለን ወሬአችንን ቀጠልን።
“የልቦለድ ገፀ-ባህሪዎችዎ ከልቤ አይወጡም።” አልኩት
“የእውነት ሰዎች እኮ ናቸው” አለኝ
“ሁሉም?”
“ሁሉም!”
እነ ፀሃይ፣ እነ ማሚት፣ እነ ክንፈ፣ እነ ሲልቪ፣ እነ አጋፋሪ እንደሻው----በዓይነ ህሊናዬ መጡብኝ። ተከታትለው አለፉ።
“አሁን ልቦለድ ቢፅፉልን አሪፍ ነበር።”
“እየፃፍኩ እኮ  ነው። ቆይማ ርዕሱን ልንገርህ። እማሆይ ጸዳለ-ማርያም (እና ባሎቻቸው)”
ሳቅኩኝ።
“ገብቶሃል?” አለኝ
“አዎን!” አልኩት
“መነኩሲት ናቸው እኮ” አብሮኝ ተገረመ።
መንገዱ ዳር፣ ታክሲዎቹ ውስጥ ቁጭ ብለው፣ ታክሲዎቹ እስኪሞሉ የሚጠባበቁ ወጣት ሴቶች፣ ስብሃትን በመንገድ መብራቶቹ ብርሃን ታግዘው በርቀት እያዩ፣ በመኪኖቹ የመስታወት መስኮቶች በኩል ከርቀት እያሻገሩ፣ እጃቸውን ከፈገግታ ጋር ያውለበልቡለታል። እሱም ከፈገግታ ጋር በምልክት ያጫውታቸዋል። ከእኔም ጋር ወሬውን ቀጥሏል።
“እንደ እርስዎ ዓይነት ደራሲ የሚመጣ አይመስለኝም።” አልኩት፡፡ ፈፅሞ በስሜት ተሞልቼ ነበር፡፡
“ማን ያውቃል? አንተም ትሆን ይሆናል።” አለ
ዝም አልኩ።
“በእግዚአብሄር አታምንም እንዴ?” ጠየቀኝ።
አሁንም ዝም አልኩ።
ራሱ ጥያቄውን ቀጠለው። “ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በአንድ ስዕል ውስጥ፣ የቤት መዝጊያ ሲያንኳኳ አላየህም?”
“አይቻለሁ።”
“ታዲያ፣ ያንተን ልብ እኮ ነው የሚያንኳኳው። ከከፈትክለት ነው የሚገባው።”
አንዳች የምጠይቀውን ጥያቄ በውስጤ ሳውጠነጥን፣ ቀደም ብሎ የጀመረውን ዓረፍተ ነገር ከቆይታ በኋላ ጨረሰው።
“ሰይጣን ቢሆን በርግዶት ይገባል!”
እዚህ ጋ አንድ ታክሲ ወደ እግረኛው መስመር እጅግ ተጠግቶ፣ ስብሃት መሄድ የፈለገበትን አቅጣጫ ጠራ። ጋሼ ስብሃት ከተደገፈበት ግንብ ተላቅቆ፣ ፌስታሉን አንጠልጥሎ፣ ወደ መኪናው በኩል ተራመደ። ተከትዬው ወደ ታክሲው ተጠጋሁ። ዞሮ አቀፈኝ። ፈረንሳዮቹ የሚወዱትን ሰው ሲሰናበቱ እንደሚያደርጉት አንገቴን በእጁ እቅፍ አድርጎ፣ ጉንጮቼን እያፈራረቀ ሳመኝ። በጆሮዎቼም አንሾካሾከ።  
“ሁላችንም የእግዜር ትንፋሾች ነን።”
ተሰናብቶኝ ሲያበቃ፣ ከታክሲው የፊት ክፍል ገብቶ፣ የዳሯን ወንበር ይዞ ተቀመጠ። በመስታወቱ አሻግሮ እኔ ወዳለሁበት ተመለከተ። የእጆቹን መዳፎች አገጣጥሞ፣ ደረቱ ላይ አስደግፎ፣ ከአንገቱ ዝቅ ብሎ፣ የመጨረሻ የስንብት ምልክቱን አሳየኝ። በመልዕክቱ ተግባብተናል። “I bow to the divinity in you!”/ውስጥህ ላለው መለኮት እጅ እነሳለሁ!/ ማለቱ ነው። አፀፋውን መለስኩለት። ሂሳቡን አውጥቼ  ለረዳቱ ሰጠሁለት። ተመልሼ የእግረኛው መንገድ ላይ ወጥቼ፣ የታክሲውን መነሳት ተጠባበኩ። ከደቂቃዎች በኋላ መኪናው ሞልቶ፣ ሞተሩ ተነስቶ፣ ወደ ፊት በዝግታ ተንቀሳቀሰ። ስብሃት እና እኔ ለመጨረሻ ጊዜ በጭላንጭሉ የጨረቃ ብርሃን እንደ ምንም ዓይን ለዓይን ተያየን። ታክሲው ፍጥነቱን ጨምሮ ተፈተለከ። ልቤ ተከትሎት ተሰደደ።
ከዚህ ትሁት መምህሬ ጋር የነበረኝ ረዥም የግንባር ለግንባር ቆይታ ይኸው ነበር። በዚህች ውትብትብ ዓለም ውስጥ፣ የራሱን ዝቅ ያለች፣ ውብ፣ ማራኪና ሰላማዊ መንገድ ቀይሶ፣ በዚያችው መንገድ በቆራጥነት ለዓመታት ተመላልሶ፣ ያለፈ አንድ የማውቀው ልባም እሱው ነበር። ክብርን ሳይፈልጋት በብዛት የበተናት እሱው፣ በብዛት የሰበሰባትም እሱው ሆኖ  ይሰማኝ ነበር። ይሄንኑ ስሜቴን በአንድ ወቅት ለራሴው እንዲህ ስል ልገልፀው ሞክሬ ነበር - በእነ ኪፕሊንግ ቋንቋ፡፡  
“Pride is not important in life but it actually is
Blessed are those who gain it in their effort to loose!”
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው መጣጥፍ የአንጋፋውን ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር፣ መጪ የልደት ቀንን  ምክንያት በማድረግ፣ መኮንን ሽፈራው የተባሉ ጸሃፊ የላኩልን “ዝክረ ስብሃት” ሊባል የሚችል የማስታወሻ ጽሁፍ  ነው፡፡ ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 749 times