Monday, 06 May 2019 13:01

የአጭር አጭር ልቦለድ) ከሞት ሽሽት

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(19 votes)

   ሰሌዳ ላይ ጠመኔ እያንከባለልኩ ነው:: እረፍት የለሽ ነፍስ ያሰቃየችው ተማሪ «ሚስተር፤ እኔ ግን መሞት አልፈልግም» አለኝ፡፡ መች ጠየኩትና ነው --የሚዘላብደው፡፡ ወፈፌ! እንዴት እንዴት ነው -- የሚያናግረው ባካችሁ --- ጭንጋፍ!
ወደ ተማሪዎቼ ስዞር ሁሉም በአርምሞ ተዘፍቀዋል፡፡ ለካ ቆሞ ነው -- የሚቀባጥረው፡፡አይን ላይን ተፋጠጥን፡፡ ቀጥል የሚል ምልክት በግንባሬ አሳየሁት፡፡
«ሞት በጣም እፈራለሁ...» ሲል ሁሉም ተማሪዎች ማለት ይቻላል --ሳቁበት፡፡ ከኔ ጋ ግን እንደተፋጠጥን ነን፡፡ እጁን አወራጨና፤
“ሞትን ለማጥፋት ስለ ሴል አጠናለሁ:: የማይሞት ህዋስ እሰራለሁ፡፡ ለዚህ ነው -- ባለፈው ምን መሆን ትፈልጋለህ ስትለኝ -- ሳይንቲስት ያልኩህ» አለ፡፡
አሃ...የሚል ምልክት አሳየሁት፡፡ የተዝናና መንፈስ ተላበሰ፡፡ ለማሰብ ጥረት እያደረገ ይመስላል --- ሰከነ፡፡ ጥቅርሻ ፊቱ የበለጠ ጠቀረሸ፡፡ ፈገግ አለ፡፡ ጥቅጥቅ ጨለማን ሰንጥቆ የሚወርድ መብረቅ ያህል በለጨ -- ጥርሱ፡፡
የልጆቹ ፀጥ ረጭ ማለት -- አስገርሞኛል:: የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች በመሆናቸው -- ህልም መስሏቸው ይሆን? ለነገሩ ሞት ቆሞ ታይቷቸው ቢሆንስ? የዛሬ ልጅ ምን የማይታየው ነገር አለ፡፡
«ግን ሚስተር!  ሞት በማሪያም ፈረስ ነው - - እሚመጣ!... የማሪያም ፈረስ ጅራት አላት እንዴ? ባያት ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ጀርባዋን አይቼ ሞት ምን እንደሚያክል ማወቅ እችላለሁ፡፡»
«እንዴ... በረከት ...ትንጥዬ ናት እኮ፡፡ ዝንብ መሸከም የማትችል -- ቀጭን!» አለች - ትንጧ አና፡፡
«ባይንሽ አይተሻታል?» ጠየቀ፤ በረከት፡፡
«አዋ» አለችው፡፡
ጭንቅላቱን ቆፋፈረ፡፡
«እና ሚስተርዬ...የሞት መዳኒት ሳይኖር ቀርቶ ነው ... ይኸ ሁሉ ሰው ሲያልቅ ዝም የሚባለው?... ያሳዝናል፡፡ እኔ ግን ሰው ሲቀበር ማየት አልፈልግም፡፡»
ወይ  ጉድ ምኑን አሰማህኝ፡፡ መጨረሻህን ያሳየኝ! ያባቴ አምላክ ከዚህ ጉድ በገላገለኝ፡፡እንዴት እንዴት ነው -- እሚያናግረው፡፡
«ሳይንቲስት እሆንና ወደ ጨረቃ እሄዳለሁ፡፡ እዛ ሞት የለም አይደል?”
ኸረ ከኔ ራስ ውረድ... አንድየ ተስፋዬን ሊያስነጥቀኝ፡፡ ሆሆ... የምድሩ አነሰኝ! ደሞ ይሄ አሪዎስ በተማሪዎቼ ተመሳስሎ ይምጣ፡፡
«ከዛ ሄጀ አልመለስም፡፡ ምክንያቱም ስሞት እንዳይቀብሩኝ፡፡»
በሰው ላይ ያለ መከራ ... ነፍሴ ልትነጠለኝ ነበር -- ተመለሰች፡፡ እሱም ተቀመጠ፡፡ እኔም በምልክት እንደመለስኩለት ምንም ሳልተነፍስ፣ የውስጤን እሳት አምቄ፣ ወደ ጥቁር ሰሌዳዬ በመዞር ጠመኔ ማንከባለል ቀጠልኩ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 4883 times