Monday, 13 May 2019 00:00

ህጋዊ መስፈርት ያሟሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ከ20 አይበልጡም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 41 አዲስ ፓርቲዎች ምዝገባ እየተጠባበቁ ነው

           በሀገሪቱ በህጋዊነት የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች 66 ያህል ቢሆኑም የምርጫ ቦርድን የፓርቲ ህልውና ህጋዊ መስፈርት ያሟሉት ከ20 አይበልጡም ተባለ፡፡
41 አዳዲስ ፓርቲዎች የምዝገባ እውቅና ሠርተፊኬት እየተጠባበቁ ሲሆን በጠቅላላው 107 የፖለቲካ ድርጅቶች በህጋዊም ህጋዊ ሰውነት ሳይኖራቸውም በሀገሪቱ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በፓርቲዎች ምዝገባ ዙሪያ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶልያና ሽመልስ ገልፀዋል፡፡
ከአርባ አንዱ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወሰኑት ነባርና በውጭ ሀገር የነበሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል - አማካሪዋ፡፡
በሀገሪቱ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙት 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ 66 ያህሉ ህጋዊ ሠርተፊኬት ያላቸው፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ፓርቲ አቋቁመው ከቦርዱ ህጋዊ ሠርተፊኬት የሚጠባበቁና ከውጭ ሀገር መጥተው ሀገር ውስጥ ፓርቲ ለማደራጀት አስፈላጊ ሰነዶችን ከምርጫ ቦርድ የወሰዱ መሆናቸውን ወ/ት ሶልያና አብራርተዋል፡፡
በቦርዱ ከተመዘገቡ 66 ፓርቲዎች። 24ቱ ሀገር አቀፍ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 42 ክልላዊ ፓርቲዎች ናቸው ተብሏል፡፡  ከእነዚህ 66 የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ግን በየጊዜው ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ፣ የስራ አስፈፃሚ መሟላት የመሳሰሉና ሌሎች የፓርቲ ህልውና መስፈርቶችን ያሟሉት ከ20 እንደማይበልጡ ወ/ት ሶልያና ተናግረዋል፡፡ የስም ለውጥ ያደረጉት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አዲሱ ስያሜያቸው ገና በምርጫ ቦርድ እውቅና አለማግኘቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኦዴፓ የስም ለውጥ ማድረጉ እንዲፀድቅለት ማመልከቻ ማስገባቱንና ጉዳዩ በሂደት ላይ መሆኑን የገለፁት የህዝብ ግንኙነት አማካሪዋ፤ አዴፓ በበኩሉ ስለ ስያሜ ለውጡ ማመልከቻ አስገባለሁ ማለቱን ጠቁመው፣ የሁለቱ ፓርቲዎች የስያሜ ለውጥ ላይ ቦርዱ ተሰብስቦ እንደሚወስን አስረድተዋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሀገሪቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች በህግና ስርአት ለማስተዳደር የተሻሻሉ የምርጫ ህጐች መጽደቅን እየተጠባበቀ መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 9301 times