Print this page
Monday, 13 May 2019 00:00

ማህበራዊ ፍትህን ርዕዮተ ዓለሙ ያደረገው አዲስ ፓርቲ መሪዎቹን መረጠ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

                     • ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የፓርቲው መሪ ሆነው ተመረጡ
                     • የ“አርበኞች ግንቦት 7” ሰራዊትን በ3 ሚ. ብር ያቋቁማል

                ዜግነትን የፖለቲካ መሰባሰቢያ መርሁ፣ ማህበራዊ ፍትህን ርዕዮተ ዓለሙ ያደረገው አዲሱ “የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ” ፓርቲ የተመሰረተ ሲሆን የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ ሆነው የተመረጡ ሲሆን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሠፋ፣ ም/ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ መ/ር አበበ አካሉ ደግሞ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ ሆነዋል፡፡
ከ320 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች የወረዳ ም/ቤቶችን መስርቶና በወረዳ ደረጃ አስቀድሞ ተዋህዶ መስራች ጉባኤውን ትናንትናና ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ያደረገው ፓርቲው፤ በመጪው አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ከወዲሁ በሙሉ ኃይሉ ዝግጅት ያደርጋል ተብሏል፡፡
ከመላ አገሪቱ የተወከሉ 1800 አባላት በተሳተፉበት ፓርቲው የሁለት ቀናት መስራች ጉባኤ፣ የፓርቲው ደንብ፣ የፖለቲካ ፕሮግራምና ፖሊሲ የፀደቀ ሲሆን በጉባኤው 1200 አባላት በድምፅ መስጠት ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደነበሩ ታውቋል፡፡
መስራች ጉባኤው በሐሙስ ውሎው የ“አርበኞች ግንቦት 7” የሰራዊት አባላትን ለማቋቋም የቀረበለትን ሃሳብ ተወያይቶበት በ243 ድጋፍ፣ በ18 ተቃውሞና በ14 ድምፀ ተአቅቦ አፅድቋል፡፡ በዚህም መሰረት፤ የቀድሞ የ“አርበኞች ግንቦት 7” ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፤ የሰራዊት አባላቱን የማቋቋም ኃላፊነት እንዲወስዱ የተወሰነ ሲሆን ሰራዊቱን ለማቋቋም 3 ሚሊዮን ብር ከፓርቲው እንዲመደብም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
አዲስ በተቋቋመው ፓርቲ ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሆነው የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው ፖለቲከኞች በአመራርነት እንዳይሳተፉ ተወስኗል፡፡
የ“አርበኞች ግንቦት 7” ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌና የንቅናቄው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በውሳኔው መሰረት የአመራርነት ቦታ አላገኙም፡፡ ሁለቱ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች በማማከርና ድጋፍ በመስጠት ብቻ ይወስናሉ ተብሏል፡፡
የፓርቲው መሪና ም/መሪ ሆነው የተመረጡት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዷለም አራጌ፣ በፓርቲው የአደረጃጀት ስልት መሠረት፣ በቀጥታ ለመንግስት ስልጣን በብሔራዊ ምርጫ ፓርቲውን እየመሩ የሚወዳደሩ ሲሆን፤ የፓርቲው ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋና ዶ/ር ጫኔ ከበደ ደግሞ የፓርቲውን የእለት ተእለት የፖለቲካ ስራ የመምራት ኃላፊነት እንደሚኖራቸው ታውቋል፡፡
“ማህበራዊ ፍትህን” መሰባሰቢያ ርዕዮተ ዓለማቸው፣ የዜግነት ፖለቲካን መርሃቸው አድርገው የተዋሃዱት ፓርቲዎች ሰማያዊ፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ ኢዴፓ፣ መኢዴፓ፣ አትፓ፣ የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ፣ የቀድሞ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ አመራሮችና ሌሎች ግለሰብ ፖለቲከኞች መሆናቸው ታውቋል፡፡

Read 10485 times