Sunday, 12 May 2019 00:00

በፀረ ለውጥ ኃይሎች እጁን የተያዘ መንግሥት

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

ኢህአዴግ የአራቱ ክልል ገዥ ፓርቲዎች፣ የጋራ ድርጅት መሆኑ የሚጠፋው ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ሕወሓት ኢህአዴግ፣ እያልን ስንጽፍ የነበርን ሰዎች፣ ኢሕአዴግ ጠፍቶን ሳይሆን ኢሕአዴግ የሚባለው ድርጅት በራሱ ነፍስ የሌለውና በሕወሓት ደምና አጥንት የሚንቀሳቀስ መሆኑን ስለምናምን ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ የሕወሓትን የበላይነት አስረግጦ ለማሳየትም ነው፡፡
የፌደራል መንግሥቱን ሥልጣን የያዘው ገዥ ፓርቲ አባል የሆነው ሕወሓት፤ የበላይነቱ ከቀረ ወይም ቀረ ከተባለ አንድ አመት አልፏል:: በዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው “ኢሕአዴግ”፣ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘም አመት ሞልቶታል:: ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ  አንድ ወይም ሁለት ወር ውስጥ የሚደነቁ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ ብዙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ አድርገዋል፡፡ ከተፈቱት ውስጥ በተለይ ጥርስ የተነከሰባቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ የዋልድባ መነኮሳት፣ ጀኔራል አሳምነውና አቶ መላኩ ፈንታ ይገኙበታል፡፡ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ውሉ ያልለየለት ፍጥጫ በማስቀረት፣ ሁለቱ ህዝቦች በአየርና በምድር እንዲገናኙ በማድረግ በወሰዱት እርምጃም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡  
ለውጥ ፈላጊው ሕዝብና የለውጡ መሪ የሆነው ኃይል፣ ጠላቶች ግን ሁኔታው አስገድዷቸው ወዳጅ ያደረጋቸው መሆናቸውን አስቀድሜ ማስጨበጥ እፈልጋለሁ፡፡ አልተቻለም፣ አይቻልምና ነው እንጂ የሚቻል ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ በለውጥ መሪነት ወንበር ላይ ተቀምጦ የሚገኘው ምድረ ኢሕአዴግ፣ ከዳር እስከ ዳር ተለቅሞ፣ ባለፉት 27 ዓመታት፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለሠራው በደል እንደ ጥፋቱ መጠን መጠየቅ፣ ቅጣቱንም መቀበል ያለበት እንደነበር ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የዶ/ር ዐቢይ “ሕዝብ ይቅር ብሎ አንድ ሌላ እድል ሰጥቶናል” የሚለው አነጋገርም፣ ይህንኑ የድርጅቱንና የድርጅቱ አባላትን በደለኛነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
መወገድ እያለበት፣ ሊወገድ ያልቻለው ኢሕአዴግ፣ በለውጡ መሪነት ወንበር ላይ መቀመጡ በተረጋገጠበት ወቅት በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎች አንዱ፣ ተቀናቃኝ (ተቃዋሚ) ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚለው ነው:: መንግሥት ጥያቄውን አልተቀበለውም፡፡ እሱ ራሱ እንደ ሽግግር መንግሥት እንዲቆጠር እንደሚፈልግና እንደሆነም ከማስታወቁም በላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሚቀጥለው ምርጫ ድርጅታቸው ከተሸነፈ፣ ሥልጣናቸውን ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአጭር ቋንቋ፤ “እናንተ የምትፈልጉት የሽግግር መንግሥት፣ እኔ የምመራው መንግሥት ነው” ብለውናል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ “ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ካልተመሠረተ ኢሕአዴግ ብቻውን የሀገሪቱን ችግር ሊፈታ አይችልም” ሲሉ ያቀረቡት ሃሳብ፣ አንድ ራሱን የቻለ ጥያቄ ተደርጐ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ ሆኖም ዶ/ር ዐቢይም ሆኑ መንግሥታቸው ለዚህ ጥያቄ የሰጡት መልስ ስለመኖሩ አልሰማሁም፡፡ የሚገባኝ ግን ባይናገሩትም ጠ/ሚኒስትሩ፤ “አርፋችሁ ተቀመጡ” እንዳሉና “እኛው እንደጀመርን እኛው እንጨርሰዋለን” በሚል መንፈስ መቀጠላቸውን  ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነትና ዘላቂ ጠቃሚነት፣ በአንድነትና በጋራ አንድ ትልቅ አገር ስለ መገንባት ቢናገሩም፣ የራሳቸውን ድርጅት ኦሕዴድ፣ የአሁኑን ኦዴፓን ጨምሮ ክልሎች እየተመሩ ያሉት በዘር በተደራጁ ድርጅቶች መሆኑ ድብቅ አይደለም፡፡ አራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና የክልል ገዥ ፓርቲዎች፣ ሃያ ሰባት አመት ሙሉ የዘሩት ዘረኝነት እንዲሁም እነሱን ለመታገል የተሰለፉ ሌሎች ድርጅቶች ሲያስተጋቡ የኖሩት የጎሰኝነት አባዜ፣ ዛሬ  በመላው አገሪቱ ለሚታየው የሰላም መደፍረስ ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በዘሩ መሀል ካልተገኘ፣ ደህንነት የማይሰማው ደረጃ ላይ ደርሷል ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
በክልሎች መካከል በሚገኝ አዋሳኝ ቀበሌዎች በ“የእኔ ነው፣ የእኔ ነው” ሰዎች ሰላም እያጡ፣ አንዳንድ ጊዜም ወደ ግጭት እየገቡ እየተገዳደሉ ናቸው፡፡ የክልላዊነት ስሜት ይበልጥ እየገነነ እየሄደ ነው ማለት በሚያስችል ደረጃ፤ ወረዳዎች ወደ ልዩ ወረዳነት፣ ዞኖች ወደ ክልልነት ለመለወጥ ወይም ለማደግ ጥያቄ ይዘው እየተነሱ ናቸው፡፡ ይህ ጥያቄያቸው በፌደራሉ መንግሥት ዘንድ ጆሮ እንዲሰጠው ለማድረግ ከአጐራባች ክልሎች ጋር ጠብ መጫር፣ አብሮአቸው ለዘመናት በነበረው የሌላ ብሔረሰብ ተወላጅ ላይ ክንዳቸውን ማንሳት፣ ንብረቱን ማውደም፣ የአካል ጉዳት ማድረስ -- ጠና ሲልም ግድያ እየተፈጸመ  ነው፡፡
በተጐራባች ክልል ነዋሪዎች መካከልና መጤ እየተባሉ በሚሰደዱት ንፁሐን ዜጐች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት እንዳለ ሆኖ፣ ሌላም የሀገርን ሰላም የሚያሳጣ እርምጃ ተከስቷል፡፡ በቅርቡ በአማራ ክልል  በሰሜን ሸዋ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እንዲሁም በጉምዝ የተከሰተው የሰዎች ሞትና መፈናቀል፣ በተጐራባች ብሔረሰቦች መካከል እንደ ተፈጠረ ግጭት ሳይሆን በአንድ ማንነቱ ለጊዜው ባልታወቀ የተደራጀ ኃይል የተከፈተ ወረራ አድርጐ ማየት የግድ ነው፡፡ አጥቂው ቡድን  ግን አንድም ጊዜ ተይዞ አለማወቁ በግልጽ የሚታይ እውነት ነው:: መንግሥት እጁን በራሱ ሰዎች አስይዟልና፡፡
ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ በአምስትና አስር ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የተገደበ ያለመሆኑ የሚመሰክረው ወይም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው:: ያንን ሁሉ አካባቢ በአንድ የጥቃት ቀጣና ውስጥ ያስገባ ኃይል፣ እንዴትስ አልተደራጀም ይባላል? ጥቃት አድራሹ ስሙን ገልጾ፣ ኃላፊነት ባይወስድም፣ ተበዳዮቹ “ኦነግ ነው” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ ይሄንን መንግሥት ባይቀበለውም፣ ደረቁ እውነት ግን በተደራጀ ኃይል ጥቃቱ መፈፀሙ ነው፡፡
በቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግሥት በአንጉር ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች፣ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈፀመው ጥቃትና ይህን ጥቃት ለመበቀል ነው የሚል ግምት የተሰጠው፣ በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ ላይ በሚኖሩ ጉምዞች ላይ የተፈፀመው ጥቃትም ቢሆን የሚነግረን፣ አንድ በግልፅ የማይታይ የተደራጀ ኃይል፣ የአገር ሰላም እያደፈረሰ መሆኑን ነው፡፡
ቀስ በቀስ እየጐለበተ የጥቃት አድማሱን እያሰፋ፣ በሁለትና በሶስት ቀናት ልዩነት፣ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው እየተወረወረ ጥቃት እያደረሰ ለሚገኘው ለዚህ ኃይል፣ መንግሥት እየሰጠ ያለው መልስ ምንድነው? በእጅጉ የሚያነጋግር  ሆኗል:: በወንጀሉ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ከመግለፅና እየተጠና ነው የሚል መልስ ከመስጠት ያለፈ እርምጃ እስካሁን አልታየም:: የደህንነት መዋቅሩ ወይም የፌደራል ፖሊስ አሊያም የየክልሉ ልዩ ኃይል አከሸፈው የሚባል ጥቃት ለመስማት አለመታደላችንም ፍርሃትና ሥጋት ይፈጥራል፡፡  
ወንጀለኛው ቡድን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጐለበተ ሄዶ፣ በመንግሥት የመፈራት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ያሰጋል፡፡ ለእኔ አሁን የሚታየኝ፣ በስሩ ባደፈጡ ፀረ ለውጥ ኃይሎች፣ እጁን የተያዘ መንግሥት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አጠቃላይ ሁኔታው  ያስፈራል፡፡

Read 1862 times