Print this page
Monday, 13 May 2019 00:00

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ልጓም

Written by  ዶ/ር ሁሴን አዳል መሐመድ
Rate this item
(6 votes)


    “--የጠባብ ብሔርተኝነት ትግል አስደሳች ነገር ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ሕዝብ የሚጠሩ ፓርቲዎች ብቅ ብቅ አሉ፡፡ አገራችን ከገጠማት ክፉ የፖለቲካ ደዌና የአማራ ህዝብ ከደረሰበት ጉስቁልና አንጻር እርምጃው ትክክለኛ አይደለም ለማለት አያስደፍርም፡፡--”
           ዶ/ር ሁሴን አዳል መሐመድ
         
                “ከዕንቁላልና ዶሮ ማን ቀድሞ ተፈጠረ?”  የሚል እንቆቅልሽ የነገሮችንና የሒደቶችን ቅደም ተከተል በጥሞና መርምሮ፣ በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚደረግ መረጃ የማፈላለግ ዝንባሌ ማሳያ፣ የዐዋቂ ሰዎች የሂደት ግምገማ ጥያቄ እንጂ፣ የሁልጊዜ ተራ የልጆች ዕንቆቅልህ ምን አውቅልህ ጨዋታ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ መላ አገሪቱን እንደተቆጣጠረ ይዞ ብቅ ያለው በጣም አስፈላጊ መርህ፤ “ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት”፤ ከዳር ሲታይ ዓላማው በኢትዮጵያ “ብሔሮች፤ብሔረሰቦች” መካከል ሊኖር ለሚገባው ጤናማ የፖለቲካ ትግል ባህል፤ እኩልነትና አንድነት ግንባታ ጥረት ግንዛቤ ማሳደግ ይምሰል እንጂ ወደ ውስጥ ሲገባ፣ የአማራ ብሔርተኝነት ማለዘቢያ ልጓም እንዲሆን ታልሞ የመጣ ነው፡፡ ልጓሙ የተሠራው የአማራን ሕዝብ፣ የብሔርተኝነት ፍላጎት ተሽቀዳድሞ ለማፈን እንደነበረ በውጤት ተኮር ግምገማ ይረጋገጣል፡፡
ኢሕአዴግ ይህን መፈክር አስቀድሞ ሲፈጥር በአማራ ሕዝብ ውስጥ የሚብላላ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ፈጽሞ አልነበረም፡፡ መላ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የትግል ታሪኩን በአማራ ክልል ሕዝብ አእምሮ ውስጥ ጽፏል እየተባለ የሚሞካሸውን ኢሕዴን፤ የመጠሪያ ስሙን ወደ ብአዴን እንዲቀይር ያመቻቸው፣ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ፈጽሞ ያልነበረውን የአማራ ሕዝብ በዚህ መፈክር አማካይነት ለማለዘብና ገና ብሔራዊ ጥቅሞቹን ለይቶ ሳያውቅ፣ በብሔርተኝነት ቆዳ የተጠፈረ ታምቡር ሲወግሩና መሰንቆ ሲከረክሩ ከኖሩ ጽንፈኛ የብሔር ድርጅቶች ዝቅ ብሎ እንዲደራደር ለማድረግ ነበር ቢባል ስህተት አለመሆኑን ድርጅቱ ከታየበት የአገልጋይነት ባሕርይና ለአማራ ሕዝብ መብት መከበር አበረከትኩ በሚለው ተጨባጭ ውጤት መዝኖ አፉን ማዘጋት ቀላል ነው፡፡ የኢሕዴን ወደ ብአዴን መቀየር ሰሞንኛ አጀንዳ የነበረው ከክልሉ ውጭ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ፤ ግፍና በደል የወለደውን መላው የአማራ ህዝብ ድርጅት (መአድ) በስም ተቀራራቢነትና በተግባር ተቃርኖ በመገዳደር፣ የአማራን ሕዝብ ለጉሞ ለመያዝ፣ በማጭበርበሪያ ስልት ለመጠቀም እንጂ በኢሕዴን ላይ የጨመረው እሴት ኖሮ አልነበረም፡፡
የፈጣን የፖለቲካ ትርፍ ባለቤት የሚያደርገውን የጠባብ ብሔርተኝነት የፖለቲካ ፕሮጀክት ከአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች በሚገኝ ሁለንተናዊ ድጋፍ ገና በጠዋቱ ቀርጸው ለተነሱ የፖለቲካ ነጋዴ ቡድኖች፤ ለዘመናት የአቃፊነት ስነልቦና የሰረጸበትን፤ ሁሉን ቻይና አስተዋይ የሆነውን የአማራን ሕዝብ ለ27 ዓመታት ለም መሬት ለማድረግ ያስቻለውን “የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት” ልጓም ማሠራት ለኢሕአዴግ በጣም አስፈላጊ የሆነ ወቅታዊ የፖለቲካ ክንውን ነበር፡፡ በመሆኑም የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዲጓ በአስቸኳይ ተደጉሶ፤ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ይለምልም ባነር ተዘጋጅቶ በአገር አቀፍ ደረጃ በስፋት ተሰራጨ:: ብዙ ተወተወተ፡፡ ዲጓው የተወተወተው፣ የቀበሮ ለምድ ለብሰው፤ የአማራነት ካባ ደርበው በመኻሉ በተሰገሰጉ የአማራ ሕዝብ ሞግዚቶችና ከሕዝቡ ውስጥ በወጡ አርቀው በማያዩ፣ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ግንዘት በቀላሉ ታስረው፣ በጽኑ ሰመመን ውስጥ በገቡ ተላላኪዎች ነው፡፡    
“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንዲሉ፣ ቀድሞውኑ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ችግር፤ ችግሩ ላልሆነውና ከሌላው ጭቁን ሕዝብ ጋር ሆኖ በከፈለው የዴሞክራሲ መብት ማስከበርና ከመደብ ጭቆና የመላቀቅ ትግል፣ ከተጣለበት የጭቆና ቀንበር እኩል ለተላቀቀ ጭቁኑ የአማራ ሕዝብ፤ “ዴሞክራሲያዊ የአማራ ብሔርተኝነት” አደንዛዥ ዕፅ፣ ከሌላው ብሔረሰብ በበለጠ ልኬት የታዘዘለት በመሰሪነት ነበር፡፡ ይህንን መሰሪነት ለአማራ ሕዝብ የነገረው ማንም ውስጥ አዋቂ አካል ስለአልነበረ፤ ሕዝቡ የራሱን ጉድ በወቅቱ አለማወቁ ከማንም በላይ ጎድቶታል፡፡
የአማራ ሕዝብ፣ “የአማራ ገዥ መደብ መፍለቂያ አብራክ” ነው በሚል የተዛባ አደንቋሪ ትርክት፣ በከንቱ በስሙ የተነገደበት፤ በአገራችን በስፋት ተሰራጭቶ እየለፋ የሚኖር ምስኪን ሕዝብ ጭምር መሆኑን ለማስገንዘብ፤ ለተዛባው ትርክት ማስተባበያ የሚሆን ተስማሚ የሆነ ወቅታዊ መሪ ሐሳብ በማመንጨት፣ ስለ አማራ ሕዝብ የተሰራጨውን አሉታዊ ትርክት ማረም የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ትግል የሚፈታው አንድ የፖለቲካ ችግር አድርጎ መያዝ ሲገባው፣ “የደንቆሮ ልቅሶ ሁልጊዜ አበባየ” እንዲሉ፣ በእንጭጭ አእምሮ በበረሃ የተጠነሰሰው አማራ-ጠል ትርክት፣ “በአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት” ዲጓ ተደጉሶ ቢቀርብ፣ አዋጭ የማታለያ የትግል ትርክት እንደሚሆን ታመነበት፡፡ ይህን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሰሪ ትርክት፣ በአማራ ሕዝብ ውስጥ ማስረጽ በዋናነት የኢሕአዴግ የአማርኛው ክፍል (ብአዴን) ተግባርና ዓይነተኛ የሥራ  ድርሻ ሆኖ ተሰጠ፡፡
ተልዕኮውን በሚገባ ያሳኩ ጉዳይ አስፈጻሚዎችና ተላላኪዎች በስልጣን ወደ ላይ የሚዘልቁበት፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው በሐብት የሚበለጽጉበት፤ ከዚህ አቅጣጫ የሚያፈነግጡት ደግሞ የተለያየ መጠሪያ ስም እየተለጠፈባቸው እንዲገለሉና እንዲንገዋለሉ የሚደረጉበት፤ የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ጉዳይ በሚመከርበት የፖለቲካ ድርጅት ብቁ አማራ የማይሳተፍበት፤ የጉዳይ አስፈጻሚዎች ተላላኪዎች ዳር እስከ ዳር የሚሰገሰጉበት፤ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚታዘዝ ማስፈጸሚያ ማሽን ተደራጀ፡፡ ማሽኑ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ማጥዕንትን በሚያጥንበት መድረክ ሁሉ ማጥዕንቱ የአማራን ጭቁን ሕዝብ የማይመለከት ፋይዳ-ቢስ ትርክት መሆኑን በአመክንዮ ደግፎ በማስረዳት ጥያቄ የሚያቀርብ ሁሉ መድረኩን በሚመራው “የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ቀሲስ” እየታፈነ፤ ጠያቂው  ሁሉ ቁም ስቅል እያየ፤  ይህንን ተከትሎ በሚመጣ ስንብትና ክትትል፣ ከፖለቲካ ሕይወትና ከኑሮ እንዲፈናቀል የሚደረግ፤ አበሳ የሚበዛበት ሰው ቁጥር ዕለት ተዕለት እየተበራከተ ሄደ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዲጓ ተደጉሶ፤ “የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ይለምልም” ባነር ተዘጋጅቶ፣ በካድሬው መዋቅር መሰራጨት ሲጀምር፣ ድርጊቱ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚሠራ የጨዋታ ድራማ መሆኑን የተገነዘቡ፣ ለሕሊናቸው ያደሩ፣ በአማራነታቸው የሚቆረቆሩ ዜጎች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ ቅሬታቸውን በተለያየ መልክ በመቃወም የሚገልጹ ቢኖሩም፣ እየጎለበተ የሔደው የጉዳይ አስፈጻሚው ቡድን የመምታት ኃይል፣ ለሕሊናቸው ያደሩ ኃይሎችን እየጠራረገ በመሄዱ “የአማራ ዴሞክራሲዊ ብሔርተኝነት ተውኔት” በመድረክ ላይ ለረዥም ጊዜ የመቆየት ዕድል አገኘ፡፡
በየመድረኩ የጉዳይ አስፈጻሚውን ኃይል እየተጋፉ፤ ጭቁኑ የአማራ ሕዝብ፣ በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ወይም ሕብረብሔራዊነት አውድ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በተግባቦት ኖረ እንጂ በጠባብ ብሔርተኝነት ቁርበት ታጅሎ በአግላይነት ስለአልኖረ፣ የብሔርተኝነት ፖለቲካን ገና ባልተለማመደበት ወቅት የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ልጓም፣ የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካ አሻጥር ሰለባ እንዳያደርገው እንሰጋለን፤ ከሆነም አሁን ባለው የአገራችን ፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር አማራ የሚያስፈልገው ማጥዕንት የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዓይነት ሳይሆን የብሔርተኝነት ማጥዕንት መሆኑን በአስረጂ ደግፈው የሚያቀርቡ ሰዎች ብቅ ብቅ ሲሉ፣ ጉዳይ አስፈጻሚው የሚያወርደውን መመሪያ የማይቀበሉ፤ ሥራን በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የማይሠሩ መካቾች እየተባሉ ክፉ መከራ ተቀበሉ፡፡
የአገራችን ፖለቲካ ከፍታ ላይ መድረስ ተስኖት ወደ ነገድ/ጎሳ ፖለቲካ እንጦርጦስ ሲወርድ አቃፊ የሆነውን የአማራ ሕዝብ ለመታደግ በቅድሚያ ሕዝቡን እንደ ሌሎቹ በብሔርተኝነት የትግል ቅብቅብ ውስጥ በማስገባት፤ በጠባብ ብሔርተኛ ድርጅቶች እየተመሩ ብሔራዊ ማንነታቸውንና ጥቅሞቻቸውን ለይተው ካወቁ ብሔረሰቦች ጋር እኩል እንዲደራደር ማስቻል፤ ድርጅታዊ ብቃት ይፈጥርለታል ተብሎ ሲጠየቅ፣ ከጉዳይ ፈጻሚዎች አስደናቂ ምላሽ ይሰጣል፡፡ “መላ የትግል ጊዜውን በአማራ ሕዝብ መኻልና በአማራ መሬት ያሳለፈው ኢሕዴን በበረሐው ትግል ወቅት የአማራን ሕዝብ በብቃት አስተምሯል፤ ድርጅቱ የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መሲህ የሆኑ በእሳት የተፈተኑ ዴሞክራት ጓዶች አፍርቷል፤” በሚል የጋለ ቁጣ ይደመደማል፡፡ “ነፍጠኛ ሲባል ከኖረ በዴሞክራሲያዊነት ካልተቃኘ ሕዝብ” ዴሞክራሲያዊ አመራር ወጥቷል እንዴት ሊባል ይችላል? ከእህት ብሔረሰቦች ድርጅቶች በምደባ የተላኩልን ወንድምና እህት ዴሞክራሲያዊ አመራሮች፣ በበቂ ሁኔታ አሉ ካልተባለ በስተቀር የብሔርተኝነት ሀሁ ገና መጀመር ካለበት የአማራ ጭቁን ብሔረሰብ ሕዝብ ትውልድ “ዴሞክራት ብሔርተኛ አመራር” መቼ ሊወጣ እንደቻለ የሚጠይቅ ጠበቅ ያለ ክርክር ሲነሳ፣ ጠያቂውን ሰው አክራሪ ብሔርተኛ፤ ሕዝበኛ፤ ነፍጠኛ ወዘተ---በማለት ማደናገር ይቀድማል:: በሁኔታው የሚከፉ ኃላፊዎችን ልብ የሚመረምር ሆዳም ከስር እየተመደበ በሚላክ ጥቆማ “ይህች ሽምብራ ካደረች አትቆረጠምም” በሚል ፈሊጥ፣ በየወቅቱ ከቦታው በማንሳት፣ መዋቅሩ ዕለት ተዕለት ትጉህና ጠንካራ ሰው አጣ፡፡
በአንድ ወቅት የመቅደላ ወረዳ ያደረገው አመርቂ የውሃ እቀባ ልማት እንቅስቃሴ፣ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት፣ በፌደራሉና የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲጎበኝ፣ ወረዳው ላስመዘገበው ውጤት ግለሰቡ ያበረከተው በተግባር የታየ አስተዋጽዖ በቂ ሆኖ ሳለ፣ ታሪካዊቷ እሮጌ ቀበሌ ላይ በተደረገው ገለጻ ወቅት በአጋጣሚ የልማት ሥራውን ያስተባበረው ሰው በስፍራው ተገኝቶ ገለጻውን ባለማድረጉ፣ የክልሉ ከፍተኛ የፖለቲካ ኃላፊ ማብራሪያውን ካዳመጠ በኋላ “ልማቱንስ ደህና አስተባብሯል ግን ልቡን አግኝታችሁታል ወይ” በማለት የሥራ ባልደረቦቹን የጠየቀው የመስክ ጉብኝቱን ታዳሚ ያስደነገጠ ጥያቄ፣ ለዚህ መሰል ችግር ማሳያ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ለካስ ሰውየው በብሔርተኝነት ዝንባሌው ይጠረጠር ስለነበረ ነው፡፡
አንድ ሰው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ስነልቦና ከማጎልበቱ በፊት የብሔርተኝነት ስነልቦና ቀድሞ ሊኖረው ግድ እንደሚል “ከዕንቁላልና ከዶሮ ማንኛው ቀድሞ እንደተፈጠረ” በሚጠይቅ ምስለተ አመክንዮት ተደግፎ ሲቀርብ፣ የጥያቄው መልስ፣ “የአማራ ሕዝብን በዴሞክራሲያዊ የአማራ ብሔርተኝነት መስመር ማታገል የሚያስችሉ ብቁ አመራር ሰጪ ታጋዮች አሉን”፤ “ዋ! እናንት ወደ ፍየል ጥበቃችሁ ትመለሳላችሁ” በሚል ማስፈራሪያ አዝማች ይደመደማል፡፡ ምልምሉን በካድሬ ስልጠና ስናበቃው፣ በአማራ ሕዝብ ውስጥ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ቀስ በቀስ ይሰርፃል ተብሎ በጭፍን ይዘጋል፡፡ ዐይናቸውን አውቀው ጨፍነው የሚታለሉ አባላት፣ ለካድሬ ስልጠናው ተመርጠው ይላካሉ፡፡ ማጥዕንቱን ታጥነው ሲመለሱ፣ ያንኑ ትርክት ወደ ህዝብ ማድረሻ መሰላል ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ከተጠሉ ወይም ከተጠረጠሩ “የዐይናችሁ ቀለም አላማረንም” ተብለው ወዲያው ሲገፈተሩ፣ የወጣባቸው በከንቱ ሊባክን የሚችለው የስልጠና ወጭ አይታሰብም፡፡
ከላይ የተገለጸውን ሁኔታ ማስታወስ ያስፈለገበት ምክንያት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መፈክር የአማራ ሕዝብን ለመሸንገል የተቀየሰ ስልት መሆኑን፤ ከአሁን ቀደም በጠባብ ብሔራዊ ስሜት ያልታገለውን የአማራ ሕዝብ አታጋይ ድርጅት ኖሯቸው፣ የጠባብ ብሔርተኝነት ትርክት ጽንፍ ላይ ተገፍተው ከደረሱ ሌሎች ብሔረሰቦች በፊት ዴሞክራሲዊ ብሔርተኝነትን ለአማራ ህዝብ ማቀንቀን ተገቢ አለመሆኑን፤ ቀድመው የተገነዘቡ ተቆርቋሪ ዜጎች መኖራቸውን ጭምር ለማውሳት ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ “ቋንቋና ብሔርተኝነት” በሚለው መጽሐፉ፤ “ዕንቁላል ወይስ ዶሮ” በሚል ርዕስ ስር፤ ወኪልህ ነኝ በሚል ድርጅት አማካኝነት አጉል በሆነ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ልጓም፣ የአማራ ሕዝብ እንዴት እደተለጎመ በማስረዳት፣ የግዴታ የአማራ ብሔርተኝነት ትግልን አስፈላጊነት ቀደም ብሎ ለማሳየት ሞክሯል፡፡
“ቀድሞ የተፈጠረው ዕንቁላል ወይስ ዶሮ ነው” ለሚለው እንቆቅልሽ፣ ትክክለኛ አመክንዮ መስጠት ሲያከራክር ይታያል፡፡ ዳሩ ግን ከዝግመተ ለውጥ ሳይንስ ጥናት ትንታኔ አንጻር ሲታይ ቀድሞ የተፈጠረው ዕንቁላል መሆኑ አሻሚ ጉዳይ አይሆንም፡፡ በዘአካላት የዕድገት ሒደት ሽግግር ሳይንሳዊ ትንታኔ ዋቢነት፤ የሚደረግ ሕይወታዊ ሽግግር ከቀላል ወደ ውስብስብ ዘአካል ነው:: የዘአካላት መዋቅራዊ ሽግግር ከዝቅተኛ ደረጃ አካላዊ አወቃቀር ወደ ከፍተኛ ደረጃ አካላዊ አወቃቀር በመሆኑ፣ በውስብስብ የሕብረሕዋሳት አደረጃጀት ከተገነባው የዶሮ ዘአካል ይልቅ አንድ ሕዋስ ብቻ የሆነው የዕንቁላል ዘአካል ቀድሞ መፈጠሩን መገመት የተሻለ አመክንዮ ነው፡፡ ይህንን ምስለት (አናሎጂ) ብሔርተኝነት/ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ቀዳሚነት ንጽጽር ላይ ተክለን ስናይ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መደላድል ብሔርተኝነት ስለሆነ የማይቀር ጉዳይ ከሆነ፣ ቀድሞ መጎልበት ያለበት ስነልቦና የብሔርተኝነት ስነልቦና እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ግን በቋንቋ ላይ የተመሰረተው ዓይነት የብሔርተኝነት ስነልቦና ማለቴ አይደለም፡፡
ለሌሎች ብሔራዊ ማንነት ዕውቅና በመስጠት በጋራ አንድ ጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ አገር ለመገንባት በቅድሚያ የራስን ብሔረሰብ ማንነትና መብት በመገንዘብ የብሔረሰቡን ጥቅም ማስጠበቅ ቀዳሚ ዓላማ ሊሆን ግድ ነው:: በዚህ ረገድ የብሔርተኝነት የትግል ልምድ ካዳበሩ ድርጅቶች ፈጥኖ በመማር፣ ብሔርተኛ ሆኖ ያልተቀረጸውን የአማራ ሕዝብ ብሔርተኛ ሊያደርግ የሚችል ድርጅት በቅድሚያ ሊኖር ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ አንድም ከአማራ ሕዝብ ልዩ ታሪክ የተነሳ ከዚህ ቀደም ጠባብ ብሔርተኛ ድርጅት ስላልነበረው፤ ሌላም የብሔረሰቡ ሰቆቃ አልቻል ያላቸው ዜጎች የአማራ ሕዝብ ድርጅት ለማቋቋም ሙከራ ሲያደርጉ የተዘረጋው የአፈና መዋቅር ጥረቱን በውጥን እያስቀረው፤ የአማራን ሕዝብ መብት የሚያስከብር የፖለቲካ ድርጅት ሳይኖር በርካታ ዓመታት አልፏል፡፡  ባለፉት 27 ዓመታት ለአማራ ሕዝብ የሚቆረቆር ብቁ የፖለቲካ ድርጅት አለመፈጠር፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ግፍ ሲበዛበት የሚጮኽለት፤ በክልሉ የውስጥ አስተዳደር ጉዳዮች በፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት ስሜት መብቱን ለማስከበር በእኩልነት የሚደራደር ድርጅት እጦት በእጅጉ ጎድቶታል፡፡
ከአራቱ የኢሕአዴግ እህትማማች ድርጅቶች መኻል በትግሬና ኦሮሞ ብሔረሰብ ሕዝብ ስም የተቋቋሙት ሁለቱ ድርጅቶች ከሚወክሉት ከረዥም ጊዜ በፊት ጀምሮ በጠባብ ብሔርተኝነት ስሜት ሲቃኝ ከቆየ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ናቸው የሚሏቸውን ችግሮች ለይቶ ካወቀ ሕዝብ ጋር የአማራን ሕዝብ በተነጻጻሪ ብሔርተኛ ለማድረግ፣ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በፊት የብሔርተኝነት ትግል ሀሁን አጠናክሮ የሚያስቆጥር፣ ለአማራ ሕዝብ ሕልውና የቆመ፣ የራስ የሆነ እውነተኛ የፖለቲካ ድርጅት መኖር ነበረበት፡፡ ዳሩ ግን ለአማራ ሕዝብ ፖለቲካ በሞግዚትነት የተላኩ “ቁንጮ ዴሞክራሲያዊ አመራሮች” የሚፈተፍቱትን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ትርክት፣  በብሔረሰቡ ምልምሎች አእምሮ ውስጥ በመጫን፣ የአማራ ሕዝብ ይሁንታ ባልተጠየቀበት ሁኔታ ትርክቱን ሰፊ መሰረት የማስያዝ ርብርብ ተደረገ፡፡ በመሆኑም የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት መብት ጥያቄ፤ ከአንጀታቸው በማይሠሩለት ጉዳይ አስፈጻሚዎች መዳፍ ውስጥ ተጠቃልሎ ወደቀ::  
ካዳበረው ንቃተ ሕሊና ተነስቶ ለአገሩ ሉዓላዊነት መከበር ውድ ሕይወቱን የሰዋ፤ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ በማድረግ ለሌሎች ብሔረሰቦች መብት መከበር የታገለ ትውልድ ትርክት ባለቤት የሆነው የአማራ ሕዝብ፤ በሞግዚትና-ተላላኪ ውስብስብ የፖለቲካ መረብ ተጠፍሮ ታስሮ ሌሎች የሚተርኩለትን ትርክት ብቻ እንደወረደ ከመጋት በስተቀር፤ ጥያቄ መጠየቅና ለጠየቁት ጥያቄ መልስ መሻት የማይታሰብ ነገር ሆኖበት፣ በአማራ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ትርክት ልጓም፣ ዳር እስከ ዳር ተለጉሞ፣ ወደፊት በመራመድ ፈንታ፣ አንጸባራቂው የአባቶች ታሪክ ሲረክስ በቸልታ እያየና እየሰማ፣ መሳሪያ ሆኖ የኋልዮሽ ጉዞ ጀመረ፡፡ የአማራ ሕዝብ ሕልውናውን በሚመለከቱ ሰፊ የፖለቲካና ወሳኝ የአካባቢ አስተዳደር ጉዳዮች ሁሉ እንደ እርሱ ሆኖ የሚሟገትለትና ጉዳዩን የሚከታተልለት ብቁ ወኪል በማጣት እያደር የእርሱ የሆነውን ነገር ሁሉ አጣ፡፡ የብሔረሰቡ ምልምሎች፣ የጉዳይ አስፈጻሚው የፖለቲካ ቁንጮ የሚተርከውን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ማጥዕንት እንደወረደ በመታጠን፣ ያንኑ ከመሽተት በስተቀር፣ የራስ ጠረን ባለቤት መሆን፤ የራስን ንቃተ ሕሊና ተጠቅሞ የማጥዕንቱን ምስጢር መርምሮ ለማስተካከል ረዥም ጊዜ ወሰደ፡፡
“እጸድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠልጥላ ቀረች” እንዲሉ፣ ገና ሲጀመር ትሕነግ፣ በሜዳ ትግል ወቅት ሲንቀሳቀስ፣ በደግነቱ እህል ውሃ ያለውን የአማራ ሕዝብ መሬት፣ የእኔ ነው ማለት ጀመረ::  ቀስ በቀስ የአማራ መሬት ያለ ምንም ቅድመ ጥናትና አዋጅ ከወሎ፤ ሸዋ፤ ጎጃም፤ ጎንደር እየተቆራረጠ ወደፊት ይቋቋማሉ ተብለው ወደሚታሰቡ አጎራባች ክልሎች እንዲካተት የሚያደርግ ቅድመ-ዝግጅት ከግንባሩ ጊዜያዊ ሕዝባዊ አስተዳደር ወቅት ጀምሮ ተደረገ፡፡ በግብታዊነት የተጀመረውን አማራን በሁሉም ረገድ የማሳነስ ጥረት ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው ለማድረግ፣ በክልል መስተዳድር ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የአማራ መሬቶችን ለአጎራባች ክልሎች የማዛወር ሥራ በተደረገው ዝግጅትና በተሰጠው መመሪያ መሰረት ተከናወነ፡፡ የአዳዲስ ክልል መቋቋም ዓይነተኛ ተልዕኮና ተግባር በዚህ ሁኔታ “በድል ተደመደመ”:: ከእነ መሬቱ በሌላው ክልል ውስጥ ተቆርጦ የቀረው የአማራ ሕዝብ፣ በገዛ አገሩ ውስጥ እየኖረ በሁለተኛ ዜግነት እየታየ፣ ሁለንተናዊ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍትህ ተነፍጎት፣ የስቃይ ጊዜ አሳለፈ፡፡ እያሳለፈም ይገኛል፡፡
ማዕከሉን ደብረብርሃን ላይ አድርጎ የነበረው የሰሜን ሸዋ መስተዳድር ዞን፣ ለሁለት የተከፈለበት ሁኔታ ያስገርማል፡፡ ምንም ጥናት ሳይደረግ ጉዳዩን ለይስሙላ አዲስ ለተቋቋመው የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የመጀመሪያው ጉባኤ ቀርቦ፣ ለሁለት ተከፍሎ ግማሹ፤ ማዕከሉ ፍቼ ከተማ ላይ ሆኖ፣ ለኦሮሚያ ክልል እንዲጨመርለት በችሮታ ተሰጠ፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ መቀጠል የነበረበት የዚህ መሬት ወደ ኦሮሚያ ክልል የመዛወር አስቂኝ ድራማ የተከናወነው በሽግግሩ ቻርተር ዘመን ፍጻሜ የተካሄደውን የአካባቢ ምርጫ ተከትሎ በተጠራው የክልል መስተዳድር ማቋቋሚያ የመጀመሪያው ጉባኤ ነው፡፡ የክልል መስተዳድሩ አካላት እንደተሰየሙ ጉባኤው የአማራ ብሔራዊ ክልል የመጀመሪያው ፕሬዚደንት አድርጎ የሾማቸው ግለሰብ፣ ከግራር ጃርሶ ተቀስቅሰው እንዲመጡ የተደረጉትን አምስት አቤቱታ አቅራቢዎች፣ የአካባቢው የኦሮሞ ሕዝብ ለጉባኤው እንዲያሰሙለት ወክሎ የላካቸው ተወካዮች መሆናቸውን በማስተዋወቅ፤ ደብረብርሃን ለአስተዳደር ጉዳይ በጣም ስለሚርቃቸውና አማርኛ ቋንቋ መናገር ቢችሉም አፍ የፈቱት በኦሮምኛ ቋንቋ ስለሆነ ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲካለሉ የጉባኤው መልካም ፈቃድ እንዲሆንላቸው ሕዝቡ ጠይቋል የተባለበት ደብዳቤ ቀርቦ እንዲነበብና እነርሱም ተነስተው በቃል ጭምር እንዲያስረዱ ተደርጎ፣ ሁሉም ነገር እንደጠየቁት ሆኖላቸው፣ የጉባኤውን መልካም ፈቃድ እንዳገኙ በጉባኤው ላይ ሲነገር፣ ጉባኤውን በዕልልታ ሲያቀልጡት፣ ጩኸቱ ለአማራ ህዝብ የተነገረ መርዶ ሆነ፡፡
በወቅቱ ጉባኤው አስፈሪ በሆኑ ጉዳይ አስፈጻሚዎችና የልብ ትርታው በጥንቃቄ እየተፈተሸ፣ በየደረጃው እየተንጓለለ በመጣ ምልምል ጉባኤተኛ የተሞላ ስለነበር፣ በሰሜን ሸዋ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ጋር አብሮ ስለሚኖረው የአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ ፍቺ ሁኔታና ስለሚከበርለት መብት የሚጠይቅ የጉባኤ አባል አልተገኘም፡፡ ስለሆነም በአምስት መልዕክተኞች አቤቱታና ውስጥ ለውስጥ ቀድሞ ባለቀለት የድርጅቶች የርስ በርስ ስምምነት፣ ከፊሉ የአማራ ሕዝብ፣ ያለፈቃዱ ከእነ መሬቱ “ወኪልህ እኔ ነኝ” በሚለው ድርጅት ክህደት፣ “የሰሜን ሸዋ ኦሮሞ” ተብሎ፣ ዘግይቶ የኦሮሞ ክልልን እንዲቀላቀል ተመቻችቶ፣ አማራ ከአዲስ አበባ በርቀት የሚገኝ ክልል ተደረገ፡፡ የዚህ ጥረት መርዛማ ፍሬ፣ “አዲስ አበባ ኬኛ” ለሚለው የግለኝነት መፈክር መነሻ በመሆን አገለገለ፡፡
ከዚህ ሁኔታ ተነስተን ስናይ፣ የአማራን ክልል እየተለተሉ ወደ ሌላ ክልል የማካለል ዘመቻ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት” ከመረቀቁና ከመጽደቁ በፊትና በፊት ነው፡፡ ይህ ሆኖ እያለ በሕገ መንግሥት መሰረት ባልተፈጸመው የክልሎች አከላለል ላይ ቅሬታ በማሳደር “የማንነቴ ይመለስልኝና የወሰን ይከበርልኝ” አቤቱታ ሲቀርብ፣ የክልል ጉዳዮች አሁን ሊታይ የሚችለው በሕገ መንግሥቱ መሰረት ነው ብሎ ለማደናገር ድፍረቱ ከየት መጣ? የአማራን ክልል በማሳነስ የእኛ ነው የሚሉትን ግዛት ለማስፋፋት በተፈለገ ጊዜ፣ የሕገ መንግሥት መኖር አለመኖር አልገደበም፡፡ ያለአግባብ ወደማይመለከተን ክልል ያለ ይሁንታችን ቀርቅረናልና ወደሚመለከተን ክልል መልሱን የሚል የሕዝብ ጥያቄ ሲቀርብ ደግሞ የሕገ መንግሥት ማነቆ አለ የሚል የፖለቲካ እንጉርጉሮ ክሊፕ ይለቀቃል፡፡ በእውነቱ ይሄ አቀራረብ “ዐይናችሁን ጨፍናችሁ እኛ እናሙኛችሁ” የሚል የሞኞች ብሂል ነው፡፡  
እነሆ የአማራ ሕዝብ የግፍ ዋንጫ ሞልቶ ስለፈሰሰ የተጣለበትን የግፍ ቀንበር ከጫንቃው ላይ የሚያወርድለት ድርጅት የማቋቋም ዝንባሌና መደፋፈር ወቅቱን ጠብቆ መጣ፡፡ መአድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመበት አመክንዮ ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ የጠባብ ብሔርተኝነት ትግል አስደሳች ነገር ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ሕዝብ የሚጠሩ ፓርቲዎች ብቅ ብቅ አሉ፡፡ አገራችን ከገጠማት ክፉ የፖለቲካ ደዌና የአማራ ህዝብ ከደረሰበት ጉስቁልና አንጻር እርምጃው ትክክለኛ አይደለም ለማለት አያስደፍርም፡፡ የአማራ ሕዝብ ከአብራኩ በወጣ የፖለቲካ ድርጅት እጦት ምክንያት በእንግልት ሲቆራመድ የቆየ ሕዝብ በመሆኑ፣ ከእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች መኻል ባላቸው ጣዕም እየመራረጠ በጉጉት ድጋፉን ቢሰጥ አያስገርምም፡፡ አዴፓ በቀናኢነት ጥሩ ተፎካካሪ መሆን ይችላል፡፡ ትናንት የነበረው የማታለያና የሸፍጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ባለበት ሁኔታ ወደፊት ቢቀጥል፣ የአማራ ሕዝብ እየተሸነገለ መቀጠሉና የተራዘመ ጉዳት ማስተናገዱ አይቀሬ ነበር፡፡ የአማራን ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር እውነተኛ ብሔርተኛ የፖለቲካ ፓርቲ ከተገኘ፣ “ከዕንቁላልና ዶሮ ማን ቀድሞ ተፈጠረ” ለሚለው የምስለት እንቆቅልሽ መልስ ተገኘ ማለት ነው፡፡
በእርግጥ ትናንት በውርስ ባገኘው የሕብረ-ብሔራዊነት ስነልቦና የተነሳ “ትምክተኛ” ይባል የነበረ ሕዝብ፣ ዛሬ “ጽንፍ የያዘ ጠባብ ብሔርተኛ” መባሉ አስደናቂ ነገር ይሆናል፡፡ ለበርካታ ዘመናት በጠባብ ብሔርተኝነት ቁርበት ተጠቅልለው የኖሩ ቡድኖች፣ የአማራን ብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ ገና መታዘብ ሲጀምሩ አገር ፈረሰ፤ ሰማይ ተደረመሰ እያሉ ያለ ይሉኝታ አቃቂር ማውጣት፤ ጸጉር መሰንጠቅ አልከበዳቸውም፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ እጅግ በጣም ዘግይቶ የተፈጠረ ክፉ ወይም መልካም ሊባል የሚችል አጋጣሚ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል:: የአማራ ህዝብ ተነግሮ የማያልቅ ክፉ መከራ የደረሰበት፤ እጅግ በጣም ተንቆ ግዛቱ ከየማዕዘኑ የተቆራረሰበት፤ ማንም እየተነሳ የተሳለቀበት፤ ለሕብረ-ብሔራዊነት ማበብ ቅድሚያ በመስጠቱ በብሔርተኝነት ስሜት ቀድሞ ባለመደራጀቱ መከራ ሲወርድበት የደረሰለት፤ በስሙ የተጠቀመ እንጂ ብሔራዊ መብቱን ያስከበረለት ሁነኛ የፖለቲካ ድርጅት አልነበረውም፡፡
አሁን የአማራ ሕዝብ፣ የብሔርተኝነት ሽምጥ የፈረስ ግልቢያ ጀምሯል፡፡ የአማራ ወጣት ትውልድ በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ሽፋን እስካሁን የደረሰበትን በደል፣ በብሔርተኝነት ትግል ለመሻር ቆርጦ የተነሳ ይመስላል፡፡ የተቀማውን ርስትና መብት ሁሉ የማስከበር የሞራል ግዴታ አለበት፡፡ ለዚህም እንቅስቃሴ የማንም ጉዳይ አስፈጻሚ ወይም ተላላኪ ዴሞክራሲያዊ አመራር ቆሞ አይጠብቅም:: በትልቅ ዛፍ ጥላ ስር ተረጋግቶ ተኝቶ ሳለ፣ በጠራራ ፀሐይ እረኞች ቀስቅሰው ወደ ሐሩር ስለአስገቡት በሬ፣ ተወዳጇ አርቲስት ሜሪ አርምዴ ያንጎራጎረችውን ዘፈን ስንኝ ያስታውሷል፡፡
“በገዛ አገሩ ላይ የተኛውን በሬ
ቀስቅሰው ቀስቅሰው አደረጉት አውሬ፡፡”
አሁን የአማራ ወጣት ትውልድ፣ ጠባብ ብሔርተኛ ቢሆንም እንኳ አይፈረድበትም፡፡ ከአማራ ሕዝብ የወጣ ትኩስ ትውልድ በመሆኑ በህዝቡ ላይ የደረሰው በደል ለአማራ ወጣት ቀስ በቀስ የእግር እሳት እየሆነበት መጥቷል:: እርሱም የበደሉ ገፈት ግንባር ቀደም ቀማሽ ሆኗል፡፡ ጽንፍ ከያዙ ብሔርተኛ ቡድኖች ጋር ለመከራከር እንደተቀሩት በብሔርተኝነት ቁርበት ካልተጠቀለለ በስተቀር “ከዳኞች ችሎት ፊት ቀርቦ ፍትህ ማግኘት” ስለማይቻለው፣ የግድ ብሔርተኛ ሆኖ ከመቅረብ ውጭ  የተሻለ ሌላ አማራጭ ሊኖረው አልቻለም:: “የዳኝነት ስርዓቱ” ይህንን ብቻ የሚፈቅድ ስለሆነ እንደ ወቅቱ ሁኔታ የብሔርተኝነትን አቋም ይዞ መብቱን በማስከበር፣ የሌሎችን መብትና ፍላጎት በሚዛን በማየት፣ ለሕብረ-ብሔራዊነት ማበብ ከመትጋት በስተቀር የጠራ ሜዳ ላይ ለብቻው  ተገትሮ፣ ሕብረ-ብሔራዊነት እያለ መወትወት አያዋጣውም፡፡ እንዲህ ካላደረገ ደግሞ የ27 ዓመታቱ ፈተና በዚያው መልኩ ሊቀጥል ነው፡፡
የአገራችን የፖለቲካ ውድቀት መንስኤ የጠባብ ብሔርተኝነት ትግል መሆኑን ለሚገነዘብና አባቶቹ የከፈሉትን መስዋዕትነት ለሚያውቅ የአማራ ወጣት ትውልድ፣ እንዴት የጠባብ ቡድኖች የአገር ብተና እንቅስቃሴ ማዕድ ተጋሪ ለመሆን በቃ? በማለት የሚተቹ የህብረተሰብ ክፍሎች አይጠፉም፡፡ እዚህ ላይ አማራ ወደ ብሔርተኛ የትግል መስመር ለመግባት የተገደደው በመጨረሻው ሰዓት መሆኑ ሊስተዋል ይገባዋል፡፡ በአገራችን አሁን በሚታየው ሁኔታ ላይ አማራ ለብቻው ሕብረ-ብሔራዊነት (ኢትዮጵያዊነት) እያለ ቢቀጥል የመልካም ምኞት መግለጫ ማሰማት ከሚሆንበት በስተቀር የሐሳቡ ተጋሪ ማን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ለይቶ ማወቅ አይቻለውም፡፡ በአፍ የሚነገረውና በተግባር የሚታየው ነገር አንድ አልሆነለትም፡፡ ብረት የሚሳለው ከብረት ጋር በማፋጨት በመሆኑ፣ በብሔርተኝነት ትግል እየፈረሰች ያለችን አገር መልሶ አንድ ለማድረግ፣ ብሔርተኛ መሆን ግድ ይላል፡፡  “ጅብ ከሚበላህ ጅብ በልተህ ተቀደስ” የሚለው የአማራ ብሂል፣ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ይገለጻል፡፡ ከእስካሁኑ ልምድ መማር የተቻለው፣ በጽንፈኛ ብሔርተኝነት ሽምጥ የሚጋልቡትን ድርጅቶች ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያዋጣው ብሔርተኛ መሆን ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል እነርሱ ተጸጽተው ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት ጉዞ በመውጣት የጋራ ወደሆነው ሕብረ-ብሔራዊነት (ኢትዮጵያዊነት) የትግል ሜዳ ከተመለሱ፣ አማራ ሩቅ ሳይጓዝ፣ ከቅርቡ መመለስ አይቸግረውም፡፡
ዳሩ ግን ሊሰመርበት የሚገባ አንድ ጉዳይ አለ:: አይቀሬ ለሆነው የአማራ ብሔርተኝነት ትግል፣ የጠባብ ብሔርተኝነትን የከነቸረ የትግል ስልት መኮረጅ  አያስፈልግም፡፡ ከአሁን በፊት የጠባብ ብሔርተኝነት ትግል አደረግን የሚሉ ብሔርተኛ የፖለቲካ ቡድኖች፤ የብሔር ብሔረሰብ ምንነትን  ከነገድና ጎሳ ለይተው አጣርተው ባለማወቃቸው፣ ለማንና ለምን እንደታገሉ ያላወቁ፤ በትግላቸው ውጤት የኢትዮጵያ ህዝብ መዝኖ አንቅሮ የተፋቸው ኪራይ ሰብሳቢ ቡድኖች ናቸው፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት ትግል መስመር ይህን መሰል በነገድ/ጎሳ ስም የሚደረግ የቡድን ብልጽግና ሊጠየፍ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የብሔርተኝነት ትግል፣ ለግልና ለቡድን ብልጽግና የሚደረግ ትግል አለመሆኑ ከጅማሮው መታወቅ አለበት፡፡
የጠባብ ብሔርተኝነትን የትግል መስመር ይዘው እስከ ጫፍ ተጉዘው፣ በሰበሰቡት ከባድ የኪራይ ገንዘብ መክነው ከቀሩት ቡድኖች ቆም ብሎ መማር፤ ረዥም የትግል ጉዞ አድርጎ የውርደት ካባ ለብሶ ከመመለስ ይሻላል፡፡ ያካበቱትን ጥሪት ይዘው መብያና መደበቂያ ያጡት ጠባብ ብሔርተኞች ጥሩ መማሪያ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የለውጡን መንፈስ በመደገፍ በተቀበሉት የሰላም ጥሪ መሰረት በቅርቡ ከበረሃ የተመለሱት የታጠቁ ቡድኖችም እንዲሁ፡፡ አሁኑኑ የመንግሥት ስልጣን በእጃችን ካልገባ፤ ለአባላቶቻችን መተዳደሪያ ካልተሰፈረልን ወዘተ በማለት እምቧ ከረዩ የሚሉትንና የሚያንቆጫቁጩትን ስንመለከት የሚወሰደው ግንዛቤ፣ ለካስ ለብሔርተኝነት የፖለቲካ ትግል ሜዳ የሚወረደው፣ መተዳደሪያ ሐብት ለማፍራት፣ በደቦ ለመሥራት ነው የሚል ነው፡፡ ከዚህ ደም አፋሳሽ የደቦ ኑሮ ስልት፣ ሰላማዊ የሆነ ሌላ ቀላል የኑሮ ዘዴ ከጠዋቱ ማፈላለግ ይበጅ ነበር፡፡  
አማራነት የነገድ/ጎሳ አስተሳሰብ ከመሆን የተሻገረ፣ አቃፊ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ነው:: በአቃፊነት የሚደረግ የብሔርተኝነት ትግል፣ ብሔርተኝነትን ሰው-ሠራሽ በሆነ የቋንቋ መስፈርት ለክቶ የአፍ መፍቻ ቋንቋን የትግል መሳሪያ አድርጎ አይነሳም፡፡ ቋንቋ የነገድ/ጎሳ አንዱ እሴት እንጂ የብሔረሰብ ሕዝብ እሴት አይሆንም፡፡ የጋራ አገር ወይም ክፍለ ሐገር የሚጋሩ በቋንቋ የሚለያዩ፣ በሌሎች የብሔረሰብ መመዘኛ መስፈርቶች የተዋሃዱ በርካታ ነገዶች/ጎሳዎች በአንድ ላይ መኖራቸውን የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ ነገዶች/ጎሳዎች፣ ቋንቋቸውን በየግል ይዘው የጋራ አገር ወይም ክፍለ ሐገር ባለቤቶች በመሆን ለረዥም ጊዜ በአንድነት በመቆየት የተጋሩትን የብሔረሰብ ማንነት ፈጥረዋል:: የነገድ/ጎሳ ግድግዳ አጥር በማጠር አንዱ ከሌላው የተለየ ጥቅም ወይም የባለቤትነት መብት ይኑረው በማለት በጠባብ ብሔርተኛ ቡድኖች ህሊና ውስጥ የሚንገዋለል የኪራይ መሰብሰቢያ ትርክት ሊያበቃለት ይገባል፡፡ ሕዝብን በነገድ/ጎሳ ከሚለያይ የአገር አስተዳደር አወቃቀር ይልቅ የሚደራርበው የወሎየነት፤ ጎንደሬነት፤ ጎጃሜነት፤ ሸዌነትና የተቀረውም ነባሩ በመልክዓ ምድር ላይ የተመሰረተው የአገር አስተዳደር አወቃቀር ጠቃሚ በመሆኑ፣ ለውስጣዊ ብዝህነት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አብሮ የኖረው ሕዝብ ለዘመናት ያዳበረው የጋራ ስነልቦና ወደነበረበት ደረጃ ተመልሶ፤ የዴሞክራሲ መብት በተከበረበት፤ ፍትሐዊነትና እኩልነት በሰፈነበት ምህዳር አብሮ መኖር ለኢትዮጵዊያን የተሻለ ዕድል እንደሚሰጥ ሊታመንበት ይገባል፡፡ እንደ አማራ ሲታይ ግን እጅን አስሮ የማስደብደቢያና የራስን ይዞታ ለሌላው የማስረከቢያ “የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት” መሰሪ ትርክት ልጓም፣  በአማራ ወጣቶች የንቃተ ሕሊና ዕድገት፣ የአማራ ሕዝብ የወለቀለት ይመስላል::


Read 3280 times