Monday, 13 May 2019 00:00

ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያፍነው መንግስት ብቻ ነው?

Written by  መስከረም አበራ
Rate this item
(5 votes)


                 “--ሃሳቡን በመግለፁ፣ ጋዜጣ በማሳተሙ መንግስት ያሰረው ሁሉ፣ ሃሳብን የመግለፅ መብት የሚያከብር፣ ከአፋኙ መንግስት የሚሻል ነው ማለት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ፕሬስ ውስጥ በአምደኝነት በተሳተፍኩባቸው ዘመናት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አፋኙ ህወሃት መራሹ መንግስት ብቻ እንዳልሆነ በደንብ ተረድቻለሁ፡፡--”
               
                ሃገራችን ለረዥም ዘመናት በተፈራራቂ አምባገነኖች ክርን ስትደቆስ በመኖሯ ሳቢያ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት እጅጉን ተጎድቶ ኖሯል፡፡ በነዚህ አምባገነን መንግስታት ዘመን መናገር ከተቻለም የሚቻለው እነሱኑ ከእነ አፋኝ ማንነታቸው ለማወደስ ነው፡፡ በተቀረ እውነቱን ለመናገር ከሆነ ሃሳብን መግለፅ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አምባገነኖቹ ገዥዎቻችን አፈናን የሚያስኬዱበት መጠን፣ ተቺዎቻቸውን ለማሳደድ የሚሄዱበት ርቀት ብዙ የተባለለት ጉዳይ በመሆኑ ያንን መደጋገም የዚህ ፅሁፍ አላማ አይደለም፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማ በሃገራችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተግዳሮት የሚገጥመው ከመንግስት ብቻ አለመሆኑን ካየሁትና ከገጠመኝ  ተነስቼ ማሳየት ነው፡፡
በሃገራችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተግዳሮት፣ ከመንግስት ብቻ የሚመጣ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል፡፡ ይህ የሆነው መንግስት እስር ቤት ስላለው፣ የማይፈልገውን ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ሲወረውር ስለሚታይ ነው:: ነገር ግን እስር ቤት የሌላቸው፣ እንደ አምባገነኑ መንግስት የፖለቲካ ስልጣን ያልያዙ አፋኞች በሃገራችን ሞልተዋል፡፡ እነዚህ አፋኞች ምናልባትም ከእነሱ የበለጠ ጉልበት ባለው አምባገነን መንግስት “ሃሳብን ስለ መግለፅ መብት ሲታገሉ” ሲታሰሩ ሲፈቱ  የምናያቸው፣ መንግስትን በአፋኝነቱ ሲያብለጠለጥሉ የኖሩ  የሚዲያ ሰዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ሃሳቡን በመግለፁ፣ ጋዜጣ በማሳተሙ መንግስት ያሰረው ሁሉ፣ ሃሳብን የመግለፅ መብት የሚያከብር፣ ከአፋኙ መንግስት የሚሻል ነው ማለት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ፕሬስ ውስጥ በአምደኝነት በተሳተፍኩባቸው ዘመናት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አፋኙ ህወሃት መራሹ መንግስት ብቻ እንዳልሆነ በደንብ ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ በሃገራችን ሃሳብን በነፃነት ስለ መግለፅ መብት መከበር ምክክሮችና ውይይቶች ሲደረጉ፣ ራሱ ታፈንኩ የሚለው የግሉ ሚዲያ፣ የታቀፋቸው የአፋኝነት ዝንባሌዎቹን በተመለከተ መነጋገር ያስፈልጋል:: ይህ ሲደረግ ግን አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡
ከሰሞኑ በሃገራችን UNISCO ባዘጋጀው በዓል ላይም ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በማፈኑ ረገድ ከመንግስት ባሻገር ድርሻ ያላቸው አካላት ጉዳይም ተነስቶ እንደተመከረበት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ብቸኛው አፋኝ መንግስትን ብቻ አድርጎ ማቅረቡ ደግሞ ግማሽ እውነት በመሆኑ ለችግሩ ምሉዕ መፍትሄ አያመጣም:: በሁሉም የአፋኝነት ድርሻ፣ ዝንባሌና ጉልበት ባላቸው አካላት ዙሪያ መነጋገሩ ጠቃሚ ነው:: ስለሆነም እኔ በግሌ ያስተዋልኳቸውን፣ ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ አኳያ ከግሉ ሚዲያ ተዋናዮች በኩል የሚመጡ ተግዳሮቶች ናቸው ብዬ ያሰብኳቸውን ላንሳ፡፡ የማነሳቸው ሃሳቦች በሁሉም የግል ሚዲያዎች ይታያሉ ማለት ላይሆን ይችላል፡፡    
በግለሰቦች ባለቤትነት በሚታተሙ ህትመቶች ሁኔታ የጋዜጣው ባለቤት ህወሃት በሃገሪቱ ላይ ነግሶ የሚያደርገውን አፈና ለማድረግ የሚሞክረው፣ በጋዜጣው/መፅሄቱ ገፆች ላይ ይገዛ ይነዳ ዘንድ የሰሌን ዘውድ በእጆቹ ሰርቶ ለራሱ የደፋ አምባገነን ሲሆን በጋዜጣው ኤዲተርነት ወይም በሌላ ስም የተቀጠሩ ሰራተኞቹ ደግሞ የኑሮ ነገር ሆኖባቸው፣ ባለቤቱ የጠላውን ሰውም ሆነ ሃሳብ የሚጠሉ፣ ባለቤቱ የወደደውን ብቻ የሚወዱ “በእርስዎ መጀን” የሚሉ ሲሆኑ  ያጋጥማል፡፡ እነዚህ የጋዜጣ ባለቤቶች፣ ከእነርሱ የባሰው የህወሃት መንግስት፣ አንድ ሁለት ጊዜ እስር ቤት ስለወሰዳቸው ብቻ  በቅኑ የሃገራችን ህዝብ ዘንድ የሃሳብን መግለፅ ነፃነት አርበኛ ተብለው ቁጭ ብለዋል፡፡ በተግባር ግን እስር ቤትና ጠመንጃ ስላለው “የወርቅ” ዘውድ የደፋው አምባገነን የሚያሳድዳቸው “ባለ ሰሌን ዘውድ” አምባገነኖች የሆኑም አሉበት፡፡
እነዚህ ባለ ግል ፕሬስ ጋዜጠኞች፣ አምባገነንነታቸው በምን ይገለፃል ከተባለ፣ የመጀመሪያ ሆኖ የሚመጣው፣ በገዛ ጋዜጣቸው ስማቸው ተጠቅሶ እንዲተቹ ፈፅሞ የማይፈቅዱ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የእነሱ ወዳጅ የሆነ ሰው ጭምር በጋዜጣቸው እንዲተች የማይፈልጉ፣ ይህንንም በግልፅ የሚናገሩ መሆናቸው ነው፡፡ የጋዜጣውን ባለቤት ስም ጠቅሶ በእግረ መንገድም እንኳን ቢሆን መተቸት፣ ንጉስ እንደ መድፈር ተቆጥሮ፣ “ከባለ ሰሌን ዘውዱ” አምባገነን ጋር ወደ መረረ ጠብ የሚከት ነገር ሆኖ “የተደነገገባቸው” የግል የፕሬስ ውጤቶች አሉ፡፡
ከጋዜጣው ባለቤት በመቀጠል አይተቹም የሚባሉት የጋዜጣው ባለቤት ወዳጆች ደግሞ ለጋዜጣው/መፅሄቱ መቸብቸብ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ አላቸው ተብለው የሚገመቱ፣ ወይ አንዳች እርጥብ ነገር ይዘው ከጋዜጣው/መፅሄቱ ባለቤት ጋር አንድ ምንጣፍ ላይ አብረው የሚውሉ ሊሆኑ ይችላሉ:: እኔ በግሌ ያጋጠመኝን ባነሳ፣ በአንድ የፕሬስ ውጤት ላይ ልክ ያልመሰለኝን ነገር የፃፈ አምደኛን የሚተች ፅሁፍ አዘጋጅቼ ልኬ “በዚህ ጋዜጣ ላይ እንቶኔን መተቸት አይቻልም” ተብዬ አውቃለሁ፡፡ እኔም ነገሩ በጣም ስላስደነገጠኝ፤ “እንዲህ ከሆነ፣ እናንተ ግለሰቡ አይተችም እንዳላችሁኝ ጠቅሼ ለሌላ ጋዜጣ እልከዋለሁ” ብዬ ፈርጠም በማለቴ፣ “የመጀመሪያውን ክፍል ብቻ እናስተናግዳለን” ብለውኝ፣ በዚሁ ወደዚያ ሚዲያ ሳልመለስ ቀርቻለሁ፡፡ ነገሩ በጣም ስለከነከኝ፣ የአንድ የጋዜጣው ሰራተኛ ሃሳብ ሊሆንም ይችላል በሚል፣ ለጋዜጣው ባለቤት ጉዳዩን በተመለከተ ለጻፍኩለት መልዕክት መልስ ላገኝ አልቻልኩም::
ሌላው በጣም የገረመኝ አጋጣሚ ደግሞ ራሳቸው ባለቤት ባልሆኑበት ጋዜጣ ላይ ጭምር ለመተቸት የማይደፈሩ፣ እጅግ አስፈሪ አምባገነን የጋዜጣ ባለቤቶች እንዳሉ ያወቅሁበት አጋጣሚ ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ በአንድ መለስተኛ ስርጭት ባላት ጋዜጣ፣ አምደኛ ሆኜ በምፅፍበት ወቅት የተከሰተ ነው:: በዚህ አጋጣሚ ከብዙው ፅሁፌ ውስጥ በአንድ አንቀፅ ላይ፣ አንድ የሌላ ጋዜጣ ባለቤት፣ በጋዜጣው ከፃፈውና በወቅቱ ብዙ ሰው “እውነት ነው” ብሎ ከወሰደው ነገር ጋር ያለኝን ልዩነት ገለፅኩ፡፡ ፅሁፌን ያነበበው የጋዜጣው ባለቤት፣ ፅሁፉን ወደ ማተሚያ ቤት ከመላኩ በፊት ደወለልኝ፡፡ ሃሳቤን በመግለፅ ነፃነቴ ላይ ያለኝን ጠንካራ አቋም በደንብ ስለሚያውቅ “እባክሽ ይቅርታ አድርጊልኝ፤ ከፅሁፍሽ አንድ አንቀፅ ላወጣ ነው” አለኝ፡፡ “ምን ክፋት አገኘህበት? የተሳሳትኩት ነገር አለ? ከጥሬ ሃቅ አንፃር ልክ ያልሆነ ነገር አገኘህበት?” አልኩት፡፡ “አይደለም እንቶኔን ስሙን አንስተሽ ሃሳቡን አልቀበልም ብለሽ ያቀረብሽው ማስረጃ ስህተት ባይሆንም ለእኔ ግን ጥሩ አይደለም፤ በጋዜጣውም ህልውና ላይ ችግር ያመጣብኛል” አለኝ፡፡ “እኔ የምትለው ነገር ምንም አልገባኝም፤ እንዲህ ስለተፃፈ ከጋዜጣው ህልውና ጋር ምን አገናኘው? አንተስ እሱን ይህን ያህል የምትፈራው ለምንድን ነው? የሚያሳትምልህ እሱ ነው እንዴ?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡ “አያሳትምልኝም፤ ግን ነገሩ ብዙ ነው፣ በስልክ የሚሆን አይደለም፣ ስንገናኝ እነግርሻለሁ፣ አሁን ቅር ሳይልሽ ሃሳቡን እንዳወጣው ፍቀጅልኝ” አለኝ፡፡ “አሁን እየጠየቅኸኝ ያለው ነገር ልክ እንዳልሆነ ግን ታምናለህ? እሽ ብልህ እንኳን ይሄን አምነህ መሆን አለበት” አልኩኝ፤ የልጁ አቀራረብ ቢያሸንፈኝም ነገሩ እያስቆጣኝ:: “አዎ! ልክ አለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም፡፡ አንቺ አስተማሪ ስለሆንሽ እንዲህ ያለውን ነገር ላታውቂ ትችያለሽ:: እኛ አለቃችን ብዙ ነው፤ ፕሬሱ ላይ ያለው ችግር መንግስት በፕሬሱ ላይ ከሚያደርገው አይተናነስም፤ ሁሉንም ስትመጪ እናወራለን” ብሎኝ ስልኩን ዘጋ፡፡     
ስንገናኝ የነገረኝ ነገር የግሉ ፕሬስ ተግዳሮት፣ የመለስ ዜናዊ ክንድ ብቻ እንዳልሆነ አረጋገጠልኝ:: “በሃገሪቱ የግል ፕሬስ ሽያጭና ስርጭት ላይ ሰፊ እጅ ያላቸው የተወሰኑ ስመ-ጥር የጋዜጣ/መፅሄት ባለቤቶች የሆኑ ጋዜጠኞች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የጋዜጣ/መፅሄት አከፋፋዮችን በእጃቸው አድርገው ከእነሱ ጋዜጣና መፅሄት ቀጥሎ የማንን መፅሄት ስርጭት እንደሚያሳልጡና የእነማንን ጋዜጣ ስርጭት እንደሚያከስሙ ይነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ የእነሱ ስም ተጠርቶ የተተቸበትን ጋዜጣ፣ ከእነርሱ ጋር በሆነ ጉዳይ የተቀያየመ ሰው የሚያሳትመውን የህትመት ውጤት ወይም ከእነርሱ ጋዜጣ በይዘቱ የተሻለና ውሎ አድሮ የእነርሱን ጋዜጣ ሽያጭ የሚገዳደር የመሰላቸውን የህትመት ውጤት ስርጭት አዳክመው ከገበያ እንዲወጣ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በተለይ አዳዲስ የህትመት ውጤቶችን ለመጀመር ከነዚህ ጋዜጠኞችና አከፋፋዮች ጋር መልካም ግንኙነት መመስረት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደማትወጂ ባውቅም ፅሁፍሽን ቆርጬ እንዳወጣ እንድትፈቅጂልኝ በጣም ያስቸገርኩሽ” ሲል ያስጨነቀውን ነገር አጫወተኝ፡፡
በጣም ገረመኝ፣ መቀበልም አቃተኝ:: በተለይ ይህን ያደርጋል የተባለው ጋዜጠኛ ከሩቁ ያለው ምስል እንዲህ የወረደ ስላልሆነ፣ እኔም ከሩቅ ከሚያውቁት መሃል ስለሆንኩ የተነገረኝን እንደወረደ መቀበል ከበደኝ:: የሚነግረኝ ሰው በአንድ በኩል የኔን ፅሁፍ ቆርጦ ለማውጣት፣ በሌላ በኩል እኔንም ላለማስቆጣት የተጨነቀውን መጨነቅ አይሉት መርበትበት ሳስብ ደግሞ ነገሩ እውነትነት አያጣውም የሚል ነገር አስቤ በዝምታ መገረም ጀመርኩ፡፡ በሃሳቤ መሃል አንድ ጥያቄ መጣልኝ:: “አከፋፋዮቹ ግን ከእያንዳንዱ ጋዜጣ ገንዘብ ያገኛሉ አይደል?” አልኩት “አዎ” አለኝ፡፡ “ታዲያ በነዚህ አምባገነን ጋዜጠኞች ታዘው የጋዜጦችን ስርጭት ሲያግዱ፣ ራሳቸውስ አይጎዱም ወይ?” አልኩት፡፡ “ይህ እንደ አፈናው አላማ ይወሰናል፡፡ አታሰራጩ የሚሏቸው ጋዜጠኞች ስርጭቱ እንዲገታ የሚፈልጉት ጋዜጣ፣ ከእነሱ ጋዜጣ የሚበልጥ ይዘት ያለው ስለመሰላቸው ከሆነ፣ ጋዜጣው ተዳክሞ ከገበያ ሲወጣ የእነርሱ ጋዜጣ ኮፒ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ አከፋፋዮቹ ዞሮ ዞሮ ከከልካዮቹ ጋዜጠኞች፣ ጋዜጦች ኮፒ ማደግ ገንዘቡን ያገኙታል፡፡ የአፈናው አላማ ስለነሱ መጥፎ የፃፈን ወይም ሲፃፍ ዝም ብሎ ያሳተመ የጋዜጣ ባለቤትን ለመጉዳት ከሆነ ደግሞ እነዚህ ጋዜጠኞች የተሻለ ስርጭት ያለው ጋዜጣ/መፅሄት ስለሚኖራቸው ኪሳራውን እስከ መሸፈን ሊሄዱ ይችላሉ፡፡” ሲል በጣም ያስደነገጠኝን  ነገር አጫወተኝ፡፡
ይህን ጉዳይ ከሰማሁበት ቀን ጀምሮ ነገሩ ምናልባት የአንድ ጋዜጠኛ መረዳት ሊሆን ይችላል ወይስ በእውነት ያለ ነገር ነው የሚለውን ለማጣራት በግሉ ፕሬስ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በምገናኝበት ጊዜ ጉዳዩን ማንሳቴ አልቀረም፡፡ የጠየቅኳቸው ሁሉ ያረጋገጡልኝ ነገር የህትመት ውጤቶች ስርጭት ጉዳይ ከአከፋፋዮችና በመስኩ ስም ካገኙ የጋዜጣ ባለቤት ጋዜጠኞች በጎ ፈቃድ ጋር የተያያዘ ነገር እንዳለው ነው:: ስለዚህ ስለ መናገር ነፃነት መብት መከበር ሲታሰብ፣ ከመንግስት አምባገነንነት በተጨማሪ የእነዚህና ሌሎች እኔ ያላነሳኋቸው ተግዳሮቶች አንፃርም ማየቱ ተገቢ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ከመንግስት እጅ ውጭ ባለው ተግዳሮት ዙሪያ ሳይንሳዊ ጥናት ቢደረግ ተጨማሪ ግኝትም አይጠፋም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጥናቶችን አድርጎ መፍትሄ ማስቀመጡ፣ ለመናገር ነፃነት መብት መከበር አስፈላጊ ነገር ነው፡፡
ከህትመት ሚዲያው አለፍ ስንል ሃሳብን በነፃነት የመግለፅን መብት አስመልክቶ ተግዳሮት የማያጣው የብሮድካስት ሚዲያው ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ ስለ ብሮድካስት ሚዲያው የማነሳው ሃሳብ በሃገራችን መንግስት የሚተዳደሩና በሌላ ሃገር መንግስት ስር ያሉ እንደ ቪኦኤ እና የጀርመን ድምፅ (DW) ያሉ ሚዲያዎችን አይጨምርም፡፡ ከነዚህ ሚዲያዎች ውጭ ያሉ በቦርድ የሚተዳደሩም ሆኑ በሌላ መንገድ የሚሰሩ የብሮድካስት ሚዲያዎች፣ እንደ ፕሬሱ ሁሉ፣ የግለሰቦች ረዥም እጅ ጫና የሚኖርባቸው ሚዲያዎች ቢኖሩም፣ በእኔ ግላዊ ግምገማ፣ የተሻለ የሃሳብ ብዝሃነት የሚያቀርቡና በገለልተኝነቱም ጥሩ የሚባል አቋም ያላቸው አይጠፉም፡፡ በግሉ ዋዜማ ራዲዮ የሃሳብ ብዝሃነት በማቅረብ፣ ተዓማኒ ዜናዎችን በመስራት፣ የፖለቲከዊ ሁኔታዎችንና የግለሰብ ጋዜጠኞችን ግላዊ የአቋም ለውጥ እየተከተሉ የማይዋልሉ ጠንካራ ትንታኔዎችን በማቅረብም ሆነ በገለልተኝነቱ በኩል ጥሩ የሚባል ሚዲያ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ይህ ሚዲያ ወደ ቴሌቪዥን/ሬዲዮ አድጎ፣ አብዛኛው ህዝብ የሚከታተለው ቢሆን መልካም ነበር፡፡   
ሌላው የብሮድካስት ሚዲያ ኢሳት ነው:: ኢሳት ህወሃትን በመታገሉ በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረገ ሚዲያ ቢሆንም፣ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የፓርቲ ንብረትነትም ስለማያጣው፣ በገለልተኝነቱ በኩል አፍ ሞልቶ የሚያናገር ነገር የለውም፡፡ ይህ ገለልተኝነት የሚያንሰው የኢሳት ተፈጥሮ፣ አምባገነኖችን ለመታገል አማራጭ ያልነበረው ነገር ነው ቢባል እንኳን አሁን ህወሃት ከወረደ በኋላ አንፃራዊ የመናገር ነፃነት እየታየ ነው በሚባልበት ወቅት ሊቀር የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ከገለልተኝነቱ በተጓዳኝ የሃሳብ ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድም ኢሳት የሚያንሰው ነገር ብዙ ነው፡፡ ኢሳት፤ የህወሃትን አምባገነንነት ለመታገል ተብሎ መመስረቱ፣ ህወሃትን የተካን ሁሉ ብፁዕ አድርጎ ማቅረብ ማለት እንዳልሆነ ሁሉም የሚዲያው አባላትና አካላት የተረዱ አይመስልም፡፡ በመሆኑም  ህወሃትን ለተካው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ሆደ ቡቡነት ከማሳየት አልፎ ጥብቅና የሚሞክረው ነገር የሚያሳዩ ጋዜጠኞቹን ወደ መስመር ማስገባቱ አልሆን ብሎታል፡፡
እነዚህ በዐቢይ መንግስት ላይ የማይጠና ሆድ ያላቸው የኢሳት ጋዜጠኞች፣ በተለያዩ ቦታዎች ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ወይም ሚዲያው ሲመሰረት ጀምሮ የቆዩ በመሆናቸው ከበድ ያለ እጅ ሳይኖራቸው አልቀረም፡፡ ይህ ደግሞ የሃሳብ ብዝሃነትን ለማፈን ለፈለገ ሰው አስቻይ ሁኔታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው:: እዚህ ላይ ነገሩን ለማስተካከል መስራት የሚችለው ጣቢያው ይመራበታል የሚባለው ቦርድና የጣቢያው ማኔጅመንት ነው፡፡ እነዚህ አካላት ኢሳት ብዙ ሃሳብ የሚስተናገድበት፣ የኤዲቶሪያል ነፃነነት ያለው ሚዲያ እንጂ ማንም በለጥና ከበድ ያለ እጅ እንዳይኖረው የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ የኤዲቶሪያል ነፃነት ባለበት ሚዲያ ደግሞ ጋዜጠኞች፣ የኤዲቶሪያል ሃላፊዎቻቸውን ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ የሃሳብ ብዝሃነት ያለውን ፕሮግራም ሰርተው ያቀርባሉ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ለአድማጭ ገዝፎ የሚታይ ሚዲያውን የሚገዛው አንድ ሃሳብ አይኖርም ማለት ነው፡፡ ኢሳት ግን ቀደም ካሉ ዘመናት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አንድ ገዝፎ የሚታይ ሃሳብ አንግቦ የሚራመድ ሚዲያ ነው- በፊት ህወሃትን መቃወም፣ አሁን ደግሞ የዐቢይ መንግስት በትችት እንዳይደናቀፍ ዘብ መቆም አይነት ነገር፡፡
የዐቢይን መንግስት በትችት እንዳይደናቀፍ ዘብ የመቆሙ የኢሳት አካሄድ በሁሉም የኢሳት ጋዜጠኞች የሚቀነቀን ባይሆንም፣ በጣቢያው ላይ ከበድ ያለ እጅና ሻል ያለ ስልጣን  ባላቸው ጋዜጠኞች የሚዘመር መሆኑ የጣቢያውን ገለልተኝነት ከመጉዳቱም በላይ ከህዝብ ጋርም ሊያራርቀው እየሞከረ ነው፡፡ ይህ ነገር ህወሃት “ልማታዊ ጋዜጠኛ” ከሚለው ጋር መሳ የሚሆን “የቲም ለማ ለውጥ ጥበቃ ጋዜጠኞች” የሚባል ዘይቤ እንዳያመጣብን ያሰጋል፡፡ የኢሳት “የቲም ለማ ለውጥ ጥበቃ ጋዜጠኞች” ዝንባሌ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን መጋፋቱም አልቀረም፡፡
በቅርቡ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ከጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ እንዳታቀርብ በኢሳት ኤዲቶሪያል ቦርድ መወሰኑና የኢሳት ቦርድም ሆነ ማኔጅመንት ከህዝብ በሰፊው ተቃውሞ የገጠመውን ይህንን ውሳኔ ማፅናቱ ህዝብ የማክበር ምልክት አይደለም፡፡ የህዝብን ድምፅ ችላ ማለት የአምባገነንነት ጅማሬ ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ ነገር የኢሳት ቦርድም ሆነ ስራ አስፈፃሚ ለመናገር ነፃነት ያለውን አቋም ያስገመገመበት፣ ትዝብት ላይም የወደቀበት ክስተት ነው:: “ሁለቱ ጋዜጠኞች ያደረጉት ውይይት እንዳይቀርብ የተደረገበትን ምክንያት ለጋዜጠኛ ርዕዮት አሳውቀናል” ከማለት በዘለለ ምንም አሳማኝ ነገር ለህዝብ ማቅረብ ያልቻለው የኢሳት የኤዲቶሪያል ቦርድ፣ እቃወመዋሁ እያለ ሲያብጠለጥለው የኖረውን የአፋኙን የህወሃት መልክ እንደማያጣ ለህዝብ አሳይቷል፡፡
ፕሮግራሙ ለህዝብ እንዳይቀርብ የተደረገበት ምክንያት በግልፅ ለህዝብ እስካልተነገረ ድረስ ጉዳዩ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ የጠ/ሚ ዐቢይን መንግስት ከመተቸቱ ጋር ተያይዞ የመጣ ጉዳይም ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ይቻላል::
ቴዎድሮስ ጠ/ሚኒስትሩን ሲተች፣ እንደ ሲሳይ አጌና ያሉ የኢሳት ጋዜጠኞችንም አብሮ መተቸቱ፣ በኢሳት ሚዲያ ላለመስተናገዱ ምክንያት እንዳልሆነስ አጋጁ የኤዲቶሪያል ቦርድ እንዴት ማሳመን ይችላል? “ኢሳት አፈና አያውቅም” ብሎ መግለጫ  ማውጣትና አፋኝ አለመሆንን አንድ ሁለት ብሎ ማስረዳት ይለያያሉ፡፡ በበኩሌ የኢሳት ኤዲቶሪያል ቦርድ፣ ያገደውን ፕሮግራም ያገደበትን ምክንያት ዘርዝሮ እስካላሳመነኝ ድረስ ነገሩን ከአፈና የተለየ ስም ልሰጠው አልችልም፡፡
ይህ ማለት ደግሞ ኢሳት ውስጥ በስመ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ለራሳቸው የዳንቴል ዘውድ ሰርተው የደፉ ጥቃቅን አምባገነኖች አሉ ማለት ነው ወደሚል ጥርጣሬ ይመራል፡፡ ይህን የአምባገነንነት ዝንባሌ ሃይ ማለት ያልቻለው የኢሳት ማኔጅመንትም ሆነ ቦርድ የአምባገነንነቱ ተጋሪ ነው፡፡ ኢሳትን ከሚመሩ የቦርድ አባላትም ሆነ የኤዲቶሪያል ቦርድ አባላት ውስጥ ለወትሮው አፈና ሊያደርጉ ቀርቶ እነሱ በተገኙበት መድረክ አፈና ይኖራል ተብሎ የማይታሰቡ ሰዎች መኖራቸው አምባገነንን የተቃወመ ሁሉ ራሱ አፋኝ እንደማይሆን አያረጋግጥም፡፡ ይሄ ደግሞ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያፍነው መንግስት ብቻ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

Read 9191 times